የዓለም ባንክ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ 11 ከተሞች ለሚኖሩ ከ600 ሺሕ በላይ ድሆች ድጋፍ ለሚተገበረው የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም 300 ሚሊዮን ዶላር ወይም 6.3 ቢሊዮን ብር ገደማ ብድር መፍቀዱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ በድህነት አረንቋ ውስጥ ለሚገኙ 604 ሺሕ ዜጎች ድጋፍ ይውል ዘንድ የፈቀደው ብድር ነው፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በአሳኢታ፣ በአሶሳ፣ በደሴ፣ በድሬዳዋ፣ በጋምቤላ፣ በሐዋሳ፣ በሐረር፣ በጅግጅጋ እንዲሁም በመቐለ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡
መንግሥት በከተማ ለሚኖሩ ‹‹የድሃ ድሃ›› ግለሰቦችና ቤተሰቦች የሴፍቲኔት ወይም የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ከመጪው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርግ መዘጋጀቱን የሚያሳይ የዕቅድ ሰነድ ይፋ ካደረገና ስትራቴጂ ማሰናዳቱንም ካስታወቀ ሰነባብቷል፡፡ በዕቅዱ መሠረት ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉና ከዚህም 124 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት እንደሚያስፈልግ ማቀዱን ይፋ ባደረገው ሰነድ አመላክቷል፡፡
የቀድሞው ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የአሁኑ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፣ የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች በየምዕራፉ ተግባራዊ እንደሚደረግ በሰነዱ አመላክቷል፡፡ በመሆኑም ተጠቃሚዎቹ ተከፍለው ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሥራ ለመሥራት አቅምና ጉልበት እያላቸው ሆኖም ‹‹በሥራ ላይ ባለው የተዛባ አመለካከት ምክንያት ሥራ ፈት የሆኑ፤ ሥራ የመሥራት ፍላጎት እያላቸው ሥራ በማጣታቸው ምክንያት ሥራ አጥ ሆነው የምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች ነው፤›› በማለት ሰነዱ አስፍሯል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ሰነዱ የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ አደርጋቸዋለሁ የሚላቸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች የመሥራት አቅም የሌላቸው የድሃ ድሃ የሆኑና ለምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦችና ቤተሰቦችን ነው፡፡ በጠቅላላው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በአቅም ግንባታ፣ በኑሮ ማሻሻያ፣ በማኅበረሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች እንዲሁም በማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክቶች በጠቅላላው ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዲታቀፉ መታቀዱን ሰነዱ ያብራራል፡፡
መንግሥት ያወጣውን ፕሮግራም በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ አስታውቆ፣ እንደ ችግሩ ስፋትና ክብደት ከተሞችን በተለያዩ ምድቦች በመከፋፈል ፕሮግራሙ ተግባራዊ እንደሚደረግ መታቀዱን ይዘረዝራል፡፡ በዕቅዱ መሠረት 972 ከተሞች በአምስት ምድቦች የተከፈሉ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምድብ የሕዝብ ብዛታቸው መቶ ሺሕና ከዚያ በላይ የሆኑት 19 ከተሞች ተካተዋል፡፡ በሁለተኛው ምድብ ከ50 ሺሕ እስከ መቶ ሺሕ የሕዝብ ብዛት ያላቸው 25 ከተሞች፣ በሦስተኛው ምድብ ከ50 ሺሕ በታችና ከ20 ሺሕ በላይ ሕዝብ ያላቸው 91 ከተሞች ሲኖሩ፣ በአራተኛው ምድብ የሕዝብ ብዛታቸው ከ20 ሺሕ በታችና ከአሥር ሺሕና ከዚያ በላይ ሕዝብ ያላቸው 191 ከተሞች ይካተታሉ፡፡ በአምስተኛው ምድብ ከሥር ሺሕ በታች ሕዝብ ያላቸው 646 ከተሞች ይካተታሉ፡፡
በከተሞች ለማኅበራዊ ኑሮ ጠንቆችና ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወላጅ ያጡ ሕፃናትና ሌሎችም በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይታሰባል፡፡ ከእነዚህ ባሻገር በከተሞች የሚኖሩ ሥራ አጦችና ሥራ ፈቶችን ለማሳተፍ የሚያስችሉ የሥራ መስኮች ከተባሉት ውስጥ የመንገድ ድንጋይ ንጣፍ ሥራዎች፣ የጎርፍና የውኃ ማስወገጃ መስመሮች፣ የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ መድፊያ ቦታዎች፣ የቤቶች ልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተካሄዱ ካሉትና ወጣቶችን እያሳተፉ ከሚገኙ የመንግሥት የከተማ ሥራ አጥ መቀነሻ ዘዴዎች ውስጥ ተካተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እያደራጀ ብድር በመስጠት፣ የማምረቻ ሼዶች፣ የመሸጫ ቦታዎች፣ የገበያ ማዕከላት በመገንባት ተጠቃሚ ሲያደርግ መቆየቱንም መንግሥት ይገልጻል፡፡
መንግሥት ባለፈው አምስት ዓመት ውስጥ በገጠሩ ክፍል ሥር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን 6.89 ሚሊዮን ቤተሰቦችን በሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሲያደርግ እንደቆየ፣ እነዚሁ ዜጎች የቤተሰብ ጥሪት እንዲገነቡና ከሴፍቲኔት ተጠቃሚነት ተመርቀው ራሳቸውን እንዲችሉ መደረጉን ይገልጻል፡፡ ይሁንና በአገሪቱ የተንሰራፋው ድርቅ የተመረቁትን ብቻም ሳይሆን አምራችና ራሳቸውን ችለው ይኖሩ የነበሩትን ሳይቀር ወደ ምግብ ተረጂነት እየከተተ እንደሚገኝ ታይቷል፡፡
ይሁንና መንግሥት የሴፍቲኔት ፕሮግራምን አስፋፍቶ ለመቀጠል መዘጋጀቱን በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሥት ትልቅ ሥራ እንደሠራና ስኬታማ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽበት በቆየው ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ ከሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች በተጨማሪ በአገሪቱ ለምግብ እርዳታ የተዳረጉ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎችንም ለማካታት አስገድዶታል፡፡ ለዕለት ደራሽ ምግብ እርዳታ የሚውል 1.4 ቢሊዮን ዶላር ወይም 29 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልገው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ወደ ከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ስንመለስ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከሚኖረው ሕዝብ ውስጥ 18.5 በመቶው በከተሞች የሚኖር ከመሆኑም በላይ ይህ ቁጥር በየዓመቱ በ5.1 ከመቶ እያደገ ስለሚሄድ፣ የከተሞች የሕዝብ ቁጥር ወደፊት በከፍተኛ ቁጥር እንደሚጨምር የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃን ዋቢ ያደረገው የመንግሥት ሰነድ፣ ለዚህ ይሁነኝ ካደረጋቸው የሥራ መፍጠሪያ መስኮች በተጨማሪ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንቶችንም ማዕከል አድርጓል፡፡
በከተሞች ያለው የከፋ ድህነት እየተባባሰ ከመምጣት አልፎ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ጥሪት በቀላሉ ማፍራት የሚችልበትና ከገጠሩ ነዋሪ አኳያ ሲታይ የመሬት ተጠቃሚ ባለመሆኑ ለከፋ ችግር መጋለጡን የሚያስረዱት ምሁራን፣ መንግሥት ወደፊት አስፈሪ ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት አሁን ላይ ለሚታዩት ምልክቶች ተገቢውን መፍትሔና ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ተ.ቁ |
ዋና ዋና ከተሞች |
የሥራ አጥነት ምጣኔ |
|||
2002 |
2003 |
2004 |
2005 |
||
1 |
መቀሌ |
21.5 |
23.2 |
19.8 |
18.5 |
2 |
አሳይታ |
7.5 |
11.1 |
9.2 |
12.9 |
3 |
ጎንደር |
18.6 |
18.2 |
15.8 |
14.1 |
4 |
ደሴ |
23.7 |
18.4 |
22.4 |
22.1 |
5 |
ባህር ዳር |
20.9 |
23 |
18.7 |
14.6 |
6 |
ቢሾፍቱ |
24.5 |
19.6 |
26.7 |
17.2 |
7 |
አዳማ |
27.4 |
21.1 |
24.3 |
22.5 |
8 |
ጅማ |
20.6 |
15.8 |
16.5 |
19.6 |
9 |
ሻሸመኔ |
15.8 |
15.9 |
24.3 |
24.5 |
10 |
ጅግጅጋ |
17.5 |
24.1 |
18.8 |
15.2 |
11 |
አሶሳ |
16.7 |
9.7 |
10.9 |
14 |
12 |
ሐዋሳ |
15.5 |
17.8 |
14.4 |
16 |
13 |
ጋምቤላ |
12.8 |
13.2 |
7.9 |
8.7 |
14 |
ሐረር |
15.3 |
13.6 |
12.2 |
15.4 |
15 |
አዲስ አበባ |
26.9 |
25.1 |
23 |
24.2 |
16 |
ድሬዳዋ |
30.2 |
22.9 |
22.9 |
22.3 |
በአገር አቀፍ/ከተሞች |
24.9 |
22.9 |
21.4 |
21.3 |
ምንጭ፡- የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም የአሥር ዓመት ዕቅድ ሰነድ