Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርአድልኦና ሙስና የሰፈነባት ከተማ

  አድልኦና ሙስና የሰፈነባት ከተማ

  ቀን:

  በታዬ እውነቱ

  “እዚህ አገር ያለ ከባድ ፈተና እዚህ እናወራለን እንጂ፣ ከወጣን በኋላ የተለያየ የራሳችን መረብ እንዳይነካብን እንከላከላለን፡፡ ይኼ አንዱ ትልቁ በሽታ ነው፡፡ ብቻችንን ቆመን አቋም የምንወስድበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ የእኛ ነው የምንለውን ሰው ለመደበቅና ለመሸፈን ብቻ የምንሄድ ከሆነ ለውጡ አይሠራም፡፡ በብሔር፣ በአብሮ አደግነት፣ በተለያየ ጥቅም ትስስር የምንሠራና የምንከላከል ከሆነ አይሠራም፡፡ መፍትሔው የሚመሠረተው በከፍተኛ አመራሩ ቁመና ነው፡፡ ይህን ለመለወጥ ትክክለኛ የሕዝብ ተሳትፎ ላይ ሊሠራ ይገባል፡፡” ይህ አባባል በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተናገሩት ነው፡፡

  በአሁኑ ጊዜ በከተሞች ሰፍኖ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ውስብስብ ችግር ለመፍታት የነበረውን ጨለምተኛ  አስተሳሰብ ለመለወጥ ጥቂት የተስፋ ጭላንጭል ያሳየ አባባል ነው፡፡

  ከላይ እሰከ ታችኛው የመንግሥትና መዋቅር ብቻ ሳይሆን በገዥው የፖለቲካ ድርጅት መዋቅር መደበኛ ባልሆነ ግንኙነት የተደራጁ የግል ጥቅም አሳዳጆች፣ በአገሪቱ ሥር ለሰደደው የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከሥሩ ፈንቅሎ ለማድረቅ ከተፈለገ ይህ በየአስተዳደር አካባቢውና በየዘርፉ የተዘረጋውን መደበኛ ያልሆነ የጥቅም ግንኙነትና የቡድንተኝነት መረብ  መበጣጠስ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሥውር የጥቅም አደረጃጀት ፊት ለፊት ከሚዋጋ የጠላት ጦር በበለጠ ረቂቅ የትግል መሣሪያዎችን የታጠቀ ስለሆነ፣ ፊት ለፊት ከሚገጥም ጠላት የበለጠ አደገኛ ነው፡፡

  በየስብሰባውና መደበኛ በሆኑ አደረጃጀቶች ማራኪ ቃላትን እየደረደሩ ለሕዝብ የቆሙ መስለው ራሳቸውን እየሸፈኑ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ እንዳለችው እንስሳ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም፣ ልማታችንንና ዕድገታችንን ለማኮላሸት የተነሱ አስመሳዮች የፈጠሩት የጥቅም መረብ ከሚታሰበው በላይ ጠንካራና ውስብስብ ነው፡፡ በመሆኑም ትናንት በየትግል ሜዳው ከጠላት ጋር ከተካሄደው ፍልሚያ ያላነሰ ትግልና ጀግንነት ይጠይቃል፡፡ ይህን የጥቅም አደረጃጀት ለማፈራረስ በመንግሥትና በፖለቲካ ድርጅቱ የሚገኙ ራሳቸውን ለመስጠት የቆረጡ ጀግኖች ያስፈልጋሉ፡፡ ጀግንነት የጦር መሣሪያ ይዞ መዋጋት ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የልማት ነቀርሳ የሆነ የሙስናና  የኪራይ ሰብሳቢነት አደረጃጀት በመበጣጠስ የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል የረቀቀ ታክቲክ፣ ሥልትና ቆራጥነትን፣ ራስን ለሕዝብ ጥቅም አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቅ ነው፡፡

  በዚህ አጋጣሚ  እኛም የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ከመንግሥት ጎን ቆመን ይህን ሥውር አደረጃጀትና ቡደንተኛነት ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳወቅ እንፈልጋለን፡፡ በመሆኑም በባህር ዳር ከተማ ስለሚፈጸመው የአስተዳደር በደል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለው እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ 

  በባህር ዳር ከተማ ውስጥ በጉቦ፣ በዘመድና በጎጠኝነት በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠር ቁርኝት ካልሆነ በስተቀር፣ ሚዛናዊ  ፍትሕ ማግኘት  ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ኅብረተሰቡ  በየመንገዱ፣ በየታክሲውና በየመዝናኛው መናገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡

  በከተማው ውስጥ መመርያን ሰበብ በማድረግ የሚፈልጉትን ለመጥቀም፣ የማይፈልጉትን ለመጉዳት የሚያስችል ከላይ ከመመርያ አውጪው አስከ ታችኛው ፈጻሚ የተዘረጋ መረብ እንዳለ የሚከተለውን የሰነድ ማስረጃ ማየት ይቻላል፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የፀደቀው ደንብ ቁጥር 103/2004 ዓ.ም.  ‘ሰነድ አልባ’  ለሚለው ቃል የሰጠው ትርጉም፣  “ሰነድ አልባ ይዞታ ማለት በሕጋዊ አግባብ የተያዘ ወይም በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ዕውቅና የተሰጠው ይዞታ ሆኖ አግባብ ባለው አካል የሚሰጥ የይዞታ ምስክር ወረቀት የሌለው ይዞታ ነው፤” ይላል፡፡

  በተመሳሳይ ሁኔታ በ2005 ዓ.ም. የክልሉ ኢንዱሰትሪና ከተማ ልማት ያወጣው  የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመፍቀድ የወጣ መመርያ ቁጥር 1/2005  ሰነድ አልባ ለሚለው ሐረግ ትርጉም ሲሰጥ፣ “ሰነድ አልባ ይዞታ ማለት በሕጋዊ አግባብ የተያዘ ወይም በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ዕውቅና የተሰጠው ይዞታ ሆኖ፣ አግባብ ባለው አካል የሚሰጥ የይዞታ ምስክር ወረቀት የሌለው ይዞታ ነው፤” በማለት የክልሉ ምክር ቤት የሰጠውንና በአገር አቀፍ ደረጃም የሚሠራበትን  ትክክለኛ ትርጉም  አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት ባህር ዳርን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ውጣ ውረድ ቢደርስባቸውም የቦታ ምስክር ወረቀት ወይም ካርታ አግኝተዋል፡፡

  ጥቂቶቹ ካገኙ  በኋላ ግን መመርያው በርካታ የከተማ ነዋሪዎችን ያለማንገላታትና ያለልዩነት የሚያስተናግድ ሆኖ በመገኘቱ ልዩነት በመፍጠር  የነዋሪውን ውጣ ውረድና ምልልስ በማብዛት፣ የሚፈልጉትን ጥቅም/ማማለጃ ለማግኘት ከላይ የተጠቀሰውን የክልሉ ምክር ቤት ያፀደቀውን ደንብ የሚያሻሽል የአፈጻጸም መመርያ ወጣ፡፡ ሕጋዊነትና አግባብነት በሌለው መንገድ የክልሉ ምክር ቤት ያወጣው ደንብ ቁጥር 103 የሚሻሽል ሌላ  የአፈጻጸም መመርያ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ 

  መመርው የወጣው በዚያው በ2005 ዓ.ም. ሲሆን፣  “በከተሞች ውስጥ የተሟላ ሰነድ የሌላቸው ሰነድ አልባ ይዞታዎችን በማጣራት የቦታ መጠናቸውን በመወሰን ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ/ካርታ ለመስጠት እንደገና ለመደንገግ የወጣ የአፈጻጸም መመርያ ቁጥር 2/2005”  የሚል መጠሪያ ተሰጠው፡፡  በዚህ መመርያ  “ሰነድ አልባ” የሚለው ቃል በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ትርጉም ተለውጦ፣  ባለጉዳዮችን ከፋፍሎ የተወሰኑ ሰዎችን ለመጥቀምና በሌላው ላይ ውውረድ በሚያስከትል ሁኔታ እንደሚከተለው ተተረጎመ፡፡

  “ሰነድ አልባ ይዞታ ማለት በሕጋዊ አግባብ የተያዘ ወይም አግባብ ባለው አካል/የመንግሥት መዋቅር ዕውቅና የተሰጠው ሆኖ ምንም ዓይነት ሰነድ/ማስረጃና የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት/ካርታ የሌለው ይዞታ ነው፤” በማለት “ምንም ዓይነት” የሚል ሐረግ በመጨመርና የክልሉ ምክር ቤት የሰጠው ትርጉም በማዛባት ወይም በማሻሻል ተተረጎመ፡፡ ቀጥሎ ነዋሪውን ከፋፍሎ ለማንገላታትና የሚፈልጉትን እሺ ብሎ እንዲሰጥ ሌላ በደንቡ ላይ ያልነበረ  “የተሟላ ሰነድ” የሚል  አዲስ ጽንሰ ሐሰብ  ተጨምሮ ትርጉም ተሰጠው፡፡ “የተሟላ ሰነድ ያለው ይዞታ ማለት በመሠረታዊነት በወቅቱ አግባብ ባለው አካል ተረጋግጦ የተሰጠ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት/ካርታ ያለው ሆኖ፣ የምሪት ካርኒና የግንባታ ፕላን ያለው ይዞታ ነው፤” በሚል ተተረጎመ፡፡ በዚህ ትርጉም የሚፈልጉትን የኅብረተሰብ ክፍል የቦታ ካርታ እንዲያገኝ ወይም እንዳያገኝ ለማድረግ ተጠቀሙበት፡፡

  ቀጥሎም በ2007 ዓ.ም. ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የክልሉ ምክር ቤት ያወጣውንና በአገር አቀፍ የተሰጠውን የሰነድ አልባ ትርጉም በመመንዘርና በማሻሻል “በከተሞች ውስጥ የተሟላ ሰነድ የሌላቸውና ሰነድ አልባ ይዞታዎችን በማጣራት የቦታ መጠናቸውን በመወሰን ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ/ካርታ ለመስጠት ተሻሽሎ የወጣ የአፈጻጸም መመርያ ቁጥር … /2007 ዓ.ም.” በሚል የሚጠራ አዲስ መመርያ ወጣ፡፡  በዚህ መመርያ  “ሰነድ አልባ”  ለሚለው ሐረግ በሚከተለው የተለየ ይዘት ያለው ትርጉም ተሰጠው፡፡

  ሰነድ አልባ ይዞታ ማለት በሕጋዊ አግባብ የተያዘ ወይም አግባብ ባለው አካል/የመንግሥት መዋቅር ዕውቅና የተሰጠው ሆኖ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 6 ሥር ከተመለከቱ መሥፈርቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱን የሚያሟላና የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት/ካርታ የሌለው  ይዞታ ማለት ነው፤”

  የተሰመረበትን ሐረግ በመጨመር የአፈር ግብር የተከፈለበት ካርኒ ወይም ባለፈው መንግሥት ጊዜ የተሰጠ የቤት ባለቤትነት ደብተር ካለው ሰነድ አልባ አይደለም፡፡ የከተማው ነባር ነዋሪ እንዳይጠቀም የሚያደርግና ካርታና ፕላን የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በደረጃ በመካፋፈል ለተዘረጋው ሥውር መረብ እንዲመች ተደርጎ ተተረጎመ፡፡

  በዚህ ምክንያት በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ካርታና ፕላን እንዳያገኙ ታግደው ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም  የቦታ ካርታና ፕላን ባይኖራቸውም  አዲስ በተሰጠው  የትርጉም ማሻሻያ የአፈር ግብር የከፈሉበት ካርኒ ወይም ሌላ ማስረጃ ስላለ መስተናገድ ያለባቸው  ሰነድ አልባ በሚለው ሳይሆን፣ “ያልተሟላ ሰነድ” በሚል አዲስ ተመንዝሮ በወጣው መመርያ መሠረት ነው፡፡ ይህ የሚሳየን ከላይ እስከ ታች በጥቅም ሰንሰለት በመተሳሰርና በቡደንተኛነት  ምን ያህል ኅብረተሰቡ እየተንገላታ እንዳለ ነው፡፡

  ሌላ እንጨምር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመሀል ባህር ዳር ከሚገኙ ዕድሜ ጠገብ አሮጌ ቤቶች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ከአስተዳደሩ አባላት ጋር በሚፈጥሩት  የጥቅም ግንኙነት ፈርሰው እንደገና ሲሠሩ ወይም ሲታደሱ ይታያል፡፡ ለዚህም በመሀል ባህር ዳር አካባቢ የሚዘዋር ማንኛውም ሰው በደሳሳ አሮጌ ቤቶች መካከል በአዲስ መልክ እየፈረሱ የአካባቢው ፕላን ከሚፈቅደው ውጪ በእንጨትና በብሎኬት በመገንባት ወይም በመታደስ ላይ መሆናቸውን በዓይኑ ማየት ይችላል፡፡ ለእነዚህ ቤቶች በተለየ ሁኔታ እንደተፈቀደላቸው አስተዳደሩም ሆነ የከተማው ሕንፃ ሹም ባልደረቦች ሲጠየቁ የሚያወቁት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ እነዚህን ቤቶች በሚመለከት ነዋሪው  በየአጋጣሚው ሲገናኘ ምን እንደሚል የሚከተለውን ጭውውት እንመልከት፡፡

  “… በሠፈራችን አንዳንድ የእንጨት ቤቶች ፈርሰው በብሎኬት ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ አቶ … የጭቃ ቤቱን አፍርሶ በብሎኬት ሠርቷል፡፡ … ለእሱ የተፈደለት በጉቦ ነው፡፡ አንተም እንደሱ ጀባ ብትል ኖሮ ይህን የዘመመ ቤትህን  በብሎኬት በሠራህ ነበር! … እገሌ ለተባለው ኃላፊ እገሌ 30 ሺሕ ብር ሰጥቷል፡፡ … እገሌ ደግሞ 50 ሺሕ ብር ጉቦ ከፍሏል፡፡ … አቶ እንተና ደግሞ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዘመድ ስላለው ይዞታው ፀደቀለት፡፡  … እንትና እኮ በልቶ ሥራውን ለቀቀ፡፡  … እባክህ ሌላ የተራበ ጅብ ከሚመጣ የጠገበው እሱ ይሻል ነበር፡፡ … መቼም በዚህ ጊዜ ጉቦ ሳይሰጥ ቦታ ወይም የቤት ሥራ ወይም የዕድሳት ፈቃድ ማግኘት ዘበት ነው …፤” ይላል አንዱ፣ ሌላው ተቀብሎ “… ያ አስተዳዳሪ  በልቶ ዞር ማለቱ ጎበዝ ነው…፤” በማለት አድናቆቱን ይገልጻል፡፡ እነዚህ ጭውውቶች በየመንገዱ፣ በየታክሲው በየመጠጥ ቤቱ የሚደመጡ ናቸው፡፡

  እነዚህ አባባሎች ምን ያህል እውነትነት አላቸው? በማለት ከተወያየን በኋላ እውነታውን ለማረጋገጥ ተሠሩ የተባሉ ቤቶችን መፈለግ ጀመርን፣ እንደተባለው አንዳንድ ቤቶች የከተማው ማሰተር ፕላን ከሚፈቅደው ውጪ ፈርሰው ሲሠሩ አየን፡፡

  እንዳሁኑ መረጃ ፍሰቱ ዘመናዊ ባልሆነበት በድሮው ጊዜ የነበሩ ነገሥታት አስተዳደራቸውን በሚመለከት ግብረ መልስ ወይም መረጃ የሚያገኙት ከእረኞች ዘፈንና ሽለላ ነበር ይባላል፡፡ እናም ስለአስተዳደራቸው መልካምነት ወይም መጥፎነት መረጃ ለማግኘት “እረኞች ምን አሉ?” እያሉ መረጃ ያሰባስቡ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚህም ተነስተው የአስተዳደር ዕርምጃዎችን በመወሰድ ማስተካከያ ያደርጉ ነበር፡፡

  የከተማው ወይም የክልሉ አስተዳደር ግን በዚህ ባለንበት የመረጃ ዘመን የሕዝብን ብሶት አዳምጦ ከቃል ያለፈ ተግባራዊ ዕርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ በባህር ዳር ከተማ ስላለው የአስተዳር በደል፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ኅብረተሰቡ መደበኛ ባልሆኑ ግንኙነቶችና አጋጣሚዎች  ከሚናገረው ባለፈ  በአንድ ወቅት በሪፖርተር ጋዜጣ “መልካም አስተዳደር የማታውቀው ባህር ዳር” በሚል ርዕስ  በከተማይቱ ስለሚፈጸመው የመልካም አስተዳደር ችግር የከተማዋ ነዋሪዎች  ብሶታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጽሑፉን ያነበቡት በርካታ አስታያየት ሰጪዎች ስሜታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ግን አንድም ቃል አልተነፈሰም፡፡ 

  በመሆኑም የሚመለከታቸው ሁሉ ክትትል በማድረግ ተገቢውን ዕርምጃ  እንዲወስዱና የከተማ አስተዳደሩም ለሚከተሉት ጥያቄዎች ግልጽና አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡

  1. መጋቢት 30 ቀን በታተመው በሪፖርተር ጋዜጣ “መልካም አስተዳደር የማታውቀው ባህር ዳር” በሚል ርዕስ በተጠቀሰው መሠረት የጣና ዳርቻ ከንክኪ ነፃ ሆኖ በአረንጓዴ ተክሎች እንዲለማ የሚያቅደው የከተማዋ ነባር ማስተር ፕላን ተለውጦ፣ ቦታው ለግለሰቦች እንዲሰጥ በማድረግ የከተማዋ ውበት የሆነውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የጣና ሐይቅ ሕልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደረጉ አካላት ለምን በሕግ አይጠየቁም?
  2. በሺዎች ሳይሆን በሚሊዮኖች በሚቆጠር የሕዝብ ሀብት የተሠራው የከተማው የካዳስተር ጥናት ለምን ተግባራዊ አልተደረገም? ለካዳስተር ጥናቱ ለወጣው ወይም ለባከነው ሀብት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች ወይም ደርጅቶች ለምን በሕግ አይጠየቁም?
  3. ባለፈው መንግሥት በምሪት ወይም በግዥ ቦታ ይዘው ቤታቸው ያረፈበት ቦታ መጠን ከሚገበርበት የቦታ መጠን ስለሚበልጥ ብቻ ከ30 ዓመታት በላይ ተሠርቶ የቆየውን የቤታቸውን አካል ካላፈረሳችሁ ካርታና ፕላን አይሰጣችሁም የተባሉ፣ በመሀል ባህር ዳር በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች አሉ፡፡ ከ1994 ዓ.ም. በፊት የተያዘ ይዞታ እየፀደቀ እንዴት በድሮው መንግሥት የተያዙ ይዞታዎች ሕጋዊ ሆነው በከፊል የአፈር ግብር ስለገበሩ ብቻ ካርታና ፕላን ተከለከሉ? 
  4. የከተማው ውስጥ ማስተር ፕላን ከሚፈቅደው ውጪ ቤታቸውን አፍርሰው አንደገና እንዲሠሩ አንዳንዶቹ የጭቃ ቤት የነበረውን አፍርስው በብሎኬት ሲገነቡ፣ ሌሎች የዘመመ ቤታቸውን ለማደስ ለምን ይከለካሉ? መደበኛ ባልሆነ ግንኙነት ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙ ወይም እንዲፈጸም ያደረጉ የከተማው አስተዳደር አካላት ለምን በሕግ አይጠየቁም?
  5. በተለያዩ የግል ጥቅም ለማግኘት በከተማው ውስጥ በጎጠኝነትና በዘመድ አዝማድ … ወዘተ የመሳሰሉ መደበኛ ያልሆኑ የጥቅም መረቦችን በመዝርጋት በነዋሪዎች ላይ የተፈጸሙ የአስተዳደር በደሎችን፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ደርጊቶች አጥንቶ ጥፋተኞችን ለፍርድ የሚያቀርብ በሕዝብ የተመረጠ ገለልተኛ አካል አይቋቋምም?

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

                                    

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...