Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አታካች ዘመን!

እነሆ ከሳሪስ አቦ ወደ ቦሌ ድልድይ ልንጓዝ ነው። “ነፍሱ ውረድ! ደርሰናል፤” ወያላው እኛን እንድንገባ እየጠቆመ ጭኖት ከመጣው ተሳፋሪ ጋር ይነታረካል። “አልወርድም!” ጉዞውን ያገባደደው ተሳፋሪ ይመልሳል። ፈርጣማና ኮስታራ ነው። “ለምንድነው የማትወርደው? እዚህ አገር ግን በፀባይ እየወጣ በጉልበት የሚወርድ ብቻ ነው እንዴ የሞላው?” ወያላው ወደ እኛ ዞሮ ይጠይቃል። “እዚያው እሱን ጠይቀው ወንድሜ! ምን ያነካካናል? ሰውዬው ሁለታችንን በአንድ እጁ ቢይዘን አያጨማድደንም?” ይለኛል አጠገቤ የተቀመጠው ፈራ ተባ እያለ። “እሺ ትቀጥላለህ?” ወያላው መለሳለስ ጀመረ። “አልቀጥልም፣ ብቀጥልም አልከፍልም፤” ባረቀበት። “ኧረ ስለጉልበትህ አምላክ ብለህ ተወን? አናሳዝንህም እንዴ እኛ? ከስንቱ ጋር እንታገል እናንተ?” መካከለኛው ጥንድ መቀመጫ ላይ መስኮቱን ታካ የተሰየመች ወይዘሮ። “ቆይ ለምድነው የማትወርደው?” ሾፌሩ ዝምታውን ሰብሮ ደነፋ። “ተወርዶስ የት ይኬዳል?” የተሳፈርነው ሰው መስለን ያልታየነው ጉልበተኛ እያሾፈ መለሰለት።

“እውነቱን ነው። ፓርክ የለ መጻሕፍት ቤት የለ። ምን የለ! ምን የለ!” ይላል ከጀርባ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ጎልማሳ። “ምን የለ ነው ያለው? ምን ምንድነው?” ያደርቀኛል ከጎኔ። “የሌለንን መቁጠር ስለምንወድ እንጂ ኧረ ብዙ መዝናኛ አለ ጎበዝ፤” ወይዘሮዋ እንደምታሸሙር ያስታውቅባታል። “ለምሳሌ?” ጉልቤው ወያላውንም ሾፌሩንም ረስቶ ጨዋታ ጀመረ። ወያላው፣ “እኔ ምንጨነቀኝ ይከፍላታል፤” እያለ ቦታ ያልያዙ ተሳፋሪዎችን አሸጋሽጎ አስቀመጠ። “ለምሳሌ መቃሚያ ቤት፣ መጠጫ ቤት፣ መደነሻ ቤት፣ ሽሻ ቤት ወዘተርፈ፤” አለች ወይዘሮዋ ሳቅ እየቀደማት። “ጠቅለል አድርገሽ ሱስ ማፋፋሚያ ቤቶች አትይም ነበር? ወዘተን እስከ መወዘት ምን አስኬደሽ?” ብሎ አጠገቧ የተሰየመ ንቁ ‘ፌስቡክ’ ተጠቃሚ አፋፋመላት። “ሾፌር ሞልቷል እኮ። እባክህ ንዳው። በሥራ ቀን እስኪ አሁን ሥራ መፍቻ ሥፍራ አጣን እያልን ቆመን እንዋል?” ይላል ጎልማሳው። ቆብ ቀዶ መስፋት ብትሰንፍ ልጇት ላፋታ እንዳለችው (ማን ትሆን ግን?) ሆነን አረፍነው ነው ነገሩ። ትችት ሱስ ነው ተብሎ የሚወገዝበት ቀን ናፈቀኝ፡፡

ጉዟችን ተጀምሯል። ወይዘሮዋ “እንዲያው እንዴት ተደርጎ ነው ‘አካውንት’ የሚዘጋው?” ብላ ወጣቱን ታዋየዋለች። “ምነው በደህና ነው? ሰው ‘አካውንት’ መክፈቻ 25 ብር ባጣበት ጊዜ አካውንት ማዘጋት?” ይላታል። “ምን ደህንነት አለ ‘ፌስቡክ’ እያለ። እንደ ፌስቡክ ቢሆን እኮ አገሬ ዛሬ ሶሪያ ወይ ኢራቅ ሆናለች። እኔ እኮ የምለው አገር በሟርትና በስድብ፣ መንግሥት በሐሜትና በሽሙጥ ይፈርሳል ያለው ማን ነው?” አለችው። “እህ የፌስቡክ አካውንትሽን ለመዝጋት ነው እንዴ? እኔ ደግሞ የባንክ አካውንትሽን መስሎኝ ግራ ገብቶኛል እኮ…” እያለ ወጣቱ የጠየቀችውን እንደመመለስ ፊቱን ሲያዞር ከኋላ የተቀመጠው ጎልማሳ አስግጎ፣ “በእርግጥ የእያሪኮ ከተማ የፈረሰው በጩኸት ነው። እኛ ግን የመደመጥና የመከበር ፍላጎት እንጂ አገርም ሆነ መንግሥት የማፍረስ ዓላማ የለንም፤” አላት።

“እንዴ መጀመሪያ እዚህ አጠገብ ላጠገብ ሳንከባበርና ሳንደማመጥ ነው ከላይ ያሉት አያዳምጡንም አያከብሩንም የምንለው? ምን ዓይነት ነገር ነው?” ከጎኔ የተቀመጠው ወደ ጎልማሳው ዘወር ብሎ ትክ ብሎ አየው። “እሱማ ከተናናቅን ቆይተናል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነና ደግሞ ይኼው ‘ፌስቡክ’ መጣ። የመናናቅ ክህሎታችንን በማስተርስ ‘ሌቭል’ አሳደገው፤” አለች ወይዘሮዋ። ይኼን ጊዜ ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠች ቀዘባ፣ “እኔ እኮ የሚገርመኝ ቆይ ፌስቡክ ሳይመጣ እንዴት ነበር የምንውለው የምናድረው?” ከማለቷ፣ “ሳንሰማና ሳናይ፤” ብሎ ጎልማሳው አቀበላት። “ምኑን?” ስትለው መልሳ፣ “ሁሉን! ችግር ርሃቡን፣ የአስተሳሰብ የአነጋገር ድህነቱን። ስንቱ አገር ወዳድ ስንቱ ሆድ አምላኪ የግል ዓላማውን ለማሳካት እንደተሠለፈ … ብቻ ምን አለፋሽ ‘ፌስቡክ’ መጣና አስተዋወቀን፤” ብሎ ኮራ አለ። “እውን ከዚያ በፊት አንተዋወቅም ነበር?” ስትለው፣ “ይኼን ያህል ብንተዋወቅ ያውም እንዳሁኑ ልብ ለልብ እየተናበብን?…  ሳንበታተን የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ እንተውናለን? እኔ እጠራጠራለሁ፤” ቢላት እኛም ጥርጣሬ ገባን። ያልጠረጠረ ‘ብሎክ’ ይደረጋል የተባልን ይመስል፡፡

ወያላው ሒሳብ ይቀበላል። ከብዙ ማመንታት በኋላ ጉልቤው ታሪፉን ከፈለ። ሾፌራችን ጋቢና ከተሰየሙት ወጣት ተሳፋሪዎች ጋር ሞቅ ያለ ወሬ ይዟል። ወሬው በኳስ ዙሪያ ነው። “እኔ እንዴት መሰለህ እንባዬ የመጣው? የቼልሲ ባለሀብት ብሆን ሞሪንሆ እንኳን በሕይወት እያለ ሞቶም አላባርረውም፤” ይላል አንደኛው። “እንዴ ምንድነው እሱ የሚለው?” መጨረሻ ወንበር ከቆንጂት በስተቀኝ የተሰየመ ተሳፋሪ ወደ ጎን ዞሮ አጠገቡ የተቀመጠውን ተሳፋሪ ይኮሰትረዋል። “ይኼ የምትሰማው ድምፅ የእኔ የሚለው መኖሪያ ቤት ሳይኖረው በምናብ ቼልሲን የገዛ ባላሀብት ድምፅ ነው፤” ይላል ተጠያቂው እያላገጠ። ከወደ ጋቢና ደግሞ “ማንቸስተር እንደምንም ብሎ ሞሪሆን ካልቀጠረ በበኩሌ ራሴን ከደጋፊነት አገላለሁ፤” ይላል ጥግ ላይ የተቀመጠው። ወይዘሮዋ እየሳቀች፣ “ንሳማ ቶሎ ብለህ ለማንቸስተር ባለቤቶች በእሱ ነገር አስጠንቅቃቸው፤” ትለዋለች ሞባይሉን በአገጯ እየጠቆመች ወጣቱን ጎሸም አደረገችው። “ምን ልበላቸው?” ወጣቱ ስላቅ መሆኑ ገብቶት ሳቁን መቆጣጠር እያቃተው።

“ይኼ ደጋፊ ራሱን ከደጋፊነት ካገለለ ውኃ በላችሁ በላቸው። አደራ እንደምንም ብላችሁ ሞሪንሆን ቅጠሩለት በላቸው፤” ብላ ስታበቃ በፍልቅልቅ ሳቋ እኛንም አሳቀችን። ስታበቃ፣ “ወደው አይስቁ አሉ፤” እያለች በግርምት ወደ መንገዱ አማተረች። “ግን እንዲያው ከሞሪንሆ ጋርዲዮላን ካልቀጠሩ ራሳቸውን ከደጋፊነት በማግለል ክለቦቹን የሚጎዱ ኢትዮጵያውያን አይብሱም? አንድያዬን በጥናት አስደግፌ ብጽፍላቸው አይሻልም?” ሲላት ወጣቱ ምሳጤዋን አቋርጦ፣ “ጥሩ ሐሳብ! መቼም እዚህ አገር ማን አልሚ ማን አፍራሽ እንደሆነ ጥናት ከመሥራት ማን የአርሰናል ማን የቼልሲ ማን የማንቸስተር ደጋፊ እንደሆነ ጥናት መሥራት ይቀላል። ብቻ እንደተመቸህ፤” ብላው ወደሚመቻት የሐሳብ ቀዬ ዘመተች። ‘የገዛ ፀጉርህ መመለጡን ሳታውቅ ፈርጉሰን ስንት ሽበት እንዳበቀሉ በቁጥር ታውቃለህ፤” ብሏል አሉ ያ የፈንገሳችን ተንታኝ ወጌሻ። ሰሚ ሲኖር አይደል?!

ጉዟችን ቀጥሏል። የሰዓቱ ዜና ከወደ ስፒከሩ ሞቅ ብሎ ይሰማል። አፍሪካዊውን በሥለት ወግቶ ስለገደለ ተጠርጣሪ ጋዜጠኛው ያትታል። ከሾፌሩ ጀርባ ከጉልቤው አጠገብ የተቀመጡ በዕድሜ የገፉ ተሳፋሪ አንደበታቸውን አላቀው “እግዚኦ!” ሲሉ ይደመጠሉ። “ሮሚዬ ጁልየትን ተከትሎ የሚሞተው በሼክስፒየር ድርሰት ላይ ብቻ ሆኖ ቀረ በቃ?” አሉ። “አይገርምም አባት? ሰው ጠላቱን ችሎ እየኖረ ወዳጁን ያጠቃል። ይኼው ሆኗል፤” ይላል ጉልቤው። ሰውዬው ከጉልቤው ጋር ማውጋት አልተመቻቸውም። ታዲያ እንደያው ፊት ከማዞር ብለው ነው መሰል፣ “ይኼው እያየነው እኮ ነው። ዕድሜን ያህል ትልቅ ፀጋ ጊዜን ያህል ትልቅ ስጦታ መሄጃ አጣሁ ብሎ አንዳንዱ ተቀምጦ ይውላል፤” አሉት። ሽሙጡ ሲገባው፣ “ዋናው ነገር ተቀምጦ መዋልም ሥራ ነው ብሎ ራስን ማሳመን ነው። ዋናው ማመን ነው፤” አላቸው።

ሰውዬው አንጋጠው፣ “አቤቱ ዕምነት ጨምርልን ደመወዝ ባይጨመርልንም፣ ጡረታችን ባይሻሻልልንም ዕምነት ከጨመርክልን ይበቃል፤” ሲሉ ወይዘሮዋ፣ “ምነው ፍቅርን ረሱት?” አለቻቸው። “እህ ራሱን ከመስጠት በላይ ምን ይስጠን ልጄ? ብዙ ነገሮች ላይ እኮ ያጣነው ዕውቀት ሳይሆን ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው። ፍቅር ታላቅ ምሳሌ አለው። እንግዲህ እኔን እዩ እኔን ምሰሉ ብሎ ፈጣሪ ሥጋ ለብሶ ተወልዶ ሞተ፣ ተነሳም፤” ብለው ጉሮሯቸውን  ከጠራረጉ በኋላ፣ “የዘመኑ ሰው በማስመሰልና በመመሳሰል አንደኛ ሆኖ ፍቅር ላይ ግን አልቻለበትም። እውነቴን ነው። ወንጌሉ እንኳ ቀርቶ የፈረንጅ አክተሮችንና ፊልሞቻቸውን የምናመልከውን ያህል እኩዩ እንጂ ሰናዩ አይታየንም። እንዴ እንደ ክርስቶስ መሆን ቢያቅተን እንደ አንጀሊና እና ብራድ ፒት መሆን ይከብደናል?” ከማለታቸው ተሳፋሪዎች ሳቁ። ፍቅር እስከ መቃብር እንዳልተባለ ፍቅር እስከ በረኪና ሲሆን እያዩ ምን ይበሉ ታዲያ? ፍቅር በሥለትና በዱላ የታዘዘው የትኛው ‘ሴንቸሪ’ ላይ ይሆን ግን?

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። ጆሮ ማይሰማው ዓይን የማያየው የለም። “ሞት የቀለለበት ዘመን፤” ይላሉ አዛውንቱ። “ምን ያልቀለለ ነገር አለ? እልህ ልጅ አዋቂው ላይ ቤቱን ሠርቶ፤” ይላቸዋል ወያላው ጉልቤውን ሲሸነቁጠው። “ቤት ሳይኖረን?” አዛውንቱ ያዋዙታል። አንድ አንድ ተባብለው ነገር እንዳይጋጋል የሰጉ ይመስላሉ። “ምንድነው አንተ እዚህ ሥር ያስቀመጥከው?” መጨረሻ ወንበር የተቀመጠው ጎልማሳ የሰው ፌስታል ያንሿሿል። “ኧረ እረፍ ቦምብ ይሆናል…” ይላል ከወይዘሮዋ አጠገብ የተሰየመው ወጣት እያላገጠ። ጎልማሳው የምር አድርጎት አረፈው። ተንቆራጠጠ። “ወራጅ” እያለ ጮኸ። ወያላው፣ “ማን እንዳጠመደው ሳይጣራማ ማንም ንቅንቅ አይልም፤” እያለ በጎልማሳው ፍርኃት ይዝናናል። “ፈሪን ውኃ ውስጥ ያልበዋል አሉ፤” ይላሉ አዛውንቱ። “መፍራት ይነስብን አባት? ዘመኑ እኮ የሽብር ነው፤” ትላለች ቆንጂት። ትፍራ ትድፈር ቸግሯታል።

“ዘመንን ያህል ትልቅ ነገር ለሽብር አሳልፋችሁ ከሰጣሁ በአፋችሁ ነው ይበላችሁ አዛውንቱ ተበሳጩ። የፌስቡኩ ወጣት፣ “እነሆ አሁን በተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ ምንነቱ ያልታወቀ በፌስታል የተሸፈነ ዕቃ ቦምብ ይሆናል ተብሎ እየተዋከብን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፤” ብሎ ፖስት ሲያደርግ አያለሁ። ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆመች። “መጨረሻ” ብሎ ወያላው ደግሞ ዞሮ ሊሄድ መጥራት ጀመረ። ተንጋግተን ስንወርድ ጉልቤው አሁንም ቦታውን እንደያዘ ነው። ያው ጭቅጭቅ ሲደገም ሰማን። ‘አልወርድም ትወርዳለህ!’ አዛውንቱ በአጠገቤ እየተራመዱ “ምናለበት ይኼን እልሁን ለሥራ ቢያደርገው በመድኃኒዓለም?” ሲሉ እንደሰማሁ ጎልማሳው ከየት መጣ ሳልለው አጠገቤ ቆሞ፣ “ጉልበቱን ትተን በማስተዋል ማሰብ ካልጀመርን ብዙዎቻችን የዚህን ሰው ዙረት እንደ ንፋስ በከንቱ መደጋገማችን አይቀሬ ነው። ደግሞ እኮ ዘመኑ የሐሳብ እንጂ የጉልበት አይደለም፤” እያለ ብቻውን ዘለቀ። ሐሳብ የሌለበት ብልኃቱ ስሜት ነው ያለው ገጣሚ ትዝ ሲለን ተቃርኖዎቻችን ሁሉ ገሃድ የሚወጡ ይመስላል። ‘በዚህ ቀዬ በዚህ ጎዳና፣ ሐሳብ አንሶ ስሜት የገዘፈበት ሁኔታ ነው ያለው’ ብሎ ፖስት ያደርግ ይሆን ያ ወጣት? ወይስ ‘ለዘመናት የተጠራቀሙ ብሶቶች አቅጣጫቸውን ስተው የሌሎች መጠቀሚያ እየሆኑ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው’ ይል ይሆን? ወይ ደግሞ ታክቶት ይሆን? አታካች ዘመን! መልካም ጉዞ!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት