Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርየዳኞች ተግባር ይታሰብበት

  የዳኞች ተግባር ይታሰብበት

  ቀን:

  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን (ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም.) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራዕይና ተልዕኮ የከተማው ሕዝብ እንደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሕዝቦችና ከተሞች እኩል እንዲሆን፣ ከተማዋንም ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

  ይሁን እንጂ እንደ እኔ ዕይታ በከተማው የፍርድ ቤቶች አስተዳደር የታዘብኩትን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የተቋቋሙት ፍርድ ቤቶች ለከተማው ሕዝብ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ታልመው የተቋቋሙ ቢሆንም፣ በእኔ ምልከታና ተሞክሮ ግን ፍርድ ቤቶች ብዙ መሥራት የሚጠበቅባቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ እንደ ዕቅዱ ዓላማና ተልዕኮ ከሆነ የፍርድ ቤቶቹ ሥራ በፍፁም አመርቂ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህልም የተሟላ ዳኞች፣ ጸሐፊና ሌሎች የሥራ ማስኬጃ ቁሳቁሶች እንዲሁም ተጨማሪ የሰው ኃይል ተሟልቶላቸው ሥራቸውን በብቃት ሊሠሩ ይገባ ነበር፡፡

  እንደ እውነታው ከሆነ ፍርድ ቤቶች ከመልካም አስተዳደር አንፃር ያላቸው ሚና ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከሕዝቡ የሚነሱትን ቅሬታዎች በአግባቡ ተመልክተው መፍታት እንዲችሉ መዋቅራቸውን ማስተካከል ይገባቸው ነበር፡፡ በፍርድ ቤቶች የሥራ ድርሻና የሥልጣን ወሰን መሠረት የተገልጋዮች ጥያቄ፣ የሠራተኞችን የአስተዳደር ቅሬታ ወይም አቤቱታ እንዲሁም የግብር ይግባኝ ጉዳይ፣ የይዞታና የውርስ ማጣራት በሰፊውና በጥራት እንዲሠሩ የከተማው አስተዳደርና የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ትኩረት ሰጥተው የማነጽ ሥራ ሊሠሩ ይገባል፡፡

  (መስፍን አራጋው፣ ከአዲስ አበባ)

  *******

  የሕክምና ኮሚሽን

  ሁለቱን ቃላት ምን አገናኛቸው ትሉኝ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሐኪሞች በየወሩ የሚያፍሱት ኮሚሽን ከሚከፈላቸው የወር ደመወዝ በላይ እየሆነ መምጣቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

  በመንግሥትም ሆነ በግል ሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ጥቂት የሕክምና ዶክተሮች ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድና ኤምአርአይ ላቦራቶሪ ምርመራ በሚያዙበት ጊዜ በሽተኞች የት ሄደው መመርመር እንዳለባቸው ትዕዛዝ አዘል መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ እነሱ ካዘዙት ቦታ ውጪ ሄዶ የተመረመረ ሕመምተኛ ከቁጣ በላይ የምርመራውን ውጤት እንደማይቀበሉት ስለሚነግሩት፣ ታካሚው እነሱ ወዳሉት ቦታ በመሄድ ድጋሚ ለመመርመር ይገደዳሉ፡፡

  ከላይ የተጠቀሰው የተበላሸ አሠራር ሥር እንዲሰድ ያደረጉት፣ በአንድ ጊዜ ለመክበር የሚያልሙና ተወዳድረው ወደ ገበያ መግባት ያልቻሉ የግል ድርጅቶች ባለንብረቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ባለንብረቶች በደላሎች አማካይነት ወደ  ሐኪሞች በመሄድ ምርመራዎችን ወደ እነሱ ድርጅት ቢልኩላቸው፣ የተደረጉት ምርመራዎች በየቀኑ ተመዝግበው በወሩ መጨረሻ ጠቀም ያለ ኮሚሽን እንደሚከፍሏቸው ይገልጹላቸዋል፡፡

  በነገራችን ላይ ይህንን የሚያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ሐኪሞችና ባለሀብቶች ስለሆኑ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ክትትል ቢያደርግ በቀላሉ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡

  (አስረስ ሀብታሙ፣ ከአዲስ አበባ)

  *******

  አገር ለውጭ ኩባንያዎች ጭሰኛ እንዳትሆን እንጠንቀቅ

  ኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የአገሪቱን ሸለቆዎች በማስጠናት ለእርሻ፣ ለኃይል ማመንጫና መሰል ሥራዎች ተስማሚነታቸውን ካረጋገጠች በኋላ ባለሀብቶች ለ30 ዓመታት በሚጸና የኪራይ ውል (ኮንቬሽን) ቦታ ስትሰጥ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነት ሥራ በስፋት የተጀመረው በአዋሽ ሸለቆ፣ በታችኛው አዋሽ ተንዳሆ፣ ደሳ መሐሪና በአውሳ ሚቸል ኮትስ ኩባንያ፣ በመካከለኛው አዋሽ መልካሳ፣ ዲላ ለኢጣሊያን ኩባንያ፣ በአሚባራና በገዋኒ ከሐረማያ ለተመረቁ ወጣቶችና እንዲሁም በላይኛው አዋሽ ኦራኤራ በሚባለው ሥፍራ ምንታናፊ ይባል ለነበረ ኢጣሊያዊ (ቀደም ሲል ከሰም ቀበና) ይባል በነበረው ሥፍራ ብርቱካንና ሙዝ ያመርት የነበረ ሰው ቦታ ትሰጥ ነበር፡፡

  በቲቢላ አካባቢ እንዲሁ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መሬት ተሰጥቶ በአብዛኛው የጥጥ እርሻ ተቋቁሞ በጊዜው ለነበሩት የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በሙሉ ለዓመት ፍጆታቸው የሚበቃ የተዳመጠ ጥጥ ስለሚያቀርቡ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ማለትም ሱዳንና ከግብፅ በውጭ ምንዛሪ ትገዛ የነበረውን በአገሯ አምርታ የውጭ ምንዛሪ ከማዳኗም በላይ ለአያሌ እርሻ ባለሙያዎች፣ መሐንዲሶችና መሰል ባለሙያዎች በይበልጥም ለበርካታ የቀን ሙያተኞች የሥራ ዕድል ተፈጥሮ ነበር፡፡ በከሰምና ቀበና እርሻ ይመረት የነበረው ብርቱካንና ሙዝ ለአገር ውስጥ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ ይዳረስ ነበር፡፡

  በእርግጥ በእነዚህ አካባቢዎች ደኑ ከወንዙ ዳር ብቻ ስለነበር የመስኖ እርሻው በተስፋፋበት ሥፍራ የዱር አራዊትን መኖሪያ የሚያሳጣ አልነበረም፡፡ እንዲህ ተቋቁሞ የነበረውን ሰፋፊ እርሻ ደርግ ወርሶ ሲንከለወስበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአሚባራ  የነበረውን፤ የአዋሽ ሸለቆ ባለሥልጣን የአፋር ወጣቶች ማሠልጠኛና የግል እርሻዎቹ የነበሩትን ቢወርስም እርሻውን ቀጥሎ ማካሄድ ስላልቻለ ተመልሰው ቁጥቋጦ በቀለባቸው፡፡ ደርግ እንደዚህ የተደራጀውን  እርሻ ሳያካሂድ በቆሎ አመርታለሁ ብሎ በወለጋ ክፍለ አገር ዴዴሳና አንገር ጉተን በሚባለው ሸለቆ ውስጥ የነበረውን ደን መንጥሮ የአያሌ ብርቅዬ የዱር አራዊቶች መጠለያ የነበረውን ቤታቸውን አጥፍቶ ረሃብን ለማጥፋት በሚል ዘመቻ የበቆሎ እርሻ አቋቁሞ ደፋ ቀና ይባል እንደነበርም ይታወሳል፤ ረሃቡ ግን ተመልሶ መጣ እንጂ አልጠፋም፡፡ መኖሪያውን ያጣው አገሬውና ብርቅዬ አራዊቶች ብቻ ሆነው ቀሩ፡፡

  ኢሕአዴግም በተራው የመንግሥት የልማት ድርጅት በማለት እነዚህን እርሻዎች ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ነገር ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆኖበት በተለይ በዴዴሳና በአንገር ጉተን ተቋቁሞ የነበረውን እርሻ ከሙያ አንፃር በአግባቡ ማሠራት አልቻለም፡፡ የእርሻ ባለሙያዎች ለሥራ ዘርፉ የሚጠይቁትን ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ እርሻው አትራፊ አይደለምና ሠራተኛውን አሰናብት ተብሎ በተላከለት ደብዳቤ መነሻነት እርሻዎቹን ይከታተል የነበረው ድርጅት አያሌ ሠራተኞችን አሰናብቶ የስንቱን ሕይወት እንዳናጋው የሚታወስ ነው፡፡ ሠራተኞቹ ቢሰናበቱም በኢትዮጵያ ስም ደርግ ከየኮሚኒስት አገሮች አግበስብሶ ለእርሻ ሥራ ያስመጣቸውን መሣሪያዎች ግን የመንግሥት ልማት ድርጅቱ ምን ይደረጉ ሳይል ለፀሐይና ለዝናብ አጋልጦ፣ ሳር እንዲበቅልባቸው ትቷቸው ነበር፡፡ ለሠራተኞች መኖሪያነት ተሠርተው የነበሩት የጭቃ ቤቶች እንዲሁ ወና ሆነው በመቅረታቸው የአካባቢው አህያ፣ ከብት፣ በግና ፍየል መፈንጫ ሆነው መቅረታቸውን ወደ አካባቢው ለሌላ ጥናት ተጉዞ የነበረ የባለሙያዎች ቡድን ተመልክቶት ነበር፡፡

  በወቅቱ በጣም አስገራሚ የነበረው ነገር ግን እንደዚያ አምሮ የተስተካከለው መሬት፣ ተፈጥሮ በበቂ ዝናብ ያደላቸውን ቦታ አስተካክላሁ ብሎ ለነበረው የህንድ ኩባንያ ከ3,000 ሔክታር በላይ ተሰጥቶት፣ ኩባንያው ያስመጣውን ችግኝ ይተክሉ የነበሩት ግን የአካባቢው ገበሬዎች ነበሩ፡፡ በሥፍራው የነበረው አንድ ህንዳዊ ብቻ ነበር፡፡ ታዲያስ ኢትዮጵያ በእርሻ ሙያ ከጥንት ጀምሮ ከየኮሌጁና ከየዩኒቨርሲቲው ሠልጥነው ከምዕራብ አፍሪካ ምርጥ የፓም (አፕል) ችግኝ አምጥታ በራሷ ባለሙያዎች ስታመርተው ትችል አልነበረም? ስንቱ የልዩ ልዩ ሥራ ባለሙያዎች አገር ውስጥ እጃቸውን አጣምረው ይውሉ የለም እንዴ? በአገር ውስጥ እፍኝ መሬት ያጡ ባለሙያዎች ወደ ሌሎች አገሮች ተሰደው በሙያቸው ተከብረው ይኖሩ የለምን?

  ያለፈውስ ይቅር ዛሬም ያለመስኖ ሥራ እርሻቸውን በዝናብ ብቻ ለሚያካሄዱ መሬት በሊዝ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ደግሞም ተገቢውን መሬት ለተገቢው ሥራ ማዋል ይበጃል እንጂ እንደ ጋምቤላ ክልል በብርቅዬ አራዊት የተሞላውን የደን ስፍራ መንጥሮ ነዋሪውንም ከግጦሽ ሥፍራው፣ አራዊቱንም ተፈጥሮ ከልሎ የሰጠውን ጫካ መመንጠር ተገቢ ይሆን? ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በኮንቬሽን መሬት ቢሰጥም ምርቱ ግን በአገርም የውጭ ምንዛሪ እያዳነ፤ ከውጭም ቦለቄና ሰሊጥ በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝ እንደነበር በሥራው የነበሩ ባንኮች የሚያረጋግጡት ነው፡፡

  ዛሬ ግን ኢትዮጵያ በስመ ኢንቨስተር ለሳውዲ፣ ለህንድና ለቻይና ከሰጠችው መሬት አገር በረሃብ ስትናጥ አንድ ቁና እህል ከእነዚህ ኩባንያዎች እርሻ ላይ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ይብሱን አገራችን የእነዚህ ኩባንያዎች ጭሰኛ የሆነች ይመስላል፡፡

  ደርግ አለማሁ ብሎ የስንቱን ብርቅዬ የዱር አራዊቶች ቤት አጥፍቶ ሲወቀስበት የነበረውን ጥፋት ኢሕአዴግም እየደገመው ይመስላል፡፡ ለመሆኑ በጋምቤላ ክልል ለኢንቨስተር ተብዬዎች የተቸረው መሬት፣ በክልሉ ሕዝብና በብርቅዬ አራዊቶች ላይ የሚያደርሰውን ስደት መንግሥት በእውነት ተመልክቶት ይሆን? አገር መልማት የምትችለው ተፈጥሮ ያደላትን እያጠፋች ሳይሆን በአግባቡ እየተንከባከበች መሆን ይኖርበታል፡፡ ተገቢውን መሬት ለተገቢው ሥራ ማዋልም ብልኅነት ነው፡፡

  እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ያሉት ጎረቤት አገሮች እንደ እኛ ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ሀብት አጥፍተው ሳይሆን ተገቢውን ሥፍራ ለተገቢው የልማት ሥራ በማዋላቸው ከ40 እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን ዓመታዊ በጀታቸውን የሚያገኙት ከቱሪስት በሚሰበስቡት ገንዘብ ነው፡፡ ይኸውም የዱር አራዊቶችን መኖሪያ የሆነውን ደን ሳይመነጥሩ አራዊቱን ለስደት ስላልዳረጉ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ በተለይ በጋምቤላ ክልል ያሏትን አያሌ ብርቅዬ የዱር አራዊት መኖሪያ (ያውም ከኢንቨስተሮቹ ምንም ለማታገኝበት እርሻ) መንጥረን አራዊቱ ወደ ጎረቤት አገር እንዲሰደዱ ማድረጋችን በእውነት የአገራችንን ጥቅም ያስከበርን ይመስለን ይሆን? ነዋሪውስ በግጦሽ ለሚጠቀመው መሬት ምን ተደርጎለት ይሆን? ከእነዚህ ኢንቨስተሮች በዓመት ከምታገኘው ጥቅም ይልቅ የዱር አራዊቶችና ደኑን እየተንከባበች ብታስጎበኝ አንድ ሰዓት እጅ ብልጫ ያለው የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ የሙያው ባለቤቶች በትክክል የሚያረጋግጡት ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች እኮ ለመስኖ የሚያገለግል ግድብ አልሠሩም፡፡ አገሩ ብዙ ዝናብ ስላለው ይህንን በመጠቀም እንደሚያርሱ እየታወቀ መሬት በገፍ ይሰጣቸዋል፡፡ የተትረፈረፉት የአገራችንን የእርሻ ባለሙያዎችና ባለሀብቶችን አቀናጅተን ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ ቢደረግ ይቻልስ የለ አልነበረም እንዴ? ወደድንም ጠላን በየክልሉ የገቡት ኢንቨስተሮች እየገጠማቸው ያለውን ችግር መቋቋም እንዳልቻሉና ጠቅልለው ለመውጣት እንዳኮበኮቡ ይደመጣል፡፡ በተለይ ጋምቤላ ያለው የህንድ ኩባንያ እርሻውን የሚረከበው ሌላ የህንድ ኩባንያ እያፈላለገ እንደሆነ ስለጉዳዩ በቅርብ ከሚያውቁ ዘንድ ዜናው እየተሰማ ነው፡፡ ተረካቢ ካጣ ሊዘጋው ይሆን? ካገኘስ? ማስተላለፍ ይችል ይሆን? ይህ የሕግ ባለሙያዎችን አስተያየት የሚጠይቅ ነው፡፡

  ታዲያ የስንቱ ከብት አርቢ የግጦሽ ቦታ ከሰሎ፣ ነዋሪውን አስወጥቶ የብርቅዬ አራዊቶቻችንን ደን መንጥሮ ሲያበቃ፣ ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ እንዲሉ ገና እልፍ ሳይል ለሚፍረከረክ ኩባንያ ያን ሁሉ መሬት ተሰጥቶ ሁለቱን ጥፋቶች ተቀብለን ተስፋ የጣልንበትን ምርትም እንድናጣው እየተሽቆለቆልን ነው፡፡ እንደዚህ ለማይሳካ እርሻ ሕዝቡንና የዱር አራዊቱንም መኖሪያ ባናሳጣቸው ይሻላልና እባካችሁ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንዲሉ››፣ የአገራችንን ባለሙያዎችና ባለንብረቶች በማቀናጀት በራሳችን ወገን አምርተን እንድንጠቀም ይደረግ እንጂ የራሳቸውን ረሃብተኛ ለመመገብ ለሚንቀሳቀሱ አገራችንን አሳልፈን መስጠት አልገባንም፡፡

  (እንድርያስ መንገሻ ቆቱ፣ ከአዲስ አበባ)

  *******

  ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ ቃልዎን እንዳያጥፉ

  ክቡር ሆይ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአገሪቱ ውስጥ የመልካም አስተዳዳርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ዙሪያ የተደረገውን ጥናት አስመልክቶ ከከፍተኛ የአመራር አካላት ጋር ያደረጉትን ውይይት በጥሞና ተከታትየዋለሁ፡፡ ውይይቱ ለሕዝብ በቀጥታ መተላለፉ መንግሥት ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻው ሙስናን ከአገሪቱ ለማጥፋት በማለት ሞት ሽረት ትግል ቆርጦ እንደተነሳ በመታየቱ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ተስፋ እንዲጭር አድርጎታል፡፡

  ለዚህ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ አርሶ አደሩና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው ወቅት ሲሰጡ የነበረው አስተያየት ነው፡፡ በወቅቱ በስብሰባው ላይ ለነበሩ የከፍተኛ አመራሮች የሰጡት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሲሰጡ፣ በተለይ ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው (ኔትወርክ የፈጠሩ) ኃላፊዎች ከስብሰባው እንደወጡ ማቋረጥ እንዳለባቸው የገለጹት መንገድ በመልካም የሚታይ ነው፡፡

  እንግዲህ ሕዝቡ ከዚህ መመርያ የሚረዳው አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ በአገራችን የተንሰራፋው ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር በቅድሚያ የማጥራቱ እርምጃ መወሰድ ያለበት ከዋና ምንጩ ማለትም ከከፍተኛ አመራሮች መሆን ይገባዋል የሚለው ነው፡፡ የመጀመርያው ዕርምጃ ስንዴና እንክርዳዱን መለየት መሆን አለበት፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ አስተደደር በቀበሌና በክፍለ ከተሞች አመራሮች ላይ የተወሰደው የማጥራቱ ዕርምጃ አንዱ አካል ቢሆንም፣ ከላይ በሲቪሉና በከፍተኛ የጦር መኮንኖች አካባቢ ባሉት ላይ የማጥራቱ ዕርምጃ ካልተወሰደ በቀር በዝቅተኛው አመራር ላይ ብቻ የሚወሰደው ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› እንደሚባለው እንዳይሆን አካሄዱ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡

  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ትግሉ ለመንግሥትዎ ፈታኝ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ትግሉ ጡንቻቸው ከፈረጠመና ሥር የሰደደ ኔትወርክ ካላቸው ጋር የሚደረግ በመሆኑ ነው፡፡ በአካባቢዎ ካሉት መካከል ጥቂት የማይባሉ ባለሥልጣናት ከእርሶ በተቃራኒ እንደሚቆሙ እንገምታለን፡፡ በቆራጥነት ተነሳስተው ለሕዝብ የገቡትን ቃል ተግባራር ላይ ለማዋል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት የተማረረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በሙስና እጃቸው ያልቆሸሸ ከፍተኛ አመራሮች ከጎንዎ እንደሚሰለፉ አልጠራጠርም፡፡

  ነገር ግን ‹‹የሞት ሽረት ትግል›› ነው ያሉት ቃልዎ ቢታጠፍና ወደ ኋላ ማፈግፈግ ቢያመጡ፣ ለእርሶ መንግሥትም ሆነ ግዙፍ ጦር የገነባውን ደርግን ላስወገደው ኢሕአዴግ ከባድ ሽንፈት ከመሆኑም በላይ ከሚመሩትም ሕዝብ መራቅን ያስከትላል፡፡

  (ማቴዎስ ሽመሎ፣ ከሐዋሳ)

  *******

  ሹሞቻችን የእውነት ትህትናን ተላበሱ

  በባህላችን የታመመን ለመጠየቅ፣ ለታማሚው የሚሆን ምግብ ቋጥሮ ወይም ፍራፍሬ ተይዞ ይኬዳል፡፡ ካልሆነም ባዶ እጅ ከጥሩ ፈገግታና ሐዘኔታ ጋር በመላበስ በሽተኛን ማጽናናት የተለመደ ነው፡፡

  ሰሞኑን በቴሌቪዥን መስኮት የተከበሩ ከንቲባ በአንዋር መስጊድ በፈንጅ የተጎዱትን ሲጠየቁ ሁለት እጃቸው ከኪሳቸው ውስጥ ከተው ነበር፡፡ ከንቲባው ሊያጽናኑ ሳይሆን ጎሽ በሚመስል አኳኋን ተጎጂዎችን ሲጠየቁ በማየቴ በጣም አዘንኩ፡፡ ጉዳተኛ እንዴት እንደሚጠየም ከባራክ ኦባማና ከባን ኪሙን ቢማሩ ምናለበት? ለማንኛውም  ጤንነትን፣ ለዘመዶቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

  (አለባቸው ተሰማ፣ ከአዲስ አበባ)

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...