Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮምን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አሳጥተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም ራሱ በዘረጋው ኔትወርክ በኩል ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ አገር ውስጥ በሚደረጉ ጥሪዎች ሊያገኝ ይችል የነበረን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በማሳጣት በተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ላይ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረተ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ታኅሳስ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ካሳሁን አያሌው የተባሉት ተከሳሽ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ የላቸውም፡፡ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ጂኤስኤም ጌትዌይ የሚባል የቴሌኮም መሣሪያ በመጠቀም ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ስልክ ጥሪዎችን ተቀብለዋል፡፡ የተቀበሏቸው የጥሪ ብዛቶች ሲሰላ 2,746,510 ደቂቃዎች ይሆናል፡፡ ይኼንን ጥሪ ያስተላለፉት ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን ኔትወርክ በማሳለፍ (Bypass) መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡

ጥሪዎቹ ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ ቢተላለፉ 11,115,106 ብር ገቢ ይገኝ እንደነበር የገለጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ግለሰቡ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪው ድርጅት (ኢትዮ ቴሌኮም) የዘረጋውን መሠረተ ልማት ወደ ጐን ትቶ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ወንጀል መከሰሳቸውን ገልጿል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ዓቃቤ ሕግ በደንበኛቸው አቶ ካሳሁን አያሌው ላይ ያቀረበውን ክስ ላይ ባቀረቡት ተቃውሞ እንደገለጹት፣ ተጠርጣሪው ተጠቀሙ የተባለውን ጊዜ በደቂቃ ከፋፍሎ ማቅረብ የተፈለገው ክሱን ሆን ብሎ ለማክበድ ነው፡፡ ክሱ መቅረብ ያለበት የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 አንቀጽ 9(1ሀ) እና (1ለ) ሥር በሚገኘው ድንጋጌ ሳይሆን፣ በአዋጁ አንቀጽ 3 (2/3) መሠረት ነው፡፡ ጂኤስኤም የተባለው የቴሌኮም መሣሪያ ዳታ ሪከርድ እንደማያደርግ ጠቁመው፣ ዓቃቤ ሕግ ዳታውን እንዴት እንዳሰላው አለመግለጹን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብላቸውና ደንበኛቸውም የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን አቶ አመሐ ጠይቀዋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ ያቀረቡትን ተቃውሞ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በመቃወም ውድቅ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪው እስከዚያው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተመሳሳይ ቀንና ችሎት ሌላው ያቀረበው ተመሳሳይ ክስ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ነዋሪ በሆኑት ተጠርጣሪ አቶ መሐመድ ሙክታር ሙአሚል በሚባሉ ግለሰብ ላይ ነው፡፡

አቶ መሐመድም የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ ከሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ለ1,103,513 ደቂቃዎች ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ተጠቅመዋል፡፡ ጥሪውን ያስተላለፉት ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን እሱን በማለፍ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ፣ 4,465,907 ብር ጉዳት ማድረሳቸውንም በክሱ አስፍሯል፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡  

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች