Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአሜሪካ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ተጨማሪ 68 ሚሊዮን ዶላር ሰጠች

አሜሪካ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ተጨማሪ 68 ሚሊዮን ዶላር ሰጠች

ቀን:

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኢትዮጵያ በኤልኒኖ ምክንያት የገጠማትን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ተጨማሪ 88 ሚሊዮን ዶላር ማበርከቱን አስታወቀ፡፡ ይህም አሜሪካ ከጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ያደረገችውን አጠቃላይ ዕርዳታ ወደ 435 ሚሊዮን ዶላር ከፍ የሚያደርግ መሆኑንና በሥርዓተ ምግብ፣ በምግብ አቅርቦትና በንፅህና አጠባበቅ ረገድ የሚደረገውንም ድጋፍ እንደሚያሳድግ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ኤም. ሃስላክ የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠው ዕርዳታ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹የአሜሪካ ሕዝብና መንግሥት ምግብ ነክና ያልሆኑ ዕርዳታዎችን ወቅቱን በጠበቀና በተጠናከረ ሁኔታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተፈጥሮዓዊ በሆነው የኤልኒኖ ክስተት ምክንያት ከገጠማት ከዚህ ቀውስ ጋር ለምታደርገው ፍልሚያ ድጋፋችንን መስጠት እንቀጥላለን፤›› ማለታቸውን ኤምባሲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት ግምት እ.ኤ.አ. በ2016 የመጀመርያዎቹ ወራት አጠቃላይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው የተረጂዎች ቁጥር ወደ 10.2 ሚሊዮን ከፍ ሊል ቢችልም፣ ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ በውጤታማ የሴፍቲኔት ፕሮግራሙ በኩል የሚረዳቸውን 7.9 ሚሊዮን ዜጎች እንደማየጨምር በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 5.8 ሚሊዮን ዜጎች የንፁህ ውኃ አቅርቦት፣ 1.7 ሚሊዮን ሕፃናትና እመጫቶች በጠቃሚ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ተጨማሪ ምግቦች፣ እንዲሁም 435,000 የሚሆኑ ሕፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት በመጋለጣቸው ምክንያት ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሃስላክና በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኤዲያን ኦሃራ በኢትዮጵያ የሕፃናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር ከጆን ግራሃም ጋር በመሆን፣ በሰሜን ወሎ በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች በድርቁ እየደረሰባቸው ያለውን ጉዳት ለመመልከትና ስለችግሩ ከነዋሪዎቹ ለመስማት፣ እነዚህን ቦታዎች ተዘዋውረው መጎብኘታቸው በመግለጫው ተገልጿል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት አምባሳደሮቹ በመቄት ወረዳ በደንከን ቀበሌ በሚገኘው እስታየሽ የዕርዳታ እህል ማከፋፈያ ማዕከል ተገኝተዋል፡፡ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ የተቀናጀ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ፣ በካቶሊክ የዕርዳታ ድርጅት የሚመራ የጋራ ጥረት፣ በሕፃናት አድን ድርጅት፣ እንዲሁም ምግብ ለተራቡ ሰዎች/ኢትዮጵያ በወረዳው ለሚገኙ ከ26,000 በላይ ተጎጂዎች አስቸኳይ ዕርዳታ በመከፋፈል ላይ መሆኑ ተወስቷል፡፡ በደንከን ቀበሌ እስካሁን 4,000 ሰዎች የምግብ ዕርዳታ መቀበላቸውን፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ መጠየቂያ ሰነዱ መሠረት በዚህ ወረዳ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት 39,087 ነዋሪዎች ወይም ከወረዳው ሕዝብ 16 በመቶ የሚሆኑት የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የቀረበው ትንበያ እንደሚያመለክት መግለጫው አስረድቷል፡፡

አምባሳደሮቹ ከማኅበረሰቡ ጋር ባካሄዱት ውይይት፣ የምግብ ዕርዳታው ከአካባቢያቸው ለመሰደድ በሚያስቡበት ወቅት በትክክለኛው ሰዓት እንደደረሰላቸው እንደገለጹላቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም አምባሳደሮቹ በ1977 ዓ.ም. በአገሪቱ በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ከተመታው የቆቦ ወረዳ ነዋሪዎችንም ጎብኝተው ኅብረተሰቡንና የቀበሌ አመራር አካላትን አወያይተዋል ተብሏል፡፡ ቆቦ በእጅጉ ተጋላጭ ከሆኑ ወረዳዎች ተርታ የምትመደብ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ፣ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ በኩል ድጋፍ የሚደረግላቸው የሴፍቲኔትና የሕፃናት አድን ድርጅት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በሰብዓዊ ዕርዳታ መጠየቂያ ሰነድ ላይ በተመለከተው መሠረት ለሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት 200,000 የሚሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ነዋሪዎቹ በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚደረግላቸውን ዕርዳታ አድንቀው፣ ለቀጣዩ ዓመት ያላቸውን ሥጋት መናገራቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች የዘሩት እህል መና መቅረቱንና ልጆቻቸውን የዕርዳታ እህል ባይሰጣቸው ኖሮ ሊመግቧቸው እንደማይችሉ በምሬት መናገራቸውም ታክሏል፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም የተመደቡ የዕርዳታ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ዕርዳታውን ለተረጂዎቹ ለማድረስ ያሉትን አማራጮች በሙሉ በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ መግለጫው አስታውቋል፡፡ ኤጀንሲው የሥርዓተ ምግብና አጠቃላይ የምግብ ዕርዳታን በስፋት ለማቅረብና ሌሎች አጋሮቹ የዕርዳታ ማቅረቢየ ሥርዓቶችን ዘርግተው በተለይ ችግሩ ጎልቶ ሊታይ በሚችልበት ከሰኔ 2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. ለሚኖረው አስቸጋሪ ወቅት በቂ የዕርዳታ እህል እንዲከማች በማድርግ ላይ እንደሚገኝ፣ በአጠቃላይ ኤጀንሲው መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል 3.9 ሚሊዮን ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዕርዳታ በማቅረብ ላይ እንደሆነ ተወስቷል፡፡

‹‹የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ ወደ 297 ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ግብዓቶችን ማቅረቡንም ያደንቃል፡፡ ለወቅቱ ችግር የኢትዮጵያ መንግሥት በቂ ምላሽ መስጠት ይችል ዘንድ አሜሪካ አስፈላጊ ግብዓቶች በወቅቱ እንዲሰበሰቡ የማስተባበር ሥራውን ለማከናወን ጎን ለጎን፣ ኢትዮጵያውያን ዘላቂ የሆነ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማጠናከር ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ጠንካራ ትሠራለች፤›› ሲል ኤምባሲው በመግለጫው አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...