Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ክልል የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ሰመጉ ጠየቀ

በኦሮሚያ ክልል የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ሰመጉ ጠየቀ

ቀን:

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭት ምክንያት፣ የደረሰውን ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት የሚያጣራ ገለልተኛ የሆነ አካል እንዲቋቋም ጥሪ አቀረበ፡፡

ሰመጉ ይህን ያስታወቀው ‹‹ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ይቁሙ›› በሚል ርዕስ ታኅሳስ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አማካይነት ነው፡፡

ሰመጉ በመግለጫው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ በወሰዷቸው የኃይል ዕርምጃዎች፣ በኋላም በፀጥታ ኃይሎችና ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች መካከል በተነሱ ግጭቶች በተፈጸሙ የኃይል ድርጊቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንዳለፈ፣ ብዙዎች ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ፣ እንደታሰሩ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረትም እንደወደመ አመልክቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል፡፡

ግጭቱ በአሁኑ ወቅት የመርገብ ሁኔታ ማሳየቱን የሚገልጸው የሰመጉ መግለጫ፣ ‹‹በተቃውሞ እንቅስቃሴው የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መንግሥት በገለልተኛ አካል እንዲያጣራ፣ ለጥሰቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢው ካሳ እንዲከፈልና ቤታቸው ለተቃጠለባቸው፣ ንብረት ለወደመባቸውና ከኑሮዋቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ የማቋቋም ሥራ እንዲከናወን፤›› በማለትም ቀጣዩ ትኩረት ክስተቱን ማጣራት እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሰመጉ መንግሥት የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን በማርቀቅ ሒደት ዜጎችን በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን አለማሳተፉን ተችቷል፡፡ ይህም የብዙ ዜጎችን ሕይወት ለቀጠፈውና የአካልና የንብረት ጉዳት ላስከተለው ቀውስ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡

‹‹በሁኔታዎች አያያዝ ጉድለት የተነሳ ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ ሠልፍ በወጡ ዜጎችና የፀጥታ ኃይሎች መካከል አላስፈላጊ ውጥረትና ግጭት ተከስቷል፤›› ሲልም መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡

በግጭቱ የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል ስለመጠቀማቸው፣ በዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መጉደል ደርሷል የሚሉ አቤቱታዎችን ጨምሮ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጉባዔው በመመርመር ላይ እንደሚገኝና የምርመራውን ውጤት በቅርቡ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት የተለየ አጀንዳና አማራጭ አለን ከሚሉ ዜጎችና ስብስቦች ጋር ተቀምጦ የሚነጋገርበትና መግባባት የሚፈጠርበትን የውይይት ሥርዓት እንዲዘረጋና ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ ሰመጉ ጥሪውን ለመንግሥት አስተላልፏል፡፡

ሰመጉ ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው ቦታዎች ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ከተሞች፣ የምዕራብ ወለጋ፣ የአርሲ፣ የባሌና የምሥራቅና የምዕራብ የሐረርጌ አካባቢዎችን እንደሚያካትቱም ጠቅሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...