ከሰባት ወራት በኋላ በብራዚል ሪዮ ዲጂኔሮ በሚካሄደው 31ኛው ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያ በአራት የስፖርት ዓይነቶች እንደምትወዳደር ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ይፋ አደረገ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችም የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ዕቅድ ዝግጅቶቻቸውን ሲያስታውቁ አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ለማስመዝገብ ታቅዷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታኅሣሥ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ሪዮ በሚካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የምትካፈልባቸው ስፖርቶች አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶና ቦክስ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡ የየብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችም ስለዕቅዶቻቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጪው ክረምት ላይ በሚከናወነው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአራቱ ስፖርቶች ለኦሊምፒክ የሚያበቁ ሚኒማ (የማጣሪያ ውድድሮች) እንደተጠበቁ ሆኖ ተሳትፎ እንደሚኖራትና የልዑካን ቡድኑም ከ70 እስከ 80 ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የልዑካኑ ምክትል የቡድን መሪ ኢንጂነር ግርማ ዘውዱ እንዳወሱት፣ ኢትዮጵያ በምትካፈልባቸው የስፖርት ዓይነቶች እንደ አትሌቲክሱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ትችል ዘንድ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረጉ ጎን ለጎን ከፌዴሬሽኖቹ ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው፡፡
የአገሪቱን መልካም ገጽታ ከመገንባት አኳያ ባህላዊና የማንነት መገለጫን የሚያመላክቱ ዝግጅቶች በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ እንደሚከናወኑ ለዚህም በብራዚል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚያሳይ በፊልም የተደገፈ ዕቅድና ክንውን በኦሊምፒክ ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል አበበ አማካይነት ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች መሳተፍ የጀመረችው በ1949 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1956) በሚልቦርን ኦሊምፒክ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየአራት ዓመቱ በተደረጉት ጨዋታዎች ከሦስቱ በሞንትሪያል በ1968 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ1976)፣ በሎስ አንጀለስ በ1976 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1984)፣ በሴዑል በ1980 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1988) ከተደረጉት በስተቀር በሌሎቹ በ12ቱ ጨዋታዎች መሳተፉ ይታወሳል፡፡
በክረምት ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1998 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2006) በቱሪን፣ በ2002 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2010) ቫንኮቨር በአንድ አትሌት መሳተፏ ይታወቃል፡፡
በውጤት ደረጃ በአትሌቲክስ ብቻ በ25 አትሌቶች አማካይነት 21 የወርቅ፣ ሰባት የብርና 17 የነሐስ በድምሩ 45 ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች፡፡
የ31ኛው ኦሊምፒያድ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ፣ 206 ብሔራዊ ኮሚቴዎች፣ 10,903 አትሌቶች ለ19 የውድድር ቀናት እንደሚፎካከሩ፣ ከ45,000 በላይ በጎ ፈቃደኞች የዝግጅቱ አካል እንደሚሆኑ፣ ውድድሩን ለመዘገብ 25,100 እክርድቴሸን የተሰጣቸው የሚዲያ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ፣ ከ206 አገሮች 7,000 ብሔራዊ ኮሚቴዎች እንደሚታደሙ፣ 3,200 ዳኞችና ረዳቶቻቸው እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡
የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በአትሌቲክሱ እየተከናወነ ስላለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደሳቸው አገላለጽ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል ከነበሩ ክፍተቶች በመነሳት 350 አትሌቶችን ከማራቶን እስከ አጭር ርቀት በዕድሜ ጭምር በመለየት የሥልጠና ዝግጅት ተጀምሯል፡፡ በክለብ፣ በክልልና በአትሌት ማናጀሮች መካከል ሲስተዋሉ የቆዩ አለመግባባቶችና የአሠልጣኞችን ምርጫና ምደባን በሚመለከትም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገምግሞ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ጭምር ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የብስክሌት፣ የቦክስና የወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ኃላፊዎች ለሪዮ ኦሊምፒክ የሚያበቃቸውን ዝግጅት ከወዲሁ መጀመራቸውን በመግለጫቸው አስረድተዋል፡፡ በተለይም ለሪዮ ኦሊምፒክ የሚያበቃውን ትኬት መቁረጡን ያረጋገጠው ብሔራዊ ብስክሌት ፌዴሬሽን ለተወዳዳሪዎቹ የሚመጥኑ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ የመወዳደሪያ ብስክሌቶችን ግዥ ፈጽሞ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ መሳይ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡
አትሌቶቻቸው የሚገኙበትን የብቃት ደረጃ ግምት ውስጥ በማስገባት በተመሳሳይ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ወርልድ ቴኳንዶና ቦክስ ፌዴሬሽኖችም በአሁኑ ወቅት የሚኒማ ጉዳይ እንደማያሳስባቸው ይልቁንም በሪዮ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ላይ ትኩረት አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በቀድሞዎቹ ዓመታት በኦሊምፒክ ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ ጠንካራ ተሳትፎ እንደነበረው የሚነገርለት ቦክስ ለዕድገቱ ማነቆ ተብለው ከሚጠቀሱ ችግሮች ዘመናዊ የመወዳደሪያ ቁሳቁስ ውስጥ የመወዳደሪያ ሪንግ በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካይነት የተሟላለት መሆኑም ተነግሯል፡፡
እንደ ቦክሱ ሁሉ ተጨማሪ ማጣሪያ የሚጠብቀው የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በበኩሉ በአሁኑ ወቅት አራት ወንዶችና ሦስት ሴቶችን መርጦ መደበኛውን ዝግጅት በሳምንት ስድስት ቀን በብሔራዊ ወጣቶች አካዴሚ እያደረገ እንደሚገኝ የፌዴሬሽኑ የሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡