ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በገፍ የሚፈልጉትን የጽሕፈት መሣሪያዎች ግዥ ለመፈጸም የወጣውን ጨረታ፣ 15 በመቶ የፋይናንስ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው አሸናፊ የሆኑ አገር በቀል ኩባንያዎች የ340 ሚሊዮን ብር ስምምነት ሊፈራረሙ ነው፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በገፍ የሚፈልጉትን የጽሕፈት መሣሪያዎችና የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎች ለመግዛት ያወጣውን ጨረታ 16 አገር በቀል ኩባንያዎች አሸንፈዋል፡፡
ነገር ግን የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከተለያዩ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ጨረታውን ያወጣው፣ 1.9 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የጽሕፈትና የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎችን ለመግዛት ነበር፡፡
ከዚህ ውስጥ 16 የሚሆኑት አገር በቀል ኩባንያዎች አሸናፊ የሆኑት 340 ሚሊዮን ብር በሚያወጡ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ነው፡፡ ቁሳቁሶቹ በዋነኛነት የማስታወሻ ደብተሮች፣ የፎቶ ኮፒ ወረቀቶች፣ ቶነሮች፣ ሳሙናዎችና የተለያዩ የፅዳት ዕቃዎች መሆናቸውን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደሳሊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የተቀረውን ጨረታ አሸናፊ የሆኑት የውጭ ኩባንያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚያቀርቧቸው ምርቶቸ ላይ 35 በመቶ እሴት የሚጨምሩ ከሆነ፣ በመንግሥት ግዥ ጨረታዎች ላይ 15 በመቶ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የግዥ መመርያው ፈቅዶላቸዋል፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት ይህንን ልዩ ጥቅም ያገኙት ከስምንት ኩባንያዎች ያልበለጡ ሲሆኑ፣ ዘንድሮ የኩባንያዎቹ ቁጥር በእጥፍ አድጓል፡፡
አቶ መልካሙ እንደገለጹት፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ መንግሥት በፋይናንስ መወዳደሪያ ላይ 15 በመቶ ከፍ አድርገው ቢያቀርቡ እንኳ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በዚህ መሠረት ሌሎችም አምራቾች የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቶ መልካሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ከአገር በቀል አሸናፊ ኩባንያዎች ጋር ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚፈራረም ታውቋል፡፡