Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአደገኛው ምርጫ

አደገኛው ምርጫ

ቀን:

አራት ኪሎ አካባቢ መንደር ውስጥ የሚገኝ መደብር ነው፡፡ የመደብሩ ባለቤትና ዘወትር ቆመው የሚቸረችሩት ወ/ሮ አበራሽ ታደሰ ከሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር እየገዙ ዘይት ይቸረችሩ ነበር፡፡ አሁን እንደ ስኳር ያሉና ሌሎችን ነገሮች ከማኅበሩ ገዝተው የሚቸረችሩ ቢሆንም የሚፈጠረው ግርግር ከዕድሜም ከጤናም አንፃር ስለከበዳቸው ከሁለት ወራት በፊት ዘይት ማምጣት ማቆማቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዘይት መጣ ከተባለ በአንድ ጊዜ ሠልፍ በሠልፍ ይሆናል፡፡ ግርግሩ መከራ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ አበራሽ ግርግሩ ከሸማች ማኅበር አንድ ሁለት ሠራተኞች ሱቆች ላይ ቆመው ሽያጩን እንዲቆጣጠሩ ሁሉ ግድ ይል እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ተወካዮች የሚቆጣጠሩት አንድ ሰው መግዛት የሚችለው አንድ በመሆኑ ሽያጩ በዚያ መልኩ መካሄዱን፤ በሌላ በኩል ነጋዴዎች በጓሮ በር ሳያስወጡ ለተጠቃሚው ማድረሱን ነው፡፡

እሳቸው እንደገለጹልን ከሸማቾች ማኅበር ገዝተው ለተጠቃሚው ከሚቸረችሯቸው የረጉ ዘይቶች ቺፍ፣ ቫይኪንግ፣ አቢና የተሰኙና ሌሎችም ሲሆኑ ከሦስት ሊትር ጀምሮ እስከ ሃያ ሊትር ድረስ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የተለያዩ ዘይቶች ዋጋቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሦስቱ ሊትር በ72 ብር ሲሸጥ አምስቱ በ115 ብር ይሸጣል፡፡ እሳቸው በሚኖሩበት ወረዳ የሚገኘው የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ዘይት እንደ እሳቸው ላሉ ነጋዴዎች የሚያከፋፍለው በየ15 ቀኑ ነው፡፡ እንዲህ በየአሥራ አምስት ቀኑ ተጠቃሚው የመግዛት ዕድል ካለው ግፊያውና ግርግሩ ለምንድነው? የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር፡፡ ‹‹ሰው ለሚበላው ብቻ ሳይሆን ለምግብ ቤቶች አትርፎ ለመሸጥም ነው የሚገዛው፤›› የሚሉት ወ/ሮ አበራሽ ብዙዎች ከእሳቸው ብቻም ሳይሆን አጠገባቸው ካሉ ሌሎችም ሱቆች እየተሠለፉ እንደሚገዙ ይናገራሉ፡፡

ብዙዎች እንዲህ እየተጋፉ የሚገዙት የረጋ ዘይት ምን ያህል ለጤና አደገኛ ነው? እነዚህ ዘይቶች በትርፍ ወ/ሮ አበራሽ ባሉት መንገድ የሚሸጡ ከሆነ ውጭ የሚመገቡ የሚመገቡት ምግብ በረጋ ዘይት የተዘጋጀ ላለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይችላሉ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የተከሰቱን ጨምሮ ስለድንገተኛ ህልፈቶች ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ልብ ህመምና ደም ግፊት ያሉ ችግሮች በዕድሜ በገፉ ብቻም ሳይሆን በወጣቶች ላይም እየታዩ ነው፡፡ እነዚህ የጤና እክሎች ብዙ ጊዜ ከኮሌስትሮል፣ ከልብና ከደም ተያያዥ በመሆኑ ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ቀድም ባሉት ጊዜያት የሕዝብ የጤና ችግር የነበሩት ተላላፊ በሽታዎች ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ ልብና ከደም ተያያዥ የሆኑ፣ ካንሰር፣ ስኳር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የኅብረተሰብ ጤና ችግር መሆን ከጀመሩ ቆየት ብለዋል፡፡ እነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሳደሩ ባለው ተፅዕኖ በዓለም የጤና ድርጅት የልብና፣ የደም ሥር ችግሮች፣ የስኳር፣ የካንሰርና ዘላቂ የአየር ቧንቧ ችግሮች ተብለው ተለይተዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየጨመሩ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቶች ይገልጻሉ፡፡ የእነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ችግር መሆን መጀመር በቀዳሚነት ተያያዥ የሚሆነው ጤናማ ካልሆነ የአኗኗር ዘዬ ጋር ሲሆን በዚህ ትልቁ ነገር ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ነው፡፡ እዚህ ላይ የረጋ ዘይትን መመገብ ዋነኛው ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ እንደ ቅቤና ሥጋ ያሉን አብዝቶ መመገብ የሚያስከትለው ችግር እንዳለ ሆኖ በተፈጥሮ የሚረጉ ዘይቶችን ለምሳሌ በግል ኩባንያዎች በመንግሥትም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትና በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ፓልም ዘይቶችን፤ እንዲሁም በፋብሪካ እንዲረጉ የሚደረጉትን መጠቀም የሰውነትን የቅባት መጠን ከመደበኛው ከፍ እንደሚያደርግና ለአደጋ እንደሚያጋልጥ በጥናቶች ተመልክቷል፡፡

የህመምተኞች የጤና ችግር በተለያየ መንገድ በምን ያህል ደረጃ ከሚረጋ ዘይት ጋር የተገናኘ ነው የሚለው ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም የብዙዎች የእግርና የወገብ ችግር የረጋ ዘይት ከመጠቀም ጋር የተገናኘ እንደሚሆን የገለጹልን የሕክምና ባለሙያዎች አሉ፡፡ እነዚህን የረጉ ዘይቶች ለጤና ጠንቅ እንዲሆኑ ያደረጋቸው በውስጣቸው ያለው የፋቲ አሲድ (ደቂቀ ስብ) ዓይነት ነው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚያስቀምጡት በረጋ ዘይት ውስጥ የሚገኘው ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ አደገኛ ሲሆን በተለይም የልብና ተያያዥ ችግር ባለባቸው የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ዘይቶችን በፋብሪካ ለማርጋት በሚደረገው ሒደት (ሃይድሮጅኔሽን) በዘይቱ ላይ የሚመጡ ለውጦች ዘይቱን ለጤና ጠንቅ እንዲሆን እንደሚያደርገውም ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሒደት የዘይቱ ባህሪ ወደ ትራንስ ፋቲ አሲድነት ይቀየራል፡፡ ይህ ደግሞ ለጤና ትልቅ ችግር ነው፡፡

የ35 ዓመቱ መርዕድ ዓለሙ የረጋ ዘይት የሚያደርሰውን የጤና ተፅዕኖ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በቤት ውስጥ እንዲጠቀሙ የሚያደርገው ከደቡብ አፍሪካ የሚገባውን ሰን ፍላወር ነው፡፡ እንዲህ መርጦ እንዲጠቀም ያደረገው ከፍተኛ የሆነ የዩሪክ አሲድ መጠን ስለተገኘበት ነው፡፡ ሥጋና ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸውን ምግቦች ከማስወገድ ቀጥሎ ትኩረት ያደረገው የምግብ ዘይት ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያ አማራጭ ያደረገው በአገር ውስጥ የሚመረት የኑግ ዘይት መጠቀም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህም ለጨጓራው አልተስማማውም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ጥሩ የሚባሉት ከውጭ የሚገቡት ዘይቶችም ቢሆኑ ከሚረጋው የፓልም ዘይት ጋር ይደባለቃል የሚል ሥጋት በመኖሩ የሚጠቀመውን ሰንፍላወርም ከሚያምነው ቦታ ብቻ ነው የሚገዛው፡፡ ይህን ያህል ቢጠነቀቅም ውጭም ስልሚመገብ ሙሉ በሙሉ የረጋ ዘይትን አስወግጃለሁ ብሎ አያስብም፡፡ ከባለኮከብ ሆቴሎች ጓሮ ጭምር የረጋ ዘይት ጀሪካኖች መስተዋል ደግሞ ማነው የረጋ ዘይት የማይመገብ? ያሰኛል፡፡  

ምን ያህል ሰው የረጋ ዘይት ይጠቀማል? የሚጠቀመው መጠንስ በምን ያህል ደረጃ ለጤና ችግር ያጋልጣል? ወደ ሆስፒታል ከሚሄዱ ታማሚዎች ምን ያህሉ የረጋ ዘይት ተጠቅመዋል? ይህስ ከገጠማቸው ችግር ጋር እንዴት ይያያዛል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ጥናቶች ስላልተሠሩ የረጋ ዘይት በዚህ ደረጃ ችግር እያስከተለ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሥርዓተ ምግብ መምህር ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም ግን የረጋ ዘይት ወደ አገሪቱ በስፋት እየገባ፣ በዚሁ መጠን ጥቅም ላይም እየዋለ ከመሆኑ በመነሳት የረጋ ዘይት ትልቅ ችግርና ተላላፊ ላልሆኑ እንደ ልብ ህመም ላሉ የማጋለጥ ነገሩ ከፍተኛ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት በተለያዩ ጥናቶች እንደተመለከተውም የረጋ ዘይት (ሳቹሬትድ ፋቲ አሲዱ ከፍተኛ የሆነ) የደም ቱቦዎች መጥበብን ያስከትላል፡፡ ይህም ለልብ ህመምና ለሌሎችም ያጋልጣል፡፡ ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ በቅቤና በሥጋም እንደሚገኝ የሚናገሩት መምህሩ አደጋው ምን ያህል ይሆናል የሚለውን መናገር የሚቻለው ከሚወሰደው መጠን፣ ከአኗኗር ዘዬ (እንቅስቃሴ ማድረግ አለማድረግ፣ የሚጠባበሱ ምግቦችን ከማዘውተርና ከሌሎችም ከከተሜነት ጋር ተያያዥ ከሆኑ ነገሮች) አንፃር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ በፊት በወጣቶች ላይ ይታዩ ያልነበሩ እንደ ልብ ህመም ያሉ በወጣቶች ላይ መታየት መጀመራቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምን ያህል የማኅበረሰቡ የጤና አደጋ መሆን እየጀመሩ እንደሆነ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በቀጥታ የሚያያዘው ከከተሜነት የአኗኗር ዘዬ ጋር ሲሆን በዚህ ውስጥ የረጋ ዘይት መጠቀም አንዱ የጤና አደጋውን የሚጨምር ነገር ነው፡፡

የግንዛቤ ችግር በተወሰነ መልኩ ቢኖርም የረጋ ዘይት ከመጠቀም ጀርባ ያለው ትልቁ ነገር ዋጋ ነው፡፡ የማይረጉና ጥሩ ከሚባሉ ዘይቶች ጋር ሲነፃፀር ርካሽ የሆነውን የሚረጋ ዘይት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ እያደረገ ያለው መንግሥት ነው፡፡ ያለው የዘይት ፍላጐት በዝቅተኛ ዋጋ ይሟላ ዘንድም የግልም የመንግሥት ኩባንያዎች ይህን የረጋ ዘይት በማስገባት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የረጋ ዘይት ለጤና አደጋ ስለሚያስከትል ተጠቃሚዎች ሊጠነቀቁ ይገባል ወይም አይጠቀሙ ሲባል አማራጩ ምንድነው? የሚለው ቀጣይ ጥያቄ ይሆናል፡፡ መምህሩም ‹‹ይህ ጉዳይ ስሱ ነው፡፡ አማራጭ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡

የረጋ ዘይት ስለሚያስከትለው የጤና ጉዳት ግንዛቤ መፍጠር እሳቸው እንደ መጀመሪያ እርምጃ የሚያስቀምጡት ነው፡፡ ይህን ዘይት በመጠቀም የሚደርሰው የጤና ቀውስን ለመመለስ የሚወጣውን ገንዘብ፣ ጊዜ በማስላት ተጠቃሚው ምርጫውን እንዲያስተካክል ተፅዕኖ የሚያደርጉ ጥናቶችን መሥራት ሁለተኛው ነጥባቸው ነው፡፡

የአገር ውስጥ የዘይት ምርትስ አማራጭ መሆን የሚችልበት ዕድል አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ‹‹የአገር ውስጥ ዘይቶች የሚመረቱበት መንገድ ራሱ ብዙ ችግር አለው፡፡ ለምሳሌ በደንብ ስለማይጣሩ ድፍድፍ የመሆን ጸባይ አላቸው ይህ ደግሞ ለጨጓራ አስቸጋሪ ነው፤›› የሚል ነበር መልሳቸው፡፡

ሼፍ አላዛር በሪሁን ደግሞ የረጉ ዘይቶችን የጤና አደጋ የሚመለከተው በምግብ አበሳሰል ወቅት ከሚፈጠረው የኬሚካል ለውጥ አንፃር ነው፡፡ አንዳንዶቹ ዘይቶች ከተወሰነ ደረጃ በላይ እንዲበስሉ ከተደረጉ ለጤና አደገኛ የሆነ የኬሚካል ለውጥ ያስከትላል፡፡

ሰን ፍላወር እስከ 180 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊበስል እንደሚችል ይናገራል፡፡ አበሳሰል ላይ መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ አላዛር ሰዎች የረጉ ዘይቶችን (ፓልም ዘይት) እንዳይጠቀሙ ይመክራል፡፡ በሌላ በኩል የዘይቶችን የተለያየ አጠቃቀም ማስተዋልም ያስፈልጋል ይላል፡፡  

እሳቸው እንደሚሉት አገሪቷ ይኼን ያህል ዘይት ከውጭ የምታስገባው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው፡፡ ይህን ለመመለስ ደግሞ የአገሪቱ የዘይት ምርትና አጠቃቀም ላይ ያለውን ነገር ዳግም መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከኢኮኖሚ አንፃር የተቃኘው የዘይት ገበያና አጠቃቀም በተጨማሪ ከጤና አንፃር መታየት ይኖርበታል፡፡    

እነዚህ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉ የረጉ ዘይቶችን ላለመጠቀም ጥሩ የሚባሉ ከውጭ የሚገቡ ዘይቶችን የሚጠቀሙ ጥቂት ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ዘይቶች ዋጋቸው ቀላል አይደለምና፡፡ ለምሳሌ ኦርካይድ የተሰኘው ፈሳሽ ዘይት ባለአምስት ሊትር ከ340 እስከ 360 ብር ሲሸጥ ሀቱን አንድ ሊትር ሰባ ብር ይሸጣል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ዘይቶችን ምርጫ የማድረግ ነገር ሲነሳ ደገሞ የጥራትና የንፅህና ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በጥራት ይዘጋጃሉ የሚባሉም ቢሆን ዋጋቸው ከውጭ ከሚገቡት የሚተናነስ አይደለም፡፡ ባለአምስት ሊትሩ ለምሳሌ ቅቤ ለምኔ የተሰኘው ዘይት 350 ብር ይሸጣል፡፡

በአገር ውስጥ ከሚመረቱ ዘይቶች ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ችግሮች መታየታቸው በመገናኛ ብዙኃን ለአደባባይ በቅቷል፡፡ ባዕድ ነገር መቀላቀል ጤናን በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ በሚጥል አካባቢ ማምረት ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የተዘጋጁት ዘይቶች በአዲስ አበባ ሳይወሰኑ ወደ ክፍለ ሀገር እስከመላክም የደረሱበት አጋጣሚ ነበር፡፡ የአገር ውስጥ የዘይት ምርት ጥራት ቁጥጥር የሚመለከተው የአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጥና ቁጥጥር ዋና ሥራ ሒደት መሪ አቶ ይታይህ ታደሰ የተጠቀሱት ችግሮች የሚታዩት ፈቃድ አውጥተው ዘይት በሚያመርቱ ሳይሆን በሕገወጦች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ዘይት አምራቾቹን የእሳቸው ተቋም በየጊዜው ይቆጣጠራል፡፡ የተስማሚነትና ምዘናም እንዲሁ ምርቶቹን ይመለከታል፡፡ ባለሥልጣኑም ምርቱን ከኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ያስመረምራል፡፡

የአገር ውስጥ ዘይቶች ሲነሱ አለ የሚባለው ችግር ፈቃድ በሌላቸው የሚደረገው የባዕድ ነገር መደባለቅና ንፅህና ብቻ አይደለም፡፡ ፈቃድ ኖሯቸው በሚሠሩም የተለያዩ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ይታይህ ሲመልሱ ‹‹ከአሲዲቲና ከመርዛማነት መጠን ጋር በተያያዘ ችግር አለ፤›› ብለዋል፡፡ የመጣራት ደረጃቸው ላይ የሚታየው ችግር ደግሞ አብዛኞቹ በባህላዊ መንገድ የሚያመርቱ ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሥራውን እያከናወነ ቢሆንም ውስንነቶች እንዳሉበትም አይክዱም፡፡  

በሌላ በኩል በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በድንበሩ ገረመውና በለጠ ባዲሞ ከአራት ዓመታት በፊት ከውጭ በሚገቡና በአገር ውስጥ ዘይቶች የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ከኮሌስትሮል ነፃ ተብለው ለገበያ በበቁ ዘይቶች ላይ ኮሌስትሮል ተገኝቷል፡፡ በአንዳንዶቹ ዘይቶች ላይ የተገኘው የኮሌስትሮል መጠን ፓልም ዘይት ውስጥ ከሚኖረው በልጦም ተገኝቷል፡፡ ጥናቱ ከኮሌስትሮል ነፃ የሚባል ዘይት በወቅቱ ገበያው ላይ እንዳልነበር ደምድሟል፡፡ በምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የምግብ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ገበያ ላይ ዘይቶች ከኮሌስትሮል ነፃ እየተባሉ መሸጣቸውን በሚመለከት መረጃ እንደሌላቸው ነገር ግን ጉዳዩን እንደሚያጣሩ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ዘይትን በመቆጣጠር ረገድ ትኩረት የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ደረጃን የማያሟሉ የፓልም ዘይቶችን መቆጣጠር ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ መጠናቸው 80 በመቶ የሆኑ ፓልም ዘይቶች ወደ አገር ውስጥ ይገቡ እንደነበር በማሰታወስ አሁን በሚገቡት ይህ ወደ 40/43 በመቶ መውረዱን አቶ ቴዎድሮስ ያስረዳሉ፡፡

የተወሰኑ ክፍተቶች ቢኖሩም ባለሥልጣኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዘይቶችን በሚገባ እንደሚቆጣጠር ይገልጻሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ ዘይት ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ መኖራቸውን፤ ተቋሙ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የጀመረው ከሁለት ዓመት ወዲህ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡  

በምሕረት አስቻለውና በጥበበሥላሴ ጥጋቡ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ