Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠርሙስና ብርጭቆ ኢንዱስትሪ ከአንድ ወደ ሁለት

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከውጭ ለሚገባ የጠርሙስ ግዥ 1.2 ቢሊዮን ብር ይወጣል

በኢትዮጵያ ሁለተኛው የጠርሙስና ብርጭቆ ማምረቻ ይሆናል የተባለው የጎዳ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ከተቋቋመ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የብርጭቆ፣ የጠርሙስና የተመሳሳይ ምርቶች እጥረትን በማየትና እነዚህን ምርቶች የሚያመርት ፋብሪካ ማቋቋም አዋጭ መሆኑን በማረጋገጥ ወደ አክሲዮን ሽያጭ በመግባት 120 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖችን ሽጧል፡፡ እስካሁን በአክሲዮኖች ሽያጭ ላይ የቆየው ጎዳ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ወደ ግንባታ ለመግባት ጊዜ ቢወስድበትም፣ በዚህ ሳምንት ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

 በኢትዮጵያ ውስጥ በጠርሙስና ብርጭቆ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማራው አንድ ፋብሪካ ብቻ በመሆኑ፣ የጎዳ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ ዕውን መሆን ሁለተኛው ሆኖ ከሁለት ዓመት በኋላ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታም 39 ሔክታር መሬት ተረክቧል፡፡

በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን ሕዳጋ ሐሙስ አካባቢ የሚገነባው የጎዳ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ ግንባታን ለማስጀመር ያስችላል የተባለው ስምምነት በሁለት ተከፍሎ የተፈረመ ነው፡፡ የመጀመርያው ስምምነት በጥምረት ከቀረቡት ኢምሃርትና ግላስ ሰርቢስስ ከተባሉ የስዊድንና የጣሊያን ኩባንያዎች ጋር የተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ተጣምረው የጠርሙስና ብርጭቆ ማምረቻ ማሽኖችን ያቀርባሉ፡፡ ጄፋር ኢንጂነሪንግ የተባለው የቻይና ኩባንያ ደግሞ የፋብሪካውን ስቲል ስትራክቸሩን ለመሥራት ከጎዳ አክሲዮን ማኅበር ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡

ለኩባንያዎቹ አገልግሎትም ጎዳ አክሲዮን 26.9 ሚሊዮን ዶላር የሚከፍል ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ የፋብሪካ ማሽነሪዎቹን አምርተውና ተክለው እንዲሁም ሙሉ የኮንስትራክሽን ግባታውን አጠናቀው በ18 ወራት ለማስረከብ ተስማምተዋል፡፡ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ይህ ፋብሪካ፣ በዓመት 90 ሚሊዮን ጠርሙሶችን የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ ፋብሪካው በዓመት ሊያመርተው የሚችለው  ጠርሙስና ብርጭቆ አሁንም የአገሪቱን ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ያለመሆኑ ተገልጿል፡፡ እንደ አክሲዮን ማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ፣ አሁን ካለው የጠርሙስ ፍላጎት አንፃር ጎዳ የተወሰነውን ብቻ የሚሸፈን ይሆናል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት እየተስፋፉ ካለው የቢራ ፋብሪዎች የጠርሙስ ፍላጎት አንፃር ሲታይ የአገሪቱ የጠርሙስ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ፋብሪካዎችም ቢከፈቱም ገበያው ይኖራቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ጥናት እንደሚያመለክተውም፣ በአሁኑ ወቅት ብቸኛው አዲስ አበባ የጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ የሚያመርተው ምርት አሁን ያለውን የጠርሙስ ፍላጎት ማሟላት የሚችለው አሥር በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ዘጠና በመቶው አሁንም ከውጭ የሚገባ ነው፡፡

አዲስ አበባ ብርጭቆና ጠርሙስ ፋብሪካ በቀን 20 ያህል ቶን ጠርሙስ ማምረት ይቻላል፡፡

 ከቢጂአይ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከሚያስፈልገው ጠርሙሶች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን እስካሁን ከውጭ ያስገባል፡፡

ሌሎቹም የቢራ ፋብሪካዎች ለምርቶቻቸው የሚሆነውን ጠርሙስ የሚጠቀሙት ከውጭ በማስመጣት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጎዳ አክሲዮን ማኅበር ጥናት እንደሚያመላክተውም፣ የጠርሙስና ብርጭቆ ፍላጎት በየዓመቱ እየጨመረ የሚመጣ ነው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ባስጠናው ጥናት እ.ኤ.አ. በ2014 ለለስላሳ፣ ለቢራ፣ ለማዕድን ወኃ፣ ለወይን፣ ለአልኮልና ለመሳሰሉት ምርቶች ማሸጊያነት የሚያስፈልጉ ጠርሙሶች ፍላጎት 64,419 ቶን ወይም 192 ሚሊዮን ጠርሙሶች ነበር፡፡ ይህ ፍላጎት እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ 74,609 ቶን ወይም ወደ 221 ሚሊዮን ጠርሙሶች ማደጉን ይጠቁማል፡፡ በቀጣይነትም ሊኖር ይችላል የተባለውን ፍላጎት የተነበየው ይህ ጥናት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 የጠርሙስ ፍላጎቱ መጠን 110,143 ቶን ወይም 327 ሚሊዮን ጠርሙሶች ይደርሳል፡፡

የጠርሙስ ፍላጎት ብቻውን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎች፣ አገሪቱ ለጠርሙስ ምርት ብቻ እያወጣች ያለው የውጭ ምንዛሪ እያደገ መምጣቱንም ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከዚህ መረጃ ዋቢ ያደረገውና ከአክሲዮን ማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ አገር ውስጥ የገባው ጠርሙስ መጠን 40,000 ቶን ሲሆን፣ ለዚህም ግዥ 517 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 ደግሞ ለጠርሙስ የወጣው ወጪ 732 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ወደ አገሪቱ የገባው የጠርሙስ መጠን ወደ 65,500 ቶን ከፍ በማለቱ 970 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የሆነ የጠርሙስ ግዥ ፍላጎት ስለነበረው ለጠርሙስ ግዥ ከ1.19 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ይጠቁማል፡፡ በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መብራቱ መለስ እንደገለጹትም፣ የጠርሙስና ብርጭቆ ምርት ከፍተኛ ገበያ ያለው መሆኑን ነው፡፡

የጎዳ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ እውን መሆንም ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ በመተካቱ ረገድ የራሱ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡  ለዚህም ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጠርሙና ብርጭቆ ፋብሪካው እውን መሆን ለዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚጠቁሙት የአክሲዮን ማኅበሩ ኃላፊዎች ደግሞ፣ በተለይ ለፋብሪካው የሚሆን ጥሬ ዕቃ እዚሁ አገር ውስጥ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደፊትም የፋብሪካውን አቅም በማሳደግ ከውጭ የሚመጣውን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ኤክስፖርት ማድረግ የሚቻል መሆኑን ነው፡፡ ለጠርሙስና ብርጭቆ ለምርት ግብዓት የሚሆኑ አምስቱ ዋና ዋና ጥሬ ዕቃዎች እዚሁ አገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

የጎዳ ፋብሪካ የግንባታ ሥፍራም ይህንኑ ጥሬ ዕቃ ከግንዛቤ በማስገባት የተመረጠ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ ከሚያስፈልጉት አምስቱ የጥሬ ዕቃ ዓይነቶች ከፋብሪካው አሥር ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ይህ ለፋብሪካው ትልቅ ዕድል ሲሆን የጥሬ ዕቃ ክምችቶቹም ለመቶ ዓመታት የሚበቃ መሆኑን የተደረገው ጥናት ያረጋግጣል ተብሏል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ እስካሁን 120 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አክሲዮኖች ተሽጧል ብሏል፡፡ ከባለአክሲዮኖች ማሰባሰብ ከሚፈለገው 150 ሚሊዮን ብር ውስጥ 120 ሚሊዮን ብር በማግኘቱ ቀሪውን 30 ሚሊዮን ብር ይሞላል፡፡ ቀሪውን የ30 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ከሸጠ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንሞላለን ብለዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ለፋብሪካው ግንባታ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ የኢንቨስትመንት ወጪ 25 በመቶውን ይሞላል፡፡ ቀሪውን 75 በመቶው ደግሞ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሚገኝ ብድር የሚሸፈን  ሲሆን፣ ለፋብሪካው ግንባታ የተደረሰው ስምምነት ለባንኩ ቀርቦ  ብድሩ ይለቀቃል የሚል እምነት አላቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች