Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ግጭት ጉዳቱ ከባድ መሆኑ ተጠቆመ

በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ግጭት ጉዳቱ ከባድ መሆኑ ተጠቆመ

ቀን:

– በመድረክና በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው ሠልፍ ዕውቅና ተነፈገው

በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ግጭት በርካታ ሕይወትና ንብረት ውድመት ካስከተለ በኋላ በአምስተኛው ሳምንት አንፃራዊ ሰላም ይታያል፡፡ ሆኖም ግጭቱን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድና ኦሮሚያን ወደ ነበረችበት የመመለስ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በግጭቱ ምክንያት ከባድ ጉዳት መድረሱ እየተነገረ ነው፡፡

የደረሰውን የጉዳት መጠን አስመልክቶ ከመንግሥት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ምን ያህል ሰዎች ሞተዋል የሚለውን አሁን መነጋገር ትርጉም አልባ ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ነገር ግን የኦሮሚያ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የሟቾች ቁጥር 85 መድረሱንና ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነገአ ለሪፖርተር እንደገለጹት የተደበደቡ፣ የቆሰሉና የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺሕ በላይ ነው፡፡ ‹‹እስካሁን ከሦስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤›› ሲሉም አቶ በቀለ አክለዋል፡፡

አምስት ሳምንታት ባስቆጠረው ግጭት በፀጥታ ኃይሎች ላይ የሕይወት መጥፋትና የአካል መጉደል ከማስከተሉም በላይ፣ በርካታ ለፀጥታ ሥራ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የፌዴራል ፖሊስ ምንጮች አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን የአደጋው መጠን መግለጽ አስፈላጊ አለመሆኑን እነዚሁ የፌዴራል ፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሞት ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ከማድረስ በተጨማሪ ግጭቱ በሕዝብ መገልገያዎች፣ በግለሰቦች ንብረት፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በተሽከርካሪዎችና በመሳሰሉ ንብረቶች ላይ ቁጥሩ ለጊዜው ያልታወቀ ከባድ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል፡፡ በመንግሥት በኩል ያሉ ምንጮች በተቃዋሚዎች እየተገለጸ ያለው ቁጥር በተለይ በሕይወት ላይ የተጋነነ ነው ይላሉ፡፡

ከኅዳር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ ግጭት ሲካሄድባቸው የቆዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን፣ በሥፍራዎቹ የሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የሁከቱ መነሻ የነበሩት የምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ወለን ኮሚና ጊንጪ በአንፃራዊ ሁኔታ ሰላም ናቸው፡፡

ግጭቱ ጥሎ ያለፈው አሻራ ግን በግልጽ የሚታይ ሲሆን፣ ሞትና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች ሐዘን፣ የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች፣ የንግድና መኖሪያ ቤቶች እዚህም እዚያም በግልጽ ይታያሉ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችና የገበያ ሥፍራዎች የወትሮ መልካቸውን አለመያዛቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ በተለይ ችግሩ የተፈጠረባቸው አካቢዎች ከገቡበት ድብርት መውጣት አልቻሉም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን መነሻ ይሁነው እንጂ፣ ሌሎች ጥያቄዎችን ይዞ የተነሳውን ግጭት ለማብረድና የነበረውን ሰላም ለመመለስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ግጭቱን ለማብረድ ከሚወስደው ዕርምጃ ጎን ለጎን፣ የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማወያየት ሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡም ከዚህ ውይይት ባሻገር ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው የሚባሉ አካላትን ለማውጣጣት ግምገማ እንደሚደረግ የኦሮሚያ ክልል ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣው ከሕዝብ ጋር የሚደረግ ውይይት፣ የድርጊቱ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን የክልሉን የሥራ ኃላፊዎች በሚካሄዱ ግምገማዎች ለይቶ ማወቅና ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ እንዲታመንበት ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በውይይት መድረኮቹ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ግልጽና ያልተገደበ ውይይት በማድረግ በችግሩ መነሻ ምክንያቶችና ምንጮች፣ በአጥፊ አካላትና አስፈላጊ በሆነው የተጠያቂነት ሥርዓት፣ ስለችግሩ ተፅዕኖና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ከመለየት ይልቅ የውይይት መድረኮቹን ለፕሮፓጋንዳ ግብዓት መጠቀም ትክክል አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ይልቁንም ግጭቱን ማውገዝና ለችግሩ ተጠያቂነት ሙሉ በሙሉ መንግሥትን የማስወገድ አዝማሚያ ለዘላቂ መፍትሔ የማይጠቅም በመሆኑ፣ መንግሥት ድርጊቱን ዳግም እንዲመለከተው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ቀውስ ለጊዜው የረገበ ቢመስልም፣ አሁንም በጥንቃቄ ካልተያዘና ስህተቶች ካልታረሙ ማገርሸቱ የሚያሳስባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ናቸው፡፡ እኝህ ስማቸው በፍጹም እንዳይገለጽ የፈለጉ ምሁር፣ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት ከዜጎች ጋር ያላቸውን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንዲያስተካክሉ ይጠይቃሉ፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ለችግሮች ምክንያት የሆነው የጋራ ማስተር ፕላኑ፣ በክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ) የፀደቀው የከተሞች አዋጅ፣ የመልካም አስተዳዳር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሙስና ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ተቃውሞ በተነሳበት ወቅት በተፈጠረው ብጥብጥ የደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት ውድመት ዳግም እንዳይፈጠር ከተፈለገ የሕዝቡ አስተያየት መደመጥ አለበት ያሉት ምሁሩ፣ መንግሥት የተለየ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች በግልጽ ፍላጎታቸውን መስማት አለበት ብለዋል፡፡ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ካኮረፉ ማናቸውም ወገኖች ጋር በመቀራረብ መነጋገርና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ወሳኝ ነው ካሉ በኋላ፣ ይህንን ችላ ማለት ግን ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አሠራለሁ ማለት ትርጉም አልባ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ታኅሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ግጭት አሜሪካ ሥጋት እንደገባት አመልክቷል፡፡ መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ አካላት ላይ የኃይል ዕርምጃ ከመውሰድ እንዲታቀብ ይጠይቃል፡፡ መንግሥት ማስተር ፕላኑ ከሕዝብ ጋር ውይይት ሳይደረግበት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ያስታወሰው መግለጫው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በፍጥነት ውይይት እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

ታኅሳስ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይት ስዎች በበኩሉ፣ በግጭቱ 75 ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ የፈጸሙት ጥቃትና መንግሥት ተሳታፊዎችን ‹‹ሽብርተኞች›› ማለቱ ችግሩን አባብሶታል ብሏል፡፡

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲ የፊታችን እሑድ ታኅሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ለማድረግ ያሰቡት ሰላማዊ ሠልፍ እንደማይካሄድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በመድረክ አማካይነት የዕውቅና ጥያቄ የቀረበለት ሰላማዊ ሠልፍ፣ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተፈጠረው ሁከት በፀጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ግድያና የኃይል ተግባር ለማውገዝ ነው፡፡ አስተዳደሩ ግን ሰላማዊ ሠልፉ የሚካሄድበት ከራስ መኮንን ድልድይ እስከ ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት መናፈሻ (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ) የትራፊክ መጨናነቅ የሚበዛበት፣ ትላልቅ የመንግሥት ተቋማትና በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለሚገኙበት ለሰላማዊ ሠልፉ ዕውቅና መስጠት መቸገሩን አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...