Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በስህተት ወይዘሪት ዩኒቨርስ የተባለችው ኮሎምቢያዊት አክሊሏን ተነጠቀች

ትኩስ ፅሁፎች

የ2015 የፈረንጆች ዓመት ወይዘሪት ዩኒቨርስ ተብላ አክሊል የተደፋላት ኮሎምቢያዊቷ አሪያድና ጉትሬስ እውነትም ውድድሩን በአሸናፊነት ማጠናቀቋን ነበር የምታውቀው፡፡ ነገር ግን ወዲያው የመድረኩ መሪ ስቲቭ ሐርቬይ አሸናፊዋን ሲጠራ ስህተት መፈጸሙን ‹‹እሺ ታዳሚዎችን ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ፤›› በማለት ተናግሯል፡፡ ቀጥሎም የውድድሩ ውጤት የሰፈረበትን ካርድ እየተመለከተ አሸናፊ የተባለችው ኮሎምቢያዊት ሁለተኛ ስትሆን፣ ትክክለኛዋ አሸናፊ ወይዘሪት ፊሊፒንስ ፒያ አሎንዞ ውርትዝባች መሆኗን አስረግጧል፡፡ ይህ ክስተት የታየበት የቁንጅና ውድድር እሑድ ምሽት (ታኅሳስ 10 ቀን 2008 ዓ.ም.) አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በቀጥታ ሥርጭት ሲተላለፍ ነበር፡፡ እውነተኛዋ አሸናፊ ውርትዝባች ሐርቬይ ማስተካከያውን ሲያደርግ በድንጋጤ ከተዋጠች በኋላ ወደ መድረኩ በመሄድ ኮሎምቢያዊቷ በስህተት የተደፋላትን አክሊል አውልቃ እንድትሰጣት ጠብቃለች፡፡ ሐርቬይ የፈጸመው ስህተት ከባድ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

*********

እኛና ‹‹አዲስ ዘመን››

     ልክ እንደ አራስ ገንፎ፣
አፍ እየተፋጀ – ጉሮሮ እንደገባ – ባ‘ፍታ እንደተዋጠ፤
እንደ ችፍርግ ጤዛ፣
በማለዳ ረግፎ – ከፀሐይ ነበልባል – ቀድሞ እንዳመለጠ፤

እንደ ዱር ሚዳቋ፣
ካ‘ዳኙ በዝላይ – እንዳፈተለከ
ግን ከድንጋጤው – እንዳላገገመ – እንደበረገገ – ጆሮው እንደቆመ፤
እንደ ሐመር ወጣት፣
ጉብሉን ለማግኘት – እንዳለከለከ
ወደ ሰማይ ጉኖ – ከበሬ ጀርባ ላይ – እመር እመር ብሎ – ወድቆ እንደደከመ፤

ምናለ ዘመንም
መሽከርከር ባቆመ
ከምህዋሩ ወጥቶ
በራቀ – በራራራራራ…..ቀ
ሺሕ ጊዜ እየመጣ
እየተቀየረ
በጉስኩል ኑሮ ላይ
ሰው ባላሳቀቀ፤

እ-ል-ም በል ዘመን – ጭልጥ በል ጊዜ
አሥሬ እየመጣህ
ተቀየርኩኝ እያልክ
ይህን ያገሬን ሰው – አትዳርግ ለትካዜ፤

አደይ ምን ብታብብ
ጨፌ ምን ቢንጫለል – በወንዙ በመስኩ
ሕይወት ሲለመልም
ኑሮ ሲታደስ ነው – የመለወጥ ልኩ፤

ይህን እንዲሆን ለኛ
ስናልም ብንውልም – ስንሻም ብንባጅ – በጥልቅ ሰመመን
እንቁጣጣሹ ሁል
አዲስ ዘመኑ ሁል
ከአሮጌ ኑሮና
ከጉስቁል ሕይወት ጋር – እየጣለን ያልፋል – ሰርክ እያሳመመን!!!

  • በደመቀ ከበደ – መሀል ሸገር

**********

በሳክስፎን የታጀበው የአእምሮ ቀዶ ሕክምና

በስፔን ማላጋ ሃያ ሆስፒታል ውስጥ የ27 ዓመት ወጣት ሙዚቀኛ ሳክስፎን እየተጫወተ የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና እንደተደረገለት ተዘገበ፡፡ ካርሎስ አጉሌራ የሙዚቃ መሣሪያውን እየተጫወተ ቀዶ ሕክምናው የተደረገለት በሕክምናው ወቅት የአእምሮ የመሥራት ብቃት (በተለይም ሳክስፎን መጫወት) እንዳለ መሆኑን እርግጠኛ ለመሆን ሲባል ነው፡፡ ካርሎስ ቀዶ ሕክምናው የተደረገለት በጭንቅላቱ ውስጥ የነበረ እጢን ለማስወገድ ሲባል ነበር፡፡ ከቀዶ ሕክምናው መጠናቀቅ በኋላ ካርሎስና ሕክምናውን ያካሄዱት ዶክተሮች ቀዶ ሕክምናው በጥሩ ሁኔታ ስለመጠናቀቁ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ሳክስፎን የመጫወት ችሎታው እንዳለ በመቀጠሉ ሐኪሞችን ያመሰገነው ካርሎስ ‹‹ከሁለት ወራት በፊት በቀዶ ሕክምና አልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ አሁን ሕይወቴ ተመልሶልኛል፤›› ብሏል፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች