Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደቡብ ግሎባል ባንክ ትርፌን በ22 በመቶ አሳደግሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ 78 ሚሊዮን ብር አተረፈ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪ እንዲቀላቀሉ ከሦስት ዓመት በፊት ፈቃድ ከሰጣቸው ሁለት የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ደቡብ ግሎባል ባንክ በ2007 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ገለጸ፡፡

ባንኩ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመታት ያልሞላው ታዳጊ ባንክ ቢሆንም፣ የ2007 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ ግን ከቀደሙት ሁለት ዓመታት የተሻለ ስለመሆኑና በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 22.6 ሚሊዮን ብር ማትረፉን የባንኩ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀደመው በጀት ዓመት ተገኝቶ ከነበረው ትርፍ 22.3 በመቶ ብልጫ አለው ብሏል፡፡

ይህ የደቡብ ግሎባል ባንክ ትርፍ ግን ከ16ቱ የግል ባንኮች ካገኙት የትርፍ መጠን ጋር ሲተያይ አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ግን በዚህ በአጭር ጊዜ በተለይ በ2007 በጀት ዓመት የተገኘው ውጤት የባንኩን ዕድገት ያሳያል ይላሉ፡፡

ባንኩ በ2007 በጀት ዓመት ያሳየው ዕድገትም በተለያየ መንገዶች ሊገለጽ እንደሚችል ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በ2006 በጀት ዓመት 874.8 ሚሊዮን ብር የነበረው የባንኩ እሴት፣ በ2007 በጀት ዓመት ወደ 1.14 ቢሊዮን ብር ማደጉ አንዱ ነው፡፡

የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን ከ500.2 ሚሊዮን ብር ወደ 819.3 ሚሊዮን ብርም ማድረስ ችሏል፡፡ የተቀማጭ ገንዘቡን መጠን በ63.8 በመቶ ማሳደግ የተቻለውም በ2006 በጀት ዓመት 15,835 የነበሩትን አስቀማጮቹን፣ በ2007 መጨረሻ ላይ 25,351 በማድረሱ ነው፡፡ የብድር መጠኑንም ከ270.3 ሚሊዮን ብር ወደ 338.9 ሚሊዮን ብር ማሳደጉን የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡

በ2007 በጀት ዓመት ባንኩ ያገኘው ገቢም በ40 በመቶ አድጓል፡፡ ባንኩ በ2006 በጀት ዓመት አግኝቶ የነበረው ጠቅላላ ገቢ 78.9 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያስታውሰው የባንኩ መረጃ፣ በ2007 ግን 111.1 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ በአሁኑ ወቅት ያለው የተከፈለ ካፒታል መጠን 197.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በቀደመው ዓመት ግን 177.2 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉን በአንድ ዓመት ውስጥ ያሳደገው በ11.7 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ይህ አፈጻጸሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ባወጣው መመርያ መሠረት ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ አለበት የሚለውን ሊያሟላ አላስቻለውም፡፡

በቅርቡም ባንኩ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታሉን ለማሟላት ባልቻለበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በድጋሜ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ አለባቸው የሚለው መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ መመርያ አንፃር ደቡብ ግሎባል ባንክ የሚፈለገውን ካፒታል ለማሟላት ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ደቡብ ግሎባል ባንክ በተለይ ዛሬ በሚካሄደው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግና ተጨማሪ አክሲዮኖችን ለመሸጥ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ሥራ ከገባ አምስተኛ ዓመቱን የያዘው አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክም የ2007 በጀት ዓመት ክንውኑን የሚያመለክተውን ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡

ባንኩ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 78.4 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው በጀት ዓመት የ30 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አስታውቋል፡፡

እንደ ባንኩ ሪፖርት ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ40 በመቶ በማሳደግ 1.1 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ በተቀዳሚው ዓመት መጨረሻ ላይ ባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 792.4 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

በበጀት ዓመቱ የወጣው ብድርም 771.2 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውቋል፡፡ ይህ የብድር መጠን ከቀዳሚው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ260.6 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ዓመታዊ ገቢውን በ61.7 ሚሊዮን ብር በመጨመር በ2007 መጨረሻ ላይ 207.4 ሚሊዮን ብር ማድረሱንም ገልጿል፡፡

እንደ ደቡብ ግሎባል ባንክ ሁሉ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክም የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ አልቻለም፡፡ የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት የሚያሳየውም በ2007 መጨረሻም የተከፈለ ካፒታሉ መጠን 366.3 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ የተከፈለ ካፒታሉን ለማሳደግ በሠራው ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ 104.7 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማሰባሰብ ችሏል፡፡ በ2006 መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 261.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ባንኩ በ2007 በጀት ዓመት 13 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ ቅርንጫፎቹን 32 አድርሷል፡፡ ባንኩ አዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ለመጀመር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጾ፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው ፈቃድ መሠረት የወኪል ባንኪንግ አገልግሎት የሙከራ ሥራ ጀምሯል፡፡

የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን ለመጀመርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድን በመጠባበቅ ላይ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ ቀደም ያለውን የብሔራዊ ባንክ መመርያና በቅርቡ ባንኮች ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ አለባቸው የሚለውን መመርያ የሚጠይቀውን ካፒታል ለማሟላት፣ ተጨማሪ አክሲዮኖችን ይሸጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ7,600 በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች