አዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን መነሻ አድርጎ የተነሳው አለመግባባት ወደ ግጭት ከዞረ አራተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል፡፡ በግጭቱ ከባድ የሰውና የንብረት ጉዳት መከሰቱ ቢነገርም የጉዳቱን መጠን መንግሥት አላሳወቀም፡፡ ይሁንና እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ገለጻ፣ የሟቾች ቁጥር ከ81 በላይ ሲደርስ የተጎጂዎች ቁጥር ደግሞ ከ500 በላይ ነው፡፡ መንግሥት ግን በቃል አቀባዩ በኩል ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን በመግለጽ የቁጥር ጨዋታ ውስጥ አልገባም ብሏል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነገአ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሟቾችንና የተጎጂዎችን ቁጥር በሚመለከት ፓርቲያቸው በቂ መረጃ አለው፡፡ በዚህ ቁጥር ላይ ከኦሮሚያ ክልል የተሰጠ መረጃ የለም፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሲባባስ የቆየው ግጭት ለሕይወትና ንብረት መጥፋት መንስዔ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለአካባቢው ሕዝብ ሥጋት ሆኗል፡፡
በሥጋት ውስጥ ከሚዳክሩት መካከል የአርሲ በቆጂው እህል ነጋዴ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለደኅንነቱ በመሥጋት ስሙን ለመግለጽ ያልፈለገው ጎልማሳ፣ ሪፖርተር በምዕራብ አርሲ ዶዶላ ከተማ አግኝቶ አነጋግሮታል፡፡
በምዕራብ አርሲ የምትገኘው ዶዶላ ከአዲስ አበባ ከተማ በምሥራቅ በኩል በግምት 234 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በስንዴ ምርቷ የምትታወቀው ዶዶላ በሳምንት ሁለት ጊዜ የገበያ ቀናት አሏት፡፡
አንደኛውና ትልቁ ገበያ ሰኞ ሲውል ሁለተኛውና አነስ ያለው ገበያ ዘወትር ሐሙስ ይውላል፡፡ የበቆጂው ነጋዴ ከአንድ ሳምንት በፊት ሐሙስ ገበያው እንደቆመ፣ እንደተለመደው የስንዴ ግብይቱን በሚፈጸምበት ወቅት የዶዶላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ላይ ሲለቀቁ፣ ድንገት ግጭት ተቀስቅሷል፡፡ ግጭቱ ለገበያ የወጡ ሰዎች የተቀላቀሉበት በመሆኑ የከፋ ቀውስ ማስከተሉን ጎልማሳው ነጋዴ ገልጿል፡፡
ዶዶላ ከተማ ወደ ባሌ ዞንና ወደ ሻሸመኔ ከተማ የሚያስወጡ መንገዶች አሏት፡፡ የማስተር ፕላን ጥያቄ በዋናነት በማንሳት ከኋላው የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተስተጋቡበት ግጭት፣ ወዲያውኑ ሁለቱም መንገዶች በትላልቅ ድንጋዮች የተዘጉ ሲሆን በተለያዩ ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ነጋዴው ተናግሯል፡፡
በዚህ ግጭት ጥቃት ከተሰነዘረባቸው መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የወረዳው ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት፣ የገቢዎች ጽሕፈት ቤት፣ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ኮንቴነሮች ይገኙበታል፡፡
ከዚህ ባሻገር ከከተማው አመራሮች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ነጋዴዎች የገነቧቸው የንግድ ተቋማት፣ አምቡላንሶችን ጨምሮ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል፡፡
ጎልማሳው ነጋዴና የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ጥቃት የአራት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና በርካታ ሰዎችም መቁሰላቸውን ሲናገሩ፣ የምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላ ከተማ የሕዝብ ሐሳብ ጥናትና ሚዲያዎች ምርመራ የሥራ ሒደት መሪ አቶ አልይ ጉገቶ ግጭቱ መነሳቱን ቢያምኑም የሞተ ሰው እንደሌለ አስተባብለዋል፡፡
አቶ አልይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ ‹‹ተማሪዎችን በመጠቀም ፀረ ሰላም ኃይሎች ለሁከቱ መባባስ መንስዔ ነበሩ፤›› ሲሉ አቶ አልይ አስረድተዋል፡፡
አቶ አልይ የፀረ ሰላም ኃይሎች ጉዳዩ ያልገባቸውን ተማሪዎች ከፊት በማድረግ በአካባቢው ትልቅ ገበያ በሚቆምበት ሰኞ ዕለት፣ ከፍተኛ ጥፋት ለማድረስ አቅደው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይህንን ሁከት ለማስቀረት የከተማው አስተዳደር በዕለቱ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ በማድረግ ክስተቱን ማስቀረቱንም ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር በሥፍራው በተገኘበት ወቅት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የንግድ ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ሁኔታው ከፍተኛ ሥጋት በመፈጠሩም የከተማው ነዋሪዎች በጊዜ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ለመግባት መገደዳቸውንም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ግጭቱ የተባባሰው በማስተር ፕላኑ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የነዋሪው ሕዝብ የቆየ ብሶት፣ በከተማው የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ኅበረተሰቡ ለሚጠይቀው አገልግሎት ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት ጭምር ነው፡፡
እንደ በቆጂው ነጋዴ በአካባቢው የንግድ ሥራ ለማከናወን ለመጡ ዜጎችም ክስተቱ አስፈሪና ለከፍተኛ ችግርም የዳረገ ነበር፡፡
የበቆጂው ነጋዴ እንደገለጸው የሸመተውን ስንዴ ሸክፎ ከአካባቢው ለመውጣት ቢያስብም፣ ከከተማው የሚያስወጡት መንገዶች በመዘጋታቸውና ዝር የሚል ተሽከርካሪም በመጥፋቱ ለከፍተኛ ችግር ዳርጎታል፡፡
ከግጭቱ በኋላ ያሉት ቀናት ግጭት ያረገዙ በመሆናቸውም ገበሬው ምርት ወደ ገበያ እያወጣ አለመሆኑን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አቶ አልይ ግን ባለፈው ዓርብ ሪፖርተር ወደ ኅትመት ከመግባቱ በፊት በቴሌፎን እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ገበያውም በሰላም እንዲካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው በማለት አቶ አልይ ገልጸዋል፡፡
ከዶዶላ ከተማ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዳባ ከተማ፣ ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል፡፡ እንዲያውም ከዶዶላ ከበድ ያለ ውድመት መከሰቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የተነሳው ግጭትም ለአራት ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑንና በርካታ ንብረት መውደሙን እንደሰሙ አቶ አልይ ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ በአዳባና ዶዶላ ብቻ አይበቃም፡፡ ይልቁኑ በመላው ኦሮሚያ ድንገት ተቀስቅሶ ከባድ ውድመት ማድረሱ እየተነገረ ነው፡፡
በመካከለኛ ኢትዮጵያ የሚገኘው ኦሮሚያ ክልል፣ በጠቅላላ 363,375 ካሬ ኪሎ ሜትር (ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 34.3 በመቶ) ይሸፍናል፡፡
ኦሮሚያ ክልል ከትግራይ በስተቀር ከሁሉም ብሔራዊ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡ ክልሉ 18 ዞኖች፣ 309 መስተዳድሮች፣ 564 የከተማ መስተዳድሮችና 6,712 ቀበሌዎች አሉት፡፡
የግጭት መንስዔ የሆነው ከስድስት ዓመታት በፊት የተዋቀረው አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት በየአሥር ዓመቱ ተግባራዊ የሚደረግ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይ በ1996 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ሲተገበር የቆየው ማስተር ፕላን በ2006 ዓ.ም. የመጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል፡፡
ይህ ማስተር ፕላን የመጠቀሚያ ጊዜው ከመብቃቱ በፊት ለአሥር ዓመት የሚሆን ማስተር ፕላን መዘጋጀት ነበረበት፡፡ በዚህ ወቅት ይህንን ማስተር ፕላን የሚያዘጋጅ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሚቋቁምበት ወቅት አንድ ገዢና ጠቃሚ የተባለ ሐሳብ ከባለሙያዎች ተነስቷል፡፡
ይህ ሐሳብ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አዲስ አበባን ከቦ የሚገኝ በመሆኑ፣ የሁለቱ አስተዳደር አካላት ፕላኑ በተቀናጀ መንገድ ቢዘጋጅ ጠቀሜታው የጎላ ነው የሚል ነው፡፡
ይህ ሐሳብ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ከሁለቱም አካላት በተውጣጡ ባለሙያዎች የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት ተቋቁሟል፡፡
የጋራ ማስተር ፕላኑ የሁለቱን አስተዳደር አካላት ጥቅም ያስጠብቃል ከመባሉ በተጨማሪ፣ ሁለቱም የአስተዳደር አካላት በራሳቸው ክልል ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
የተዘጋጀው ማስተር ፕላንም በአዲስ አበባ በኩል ያለው በአዲስ አበባ ምክር ቤት፣ በልዩ ዞኑ በኩል ያለው በጨፌ ኦሮሚያ ሲፀድቅ ብቻ ወደ ሥራ እንዲገባም በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ነገር ግን በማስተር ፕላኑ ምክንያት የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ከነዋሪዎች በመነሳታቸው ጉዳዩ ወደለየለት ደም አፋሳሽ ግጭት አምርቷል፡፡
በተለይ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ፣ በምዕራብ ሐረርጌ በደኖ ወረዳ፣ በምዕራብ ሸዋ ቶሌ ወረዳ፣ አዳበርጋ ወረዳ (ሙገር)፣ ምዕራብ ሸዋ ጨሊያ፣ ባብች ከተማና ጌዶ ከተማ፣ ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ፣ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ ከተማ፣ ወንጭ ከተማ፣ ግንደ በረት ወረዳ፣ ጊንጪ ወረዳ፣ ጪቱ ከተማና በመሳሰሉት የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭት ተከስቷል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የተነሳው ግጭት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን፣ በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች ቀላል የማይባል ግጭት ተነስቷል፡፡ ባለፈው ዓመትም በአምቦና በአካባቢው በዚሁ ምክንያት ሁከት ተነስቶ የሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱ አይዘነጋም፡፡
ይህ ክስተት በዋነኛነት ማስተር ፕላኑን መነሻ ያድርግ እንጂ፣ በኦሮሚያ ክልል የተንሰራፋው መጠነ ሰፊ ብልሹ አሠራር የወለደው እንደሆነ የክልሉ ልሂቃን ይናገራሉ፡፡
የክልሉ መንግሥት በበኩሉ በተለይ ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ኅብረተሰቡን በማወያየት በኩል ክፍተት መኖሩን በማመን፣ ጉዳዩ ወደ ጥፋት መዞሩ ላይ ግን ፀረ ሰላም በሚላቸው ኃይሎች ላይ ጣቱን ቀስሯል፡፡
ይህንን ችግር ለመቆጣጠር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ፣ የክልሉ የፀጥታ ጉዳይ አመራሮች፣ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት የፀጥታና የፖለቲካ አመራሮች ቡድን ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ከትሟል፡፡
‹‹ኮማንድ ፖስት›› በሚል ስያሜ የተቋቋመ ቡድን ችግሩ የተከሰተባቸውን ቦታዎች ላይ ከሚገኙ የፀጥታና የፖለቲካ አመራሮች ጋር ቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሞከረ መሆኑ ተስተውሏል፡፡
ግጭቱ በተነሳባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶች በቀላሉ ሊነሳ በማይቻል የድንጋይ ክምር፣ የነዳጅና የጭነት ከባድ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲገታ ማድረጋቸው ታይቷል፡፡
የክልሉ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች፣ የየአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ ሳይቀር ጥቃት ደርሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአበባ እርሻዎች የሲሚንቶ ማምረቻዎች በተለያየ ደረጃ የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ተብሏል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው የተከሰተውን የሰላም ዕጦት ወደ ቦታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ መሰንበቱ ተነግሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል የካቢኔ አባላት ችግሩ ጎልቶ በታየባቸው አካባቢዎችና ችግር ቢፈጠር አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠርባቸው ይችላል በሚባሉ ቦታዎች በመጓዝ፣ ሕዝቡን በማወያየት ሥራ ተጠምደዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምንጮች እንደተናገሩት፣ በተለይ ውይይት በተካሄደባቸው አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም መጥቷል፡፡ የአስተዳደር አካላትም ወደ ዕለት ተዕለት ሥራ እንዲመለሱ እየተደረገ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለግጭቱ መባባስ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ አካላትም በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ግጭት አውግዘዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታኅሳስ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥት የሚረቀቁ የልማት ዕቅዶች ሦስት ምሰሶዎችን የተከተሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ሥልጣን ባለቤትነት የተከተሉ፣ የክልል ወሰኖችንና የመንግሥታቱ ሥልጣን የሚያከብሩና የሕዝብን የነቃ ተሳትፎና ባለቤትነት ያረጋገጡ ናቸው፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞንና የአዲስ አበባ የተቀናጀ የልማት ዕቅድ በረቂቅ ደረጃ ያለ፣ ሕዝቡ ተወያይቶበት ሊሻሻል የሚችል፣ የሕዝቡን ይሁንታ ካላገኘም እስከመቅረት የሚሄድ ነው ብለዋል፡፡
ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ሰነዱም በረቂቅ ደረጃ እያለ የተከሰተው ሁከት ፀረ ሰላም ኃይሎች የፈጠሩት ነው በማለት፣ በእነዚህ አካላት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወስድና እየተወሰደም እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳም በዕለቱ ተመሳሳይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ቴክኒክ ኮሌጆች የመማር ማስተማር ሒደት ተስተጓጉሏል፡፡ የትራፊክ እንቅስቃሴዎችም እየተስተጓጎሉ በመሆናቸው በሰላም ወጥቶ መግባት ሥጋት እየሆነ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ለክልሉ ሕዝብና አጎራባች አካባቢዎች ሰላም ለማምጣት ኮማንድ ፖስቱና ብሔራዊ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ታች ላይ እያሉ እንደሚገኙ ታይቷል፡፡ የበቆጂው ጎልማሳ ነጋዴ የተለመደው ሰላም ሰፍኖ፣ ወደ ንግዱ ሥራው መግባትን ይሻል፡፡ በሌላ በኩል በግጭቱ መንግሥትን እስከ መገልበጥ የሚያደርስ አመፅ መነሳት አለበት የሚሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይቀሰቅሳሉ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ መነሻው ማስተር ፕላኑ ቢሆንም፣ በግጭቱ ውስጥ ነፍስ የሚዘሩ ተገቢነት ያላቸው ጥያቄዎች መነሳታቸውን መንግሥት መቀበል እንደሚኖርበት በብዙዎች ይታመናል፡፡
በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሙስና፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን በሚመለከት ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቁ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን በማንሳት ጥያቄ የሚያቀርቡም አሉ፡፡ መንግሥት ሁሉም ነገር በሕዝቡ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ይከናወናል እያለ ነው፡፡ በፍራቻ ምክንያት ኮሽ ሲል የሚበረግጉ ዜጎች የኦሮሚያ የቀድሞ ሰላም ተረጋግቶ ይመለስ ዘንድ ይጠብቃሉ፡፡
ውድነህ ዘነበ እና ዳዊት ቶሎሳ