ዶ/ር ተፈሪ ገድፍ፣ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ፕሬዚዳንት
ዶ/ር ተፈሪ ገድፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፋርማሲ ትምህርት ቤት የፋርማሲዩቲክስና ሶሻል ፋርማሲ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉትና የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በፍኖተሰላም ከተማ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፋርማሲ ትምህርት ቤት ገብተው በፋርማሲ ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ ጤና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን፤ እንዲሁም በጀርመን የማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ በፋርማኮኢምፒዲዮሞሎጂ የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በፋርማሲ ሙያና በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮአቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር እንቅስቃሴን በአጭሩ ቢያብራሩልን፡-
ዶ/ር ተፈሪ፡- የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ከተቋቋመ 42 ዓመታት ሆኖታል፡፡ አምስት ሺሕ አባላትን ያቀፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ወደ 54 የሚጠጉት የተቋም አባላት ናቸው፡፡ ማኅበሩ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ሙያው አድጎ ኅብረተሰቡ ከሙያው የሚጠብቀውን አገልግሎት እንዲያገኝ ነው፡፡ የአባላቱን መብት ለማስጠበቅና ግንባታ ለመስጠት ይንቀሳቀሳል፡፡ ከመንግሥት ተቋማት ጋር አብሮ የመሥራት ባህል አዳብሯል፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በሚኒስቴሩ ስር የሚገኙ ኤጀንሲዎች በሚያቋቁሙት ጊዜያዊና ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ በንቃት ይሳተፋል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበሩ የስትራቴጂክ አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡ በዚህም ስትራቴጂ ከታቀፉት አቅጣጫዎች አንዱና ዋነኛው የማኅበሩን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃ መገንባት ይገኝበታል፡፡ ሕንፃው የሚያርፈው በ630 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ ነው፡፡ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢ በግዢ ባገኘነው ስፍራ እንገነባለን፡፡ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ዓለም አቀፍ የፋርማሲ ፌዴሬሽን አባል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ፋርማሲዎች በተቀራረበ መልኩ ተከፍተው ይታያሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ቅርርብ በመካከላቸው አላስፈላጊ የሆነ የሥነ ምግባር ጥሰት አያስከትልም?
ዶ/ር ተፈሪ፡- ቀደም ብሎ የነበረው መመሪያ በ500 ሜትር አካባቢ መኖር ያለበት አንድ ፋርማሲ ብቻ ነው በሚል ያስገድድ ነበር፡፡ አሁን እንደሌሎች የችርቻሮ መደብሮች ፋርማሲዎችም ተቀራርበው ሲከፈቱ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ አላስፈላጊ የሆነ ውድድር አምጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ሙያው ሥነ ምግባሩን ጠብቆ በትክክል እንዳይካሄድ አድርጓል የሚል ሥጋት በባለሙያዎች ይገለጻል፡፡ የሥጋቱም መንስኤ አንዱ ሙያው በሚፈቅደው መሠረት ሲንቀሳቀስ፤ ከጎኑ ያለው ደግሞ ገበያን ለመሻማት ወይም ገቢን ለመሳብ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መሸጥና ታካሚው ከመጠኑ በታች እንዲሸጥለት ሲጠይቅ የመስማማት ነገር ይከሰታል ከሚል ነው፡፡ ማኅበሩ ደግሞ ሥጋቱ በጥናት መረጋገጥ እንዳለበት ነው የሚያምነው፡፡ ለፖሊሲ አውጪዎችም የሚቀርበው ጥናትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አለበለዚያ አየር ላይ ያለ ሥጋት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሥጋት ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ጋር በጋራ አጥንተን ለሙያው እንደ ማነቆ ሆኖ ከተገኘ አሠራሩ እንዲሻሻል ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር የሙያ ምዝገባ ለመስጠት ምን ያህል አቅምና ዝግጁነት አለው?
ዶ/ር ተፈሪ፡- በአገራችን እስካሁን ድረስ የሙያ ማኅበራት ጥንካሬ እምብዛም ስለሆነ ነው እንጂ በሌሎች አገሮች የሙያ ምዝገባ የሚያካሂዱት የሙያ ማኅበራት ናቸው፡፡ አሁንም እኛ ይኸው እንዲፈጸም እየጠየቅን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በፋርማሲ ሙያ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀና ከሙያው ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አሟልቶ ከተገኘ በሙያ ማኅበር መመዝገብ አለበት፡፡ ይህም ሁኔታ የሙያ ማኅበራቱ ጠንካራ እንዲሆኑና በተለይ በሥነ ምግባር ዙሪያ ራሳቸው እንዲስተካከሉ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ምዝገባው ወደ እኛ እንዲመጣ እየሞከርን ያለነው፡፡ ማኅበራችንም ምዝገባውን ለማከናወን የተሟላ ሙያዊ አቅምና ብቃት አለው፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት የፋርማሲ ባለሙያዎች ከሚፈለገው በላይ በዝተዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ሥራ የማግኘቱን ዕድል ያጣብባል ተብሎ ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ የተደረገ ጥናት ካለና ሁኔታው አሁን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቢያብራሩልን፡-
ዶ/ር ተፈሪ፡- ከሦስት ዓመት በፊት ፋርማሲስት በዝቷል የሚለው ነገር በመንግሥትና በተለይ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አካባቢ ይቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን የፋርማሲ ማኅበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፋርማሲ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር በፋርማሲ ግብረ ኃይል ላይ ያተኮረ ጥናት አካሂዷል፡፡ በጥናቱም ላይ ለ100 ሺሕ ሕዝብ ምን ያህል ፋርማሲስት ያስፈልጋል? በሚለው ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ ተዳስሷል፡፡ እንዲሁም በጎረቤት አገሮችና በአጠቃላይ በአፍሪካ ደረጃ ያለው አማካይ ውጤትም በማነፃፀሪያነት ቀርቧል፡፡ በተለይ በአፍሪካ ደረጃ ለ100 ሺሕ ሕዝብ ስምንት ፋርማሲስቶች ሲያስፈልጉ በኢትዮጵያ ግን ለ100 ሺሕ ሕዝብ 2.9 ፋርማሲስቶች እንደነበሩ ታውቋል፡፡ ፍትሃዊ ያልሆነ የፋርማሲስት አመዳደብ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ ያህል አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፋርማሲስት ቁጥር ሲኖር፣ በአንፃሩ ደግሞ ምንም ፋርማሲስት የሌለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡ ፋርማሲስቶች መሥራት የሚገባቸውን ደግሞ ሌሎች ባለሙያዎች እንዲሠሩ የተደረገበት ክልል አለ፡፡ ይህን የመሰለ መረጃ አስደግፎ የተካሄደው ጥናት የደረሰበት ግኝት የሚያሳየው የፋርማሲ ባለሙያ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ሆኖ እንዳልተገኘ ነው፡፡ መጀመሪያውኑም ከመጠን በላይ ሆኖ ሊታይ የቻለው አግባብ ያልሆነ አመዳደብ በመኖሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሽፋኑንና የጥራትን ጉዳይ እንዴት ታዩታላችሁ?
ዶ/ር ተፈሪ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ90 ሚሊዮን ወደ 100 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው፡፡ የፋርማሲስት ቁጥር ደግሞ አምስት ሺሕ ቢሆን ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ፋርማሲስቶችን ማብቃት ይጠበቅብናል በሚል አዳዲስ የፋርማሲ ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱና የቅበላቸውም አቅም እየጨመረ ነው፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በዘርፉ የተማረ ኃይል እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡ የጥራት ጉዳይን በተመለከተ በግሉ ዘርፍ የጥራቱ ጉዳይ ደከም ይላል አንዳንዱ የመንግሥት ተቋማት ይሻላሉ ይላል፡፡ ሆኖም በመንግሥት ትምህርት ተቋማት በኩል ሲታይ አንዱ ከሌላው ይለያያል፡፡ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ትልቁ ጠንካራ ጎናቸው በአንድ ደረጃ የተዘጋጀ አንድ ዓይነት ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ የተቃኘው ‹‹ፊት ፎር ፕራክቲስ ፋርማሲስትስ›› በሚል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከጥናቱ በኋላ ምን ተደረገ?
ዶ/ር ተፈሪ፡- የጥናቱን ውጤት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቀረብን ውይይትም አካሄድን፡፡ በጥናቱ ውጤት ላይ ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ስትሆን ምን ያህል ፋርማሲስች ያስፈልጓታል? ይህንን ለማምረት ደግሞ በየዓመቱ ምን ያህል መመረቅ አለባቸው? የሚለውን ሁሉ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ዙሪያ ላይ የፋርማሲ ሙያ የመድኃኒት ሥርጭትና ቆጠራ ላይ ብቻ ከሚያነጣጥር፣ የበሽተኛና የመድኃኒት የምክር አገልግሎት ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ተማመንን፡፡ በሆስፒታሎች ደግሞ በየሕሙማን መኝታ ክፍሎች በፋርማሲስቶች ሊከናወኑ የሚችሉ ብዙ ሥራዎች እንዳሉም በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ‹‹ታስክ ሺፍቲንግ›› (የሥራ ኃላፊነትን መቀየር) የሚባል አካሄድ ተግባራዊ ሆነ፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የቅድመ ምረቃ (አንደር ግራጅዌት) ፕሮግራም ካሪኩለም በሽተኛ ተኮር በሆነ መልኩ ተቀየረ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መንግሥት ሆስፒታል ማሻሻያ ትግበራ መመሪያ ‹‹ሪፎርም ኢምፕሊመንቴሽን ጋይድ ላይን›› በሚያዘጋጅበት ሰዓት ይህንኑ አካቶ አወጣ፡፡ በዚህም የተነሳ በየሆስፒታሎቹ የሚያስፈልገው የፋርማሲስቶች ቁጥር ጨመረ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ የፋርማሲስቶችን እጥረት ፈጠረ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የፋርማሲስቶቹ እጥረት አለ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው አግባብነት ያለው አመዳደብና ታክስ ሺፍቲንግ ያመጣው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሞዴል ማኅበረሰብ ፋርማሲ ኢንሼቲቭ የሚል ፕሮግራም ማኅበሩ ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቶ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
ዶ/ር ተፈሪ፡- የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ሞዴል የማኅበረሰብ ፋርማሲ ኢንሼቲቭ ፕሮግራምን በሥራ ላይ ለማዋል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በጋራ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በማኅበሩ አስተባባሪነት የሚካሄደው ይህ ኢንሼቲቭ አዳዲስ ተግባራትን ዕውን የምናደርግበትና የምንሞክርበት ነው፡፡ ሞዴል የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች መንግሥት የሚያወጣውን መመዘኛ በላቀ ደረጃ የሚያሟሉ ናቸው፡፡ ሁሉም የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች መንግሥት የሚጠይቀውን ፍላጎት በመጠኑም ቢሆን አሟልተው ከተገኙ ነው ፈቃድ የሚሰጣቸው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ፋርማሲ ሞዴል ለመባል፣ ከፋርማሲው ባለቤትና ከእኛ የሚጠበቅ አስተዋጽኦ አለ፡፡ ከማኅበራችን የሚጠበቀው የአቅም ግንባታ ሥልጠናና ሶፍትዌር መስጠት፣ መሠረታዊና ተፈላጊ መድኃኒች በሽያጭ ማቅረብ ነው፡፡ ከፋርማሲ ባለቤቶች የሚጠበቀው ደግሞ ለኅብረተሰቡ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸጥ፣ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማበርከት፣ መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ማዘዣና ከዶዝ በታች አለመስጠት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ፋርማሲው ቢያንስ ሁለትና ከዛም በላይ የሆኑ ፋርማሲስቶችና ሁለት የተለያዩ ክፍሎችም ሊኖሩት ይገባል፡፡ አንደኛው ክፍል የታዘዘለትን መድኃኒት ለመግዛት የሚመጣው ታካሚና ፋርማሲስቱ አንድ ላይ ሆነው የሚመካከሩበት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን ዝርዝር ያሟሉ ሞዴል የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች አሉ?
ዶ/ር ተፈሪ፡- የሉም፡፡ ነገር ግን ሊያሟሉ የሚችሉና አቅም ያላቸው የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች አሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሞዴል የሚል ደረጃ አልተሰጣቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- የተጠቀሰውን ደረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ የተከናወኑ ጥረቶች አሉ?
ዶ/ር ተፈሪ፡- ሞዴል የሚል ደረጃ ለመስጠት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች ማኅበሩ ጥሪ አድርጓል፡፡ ከጥሪውም በኋላ ወደ 80 የሚጠጉ የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች ተመዘገቡና ዓላማውን አስረዳናቸው፡፡ ይህም ከተገለጸላቸው በኋላ 35ቱ ሞዴል የማኅበረሰብ ፋርማሲ ለመሆን ፈቃደኝነታቸውን አሳዩ፡፡ እነዚህም የኋላ ታሪካቸው ተጠንቶ ቁጥራቸው ወደ 20 ዝቅ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሥልጠና ሲጠሩ የመጡት 16 ብቻ ነበሩ፡፡ ከሥልጠናውም በኋላ የእነሱንና የእኛን ግዴታ የያዘ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ስንጠራቸው 13 ብቻ መጡ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ 13 የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች ጋር ተፈራርመን ሥራው ተጀመረ፡፡ እነዚህን የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች ወደ ሞዴል ደረጃ ለማድረስ የማብቃት ሥራ እያከናወንን ነው፡፡