Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሁሉንም ባንኮች ካፒታል የሚያሳድግና ውህደት እንዲፈጥሩ የሚያደርግ ስትራቴጂ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ ለማጠናከር ያስችላሉ የተባሉ አዳዲስ አሠራሮችን የያዘ ስትራቴጂ፣ በተለያዩ አማራጮች ለመንግሥት እንደሚቀርብ ተጠቆመ፡፡ በስትራቴጂው መሠረት በተለይ ባንኮች ካፒታላቸውን ከማሳደግ አልፈው ወደ ውህደት እንደሚያመሩ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት ይቀርባል የተባለው አዳዲስ አሠራሮችን የያዘው የስትራቴጂ ሰነድ፣ የፋይናንስ ተቋማትን አሠራር ለማጠናከር የታለመ ነው፡፡ በመጪው መስከረም 2010 ዓ.ም. ለመንግሥት እንደሚቀርብ ሪፖርተር ከብሔራዊ ባንክ ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጎልበትና ወደ ዘመናዊ አሠራር እንዲያቀና ያስችላል ተብሎ የታመነበት ሰነድ፣ በዋናነት የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ከማገዝም በላይ፣ ውህደት እንዲፈጥሩ ያመቻቻል ተብሏል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ አገሪቱ በ2025 በፋይናንስ ዘርፍ ትደርሳለች ተብሎ የተቀረፀውን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የተዘጋጀው ይህ ሰነድ፣ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት አሁን ያላቸውን ካፒታል እንዲያሳድጉ የሚያስገድድ ነው፡፡

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መድረስ አለባቸው ተብሎ የሚጠበቀውን የዕድገት ደረጃ ለማምጣት አሁን ያሉት 18 ባንኮች ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ከማድረግ በተጨማሪ፣ እንዲዋሀዱ በማድረግ የተወሰኑ ጠንካራ ባንኮችን መፍጠርንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ስትራቴጂ ጠንካራ ባንኮችን ለመፍጠር ውህደትን እንደ አንድ አማራጭ አካትቶ መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንኮቹ ውህደት እንዴት መከናወን አለበት ለሚለው የተለያዩ አማራጮች እንደተቀረፁና የውህደቱ አስፈላጊነት በመንግሥት ተቀባይነት ካገኘ፣ የተሻለውን አማራጭ በመያዝ ውህደቱን እንደሚያስፈጽም የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያስረዳል፡፡

‹‹ዝም ብሎ ውህደት ይፈጸም አይባልም፤›› ያሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ፣ ወደ ውህደት ከመገባቱ በፊት በቅድሚያ አዲስ የካፒታል ጣሪያ ይቀመጣል ብለዋል፡፡ ‹‹ባንኮቹ ካፒታል ለማሳደግ የጊዜ ገደብ ይሰጣቸዋል፡፡ የተቀመጠውን የካፒታል መጠን በጊዜ ገደቡ የማያሟሉ ከሆነ የውህደት መንገዱን እንመርጣለን፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ባንኮች እንዲያሟሉ የሚፈለገውን ካፒታል ካሟሉ የግዴታ ውህደቱ እንደማይኖር፣ ይህ ግን እንደ አንድ አማራጭ የቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የመጀመሪያው ዕርምጃችን ትዋሀዳላችሁ የሚል ሳይሆን ካፒታላችሁን በዚህ ጊዜ ውስጥ እዚህ ደረጃ ማድረስ አለባችሁ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የጊዜ ገደቡ ይሰጥና የሚፈለገውን ካፒታል ካላሟሉ፣ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊነቱን ወስዶ የውህደቱን ጉዳይ ይሠራበታል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ካፒታሉን ያላሟሉትንም ያሟሉትንም ባንኮች እንዴት ማዋሀድ ይቻላል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የተሰናዳው ረቂቅ ፖሊሲ አማራጭ እንደሚኖሩት፣ ሆኖም የሚፈለገውን ካፒታል ያላሟሉትን ወይም አነስተኛ ካፒታል ያላቸውን አንድ ላይ እንዲዋሀዱ አይደረግም ብለዋል፡፡ ውህደቱ ከፀደቀ ግን ሁሉንም ባንኮች የሚመለከት እንደሚሆን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ካፒታል ያላሟሉትን ካሟሉት ጋር እንዲዋሀዱ የማድረግ አማራጭም ተይዟል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ባንኮች የያዙት የሕዝብ ገንዘብ ስለሆነ፣ ትንሽ ወይም ትልቅ በማለት የሚነጣጠል እንደማይኖርና የተቀረፀው የስትራቴጂ ሰነድ ይህንንም በአማራጭነት መያዙ ተገልጿል፡፡  

እንደ ኃላፊው ገለጻ የባንኮች የውህደት አማራጮች ብዙ ስለሆኑ በሚቀርቡት አማራጮች መሠረት የሚሰጠው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ውህደቱ ካፒታሉን ላሟሉት ለትልልቆቹም አይቀርም ተብሏል፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድ የጠቀሱት ኃላፊው ትንንሽ ባንኮችን እንዲዋሀዱ ሲደረግ የውጭ ኮረስፖንደንት ባንኮች አይቀበሉም ብለዋል፡፡ ‹‹ውህደት ውስጥ ከተገባ ትንሹንም ትልቁንም ሊመለከት ይገባል፡፡ ባንክ የሕዝብ ስለሆነ አንድ ላይ ታደርጋለህ ወይም በመካከለኛ ደረጃ ያሉትን እንዲዋሀዱ ታደርጋለህ፡፡ ካልሆነም ትልልቁን ከትንንሹ ጋር ማድረግ ይቻላል፡፡ የትኛው ይሻላል ለሚለው ግን ጊዜው ሲደርስና በመንግሥት ሲወሰን ይታወቃል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ውሳኔ የሚያርፈውም ካፒታል የማሳደግና የውህደት ጉዳይን የሚመለከቱ አማራጮች ጠቀሜታቸውና ጉዳታቸው ታይቶ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ባንኮችን ማዋሀድ ያጠናክራቸዋል ተብሎ ከታመነ በቀጥታ ወደዚያ ይገባል፡፡ በባንኮች ውህደት ላይ የሌሎች አገሮች ልምዶች ስላሉ እነሱም ታሳቢ ይደረጋሉ፤›› ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  

ባንኮችም ሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት እንዲጠናከሩ የሚፈለገው በካፒታል አቅማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሊኖሩዋቸው በሚገቡ ቴክኖሎጂዎች ጭምር መሆኑ ተወስቷል፡፡ ሌላው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ሲገባ አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባቸውን አቅም በማየት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚያስችል ፖሊሲ ሊቀረፅ የሚችልበት ዕድል ይኖራል ተብሏል፡፡ አሁን የአገሪቱ ባንኮች ባሉበት አቅም ተወዳዳሪ በመሆን ኢኮኖሚውን ለመምራትና ለማገዝ ስለማይችሉ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ሲገባ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ገብተው ማገዝ አለባቸው የሚለው ጉዳይ በመንግሥት እንደሚፈተሽ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከር የሚወሰደው አዲሱ ዕርምጃ በሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች የተቃኘ መሆኑን ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አንደኛው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ውስጥ ከተገባ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ብቻ በቂ ናቸው የሚል እምነት ላይኖር ስለሚችል፣ ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት በሩ ክፍት መሆን ስላለበት ነው፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ በዓለም ገንዘብ አልባ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፤›› ያሉት የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ፣ ‹‹ኢ ባንኪንግ ትልቁን ድርሻ እየያዘ በመሆኑ የፋይናንስ ተቋማት በኤሌክትሮኒክ አሠራር ራሳቸውን በማላመድ አሠራሩን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታየውን የተለመደ የባንክ አሠራር ይዘው ለመራመድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠበቁት አሠራሮች በሙሉ የአደጋ ሥጋት (ሪስክ) ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው፣ ዲጂታል አሠራር ውስጥ ሲገባ እንዳሁኑ በማንዋል መጠቀም አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ከሳይበር ጥቃት ጋር የተያያዙ ሥጋቶች ይኖራሉ፡፡ ቁጭ ብሎ በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ የሚሰበስብበት አሠራር አይኖርም ማለት ነው፡፡ አልጋ በአልጋ ሆኖ ቴክኖሎጂው ይዞት የሚመጣውን አደጋ መቋቋም የሚቻለው ከፍተኛ ካፒታል በመያዝ ነው፡፡ አንድ ባንክ አንድ ሚሊዮን ብር ሊበላ ይችላል፡፡ ምናልባት 800 ሚሊዮን ብር ሊበላ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ዘመናዊ አሠራር ሲጀምርና እንደ ባንክ የሚቀጥል ከሆነ ይህንን የሳይበር ጥቃት የሚከላከል ካፒታል ሊኖር ይገባል፡፡ ስለዚህ የአደጋ ሥጋት ወዳለበት የባንኪንግ ሲስተም እየገባን ስለሆነ የፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን ካላሳደጉ በስተቀር ሊጠፉ ይችላሉ የሚባለው እንዲህ ካለው ተጨባጭ እውነታ አንፃር ነው፤›› በማለት ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉ ወደ አዲስ አሠራር እንዲገባ ለማድረግ እያደረጋቸው ካሉ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን እንዲህ ያለው አሠራር ውስጥ እንደሚገቡ በማሳወቅ፣ ከወዲሁ የፋይናንስ ተቋማቱ ከዓመታዊ ገቢያቸው ሁለት በመቶ የሰው ኃይል ሥልጠና ላይ እንዲያውሉ መመርያ በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በመመርያው መሠረት ባንኮች ከገቢያቸው ሁለት በመቶ የሚሆነውን የሰው ኃይል ለማብቃት የሚያስችል አቅም ግንባታ ላይ ካላዋሉ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘቡን ወስዶ ራሱ ሥልጠና ይሰጣል ተብሏል፡፡ ሥልጠናው ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ያሉትን ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን፣ ከዝቅተኛ ጀምሮ ያሉትን የሚያካትትና መመርያው የወጣውም መጪውን ጊዜ በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

እንዲህ ባሉ ዕርምጃዎች የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን በማስፋት ነው ዜጎች የሞባይልና የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ያሉት ኃላፊው፣ ስትራቴጂው በብሔራዊ ባንክ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተጓዳኝ መሠረተ ልማቶች መደገፍ አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ከወዲሁ ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል ተብለው ከሚታሰቡት ውስጥ ደግሞ አንድ ወጥ የሆነ ብሔራዊ መታወቂያ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ካልተደረገ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የተለያዩ መታወቂያዎች ተይዞ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ወደ ኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ከገባ በኋላ ሺሕ ዓይነት መታወቂያ ከተያዘ ችግር ውስጥ እንገባለን፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ መታወቂያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራው መገባት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በፋይናንስ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የተቀረፀውን ስትራቴጂ በትክክል ሥራ ላይ ለማዋል ሌላው የሚጠበቀው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን አቅም ማጎልበት የሚለው ይገኝበታል፡፡ የመጪውን ጊዜ የፋይናንስ ተቋማት ዘመናዊ አሠራር ለማቀላጠፍ ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ጊዜው በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት እንዲዋቀርና እንዲጠናከር ይደረጋል ብለዋል ኃላፊው፡፡

የፋይናንስ ዘርፉ በሕዝብ አመኔታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያመለከቱት ኃላፊው፣ የፋይናንስ ተቋማት ለአዲሶቹ አሠራሮች ራሳቸውን ቢያዘጋጁ ይጠቅማቸዋል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክም በሕዝብ አመኔታ ላይ የተመሠረተው ዘርፍ አደጋ ሳያጋጥመው ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ ዘመናዊ አሠራሮችን በመጪው መስከረም እንደሚያስተዋውቅ አረጋግጠዋል፡፡.

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች