Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

እርሻ ሚኒስቴር የሰፋፊ እርሻ ልማት ፕሮጀክቶችን በአግባቡ እያስተዳደረ አለመሆኑን አመነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከክልሎች በውክልና የተረከባቸውን ሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬቶች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንዳልቻለ አመነ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን የገለጸው ሐሙስ ታኅሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከከፍተኛና ከመካከለኛ አመራሮች ጋር በተወያየበት ወቅት ነበር፡፡

በዚህ ውይይት መድረክ ስድስት አባላት ባሉት ኮሚቴ የተዘጋጀውን ጥናት ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳዳር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት እንደተናገሩት፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ 3.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከክልሎች በውክልና ተረክቧል፡፡

‹‹ከዚህ መሬት ውስጥ ክልሎች በራሳቸው መንገድ 2.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለኢንቨስተሮች አስረክበዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ መሬት ውስጥ ወደ ልማት የገባው ከ30 ወይም ከ35 በመቶ አይበልጥም፣›› በማለት አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው ቦታዎችን ማስተዳደር ያልቻለበትን ምክንያት ያብራሩት አቶ አበራ በክልሎች የሚገኙ አመራሮች የአመለካከት ችግር፣ የተሰጡ መሬቶችን ተከታትሎ ወደ ልማት አለማስገባት፣ የባለሀብቶች አቅም ሳይታይ ሰፋፊ መሬት ማስረከብ፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራና የፀጥታ ችግሮች ተጠቃሽ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በ2002 እና በ2003 ዓ.ም. የባለሀብቶች አቅም በአግባቡ ሳይታይ ሰፋፊ መሬት መሰጠቱ ተገልጿል፡፡ በወቅቱ በአብዛኛው አሥርና 20 ሺሕ ሔክታር መሬት የተሰጠ መሆኑን አቶ አበራ ገልጸው፣ ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን ኤጀንሲው እየሰጠ የሚገኘው ከሦስት ሺሕ ሔክታር መሬት ያልበለጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የመሬት አሰጣጡ በጥብቅ ሥርዓት መመራት አለበት፤›› ያሉት አቶ አበራ፣ የእርሻ መሬት በተሰጠባቸው አካባቢዎች በየጊዜው የሚነሳው የፀጥታ ችግርን ለሥራ አፈጻጸሙ ደካማነት እንደ ምክንያት አንስተዋል፡፡

‹‹ባለሀብቶችን ምን ያህል ተከታተልን? ምን ያህል ድጋፍ ሰጠን? የሚለው ጉዳይም መታየት አለበት፤›› ያሉት አቶ አበራ፣ ይህ ችግር ተቀርፎ በዘርፉ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በተለይ በ2008 ዓ.ም. ችግሩን ለመፍታት ስትራቴጂዎች መነደፋቸውንም አመልክተዋል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ክልሎች ለበርካታ ኩባንያዎች የእርሻ መሬት ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን የሰፋፊ እርሻዎች ፕሮጀክት ከጅምሩ ብዙ ቢባልለትም፣ ያን ያህል ውጤቱ መታየት እንዳልቻለ ሲተች ቆይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች