በቀድሞ መጠሪያው ሐረር ቢራ፣ የምሥራቁን የአገሪቱን ክፍል በመወከል ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲወዳደር የሚታወቀው የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ከአምናው የውድድር ዓመት ጀምሮ በብሔራዊ ሊግ አሥር ክለቦች በሚገኙበት ምሥራቅ ዞን ሲወዳደር ቆይቷል፡፡ ውድድሩን በበላይነት የሚያስተዳድረው ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብሔራዊ ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ብዛት ከ80 በላይ በመሆኑ የክለቦቹን አኗኗርና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ግምት ውስጥ በማስገባት ምሥራቅ ዞን፣ ማዕከላዊ ዞን ምድብ ‹‹ሀ››፣ ማዕከላዊ ዞን ምድብ ‹‹ለ››፣ ሰሜን ዞን ምድብ ‹‹ሀ››፣ ሰሜን ዞን ምድብ ‹‹ለ››፣ ምዕራብ ዞን ምድብ ‹‹ሀ››፣ ምዕራብ ዞን ምድብ ‹‹ለ›› እና ደቡብ ዞን በሚል ከፋፍሎ መርሐ ግብሩን ማከናወኑ ይታወሳል፡፡
በዚሁ የውድድር መርሐ ግብር መሠረት ከምሥራቅ ዞን 29 ነጥብ በመያዝ ከምድቡ አምስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ሊግ (ሱፐር ሊግ) የሚል መጠሪያ 32 ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፋፍለው በ2008 የውድድር ዓመት ሊያከናውነው ያሰበው የሊግ ምደባን ተከትሎ በሐረር ሲቲ ክለብና በፌዴሬሽኑ መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ ሐረር ሲቲ ‹‹ለሱፐር ሊጉ ውድድር በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እመጥናለሁ፤›› ሲል ፌዴሬሽኑ ደግሞ ‹‹በጠቅላላ ጉባኤ በተሰጠኝ የሥራ መመርያ (ማንዴት) ሱፐር ሊጉን ለመመሥረት ባዘጋጀሁት ደንብና መመርያ መሠረት መሥፈርቱን አታሟላም፤›› በሚል አለመግባባቱ መፈጠሩን ሁለቱም አካላት በየፊናቸው ይናገራሉ፡፡
የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተከትሎ በደብዳቤ ቁጥር ሀ/ሲ/ሰ/ክ/081 በቀን 07/04/2008 ለፌዴሬሽኑ የጻፈው ደብዳቤ የቀድሞ ሐረር ቢራ ፋብሪካ እግር ኳስ ክለብ ከ2006 የውድድር ዓመት ጀምሮ ‹‹ሐረር ሲቲ›› በሚል መጠሪያ ወደ ግል ይዞታ ተዘዋውሮ በፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመቱን ጨርሷል፡፡ በ2007 የውድድር ዓመት ደግሞ ወደ ብሔራዊ ሊግ ወርዶ ሲወዳደር መቆየቱን ይገልጻል፡፡
የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ በ2008 የውድድር ዓመት የነበሩትን ክፍተቶችና ችግሮች በመቅረፍ በተሻለ ሁኔታ ለመቅረብ እየተዘጋጀ በሚገኝበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብሔራዊ ሊጉና በፕሪሚየር ሊጉ መካከል ‹‹ከፍተኛ ሊግ (ሱፐር ሊግ)›› የሚል በመፍጠር 32 ቡድኖችን መምረጡን ይፋ አድርጓል፡፡ የሐረር ሲቲ ክለብን ግን በዚያው በብሔራዊ ሊግ መወዳደር እንዳለበት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ምክንያቱ ተብሎ የቀረበው ክለቡ በ2007 የውድድር ዓመት ያስመዘገው ውጤትና ደረጃውም አምስተኛ በመሆኑ፣ በምድቡ ተደልድሎና በነበረው ውጤት ላይ ተመሥርቶ ከክለቡ ጋር የተጫውተው ቡድን ከውድድሩ ቢወጣ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ ያገኘ ቡድን ይገባል የሚል የውድድር ደንብ የሌለ መሆኑ፣ በዚሁ ምድብ ሲወዳደር ቆይቶ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወደ ሱፐር ሊጉ ገብቶ የነበረው የሼር ኢትዮጵያ ቡድን የኦሮሚያ ክልል ቡድን በመሆኑ፣ ዕድሉም ለኦሮሚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተሰጥቶ፣ የነቀምቴ ከተማ ክለብ እንዲገባ የተደረገ መሆኑ መጠቀሱን ይገልጻል፡፡
ይሁንና ፌዴሬሽኑ በመደበኛነት ሲሠራበት የቆየው የውድድር ደንብ በአንድ ምድብ ከተደለደሉ ቡድኖች አንድ ቡድን የመፍረስ ዕድል ቢገጥመው በምድቡ ካሉት ቡድኖች ባላቸው ነጥብ መሠረት የደረጃ መተካካት ያደርጋሉ እንደሚል የሚገልጸው ሐረር ሲቲ አሁን ፌዴሬሽኑ በደንቡ መሠረት እያለ የሚናገረው አዲስ ደንብ ከየት እንደመጣ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ጭምር ይገልጻል፡፡
የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ የታየ መሆኑ፣ የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ እየጠየቀ ያለው ከደንብና መመርያ ውጪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በፌዴሬሽኑ የሚታወቀው የውድድር ደንብ በአንድ ምድብ ከተደለደሉ ቡድኖች በአጋጣሚ አንድ ቡድን የመፍረስ ዕጣ ቢገጥመው ከሥሩ ያለው ቡድን የደረጃ ሽግሽግ እንደሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ እንዴት ይታያል? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ ወንድምኩን፣ ‹‹ይኼ የውድድር ደንብ ለዚህ ለአዲሱ ሱፐር ሊግ በሚል ለተጀመረው የሊግ አደረጃጀት አይሠራም፡፡ ለዚህም ነው የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ እየሄደበት ያለው አግባብ ትክክል አይደለም ያልኩት፤›› ብለዋል፡፡
ከምድቡ አራተኛ ደረጃ አግኝቶ ወደ ሱፐር ሊጉ የገባው የሼር ኢትዮጵያ ቡድን ሲፈርስ ቀጥሎ ያለው የሐረር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ መተካት ሲገባው የኦሮሚያ ቡድን የሆነውና በምዕራብ ዞን ምድብ ‹‹ለ›› የተደለደለው ነቀምቴ ከተማ መግባቱ ለምን? ለሚለው ተከታይ ጥያቄ፣ ‹‹ይሄ በልዩ ሁኔታ (ስፔሻል ኬዝ) የተወሰነ ውሳኔ ነው፡፡ ከምሥራቅ ዞን የፈረሰው ሸር ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ መተካት ያለበት የክልሉ ቡድን ነው፤›› በማለት አቶ ወንድምኩን ያብራራሉ፡፡