Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አንዳንድ ጊዜ በጣም ከሚገርሙኝ ጉዳዮች መካከል የሰው ልጅ የባህሪ ተለዋዋጭነት አንዱ ነው፡፡ የሰው ልጅ በተለያዩ ጊዜየት ከገጠሙት ወይም ከአስተዳደጉ የተነሳ የራሱ መገለጫ የሆኑ ባህሪያት ይኖሩታል፡፡ ባህሪያት ግን ቶሎ ቶሎ ሲለዋወጡ የጤንነት መገለጫ አይመስለኘም፡፡ እንደ አየሩ ጠባይ ልውጥውጥ የሚሉ ሰዎች በአቅራቢያችሁ አጋጥመዋችሁ ያውቃሉ? እኔ በሥራዬ ምክንያት ብዙዎችን አይቻለሁ፡፡ በቅርቡ የገጠመኝ ግን ለማመን የሚያዳግት ነው፡፡

በሥራ ምክንያት የተዋወቅኩት ግለሰብ ዕድሜው በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በትምህርቱ የማስተርስ ዲግሪ አለው፡፡ ቁመናውን ሊያዩት የሚከበር የሚመስለውና አኳኋኑ የጨዋ ዳርቻ የሚባልለት ይህ ግለሰብ፣ ጭራና ቀንድ የለውም እንጂ አውሬ ነው፡፡ አውሬ ካለመዱት ገራም ሊሆን ስለሚችል ይኼኛው ግን ሰይጣን ነው ማለቱ ይቀላል፡፡ ይህንን ያህል ከነገርኳችሁ ገጠመኜን ላዋያችሁ፡፡

በቀደም ዕለት ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ የኮንትራት ሥራችንን እያከናወንን እያለ፣ ደንበኛችን የደረስንበትን ደረጃ ለማየት ቢሮ ይመጣል፡፡ ከደንበኛችን ጋር በሥራው ቅልጥፍናና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ተወያያተን እንለያያለን፡፡ እኛም እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ሥራችንን ቀጥለን ወደ ቤታችን እንሄዳለን፡፡ ቤት ገብቼ ያገኘሁትን ቀማምሼ የደከመ አካሌን ላሳርፍ ስል ስልኬ ይጮሃል፡፡ ሳነሳው ደንበኛችን ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹አቶ የትነበርክ በጣም አዝኜብሃለሁ…›› በማለት ሲያንባርቅብኝ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹እኔ አንተን አምኜ ይህንን ያህል ገንዘብ የወጣበት ትልቅ ፕሮጀክት ስሰጥህ እኮ እንድትቀልድብኝ አይደለም …›› ሲልማ ነገሩ የበለጠ ግራ ገባኝ፡፡ ሰውየው ፋታ ሳይሰጠኝ፣ ‹‹ለመሆኑ ምን ብበድልህ ነው ይህን ሁሉ ችግር የምታደርስብኝ …›› ሲለኝ በዕውኔ ይሁን በህልሜ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ‹‹አንተ እንደ ሠራህልኝ እኔም የእጥፍ እጥፍ አድርጌ እሠራልሃለሁ…›› አለኝ፡፡ እዚህ ላይ የማይጻፉ የብልግና ቃላት በእሩምታ አርከፍክፎብኝ ላዬ ላይ ስልኩን ዘጋው፡፡ ምን እንደተፈጠረ እንኳ ዕድል አልሰጠኝም፡፡

ከድንገተኛው ድንጋጤና ድንዛዜ ውስጥ ወጥቼ ብዙ ካወጣሁና ካወረድኩ በኋላ መልሼ ደወልኩ ዘጋብኝ፡፡ ደጋግሜ ደወልኩ ዘጋው፡፡ ቢቸግረኝ በጣም የተለሳለሰና በጨዋነት የታጀበ የጽሑፍ መልዕክት ላኩለት፡፡ በብልግና ቃላት የተሞሉ ስድቦችን ያዘለ ጽሑፍ መልሶ ላከልኝ፡፡ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ነገር ዓለሙን ትቼ አልጋዬ ውስጥ ገባሁ፡፡ እንቅልፍ ከየት ይምጣ? በማላውቀው ጉዳይ በደረሰብኝ ድንገተኛ ውርጅብኝ ምክንያት ውስጤ እየተቃጠለ እንዴት ልተኛ? እንቅልፍ ጠፍቶ እንዲሁ ስወራጭ ሌሊቱ እንዴት ይለቅ? አቤት ርዝመቱ? እንዲሁ ስገላበጥና ከወዲያ ወዲህ ስል በስንትና ስንት መከራ ወገግ አለ፡፡ ጭንቅላቴ ሊፈነዳ ደርሷል፡፡ መታጠቢያ ቤት ገብቼ እንደነገሩ ከተጣጠብኩ በኋላ ለብሼ ወጣሁ፡፡

የንጋቱ ቅዝቃዜ የጋለው ሰውነቴ ላይ ሲያርፍ ቢሰማኝም፣ የሌሊቱ ሙቀት የፈጠረው ግለት ይዞት እልም ይላል፡፡ መኪናዬን አስነስቼ በዚያ ማለዳ በነፃው መንገድ ላይ እንደ ጥይት ተተኮስኩ፡፡ ቢሮዬ አካባቢ ያለው ካፌ በራፍ ላይ አቁሜ ጥቁር ቡና አዝዤ ስጠባበቅ፣ ከየት መጣ የማልለው እንባ በጉንጮቼ ላይ ኮለል ብሎ ወረደ፡፡ በሕይወት ዘመኔ ማንም ሰድቦኝ የማያውቅ ሰው በምሽቱ በደረሰብኝ ስድብና ዘለፋ ቆስዬ ነበር ለካ እልህ አንዘፈዘፈኝ፡፡ የመጣልኝን ትኩስ ቡና ከእንባዬ ጋር እየታገልኩ ጠጥቼ ቢሮ ገባሁ፡፡ ወዲያው በቢሮ ስልክ ወደ ደንበኛችን ደወልኩ፡፡ ስልኩ ተነሳ፡፡ ‹‹ጤና ይስጥልኝ…›› ከማለቴ ስልኩ ተዘጋ፡፡

ወንበሬ ላይ ተለጥጬ እንደተቀመጥኩ ለካስ እንቅልፍ ይዞኝ ሄዷል፡፡ የቢሮዬ በር ተከፍቶ ሰው ሲገባ እንኳን አልሰማሁም፡፡ ነገር ግን በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሆኜ የሆነ ነገር ሲወዘውዘኝ በርግጌ ባነንኩ፡፡ አብራኝ የምትሠራ ባልደረባዬ ናት፡፡ ‹‹አንተ ምን ሆነሃል? ለምንድነው እንዲህ ሆነው የተኛኸው?…›› ስትለኝ እንድትቀመጥ ምልክት ሰጠኋት፡፡ ከተቀመጠች በኋላ የደረሰብኝን ነገር ሁሉ አንድ በአንድ ነገርኳት፡፡ እጆቿን አመሳቅላ በመገረም ከሰማችኝ በኋላ፣ ‹‹ተወው ገባኝ፡፡ እኔ እኮ ሌላ ጉዳይ ገጥሞት ነው ብዬ እንጂ፣ ይኼ ታፈሰ እኮ ትናንት በስልክ ማንን እንደሆነ አላውቅም ለሆነ ሰው ሲያማ ነበር፡፡ እኔማ ይኼ እባብ ማንን ከማን ጋር እያባላ ነው እያልኩ ስገረም ነው ያደርኩት፤›› አለችኝ፡፡ እንደ እሷ አነጋገር ያ መልከ ግቡ ጎልማሳ ሰይጣን ያደረገው ነገር አለ፡፡

ለማንኛውም እሷ ደንበኛችን ዘንድ ደውላ ምን እንደተፈጠረ እንድትጠይቀው ተስማማን፡፡ በዚህም መሠረት ደወለች፡፡ ደንበኛችን የተነገረውን ነገር በሙሉ ነገራት፡፡ ጭማቂው ሐሳብ እኔ በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት ያገኘሁትን የእሱን የንግድና የኢንቨስትመንት መረጃ አሳልፌ ለሦስተኛ ወገን እንደምሰጥና ከዚህ በፊትም በርካታ ደባዎችን እንዳፈጸምኩበት ነው የተነገረው፡፡ እሷ ደግሞ ይኼ ሁሉ የተባለው ሐሰት መሆኑንና ይልቁንም ሰይጣኑ የእሱን ትኩረት አቅጣጫ አስቀይሮ ሌላ ደባ እንዳይሠራበት አስጠነቀቀችው፡፡ በእሷ አማካይነት ያ ሰይጣን ግለሰብ ሲጠየቅ ምንም ነገር አለመናገሩን ሸምጥጦ ካደ፡፡ ሁለቱን ለማገናኘት ቀጠሮ ተያዘ፡፡

በነጋታው በቀጠሮው መሠረት ሲገናኙ ሰይጣኑ ሳይመጣ ስለቀረ ቀጠሮው ተሰረዘ፡፡ ስልክ ሲደወልለት አጥፍቶታል፡፡ በስልክ ይህንን እየነገረችኝ እያለ በፍጥነት የፖስታ መልዕክት የታሸገ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ የዲኤችኤልን የፕላስቲክ ከረጢት ከፍቼ ሳነብ ሰይጣኑ የመልቀቂያ ደብዳቤ ነው ያስገባው፡፡ እሷ ቢሮ ደርሳ በጉዳዩ ላይ ስንነጋገር ደንበኛችን በእኔ ስልክ ላይ ደወለ፡፡ ገና ከማንሳቴ፣ ‹‹ለበደልኩት ሁሉ እክሳለሁ በፈጠረህ ብለህ የትናንቱን እርሳው… ስሜታዊ ሆኜ እንደዚያ ማድረግ አልነበረብኝም…›› ሲለኝ ሰውነቴ ነደደ፡፡ ‹‹ይኼንን ሌባ በፖሊስ እያስፈለግኩት ነው፡፡ የሠራኝን ሁሉ እነግርሃለሁ…›› ሲለኝ የትናንቱ አዳሬ ታወሰኝ፡፡ በኋላ ቆይቼ ስሰማ ሰውየውን እኔ ላይ ያዘመተው ሰይጣን ለማመን የሚቸግር ጉዳት አድርሶበታል፡፡ እኔን የመስዋዕት ጠቦት አድርጎ እሱን ተጫውቶበታል፡፡ የእሱን ትኩረት እኔ ላይ አድርጎ ሸጦታል፡፡ ለካ ሰው የሚታለለው በሚያየው ሳይሆን በሚሰማው ነው፡፡ በስማ በለው አገር ምን እየሆነ እንዳለ እያየን አይደል?

(የትነበርክ አባተ፣ ከባልደራስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...