Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን ጠቀለለው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባንኮች ተዋህደው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስም አንድ ግዙፍ ባንክ እንዲፈጥሩ ተወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር ተጠቃልሏል፡፡

የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ታኅሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረጉት፣ ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች ተዋህደው ግዙፍ ባንክ እንዲፈጥሩ በመንግሥት መወሰኑንና ይህም ውህደት በአጭርና በረዥም ጊዜ ተፈጻሚ እየሆነ ይሄዳል ብለዋል፡፡

በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ሁለቱ ባንኮች ባደረጉት ውህደት እንደ አንድ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋም ሥራ ይጀምራሉ፡፡ ውህደቱ ሙሉ ለሙሉ መቼ ይጠናቀቃል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ስንታየሁ፣ ‹‹አወቃቀሩና አደረጃጀቱ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ የሚፈጸም ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ስለአወቃቀሩና ስለአደረጃጀቱ ይዘት ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት የተቆጠቡት ዶ/ር ስንታየሁ፣ አዲሱ ተቋም አንድ ባንክ ሲዋሀድና ሲቋቋም ሊያሟላቸው የሚገባቸውን መሥፈርቶች አሟልቶ የሚደራጅ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን የሁለቱ ባንኮች ሀብት፣ ሠራተኞች፣ ካፒታልና ዕዳ ተዋህደው አንድ ተቋም ሆነው ይተዳደራሉ፡፡

አዲሱ ተቋም አደረጃጀቱ ሲያልቅ በኢትዮጵያ ግዙፍ ባንክ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ባንኩ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ታማኝ ሆኖ የሚሠራ ይሆናልም ተብሏል፡፡ እንደ አንድ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋም የሚንቀሳቀሰው አዲሱ ተቋም መጠሪያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚሆን፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር የሚካተት በመሆኑ መጠሪያ ስሙ ይከስማል፡፡

ዶ/ር ስንታየሁ፣ ‹‹ውህደቱ ከተፈጸመ በኋላ መጀመርያ የሚሰጠው ስያሜ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይሆናል፡፡ ይህ ስያሜ እንዲሰጥ የተፈለገበትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ ሀብት፣ ብዙ ሠራተኞች፣ በርካታ ቅርንጫፎች ያሉትና ግዙፍ በመሆኑ ስያሜው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተብሎ እንዲቀጥል በመፈለጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይዋሀዳል የሚለው ሐሳብ የተጠነሰሰው ከዓመታት በፊት ቢሆንም፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ይህንን ሲያስተባብል መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ሪፖርተር የሁለቱን ባንኮች ውህደት አይቀሬነት በሰፊ ዘገባ አስነብቦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ማስተባበሉ አይዘነጋም፡፡ በንግድ ባንክ የሚጠቀለለው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ደካማ አፈጻጸም ነበረው ተብሎ ሲቀርብ የነበረውን ትችት መሠረት የሌለው በሚል ሲያጣጥል መቆየቱም ይታወሳል፡፡

የውህደቱ ዋነኛ ዓላማ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በመዳከሙ ነው የሚለው  አስተያየት ዶ/ር ስንታየሁም አልተቀበሉትም፡፡ ‹‹በሁለቱ ባንኮች መካከል የተደረገው ውህደት በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ስኬት ላይ የነበረ እንጂ ውድቀት ላይ ያልነበረ ባንክ ነው፤›› በማለት ውህደቱ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በመዳከሙ የተወሰደ ዕርምጃ ነው የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አስተባብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ስንታየሁ ገለጻ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኝ ባንክ ነበር፡፡ በተለይ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (በፒአር) ተግባራዊ ካደረገ በኋላ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በኩል ባንኩ የተሻለ አሠራር እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቅርንጫፎቹን ከ33 ወደ 120 ማሳደግም ችሏል በማለት ባንኩ በተሻለ አቋም ላይ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ሆኖም ይህ ውጤት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠራር ጋር ሲታይ ሁለቱም የመንግሥት ባንኮች ናቸውና በአንድ ላይ ቢሆኑ መንግሥት የሚፈልገውን ትልቅ አቅም ሊፈጥር ስለሚችል ውህደቱ እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡ መንግሥት ከመንግሥት ባንኮች የሚጠብቀው ትልቅ ጉዳይ በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት በመሆኑ፣ በዚህ መሠረት ውህደቱ መፈቀዱን ዶ/ር ስንታየሁ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ውህደቱ የራሱ ዓላማ እንደነበረው፣ ውህደቱ የተፈጸመበት ዋነኛ ዓላማ ደግሞ የኢኮኖሚ ልማቱን ለማፋጠን ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ውህደቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ ነው፤›› በማለት ያስረዱት ዶ/ር ስንታየሁ፣ ወደዚህ ዕርምጃ ከመገባቱ በፊት በሁሉም የመንግሥት ፋይናንስ ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በምን መልክ መዋቀር አለባቸው? ተብሎ ጥናት ሲደረግ እንደቆየም ዶ/ር ስንታየሁ አስታውሰዋል፡፡

ይህንኑ ጥናት መሠረት በማድረግ በየደረጃው ውይይት ከተደረገ በኋላ፣ በመጨረሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አደረጃጀት ለልማት ከሚሰጡት ፋይዳ አንፃር እንዴት መደራጀት አለባቸው? የሚለው ከታየ በኋላ ሁለቱ ባንኮች እንዲዋሀዱ መወሰኑንም አስረድተዋል፡፡

ይህ የመንግሥት ውሳኔ ተግባራዊ እየተደረገ የሚፈጸም እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ውህደቱን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚኖሩም ከእሳቸው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ውህደቱ በባንኩ ደንበኞች፣ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ላይ ምንም ለውጥ ሳያመጣ የሚቀጥል እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ደንበኞች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጠቃለላሉ ብለዋል፡፡ ‹‹ተበዳሪዎችም ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ጋር ያደረጉት ውል የፀና ውል ስለሆነ፣ በውላቸው መሠረት የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎች መፈጸም ይገባቸዋል ብለን እናምናለን፤›› ያሉት ዶ/ር ስንታየሁ፣ ሠራተኞችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በተለይ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ምንም ዓይነት ሠራተኛ እንደማይቀነስ አስታውቀዋል፡፡ ሠራተኞች ሥራቸውን እያከናወኑ ሲቀጥሉ፣ ወደፊት ደግሞ አፈጻጸሙ በዝርዝር ይገልጽላቸዋል ብለዋል፡፡

ሠራተኞች የያዙት መብትና ጥቅም እንደሚከበርላቸው፣ ደመወዛቸው በነበረበት እንደተጠበቀላቸው የሚቆይ መሆኑን፣ ከዚህ ባሻገር የሠራተኛ አመዳደቡና ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ ጉዳይ በጥናት ላይ በተመሠረተ ውሳኔ እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ግን በዝርዝር እከሌ እንዲህ ይሆናል እከሌ ምንም አይሆንም የሚል ጉዳይ ያለመኖሩን ተናግረው፣ የሠራተኞች አመዳደብ በሕግ አግባብ ሁሉንም በሚጠቅም መንገድ ይከናወናል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ሀብቱ ከ310.9 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያለው ሀብት 7.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአብዛኛዎቹ የግል ባንኮች ጋር በንፅፅር ሲቀመጥ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያለው ነው፡፡

እንደ የባንክ ባለሙያዎች ገለጻ ይህ ውህደት ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ጥያቄ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የውህደቱ መሠረት ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ ውህደቱ ከአገሪቱ የንግድ ሕግ አንፃር ስለውህደት ከተቀመጡት ውስጥ የትኛውን መንገድ የተከተለ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳየው ነገር የለም፡፡ በጥቅሉ እየተባለ ያለው ተወሀዱ የሚለው ብቻ ነው የሚለው ባለሙያዎቹን ያሳስባል፡፡

ከዚህ ቀደምም በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዲስ ባንክ እንዲዋሀዱ ሲደረግ ሕጋዊ መሠረቱ ሲያነጋግር ነበር ተብሏል፡፡ አሁንም ይህ እየታየ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ውህደቱ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡

ማክሰኞ ዕለት በተሰጠው መግለጫው ላይም ዶ/ር ስንታየሁ የሁለቱ ባንኮች ሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም ዕዳ ይዋሀዳል ከማለታቸው ውጪ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ አልነበረም፡፡ የሁለቱ ባንኮች ውህደት ጥያቄ ያጫረባቸው ሌሎች ወገኖች ደግሞ፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፈጽሞ መነካት የሌለበትና ራሱን ችሎ መሥራት የነበረበት ነው ይላሉ፡፡

በልዩ ዘርፍ የሚታየውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲያግዝ ጠንክሮ እንዲወጣ ማድረግ ሲገባ፣ በንግድ ባንክ ውስጥ መወተፉ አግባብ አልነበረም ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጡንቻ እንዲፈረጥም ዕድል የሰጠ፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በአንድ የመንግሥት ባንክ ብቻ እንዲዋጥና የተወዳዳሪነትን መንፈስ የሚያሳሳ ይሆናል የሚል ሥጋት ያላቸውም አሉ፡፡

በሁለቱ ተጣማጅ ባንኮች መካከል ያለው ልዩነት ሲታይ ደግሞ ውህደት ሊባል አይችልም የሚሉ አሉ፡፡ ንግድ ባንክ ኮንስትራክሽን ባንክን እንደጠቀለለ ይቆጠራል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ቁጥር 10.7 ሚሊዮን በላይ ሲደርስ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ደግሞ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ደንበኞች እንዳሉት ማሳያ ነው፡፡ የንግድ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ 241.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ደግሞ 5.4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ንግድ ባንክ በ2007 ዓ.ም. 84.4 ቢሊዮን ብር ሲያበድር፣ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ግን 1.6 ቢሊዮን ብር አበድሯል፡፡

ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ጥቅምት 23 ቀን 1968 የተቋቋመ ሲሆን፣ በወቅቱ የቤቶችና የገንዘብ ቁጠባ ባንክ የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ ከደርግ ለውጥ በኋላ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በሚል ስያሜ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በ1984 ዓ.ም. 71.8 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ እንደ አንድ የመንግሥት አክሲዮን ኩባንያ በ1992 ዓ.ም. በ79.1 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ ነበር፡፡ ይህ የተደረገው ባንኩን ወደ ግል ለማዛወር ነበር፡፡ እንደ ዳሸን ባንክ ያሉትም ለመግዛት ሲደራደሩ ነበር፡፡

ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ 1,993 ሠራተኞች ሲኖሩት፣ 123 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 992 ቅርንጫፎችና ከ30 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡

የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መጀመሪያ በኢትዮጵያ የንብረት ማልሚያና የገንዘብ ቁጠባ ባንክ ተብሎ እ.ኤ.አ 1965 ሲቋቋም የነበው ካፒታል ሦስት ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ የባንኩ ባለአክሲዮኖችም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት ባንክ ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች