በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከተመሠረተባቸው ክስ በነፃ ተሰናብተው የነበሩት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ፣ የአረና ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት፣ እነ ሐብታሙ አያሌው፣ የዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ይግባኝ እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ከችሎቱ እንዲነሱላቸው ጠየቁ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ፣ ከተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ የተደረጉት፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራሮች አቶ ሐብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋና ከእነሱ ጋር ተከሰው የነበሩ አቶ አብርሃም ሰለሞን መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ በነፃ ያሰናበታቸው ቢሆንም፣ በውሳኔው ቅር የተሰኘው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ በማግስቱ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርቦ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳይፈፀም አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳይፈጸም ያገደው የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ እንኳን ሳይመለከት በመሆኑ፣ ሕጉንና መሠረታዊውን የዳኝነት አሠራር መርህ በመጣስ መሆኑን እነ ሐብታሙ አያሌው ታህሣሥ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ማመልከቻ ያስረዳል፡፡
በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 27(1ሠ) መሠረት አቤቱታቸውን ያቀረቡት እነ ሐብታሙ እንዳብራሩት፤ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ለምን እንደታገደ ግልጽ ሳይደረግላቸው፣ ያለምንም የፍርድ ቤት መጥሪያ መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በጽሕፈት ቤታቸው ያስጠሯቸው አሁን ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ ያቀረቡባቸው ሰብሳቢ ዳኛ ዳኜ መላኩ ናቸው፡፡ ዳኛው ካስጠሯቸው በኋላ ‹‹ዛሬ የጠሯችሁ ሌሎች ዳኞች ናቸው›› ብለው ከነገሯቸው በኋላ፣ ለጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንደሰጧቸው ማመልከቻው ይገልጻል፡፡
አቶ ሐብታሙን ጨምሮ አምስቱ ተጠሪዎች ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በተጻፈ መጥሪያ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቃል ክርክር እንዲቀርቡ የተላከው መጥሪያ የተፈረመው፣ በሰብሳቢ ዳኛው መሆኑን በማመልከቻቸው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ዳኛው መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው የነገሯቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የተጻፈው መጥሪያ ተቃርኖ እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳይፈጸም በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ጉዳዩ ማስቀረብ አለማስቀረቡ ሳይገለጽ፣ ለቃል ክርክር ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ማዘዛቸው፣ ችሎቱን እየመሩ ያሉት ዳኛ አስቀድመው አቋም ይዘዋል የሚል ከፍተኛ ግምት ያደረባቸው መሆኑን በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ለጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ለክርክር እንዲቀርቡ ከተላከላቸው መጥሪያ ጋር ተያይዞ በተሰጣቸው የዓቃቤ ሕግ የይግባኝ ቅሬታ ነጥብ ላይ፣ በሐብታሙ፣ ዳንኤል፣ የሺዋስና አብርሃ ላይ የቀረበ የቅሬታ ነጥብ እንደሌለ ጠቁመው፣ በክርክሩ እንዲቀጥሉ ሰብሳቢ ዳኛው መፍቀዳቸው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡
ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በቀጠሯቸው መሠረት የቀረቡ መሆናቸውን የገለጹት እነ ሐብታሙ፣ በራሳቸው ሥልጣን የቀረቡ በሚመስል ሁኔታ፣ ሰብሳቢ ዳኛው ‹‹እናንተ አልተጠራችሁም ተመለሱ›› ቢሉም፣ ይግባኝ ባይ ዓቃቤ ሕግ ግን እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱንና ለክርክር ተዘጋጅተው እንዲመጡ መታዘዙን መግለጹን ተናግረዋል፡፡
እንዲነሱ ጥያቄ የቀረበባቸው ዳኛ ጉዳዩን የያዙበት አግባብ፣ ይግባኙ ‹‹ያስቀርባል›› የመባሉ ጉዳይ የማይቀርና ያለቀለት መሆኑን እንዲገምቱ እንዳደረጋቸው በማመልከቻቸው ገልጸዋል፡፡ እንደጠበቁትም ‹‹ይግባኙ ያስቀርባል›› በማለት መጀመሪያ የጠበቁትን የሚያረጋግጠው ሁለተኛ መጥሪያ እንደተላከላቸውም አክለዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ በሚኖረው የክርክር ሒደት ዳኛ ዳኜ መላኩ ችሎቱን እየመሩበት ካለው አግባብም ሆነ፣ በሕግ ከሚጠበቅባቸው ገለልተኛነት አንፃር ትክክለኛ ፍትህ እናገኛለን ብለው እንደማያምኑ በመግለጽ፣ ከችሎቱ እንዲነሱላቸው አመልክተዋል፡፡