Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  በገዛ ገንዘባችን ንፉግ የሆኑብን ኤቲኤሞች ይታረሙ

  የአገራችን ባንኮች ይዘግዩ እንጂ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምረዋል፡፡ እንደ የኢንተርኔትና የሞባልይል ባንኪንግ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወንም ለደንበኞች አማራጮችን እየፈጠሩ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ከተጠቃሚዋች አንፃር መጠኑ ዝቅተኛ ይሁን እንጂ ደንበኞች እያፈሩበት ነው፡፡

  በሌሎች አገሮች ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት የተጠጋው የኤቲኤም አገልግሎት ወደ አገራችን ገና ከገባ አሥር ዓመታት የሞላው ባይሆንም፣ ከሌሎች ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች በተሻለ በርካታ ተጠቃሚዎችን እያፈራ ነው፡፡ ከአገልግሎቱ ጠቀሜታ አንፃር ደንበኞች የሚመርጡት እየሆነ በመሄዱ፣ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎታቸውን ለማስፋት እየጣሩ ነው፡፡ እስካሁን የኤቲኤም አገልግሎት የሌላቸውም አገልግሎቱን ለመጀመር እየተዘጋጁ ነው፡፡ እንደ አንድ መወዳደሪያ እያዩትም በመሆኑ፣ ከዚህም በኋላ አገልግሎቱ እየሰፋ ይሄዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡

  ዘመናዊና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል የተባለው የኤቲኤም አገልግሎት ግን በታሰበውና በተፈለገው ደረጃ የደንበኞችን ፍላጎት እያረካ ነው ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡ በኤቲኤም ይሰጣቸዋል የተባሉ ሙሉ አገልግሎቶችም እየተሰጡ አይደሉም፡፡

  አሁን ባለው ደረጃም ቢሆን ግን በኔትወርክ የለም ሰበብ ከሚፈጠር መስተጓጎል ጀምሮ፣ በኤቲኤም ካርድ ገንዘብ ለማግኘት ችግር የሚሆንበት አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ  ይስተዋላሉ፡፡ የኤቲኤም ጠቀሜታዎች አንዳንድ ደንበኛ በየትኛውም ሰዓት ገንዘብ ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ቢሆንም፣ አንዳንዴ ኤቲኤሞቻችን ንፉግ ይሆናሉ፡፡

  ለምሳሌ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤቲኤምን ይዞ የተለመደ አገልግሎት ለማግኘት የተደረጉ ሙከራዎች ያለመሳካታቸው ከወትሮው የተለየ ሆኗል፡፡ ብዙ ደንበኞች በኤቲኤም ካርዳቸው ገንዘብ ለማውጣት ሲቸገሩም ነበር፡፡

  እኔ በግል የገጠመኝን ጉዳይ በምሳሌነት ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ የምሠራበት መሥሪያ ቤት ደመወዜን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የሚከፈለኝ በመሆኑ፣ ደመወዜ አካውንቴ ውስጥ መግባቱን ሳረጋግጥ ገንዘብ ለማውጣት በባንክ ደብተሬ ከመጠቀም ይልቅ በኤቲኤም ካርድ መጠቀሙን እመርጣለሁ፡፡ በዚሁ መንገድ ያለችግር ስገለገልም ቆይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ለረዥም ጊዜ ከከተማ የምወጣ ከሆነ የባንክ ደብተሬን ሳይሆን የኤቲኤም ካርዴን እይዛለሁ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ግን እስካሁን ያልገጠመኝ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ለሥራ የተጓዝኩት ባህር ዳር ነበር፡፡ እንደተለመደው ከአንድ የኤቲኤም ማሽን ሄጄ ካርዱን ከትቼ ገንዘብ ለማውጣት ስሞክር፣ ኤቲኤሙ ገንዘቡን ሊሰጠኝ እንደማይችል በጽሑፍ ጭምር ይነግረኛል፡፡

  ሙከራዬ ባይሳካም ካርዴ አገልግሎት እንደማይሰጠኝ የሚገልጸው መልክዕት ሊለወጥ ይችላል ብዬ ደጋግሜ ሞካከርኩ፡፡ ግን አልተቻለም፡፡ አንዳንድ ካርዶችን የማይቀበሉ ማሽኖች ይኖራሉ ብዬ ወደ ሌላ የኤቲኤም ማሽን ሄድኩ፡፡ እዛም በተመሳሳይ የምፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ሳልችል ቀረሁ፡፡ ገንዘቡ የግድ ያስፈልገኝ ነበርና የባህር ዳር ጎዳናዎችን ካጨናነቁት ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) አንዱን ኮንትራት ይዤ በከተማ ውስጥ ያሉትን ኤቲኤሞች እየዞርኩ ብሞክርም አልተሳካልኝም፡፡ በዛን ወቅት እንዲህ ያለው ያልተጠበቀ ችግር የገጠመኝ እኔን ብቻ አልነረበም፡፡ በአንድ ቦታ ብቻ በኤቲኤም ገንዘብ ለማውጣት ሠልፍ ይዘው ከነበሩ 15 ሰዎች መካከል ስምንትና ዘጠኝ ለሚሆኑት የኤቲኤም ማሽኑ ጥያቄዎቻቸውን ሊቀበል አልቻለም፡፡ ያልተለመደ የሆነባችሁ የባንክ ደንበኞች ‹‹ሰሞኑን ካርድ ይመርጣል፣ ለአንዱ ሰጥቶ ለአንዱ ይከለክላል፤›› እያሉ ተጠቃሚዎች ሲናገሩም ነበር፡፡

  አንዳንዶች እንደኔው ከአንዱ የኤቲኤም ማሽን ወደ ሌላ ቦታ ወዳለው ሌላኛው በመሄድ ገንዘብ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም፡፡

  በኤቲኤም ካርዳቸው ገንዘብ ለማውጣት ያልቻሉ የከተማው ነዎሪዎች በቁጠባ ደብተራቸው ገንዘብ የማውጣት ዕድል ቢኖራቸውም፣ ቀኑ እሑድ ነበርና ይህንንማ ሊያደርጉ አልቻሉም፡፡ እኔም ለምፈልገው አገልግሎት ከማውቀው ሰው መበደር ነበረብኝና ይህንኑ አድርጌያለሁ፡፡ የገረመኝ ግን ገንዘቡን ያበደረችን ወዳጄ ገንዘቡን ያወጣችው በኤቲኤም ካርድ መሆኑ ነው፡፡ እውነትም ማሽኑ ካርድ ይመርጥ ይሁን? አልኩ፡፡

  ለማንኛውም አስተማማኝ አገልግሎት ሊሰጠን ይገባ የነበረው የኤቲኤም ማሽን እንዲህ ያለ ችግር የተፈጠረበት ምክንያት ግልጽ አልነበረም፡፡ ችግሩ አንድ ቀን ሳይሆን ሁለትና ሦስት ሳምንት የዘለቀ ነበር፡፡

  ችግሩ በባህር ዳር ከተማ ላይ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ የገጠመኝ ተመሳሳይ ችግር ነው፡፡ የእኔና የአንዳንዶች ካርዶች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡ ወደ አንድ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ጎራ ብዬ ስጠይቅ የሲስተም ችግር ነው ይስተካከላል የሚል መረጃ አገኘሁ፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት ያደረኩት ሙከራ አልተሳካምና ችግሩ አሁንም አለ ማለት ነው፡፡ ባንኩ ግን መስተካከሉን መግለጹን ሰምቻለሁ፡፡

  የኤቲኤም አገልግሎት አስፈላጊነትና እየተለማመድነው በመሆኑ ሊስተጓጎልብን አይገባም የምንለው፣ አገልግሎቱ እንዲህ ያለ ችግር ሲገጥመው ብዙ ነገሮችን ስለሚያበላሽ ነው፡፡ መተማመንንም ሊያደበዝዝ ይችላል፡፡ ከሰሞኑ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ የአንድ የሥራ ባልደረባዬ ገጠመኝ የኤቲኤም አገልግሎት መስተጓጎል ሊፈጥር የሚችለውን ክፍተት ሊያሳይ ይችላል፡፡

  የሥራ ባልደረባዬ ከሰሞኑ በአንዱ ቀን የአንድ ጎረቤቱ የቤተሰብ አባል ይታመምና ይጠራል፡፡ ጥሪው የደረሰው ምሽት ላይ ነው፡፡ ሕመምተኛውን ወደ ሆስፒታል ለማውሰድ ገንዘብ ማውጣት ነበረባቸውና ወደ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የኤቲኤም ማሽን ይሄዳሉ፡፡  እንዳሰቡት አልሆነም፤ ማሽኑ ገንዘባቸውን ሊሰጣቸው ስላልቻለ ብድር ፍለጋ ወዲህና ወዲያ ማለት ነበረባቸው፡፡ ከዛም በኋላ ብድር ቢያገኙም ኤቲኤሙ ቢሠራ ኖሮ ሕመምተኛ አስቀምጠው ባልተሯሯጡ ነበር፡፡

  ስለዚህ ለፈጣን አገልግሎት ተመራጭ ነው የተባለው የኤቲኤም አገልግሎት፣ አንዳንዴ እንዲህ ንፉግ ሲሆን ያበሳጫል፡፡ በተለይ በቅርቡ የሁሉንም ባንኮች ኤቲኤም ማሽኖች ያስተሳሰረ አገልግሎት ይጀመራልና ይህንን አገልግሎቱን ያለ ችግር ለማስቀጠል የሚችል አሠራር መዘርጋት፤ ችግር ሲከሰትም በቶሎ የዕርምት ዕርምጃ በመውሰድ ሊከተል የሚችለውን መጉላላት ማስቀረት የግድ ነው፡፡ ችግሩ የአንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ላይ የሚታይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ዘመናዊ አገልግሎት ብዙ ደንበኞች እያፈራ የሚሄድ በመሆኑም ያለ ችግር እንዲሠራ መላ መፈለግ አለበት፡፡   

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት