Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለመንገድ ኮንትራክተሮች ይሰጡ የነበሩ ማበረታቻዎች ተቋረጡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንገድ ግንባታ ለተሰማሩ የአገር ውስጥ ኮንትራተሮች ይሰጡ የነበሩ ማረበረታቻዎች እንዲቋረጡ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከዚህ በኋላ የሚያወጧቸው የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች ብቃት ላይ መሠረት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም የተለያዩ ማበረታቻዎችን ሰጥቶ ያስገባቸውን ኮንትራተሮች ሲመርጥ፣ በሥራ አፈጻጸማቸው ላይ ትኩረት እንደሚያደርግና አዲስ ለሚገቡ ኮንትራክተሮች ወቅታዊ ብቃታቸው ላይ ብቻ እንደሚያተኩር ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን 100 ኮንትራተሮችን በመንገድ ዘርፍ ልማት ለማስገባት የተለያዩ ፓኬጆች ቀርፆ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ከ50 በላይ የሚሆኑ በቀጥታ በመንገድ ግንባታ መሰማራት የቻሉ ኮንትራተሮችን ማፍራቱን ገልጿል፡፡ ከዚህ ቁጥር በላይ የሚሆኑ ‘ሰብ ኮንትራት’ እየወሰዱ የሚሠሩ ኮንትራተሮችንም መፍጠሩ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን በተለይ የመንገድ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እየተጠናቀቁ ባለመሆናቸው፣ ከተለያዩ ክልሎች በየጊዜው ቅሬታዎች እየቀረቡ በመሆኑ ባለሥልጣኑ አሠራሩ ላይ ለውጥ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሚቀጠሩ አማካሪ ድርጅቶች ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ በቁጥጥሩ ላይ በመመሥረት ባለሥልጣኑ ጥብቅ ዕርምጃ የሚወስድበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ፕሮጀክት ለመንጠቅ ከመቸኮል ማስታመም ተመራጭ ነበር፡፡ አሁን ግን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ወዲያውኑ እስከመንጠቅ ያሉ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፤›› በማለት አቶ በቀለ ገልጸዋል፡፡

መንገዶች ባለሥልጣን ቀደም ሲል 100 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ ለመገንባት ቢፈልግ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራቶችን ለማስገባት በማለት ኮንትራቱ በሦስት ይከፈላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቅድመ ክፍያ ይከፍል ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህን አሠራሮች በማስቀረት በብቃት ላይ የሚያተኩር መሆኑንና ይህም ለኮንትራተሮች ጥቅም እንዳለው አቶ በቀለ ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን አቅም ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በሰፊው ለመስጠት ዕቅድ አለው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች መቀመጫ በመሆኗ የሚካሄዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ማለቅ አለባቸው፡፡

ከዚህ ቀደም የአገር ውስጥ ኮንትራተሮችን ለማበረታታት የተወሰኑ ላላ ያሉ አሠራሮች እንደነበሩ ኢንጂነር ፍቃዱ ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ጠበቅ ያለ አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

‹‹የካቲት 2007 ዓ.ም. አስፓልት መልበስ ያለባቸው መንገዶች እስካሁን አስፓልት መልበስ አልቻሉም፤›› በማለት የአገር ውስጥ ኮንትራተሮች ያለባቸውን የአቅም ውስንነት ኢንጂነር ፍቃዱ ገልጸው፣ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለው ኮንትራቶሮቹ የተሟላ መሥሪያ የሌላቸው በመሆኑ፣ አስፓልት ለማልበስ ‘ሰብ ኮንትራት’ ይሰጣሉ፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በኮንትራክተሩና በሰብ ኮንትራተሩ መካከል በሚደረግ የሁለትዮሽ ውል ውስጥ መንገዶች ባለሥልጣን ጣልቃ እንደሚገባ፣ ሦስተኛ ወገን በመሆን ሰብ ኮንትራተሩ በውሉ መሠረት ሥራ የማይሠራ ከሆነ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ኢንጂነር ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ኮንስትራክሽን ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ሥጦታው በዚህ አሠራር ይስማማሉ፡፡ አቶ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማው የሚካሄዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በወቅቱ መጠናቀቅ አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳለው ዓይነት ማስታመም እንደማይኖር አቶ አባተ አስታውቀዋል፡፡

 

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች