Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኢትዮጵያ የጫማ ፋብሪካ አዲስ ተስፋ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሞሐን ኢንተርናሽናል በሚል ሥያሜ በኢትዮጵያ በንግድ ሥራ የተጀመረው የህንዱ ኩባንያ እንቅስቃሴ፣ ቀስ በቀስ በአሁን ወቅት አምስት የተለያዩ እህት ኩባንያዎች በሥሩ አካቶ፣ የሞሐን እህት ኩባንያዎች ግሩፕ በሚል እየሠራ ይገኛል፡፡ ኩባንያው ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ማስቆጠሩ ይነገርለታል፡፡ ይሁንና በደርግ ዘመን ከተወረሱት መካከል አንዱ እንደነበርም የኩባንያው ዳይሬክተርና፣ የቤተሰብ ኩባንያውን እንደገና በማቋቋም በመሥራችነት የሚመሩት ማዩር ሱርያካንት ኮታሪ ልጅ የሆኑት ሐርሽ ኮታሪ ገልጸዋል፡፡ ሞሐን ኩባንያ ሞሐን ኢንተርናሽናል፣ ሞሐን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሞሐን ዋየር ኢንዱስትሪስ፣ ቪና ትሬድ ኤንድ ኢንዱስትሪና ሞኔት ኩባንያ የተባሉትን ኩባንያዎች የሚያስተዳድረው ሞሐን ግሩፕ፣ በፕላስቲክ ጥሬ ዕቃዎች አምራችነት ከሚታወቅበት ሥራው በተጨማሪ የጫማ ማምረቻ ፋብሪካ ባለፈው ዓመት ሥራ አስጀምሯል፡፡ ይህ ፋብሪካ ‹‹ሐይላንደር›› በሚል ሥያሜ የሲንቴቲክና የቆዳ ጫማዎችን በማምረት ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ለውጭ ገበያዎችም ማቅረብ ጀምሯል፡፡ የፕላስቲክ ውጤት የሆኑና ሙሉ ለሙሉ በኩባንያው በሚቀነባበሩ ጥሬ ዕቃዎች የሚመረቱት ጫማዎች ከውጭ የሚመጡትን በመተካት ላይ እንደሚገኝ፣ ይሁንና ከቻይና የሚገቡ የፕላስቲክ ጫማዎች የኩባንያውን ምርቶች እንደሚፈታተኑ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተስተናገደ የኢኮኖሚስት መጽሔት ጉባዔ ላይ ከቀረቡት አንዱ የነበሩት ሐርሽ ኮታሪ ስለኩባንያቸው እንቅስቃሴና ስለፕላስቲክ ኢንዱስትሪው ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሞሐን ኩባንያ ከንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በፊትም እዚህ ይሠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ኩባንያው በኢትዮጵያ ስላለው እንቅስቃሴ ቢነግሩን?

ሃርሽ ኮታሪ፡- አባቶቼ ሞሐን ኢንተርናሽናል ኩባንያን በኢትዮጵያ ማንቀሳቀስ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በጊዜው ሸቀጦችን በማስመጣት ይሠሩ ነበር፡፡ ቀስ በቀስም የፕላቲክ ጥሬ ዕቃዎችን ለኢትዮጵያ በማስመጣት ቀዳሚዎች ሆነናል፡፡ ከዚህ ጀምሮ እያደገን መጥተናል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1995 ጀምሮ ደግሞ የሚስማር ማምረቻ ፋብሪካ ከፍተናል፡፡ ከግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ የሚስማር ፋብሪካ በመክፈትም ቀዳሚዎች ነበርን፡፡ በአሁኑ ወቅት የአትሊን ቪኒል አሲቴት (የኢቪኤ) ጥሬ ዕቃ ማምረቻ አለን፡፡ የፒቪሲ ጥሬ ዕቃዎች ማምረቻና ሌሎች የፕላስቲክ ውጤት የሆኑ የከለር መሥሪያ ጥሬ ዕቃዎች ወይም ከለር ማስተርባች የሚባለውን እናመርታለን፡፡ ነጠላ ጫማ ለማምረት የሚረዱ ጥሬ ዕቃዎችንም እናመርታለን፡፡ የተለያዩ የጫማ ዓይነቶችን የምናመርትበት ፋብሪካም ገንብተናል፡፡ ቫለሪና፣ ስኒከር፣ ካንቫስ ወይም ሸራ ጫማ፣ በጣም ከፍተኛ የጥራትና የውበት ደረጃ ያላቸውን ነጠላ ጫማዎች ጨምሮ በርካታ ጫማዎችን እያመርትን እንገኛለን፡፡ በጠቅላላው አምስት የማምረቻ ፋብሪካዎች አሉን፡፡ ሁለት ተጨማሪዎች በቅርብ የተገነቡ ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በጠቅላላው ሞሃን ይህ ነው ማለት ነው?

ሐርሽ ኮታሪ፡- እርግጥ እኛ ይህ ብቻ ነን ማለት አይደለም፡፡ አበክረን የምናምናው ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን የምንወጣ ኩባንያ ጭምር እንደሆንን ነው፡፡ ወላጅ ያጡ ሕፃናትን እንደግፋለን፡፡ መስማት የተሳናቸውን እንደግፋለን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በዚህ የቤተሰብ ኩባንያ ውስጥ ስንተኛው ቤተሰብ ወይም ትውልድ ነዎት?

ሐርሽ ኮታሪ፡- እኔ አራተኛው ትውልድ ነኝ፡፡ ልጄ አምስተኛው ነው፡፡ ቤተሰቤ እዚህ አገር ከመቶ ዓመት በላይ ቆይቷል፡፡ ይህ ዓመት በዚህ ያለን ቆይታ መቶኛ ዓመት የሚዘከርበት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ይጠይቁኛል፡፡ ኩባንያችሁ በዚህ አገር ምን ያህል ኢንቨስት አድርጓል፤ እናንተ ምን ያህል ገንዘብ ኢንቨስት አድጋችኋል ይሉኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እርግጥ ይህ የሪፖርተርም ጥያቄ ነው?

ሐርሽ ኮታሪ፡- እንግዲያውስ ምላሼም አጭር ነው፡፡ እኛ የትኛውም የውጭ ኢንቨስተር ኢንቨስት ካደረገው በላይ ኢንቨስት አድርገናል፡፡ ምክንያቱም ቤተሰቦቼ የመቶ ዓመት ዕድሜያቸውን ኢንቨስት አድርገዋልና፡፡ ለዚህ ዋጋ የሚተመንለት አይመስለኝም፡፡ በነገሥታቱ ዘመን የራሳችን ንግድ ሥራዎችና ሀብትም አካብተናል፡፡ በደረግ ዘመን ሁሉ ነገር እንዳልነበር ሆኗል፡፡ አባቴ እንደገና ሁሉን ነገር ከባዶ መጀመር ነበረበት፡፡ በመሆኑም አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን በገንዘብ መመዘን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በጣም የተለየና ስሜታዊ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ አንድ ሰው መጥቶ ሽጉጥ ጭንቅላቴ ላይ ደግኖ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወይም አሥር ቢሊዮን ዶላር ውሰድና በኢትዮጵያ ያለህን ሁሉ ትተህ ሂድ ቢለኝ፣ ምላሼ አይሆንም ነው፡፡ ምክንያቱም ዕድገታችን እዚሁ ነው፡፡ ሕይወታችን እዚሁ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ እርግጥ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን የሒሳብ ባለሙያዎች ስለካፒታላችሁ ሲጠይቁ እንዲህ ያለው ምላሽ የሚመለስላቸው አይመስለኝም?

ሐርሽ ኮታሪ፡- አዎን ግን እንዲህ ያለው ነገር ከሒሳብም በላይ የሚሄድ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ ከዚህ ቀደም በኢኮኖሚስት መጽሔት በተዘጋጀው ጉባዔ ወቅት ሲናገሩ እንደሰማነው የሲንቴቲክ ምርት ውጤት የሆኑ ምርቶችን እያመረታችሁ ነው፡፡ በዓለም ላይ 60 ከመቶው ምርት ከሲንቴቲክ ምርቶች የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡ እስኪ ስለዚህ ይንገሩን?

ሐርሽ ኮታሪ፡-  ወጣቱ ትውልድ በዚህ ዘመን በሲንቴቲክ ጫማዎች ላይ አተኩሯል፡፡ ይህም ከፋሽን ጋር፣ ቀላል ክብደት ካላቸው ጫማዎች ምርጫ አኳያ እንዲሁም ለአካባቢ ተስማሚነት ካላቸው አስተዋጽኦ ጭምር ሊሆን ይችላል እነዚህን ምርቶች የሚያዘወትረው፡፡ የሲንቴቲክ ጫማዎች ለአካባቢ ያላቸው ተስማሚነት ጥርጥር የለውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በበርካታ ምክንያቶች ሳቢያ ከቬትናም የወጣ አንድ መረጃን እንዳነበብኩት ከሆነ 60 ከመቶው የዓለም ፍላጎት ሲንቴቲክ መጫሚያዎችን ምርጫው ያደረገ ሕዝብ አለ፡፡ የተቀረው የሌዘር፣ የፕላስቲክ ውጤቶች የሆኑ ጫማዎችን ይጫማል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በዓለም ደረጃም ብቻ ሳይሆን በአካባቢና በአገር ውስጥ ፍጆታ አኳያ ስናየው ትልቅ ነገር አለ፡፡ የኢትዮጵያ ዕድገት አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ዕድገቷ ፈጣን ነው፡፡ በርካታ የወጣት ትውልድ መገኛ ነች፡፡ ወጣቶች በጣም ብሩኅ፣ ብልህና ገንዘብ ያላቸው ናቸው፡፡ መካከለኛ ደረጃ ኑሮ ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ፡፡ በአኗኗር ዘይቤያቸው ረገድ ሲታይ ወጣቶቹ የራሳቸው ፍላጎት አላቸው፡፡ ይህንን ፍላጎታቸውን የሚያሟላ መኖር አለበት፡፡ በተለይ በጫማ ዘርፍ ረገድ ለወጣቶች ጥሩ አማራጭ ነን ብለን እናምናለን፡፡  ከምቾት፣ ከስታይል ምርጫ አኳያ ሲታይ ከዚህም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን በመሆናቸው ጭምር ሊደሰቱባቸው የሚችሉ ምርቶችን አቅርበናል፡፡ ሐይላንደር በሚል ብራንድ የምናመርታቸው ጫማዎች በኢትዮጵያ ተመርተው ወደ ዓለም ገበያ ለመግባት የሚያስችሉ ምርቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በአብዛኛው የኢትዮጵያ የጫማ ምርት ከቆዳ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንን ገበያ በሲንቴቲክ ምርቶች መወዳደር እንዴት ይታሰባል? እንዴትስ ወደ ውጭ ገበያ በመውጣት ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላሉ?

ሐርሽ ኮታሪ፡- በአሁኑ ወቅት የእኛ ዋና ተፎካካሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ አምራቾች አይደሉም የሚፎካከሩን፡፡ በርካታ የቻይና ጫማዎች እየገቡ ነው፡፡ በርካታ ሲንቴቲክ ጫማዎች ከቻይናና ከሌሎችም አገሮች እየገቡ ነው፡፡ ከቆዳ ጫማዎች ጋር በተያያዘ እኛም የቆዳ ጫማዎችን እናመርታለን፡፡ በአብዛኛው ለአዘቦት የሚሆኑና ለስፖርት የሚዘወተሩ ጫማዎችን ከቆዳ እናመርታለን፡፡ በተለይ ለስፖርት የሚውሉ የጫማ ሶሎችንም ራሳችንን እናመርታለን፡፡ ይህ ለየት የሚያደርገን ለምንድን ነው ካልን የራሳችንን ከጎማና ከኢቪኤ ጋር የተጣመረ ልዩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምናመርት መሆናችን በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት አምራቾች ተርታ ያሠልፈናል፡፡ በርካታ ጫማ አምራቾች ሶል ሲሠሩ አየር ለማስገባት የሚረዱ ክፍተቶችን በመተው ልስላሴን ለመፍጠር ይሞክራሉ፡፡ እኛ የምንጠቀምበት የኬሚካል ሥሪት ልስላሴን ለመፍጠር የግድ የአየር ማስገቢያን በመተው ሳይሆን አየርን በተሻለ መጠን ለማስገባት የሚያችል አሠራር ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የሰውን ጭነት በቀላሉ እንዲቋቋሙ ተደርገው ለጂምናዚየም ወይም ለሩጫ ስፖርቶች የሚውሉ ምቾት የሚሰጡ ጫማዎችን እያመረትን እንገኛለን፡፡ በርካታ የፕላስቲክ ውጤቶችንም እናመርታለን፡፡ ፕላስቲክ ይህ ምድር ካሏት ስጦታዎች መካከል ለአካባቢ ተስማሚና በጣም ጠቃሚው ነገር ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄው እንዴት ይወገዳል የሚለው መሆን አለበት ማለት ነው?

ሐርሽ ኮታሪ፡- አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር በጣም ውበት ያለው አውሮፕላን ነው፡፡ ነዳጅ ቆጣቢና ዝቅተኛ የበካይ ጋዝ መጠን የሚለቅ ነው፡፡ ይህ ለምንድን ነው ቢባል በጣም ቀላል ክብደት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የፕላስቲክ ውጤቶችና ሰው ሠራሽ ፋይበር በሚገባ ጥቅም ላይ ስለዋለበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ መለስተኛ መኪና በአማካይ 50 ከመቶው የፕላስቲክ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ይህም ሆኖ የፕላስቲኩ ክብደት ግን ከጠቅላላው አሥር ከመቶ ቢሆን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የፕላስቲክ ውጤቶች የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀትን የመቀነስ አቅም እንዳላቸው ነው፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ውጤቶች ትተን በየቀን ሕይወታችን ያለውን ሒደት እንኳ ብንመለከት አብዛኛው ነገር የፕላስቲክ፣ የእንጨት ወይም የብረት ውጤት ነው፡፡ እንጨቱ የዛፎችን መጨፍጨፍ ያስከትላል፡፡ ፕላስቲኮች ለእንዚህ ያሉ ነገሮች ጥሩ ምትክ ናቸው፡፡ በየቦታው የሚጣለው ቆሻሻ በአብዛኛው ፕላስቲክ ነው ካልን ደግሞ በአዲስ አበባ የፕላስቲክ ውጤቶችን በመሰብሰብ መልሰው ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡ ሰዎች የኑሮ ሕልውና እየሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀን ወይም በወር ምን ያህል የማምረት አቅም አላችሁ?

ሐርሽ ኮታሪ፡- እንደጫማው ዓይነት ይለያያል፡፡ ሆኖም በአማካይ በቀን 2500 ጥንድ ጫማዎችን እናመርታለን፡፡

ሪፖርተር፡-  ገበያው ውስጥ ያላችሁ ድርሻ እንዴት ይገለጻል?

ሐርሽ ኮታሪ፡- ሐይላንደር ብራንድ ጫማ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰፊው እየተለመደ መጥቷል፡፡ መርሳት የሌለብን ምርቱን ከጀመርነው ገና አንድ ዓመት ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ጥሩ የገበያ ተቀባይነት አግኝተንበታል፡፡ ሰዎች ምርታችንን በብዛት እንደሚፈልጉ አይተናል፡፡ አከፋፋዮቻችን በብዛት እንድናቀርብ እየጠየቁን ነው፡፡ ዲር የሚል ስያሜ የተሰጣቸውና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሰንደል ወይም ነጠላ ጫማዎቻችን በጣም ታዋቂነትን አትርፈዋል፡፡ ጥሩ ገበያ አላቸው፡፡ ይህ የሆነው በጥራትና በዋጋ ደረጃ ያለን ተወዳዳሪነት ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ከቻይናም ሆነ ከጎረቤት አገሮች የሚመጡ ተመሳሳይ ጫማዎች አይወዳደሩንም፡፡ በፋብሪካዎቻችን ከጥሬ ዕቃ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ጫማ ድረስ ያለውን ሒደት እኛው ስለምናመርት በገበያው ያለንን ተፎካካሪነት አጉልቶታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካለን የጥራት ምርት አኳያ እንደውም ከቻይና ከሚገቡት ምርቶች በዋጋ ደረጃ የእኛዎቹ ወደድ እያሉ ነው፡፡ ደንበኛው ምንም እንኳ በዋጋ ደረጃ ወደድ ቢልም የእኛን ምርት እየመረጠ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ተገቢ ጥራት ያለውን ምርት ምርጫው እያደረገ ነው፡፡ ጥሩ ምቾት ያለውንና ተስማሚ ዲዛይን ያለውን ምርት እየፈለገ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ለምሳሌ በእንግሊዝ ወይም በአሜሪካ ሰዎች ነጠላ ጫማ የሚጫሙት ለተወሰነ ሰዓት ነው፡፡ ቤት ሲሆኑ ወይም በመታጠቢያ ቤት ነው በአብዛኛው ነጠላ ጫማ የሚጫሙት፡፡ በኢትዮጵያ ግን ቀኑን ሙሉ ወይም የወሩን ቀናቶች በሙሉ ነጠላ ጫማ የሚጫሙ በርካቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የእኛ የጥራት ደረጃ እነዚህን ባህሪያት ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸው፡፡ ከባድ ዕቃዎችን የሚሸከሙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ያለችግር ሊገለገሉባቸው የሚችሉና ጥንካሬ ያላቸውን ምርቶች እያቀረብን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከሲንቴቲክ ምርቶች አኳያ  ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የሚያስችል አቅም ላይ ደርሳችኋል ማለት ነው?

ሐርሽ ኮታሪ፡- ለአገር ውስጥ ገበያ በተለይ ካለን የተጣመረ የምርት ሒደት አኳያ ችግር የለብንም፡፡ ይህም ሆኖ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ይቀረናል፡፡ በተለይ ከጉምሩክ ታሪፍ አኳያ በመንግሥት መታየት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እርግጥ በመንግሥት በኩል የምንሰጣቸውን ሐሳቦች ተቀብለው በመተግበር ረገድ ያላቸውን ንቁነት እናደንቃለን፡፡ ይህም ሆኖ የመንግሥት ፖሊሲ ለንግዱ ዘርፍ የሚያበረታታ ይዘት ያለው ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ያለንን ተሳትፎ በተመለከተ እስካሁን ለሁለት አገሮች ምርቶቻችን ልከናል፡፡ ጥቂትም ቢሆን ለሲንጋፖርና ለኡጋንዳ ምርቶቻችንን ልከናል፡፡ በውጤቱም ጥሩ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ምርቶቹ ያላቸው ተቀባይነት በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከአገር ውጭም ጥሩ ምርት በማምረት ጥሩ ደንበኞችን ማግኘት እንደምንችል አይተናል፡፡ ለበርካታ የጫማና የቀላል እጅ ቦርሳዎች መሥሪያነት የሚውል ጥሬ ዕቃ ነው፡፡ የፒቪሲ ቱቦዎችን ለሚያመርቱ፣ የኤሌክትሪክ ኬብሎች ለሚያመርቱና ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ኩባንያዎች በብዛት እያቀረብን እንገኛለን፡፡ ከ200 በላይ ደንበኞች አሉን፡፡ ምርቶቻችን በሁሉም የምርት እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ 20 ከመቶው የፒፒ ከረጢት እኛ ያመረትነውን ጥሬ ዕቃ የሚጠቀም ነው፡፡ ትልቅ የገቢ ምርትን በመተካት ረገድ ሚናችንን እየተወጣን ነው፡፡ የስኳር ምርትን ጨምሮ በርካታ የግብርና ውጤቶች እኛ በምናመርታቸው ጥሬ ዕቃዎች በተመረቱ የፒፒ ከረጢቶች የሚታሸጉ ናቸው፡፡ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን የሚያመርቱ፣ ቤት አልሚዎች፣ ሬስቶራንቶች ወዘተ. የእኛን ምርቶች ይጠቀማሉ፡፡ የምርት ማቅለሚያ ጥሬ ዕቃዎች፣ ውኃ ማጠጫዎች፣ ባልዲዎች በእኛ ጥሬ ዕቃዎች የሚመረቱ ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወደ ቀደመው ጨዋታችን እንደመለስና በደርግ ዘመን ከወተረሱ ኩባንያዎች አንዱ ሞሐን ነው፡፡ አሁን ደግሞ ነገሩ ተለውጧል፡፡ ይህም ሆኖ ፈታኝ ሁኔታዎች አይጠፉም፡፡ በርካታ አምራቾች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ እርስዎም ከጠቀሱት ውስጥ ጉምሩክ አንዱ ነው፡፡ መንግሥት በአምራች ኢንዱስትሪ ረገድ ለመፍጠር የሚመኘውን ያህል እንደእናንተ ላሉ አምራቾች ያመቻቸው ተስማሚ ነገር ምንድን ነው?

ሐርሽ ኮታሪ፡- ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ በተለይ የታሪፍ ተመንን የሚመለከት ጥያቄዎች ነበሩን፡፡ ሌሎች ነገሮችን አይደለም የማነሳው፡፡ የጉምሩክ ሰዎች በዚህ ረገድ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በስህተት ዕቃዎቻችንን አዘግይተውብን አያውቁም፡፡ አንዳንዴ ግልጽ እንድናደርግላቸው የሚፈልጓቸው ነገሮች ሲኖሩ ይጠይቁናል፡፡ እናስረዳቸዋለን፡፡ ስለዚህ ይህ ነው የሚባል ችግር አልገጠመንም፡፡ እንደሚሰማኝ ኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪ ምቹ ነች፡፡ የትኛውም አገር የየራሱ ችግሮች አሉት፡፡ ይሁንና ሁሉም ኩባንያ ነገሮችን የሚመለከትበት ሚዛን ነው የሚወስነው፡፡ አንዳንዱ የብርጭቆው ግማሽ ጎደሎ ሊሆንበት ይችላል፡፡ ለአንዳንዱ ደግሞ ግማሽ ሞልቶ የቀረውን መሙላት ሊሆን ይችላል የሚታየው፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የብርጭቆው ጎዶሎነት ሳይሆን የብርጭቆው መሙላት ነው፡፡ አገሪቱ በጣም እያደገች ነው፡፡ በጣም በፍጥነት ማደግ የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም ኢትዮጵያ ስታድግ እኛም እናድጋለን ብለን እናምናለን፡፡ አያቶቼ የሚያምኑትም በዚህ ነው፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ህንዶች በደርግ ዘመን ሲሄዱ አያቴ ግን የእኔነትና የኢትዮጵያ ፍቅር ስለነበራቸው፣ ኢትዮጵያ ወደፊት ዓለም የሚያያት አገር መሆኗን ስላወቁ አሁንም ድረስ በዚህ ለመኖራችን ምክንያት ሆነዋል፡፡ በአንድ ሰው እምነት፣ በቅድመ አያቴ ዕምነት ምክንያት በኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት አብረን እየኖርን ነው፡፡ አሁን ላይ 500 ሰዎችን የሚያስተዳድሩ እህት ኩባንያዎች ያሉበት ተቋም ሆነናል፡፡ መንግሥት ብቻም ሳይሆን ኩባንያዎችም ለሕዝብ ማድረግና ማበርከት ያለብንን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ቢዝነስ ስለገንዘብ ብቻ የሚሠራ መሆን የለብትም፡፡ ስለማኅበረሰቡም መሆን አለበት፡፡ ሥርዓት ባለው መንገድ፣ በሙያ መርህ የሚመራና ማኅበረሰብ ተኮር ሥራ ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ባለበት ጊዜ በተለይ ኤክስፖርት በማድረግ ላይ ነን፡፡ ሆኖም ሸቀጥም ሆነ ጥሬ ዕቃ ለሚያመጣው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ይሁንና መንግሥት ነገሩን እየተለመከተው ነው፡፡ ባንኮችም እየጣሩ ነው፡፡ አምራቹ ክፍል የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኝ ጥረቶች አሉ፡፡ ቀድሞ ማቀድና ዝግጁ መሆን ተገቢ ነው፡፡ ትዕግሥትም ይጠይቃል፡፡ በዚህ መልኩ ፋብሪካህ ሳይዘጋ መሥራት ትችል ይሆናል፡፡ እጥረቱን ለማሻሻል የውጭ ኢንቨስትመንትና ኤክስፖርት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓመት ምን ያህል ሽያጭ ታከናውናላችሁ፣ ገቢያችሁ ምን ያህል ነው?

ሐርሽ ኮታሪ፡- እንዲህ ያለውን ጥያቄ ለመመለስ መብቱ ያለው አባቴ ነው፡፡ እኔ ይህንን ለመመለስ ሥልጣን የለኝም፡፡ ይህም ሆኖ ሥራችን ግልጽ በመሆኑ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ወይም ከዓለም አቀፍ የብድር ደረጃ የሚያወጡ ተቋማት ዘንድ ሳይቀር መረጃውን እንሰጣቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ጥያቄ ያቀረብሁት ኩባንያው ለመቶ ዓመት የኖረ እንደመሆኑ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ ለመገንዘብ ይረዳል ከሚል መነሻ ነበር?

ሐርሽ ኮታሪ፡- ምንም እንኳ ለመቶ ዓመታት ቤተሰቦቻችን እዚህ ቢኖሩም፣ ኩባንያው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ነው እንደገና ሥራውን የጀመረው፡፡ ጠቃሚው ነገር ግን ምን ያህል እንሸጣለን የሚለው ሳይሆን ምን ያህል ዋጋ ያለው ነገር እያስገኘን ነው የሚለው ነው፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች