Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበሶሪያ የሚደረገው የሩሲያ ፀረ አይኤስ ዘመቻ በሳተላይቶች መታገዝ ጀመረ

በሶሪያ የሚደረገው የሩሲያ ፀረ አይኤስ ዘመቻ በሳተላይቶች መታገዝ ጀመረ

ቀን:

የሶሪያውን ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ደግፎ፣ በሶሪያ የሚገኘውን አይኤስና ለማጥፋት ወታደራዊና ቁሳዊ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው የሩሲያ ጦር በህዋ ላይ በሚገኙ ወታደራዊ ሳተላይቶች መታገዝ ጀመረ፡፡

የሩሲያ ጦር አል አሳድን ለመርዳት በሶሪያ በአይኤስ ላይ ጥቃት ከከፈተ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ጦሩ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዙ ተዋጊ ጀቶችን፣ ዘመናዊ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ የጦር መሣሪያዎችን፣ ሰርጓጅን ጨምሮ ሚሳይሎችን የሚተኩሱ የጦር መርከቦችን ጭምር አሠልፏል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ፀረ አይኤስ ዘመቻውን በዘመናዊ አኳኋን ለመምራት ከምድር በመቶዎች ማይልስ ርቀው በህዋ ላይ ከተተከሉት ሳተላይቶች በመረጃ በመታገዝ በአይኤስ ላይ ጥቃት እየፈፀመ ይገኛል፡፡

ዘ ዴይሊ ቢስት የሞስኮ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሩሲያ ወደ ጠፈር ካመጠቀቻቸው 89 ሳተላይቶቿ ውስጥ አሥሩ በሶሪያ የሚገኘውን የሩሲያ ጦር በመረጃ እንዲያግዙ አድርጋለች፡፡

ወታደራዊ ሳተላይቶቹ በሶሪያ ያለውን የመሬት አቀማመጥ፣ አቅጣጫና ለማጥቃት የሚፈለጉ ቦታዎችን ያመላክታሉ፣ የደኅንነት መረጃዎችን ይሰበስባሉ፣ የሬዲዮ መገናኛ ሞገዶችን ይጠቁማሉ፣ በአየርና በባህር ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ከምድር፣ ከአየርና ከባህር ለሚዋጋው የጦር ክፍል ያደርሳሉ፡፡

ሩሲያ በሶሪያ የሚገኘውን አይኤስ ለመደምሰስ በሳተላይት መታገዝ መጀመሯን ከማሳወቋ በፊት፣ ቱርክ የአይኤስ ታጣቂዎች ነዳጅ ዘይት እንዲሸጡ ታመቻቻለች የሚለውን ለማረጋገጥም የሳተላይት ድጋፍ ተጠቅማለች፡፡ ቱርክ የሩሲያ የጦር ጄትን መትታ ከጣለች በኋላ፣ ሩሲያ ቱርክ አይኤስን እየደገፈችና ነዳጅ ዘይት እንዲሸጡ እየተባበረች መሆኗንም አሳውቃ ነበር፡፡

አራት መቶ ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ካመጠቀችውና ከእነዚህ ውስጥ 200 ያህሉን የጦር ኃይሏን ለማገዝ ካዋለችው አሜሪካ ቀጥሎ 89 ሳተላይቶችን በማምጠቅና ከእነዚህ ውስጥ 50 ያህሉን ለወታደራዊ ጥቅም በማዋል የምትከተለው ሩሲያ፣ በሶሪያ የሚገኘውን አይኤስ ለመደምሰስ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዙ የጦር መሣሪያዎችንና ሳተላይቶችን እየተጠቀመች ነው፡፡

ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በህዋ ላይ ያላትን አቅም እያጠናከረች የምትገኘው ሩሲያ፣ አሥር ፎቶግራፍ የሚያነሱና በጦርነት ወቅት የደኅንነት መረጃዎችን የሚሰበስቡ፣ እንዲሁም ከጦርነት ውጪ ለሲቪሉ ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ በህዋ ያሉ መንኮራኩሮች በሶሪያ ያለውን ሁኔታ እንዲመረምሩና አድርጋለች፡፡

እንደ ‹‹ህዋ ሰላይ›› ከሚቆጠሩት ሳተላይቶች ዘመናዊው ሪሰርስ-ፒ2 እና ፐርሶና ሳትስ የተባሉት ፎቶግራፍ አንሺ ሳተላይቶች፣ በሶሪያው ውጊያ ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ፐርሶና የተባለው ሳተላይት ሙሉ ለሙሉ ወታደራዊ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሚባለውን የስለላ ተግባር የሚያከናውንም ነው፡፡ ከፐርሶና ጋር ሲነፃፀር ብዙም ውስብስብ ያልሆነው ሪሰርስ ደግሞ ለወታደራዊና ለሲቪል ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ሳተላይት በአንድ ጊዜ እስከ ሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሥፍራን ፎቶግራፍ እንዲያነሳ፣ እንዲሰልል፣ አንድ የሚፈለግ ግለሰብንም ሆነ ቁሳቁስ እንዲያስስ ሊታዘዝ ይችላል፡፡ ሳተላይቱ በ24 ሰዓት ውስጥ 80 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ማለትም ከሶሪያ ግዛት ግማሽ ያህሉን በፎቶግራፍ የተደገፈ መረጃ ያቀርባል፡፡

ከቱርክ ጋር በሶሪያ ጉዳይ እሰጥ እገባ የያዘችው ሩሲያ፣ በሶሪያ የሚገኙ ሸማቂዎች ከቱርክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ አጋልጣለች፡፡ ከወጪው ግማሽ ያህሉን ከነዳጅ ሽያጭ ያገኛል ለሚባለው አይኤስ፣ የነዳጅ ምርት እንዲሸጥ የቱርክ ወደቦች መጠቀሚያ መሆናቸውንም አስታውቃለች፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሪሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ውንጀላውን ቢያጣጥሉትም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአይኤስ የነዳጅ በርሜሎች በቱርክ ወደብ ተከማችተው እንደሚገኙ ሩሲያ ገልጻለች፡፡

ይህም ሩሲያ ሶሪያን ለመደገፍ ያደረገችው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከምድር ጦር ብቻ ሳይሆን ከሳተላይት ጭምር የሚታገዝ መሆኑንም የሚያሳይ ነው፡፡ ሞስኮ በመካከለኛው ምሥራቅ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ከህዋ ጭምር የሚታገዝ መሆኑንም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጠቅሶ ዴይሊ ሜይል እንደዘገበው፣ አስፈላጊ ከሆነ ሩሲያ አሁን እየተጠቀመችው ካለው ወታደራዊ አቅም በበለጠ በአይኤስ ሸማቂዎች ላይ ተጨማሪ ኃይል ታሰማራለች፡፡ ‹‹ሩሲያ ወታደራዊ አቅሟን በሙሉ እየተጠቀመች አይደለችም፡፡ ሆኖም አስፈላጊ ከሆነ ሙሉ አቅሟን ተጠቅማ የአሳድ ተቀናቃኞችን ታወድማለች፤›› ብለዋል፡፡

አሜሪካ ግን የሩሲያ አካሄድ አልተመቻትም፡፡ ሩሲያ ሰሞኑን በጀመረችው መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ምክንያት፣ አሜሪካ መራሹ ጥምር ጦር በሶሪያ በሚገኘው አይኤስ ላይ የጀመረውን ጥቃት ለማቆም ተገዷል፡፡ ከምድር ሆነው አይኤስን የሚዋጉትን የአሳድ ተቃዋሚዎችን ለመደገፍም ተቸግሯል፡፡

ይህም አይኤስን ለማጥፋት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጀመረውን ጥቃት የሚያደናቅፍ ነው ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ አሜሪካ የአሳድ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉትን የእግረኛ ውጊያ፣ በአየር ድብደባ እያገዘች የነበረ ቢሆንም ይህን ለማቆም ተገዳለች፡፡ ነገር ግን ከአሜሪካ ይልቅ የሩሲያ ጥቃት አይኤስን መላወሻ እንዳሳጣው እየተነገረ ነው፡፡

ሩሲያ በሶሪያ ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሰሞኑን አይሏል፡፡ በቅርቡ የጀመረችውን የጦር ኃይል ማጠናከርና የአየር ድብደባ አድማስ ማስፋትን በተመለከተም ለአሜሪካ ቀድማ ባለማሳወቋ፣ አሜሪካ በሶሪያ የምታደርገውን የአየር ድብደባ በድንገት እንድታቆም አስገድዷታል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም፣ የጦር ኃይላቸውን እንዴት ማሰማራት እንዳለባቸው ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር እየመከሩ ነው፡፡

በቱርክና በሶሪያ ድንበር ከኤፍራጥስ ወንዝ በምዕራብ አቅጣጫ የሚገኙትን የአይኤስ ተዋጊዎች ይዞታ ለማስለቀቅ የአሜሪካ መራሹ ጦር ጥቃት እየሰነዘረ የነበረ ቢሆንም፣ መግፋት አልተቻለም፡፡

የአሜሪካ የጦር ጄቶች ሥራቸውን ሲያቆሙ የሩሲያ የጦር ጄቶች አሜሪካ ቀድማ ትደበድበው በነበረውና የአይኤስ ሸማቂዎች የተጠናከረ ይዞታ አላቸው በሚባልበት ቦታ ድበደባ እያካሄደች ነው፡፡ ሆኖም የአሳድ ተቃዋሚዎችን የምትረዳው አሜሪካ፣ ሩሲያ በሶሪያ ተቃዋሚዎች ላይ የአየር ጥቃት እየሰነዘረች ነው ስትል ወንጅላታለች፡፡

ሩሲያ ከቱርክ ወደ ሶሪያ የሚገቡ የንግድ ተሽከርካሪዎች ላይም ጥቃት እያደረሰች ነው፡፡ ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ የሩሲያ የአየር ድብደባ በቱርክ በኩል ወደ ሶሪያ የሚገባ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደናቀፍ ምክንያት ሆኗል፡፡   

   ሶሪያን አስመልክቶ በሩሲያና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው ውጥረት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ፣ በሽር አል አሳድንና ተቃዋሚዎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማደራደር ያላቸውን ጥረት የሚያደናቅፍ ይሆናል፡፡ ሆኖም ዓርብ ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር በኒውዮርክ የሚመከሩት ኬሪ፣ አይኤስን ለማጥፋት ከሩሲያ ጋር አብረው መሥራ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ ከዚህ ቀደም በሶሪያ ለውጥ እንዲመጣ አል አሳድ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው ስትል የከረመች ቢሆንም፣ አሁን ግን፣ ‹‹አሜሪካ በሶሪያ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ዕቅድ የላትም፤›› ሲሉ ኬሪ ተናግረዋል፡፡ ሶሪያና አሜሪካ ሰሞኑን ያደረጉት ውይይትም በአሳድ ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ አልነበረም፡፡ ይልቁንም አይኤስን ከኢራቅና ከሶሪያ በማጥፋት፣ ሕዝቡ የመረጠው መንግሥት ሶሪያን እንዲመራ ምርጫውን ለሕዝቡ በመተው ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...