Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሠርግና የጋብቻ ትስስር በጋምቤላ

ሠርግና የጋብቻ ትስስር በጋምቤላ

ቀን:

ማንኛውም ኅብረተሰብ የሚጀምረው ከቤተሰብ ሲሆን፣ የቤተሰብ መሠረቱ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል ጥንዶች እርስ በርስ ተፋቅረውና ተስማምተው የሚመሠርቱት የጋራ ሕይወት ነው፡፡ ጋብቻ በኅብረተሰብ ደረጃም ይሁን በጋብቻ ፈጻሚዎቹ ዘንድ መሠረታዊ ትርጉም ያለው፣ ሰዎች ከአንድ የዕድሜ ክልል ወደሌላ የዕድሜ ክልል መሸጋገራቸውን የሚያረጋግጡበት፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖራቸው ተግባርና ኃላፊነት፣ ከበሬታና ተቀባይነት ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚቀየርበት፣ በግላዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከራሳቸው አልፈው የሌላን ሰው ሕይወት የሚጋሩበትና የራሳቸውን የሚያጋሩበት ልዩ ምዕራፍ ሲሆን፣ በብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘንድ በወጥነት የሚከወን ማኅበራዊ ሥርዓትና ክንዋኔ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የጋብቻ አፈጻጸምና ባህላዊ ክዋኔው ከቦታ ቦታ፣ ከባህል ባህል፣ ከሀገር ሀገር ይለያያል፡፡ በጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል ባሉ አምስት ነባር ብሔረሰቦች ዘንድም እንዲሁ ከመጠነኛ መቀራረብ በስተቀር የራሱ የሆኑ ልዩ ልዩ አፈጻጸሞች ያሉት ማኅበራዊ ክንዋኔ ሆኖ እናገኘዋለን ይለናል ስለጋምቤላ ክልል ሁለንተና ገጽታ የሚዘረዝረውና በብሔረሰቦች ቀን አጋጣሚ የወጣ አንድ ድርሳን፡፡

በጥንታዊነታቸው ከሚመደቡት የሠርግና የጋብቻ ባህሎች ጎራ ሊመደብ የሚችለው የጋምቤላ ትውፊት የራሱ መለያ ያለው የሠርግና የጋብቻ ትስስር የሚጎላበት ነው፡፡ በአምስቱም አካባቢዎች የሚስተዋሉት እነኚህ የሠርግና የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች እንደየትኛውም ብሔረሰብ ለየት ባለ መልኩ ተጀምሮ ይጠናቀቃል፡፡ በሞቃታማው መንደር ነፋስ የማያንቀሳቅሳቸው ዛፎች ሥር በምግብ ዝግጅትም ሆነ በእጅ ሥራ ተጠምደው ከሚታዩት ሴቶች መካከል በቀዬው በመደገስ ላይ ባለው ሠርግ ምክንያት ቅደም ዝግጅት እንዳለ ሊያሳብቅ ይችላል፡፡ እርግጥ ለወትሮው በአካባቢው ባለው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሁሉም ብሔረሰቦች ማለት በሚያስችል መልኩ ውሏቸው ደጅ (ከቤት ውጪ) በመሆኑ ማንኛውም እንቅስቃሴ ደጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ወንዶችም ቢሆኑ በቤቶቻቸው ደጃፍ በሚገኙ የዛፍ ጥላዎችና መከዳዎች ሥር ጋለል ብለው የቀኑን ሙቀት ሲያሳልፉት ይታያል፡፡

ይሁንና የሠርጉ ዝግጅት ከእነዚህ ተለምዷዊ የሰርክ ውሎዎች በመጠኑም ቢሆን ለየት ባለ አካሄድ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ከዝርዝር የሠርግ ሒደቶች መለያየት ውጪ በሠርግ ዝግጅቱና በጋብቻ ሒደቱ በአምስቱም ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ሁኔታ ቢታይም በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ያለው የሠርግና የጋብቻ ትስስር ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ይህን ይመስላል፡፡ 

በኑዌር ብሔረሰብ የጋብቻ ሥርዓት አንድ ወንድ ልጅ ለማግባት ሲፈልግ የልጅቷ አባት በቂ ከብት ያለው መሆኑንና ልጅቷ ፈቃደኛ መሆኗን በማረጋገጥ ለአባቱ ያሳውቃል፡፡ ልጅቷም ለአባቷ ነግራ ፈቃድ እንዲሰጣት ትጠይቃለች፡፡ ሁለቱም ቤተሰቦች በሚፈልጉት መልኩ ሠርጉ እንዲፈጸም የሚከለክል ጉዳይ እንደሌለ ካረጋገጡና ለጥሎሽ የሚሆን ከብት መኖሩ ከታወቀ በኋላ ፈቃድ ይሰጣል፤ በመጀመሪያ የወንድ ቤተሰቦች በርከት ያሉ የከብት ስጦታዎችን ለሴት ቤተሰቦች ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በሴቷ ቤተሰብ የደስታ ቀን ይሆናል፤ ይጨፈራል፤ ይዘፈናል፤ ግብዣም ይደረጋል፡፡ የወንድ ቤተሰቦች ተጨማሪ የከብት ስጦታ ይሰጣሉ፡፡ ግብዣ ተደርጎ ‹‹ቡል›› የተባለው አስደሳች ጭፈራ ይጨፈራል፤ የልጅቷ የመታጨት በዓልም በዘመድና በጎረቤት ፊት በከፍተኛ ደስታ ይከናወናል፡፡ ከዚህ በኋላ ወንዱ ለሙሽራዋ ልብሶችና የተለያዩ ጌጦችን ይገዛል፡፡ ይሁንና ወጣቱ እጮኛውን ለመጨረሻ ጊዜ የእርሱ አድርጎ ወደ ቤቱ የሚያስገባት የመጀመሪያ ልጅዋን ስትወልድ ነው፤ እንደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ድርሳን፡፡ በእነዚህ ወቅቶች የባልና ሚስቱ ግንኙነት በሚስቱ ቤት ብቻ የተወሰነ ይሆናል፡፡ በሠርግ ወቅት የሚዘፈኑ ዘፈኖችና ጭፈራዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ማራኪ አለባበሶች ለሠርጉ ትልቅ ድምቀት ይሰጣሉ፡፡ ዘፋኞቹ ሙሽራዋንና ቤተሰቦቿን ያሞግሳሉ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሳይደራረቡ በየተራ ይሰማሉ፤ ጭፈራው ባህሉን ጠብቆ ሴቶች ‹‹ዮሀ›› ለብሰው፣ ወንዶቹ ‹‹ጆንግ›› የተባለውን ከፈረስ ጭራ የተሠራ ጌጥ በግራ ክንዳቸው አስረውና፣ ጦር ይዘው ይጨፍራሉ፡፡

በአኙዋሃ ብሔረሰብ ዘንድ አራት ዓይነት የጋብቻ አፈጻጸሞች አሉ፡፡ እነዚህም በግልና በጓደኛ፣ በመንደር ወይም በሠፈር በማፈላለግ፣ በቤተ ዘመድ እና በውርስ የሚደረጉ ጋብቻዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የጋብቻ ዓይነቶች በመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ጥሎሽ መክፈል ግዴታ ሲሆን፣ በአራተኛው ግን ከቤተ ዘመድ የተወረሰች ስለሆነና ቀድሞ ጥሎሽ ስለተጣለላት ተጨማሪ ካላስፈለገ በስተቀር ጥሎሽ አይከፈልም፡፡ ጥሎሽ ግዴታ በሆነባቸው የጋብቻ ዓይነቶች ሠርግ የሚከናወነው ተጋቢዎች መስማማታቸው ከታወቀ በኋላ ወንዱ ጥሎሽ ለሴት ዘመዶች ከፍሎና አቅሙን አጎልብቶ ድግስ በመደገስ እኩዮቹንና የሙሽራዋን እኩዮች፣ መጠራት የሚገባቸውን ዘመዶኛ ጓደኞች በመጋበዝ ነው፡፡ አንድ ወንድ ከእርሱ የምታንስን ሴት ልጅ ቢወድ ጥሎሽ ጥሎ ለአቅመ ሔዋን እስክትደርስ ይጠብቃታል እንጂ በልጅነቷ አያገባትም፡፡ ዕድሜዋ ሲደርስም እርሷ ካልፈለገችው የመረጠችውን የማግባት መብቷ የተጠበቀ ሲሆን፣ የመረጠችውን ካገባች በኋላ ቀድማ የተቀበለችውን ጥሎሽ ትመልሳለች፡፡

በአኙዋሃ ወንዶች እንደ አቅማቸው ከሁለት በላይ ማግባት ይችላሉ፡፡ ሴቶች ግን የመጀመሪያ ባላቸውን ከፈቱ በኋላ የሚያከናውኑት ጋብቻ ክብደት የለውም፡፡ ወንድ ሊያገባ የፈለጋትን ልጅ በመረጠ ጊዜና የልጅቷንም ፈቃደኝነት ባገኘ ጊዜ በቤተሰቦቿ ፊት በልጅቷ አንገት ላይ ‹‹ድሙይ›› የሚባል ውድ ጨሌ ጥሎሽ ይጥላል፡፡ ከእነዚህ ሒደቶች በኋላ በሠርጉ ወቅት ወንዶች በእግራቸው ላይ ‹‹ገሬ›› የሚባል ጨሌ፣ በክንዳቸው ላይ ደግሞ የፈረስ ጭራ በማድረግ ይጨፍራሉ፡፡ በተመሳሳይ ሴቶችም ‹‹ሙይቶይ›› ጨሌ በወገባቸው፣ ‹‹መዳሌ›› በእግራቸው አድርገው ይጨፍራሉ፡፡ አኙዋሃዎች ሠርግ ሲከወኑ ‹‹አቡራ›› – የትንፋሽ መሣሪያ፣ ‹‹ቱም›› – ክራር እና ‹‹ቡል›› – ከበሮ በመጠቀም ይጨፍራሉ፡፡

በማጃንግ ብሔረሰብ አንድ ወንድ አቅሙ ካለው እስከ አራት ሚስቶች ማግባት የሚችል ሲሆን፣ ወንድሙ በሚሞትበት ጊዜም በውርስ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት መሠረት የወንድሙን ሚስት ማግባት ይችላል፡፡ በማጃንግ ባህል ጋብቻ በሴት ልጅ ፈቃድና ስምምነት በጠለፋ ሊከናወን ይችላል፤ በዚህ ሥርዓት ወንዱ የወደዳትን ሴት በልዩ ልዩ መንገድ ፈቃደኝነቷን ከጠየቀና ሐሳቡን በመግለጽ ካረጋገጠ በኋላ ለአባቱ ወይም ለቤተሰቡ የሚያገባትን ወይም የሚጠልፉትን ሴት እንዳገኘ ያሳውቃል፡፡ ከዚያ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ከራስዋ ጋር ተመካክሮ በስምምነት የጠለፋውን ቀንና ሰዓት ይወሰናል፤ በወሰኑት ቀንም ሁለቱ ተገናኝተው ከጓደኞቹ ጋር ራቅ ወዳለ ቦታ ግሃደው ዘመድ ቤት ይደበቃሉ፡፡ ከዚያም ደረጃ በደረጃ ግጭት ሳይነሣ ለቤተሰብ በማሳወቅና ሽማግሌ በመላክ ሕጋዊ የሆነ ጋብቻ ይመሠርታሉ፡፡ በሠርጋቸውም ወቅት ልዩ ልዩ ዜማዎች ያዜማሉ፤ በጭብጨባ፣ በከበሮ የታጀበ በእግር መሬት እየተመታ የሚዘፈን ዘፈንና ጭፈራ ይጫወታሉ፡፡ ማጃንጎች የተለያዩ የትንፋሽ፣ የክር፣ የምት፣ የሚንቀጫቀጭ ድምጽ የሚያወጡ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሠርግን ያጅባሉ፡፡

በኦፖ ብሔረሰብ ጋብቻ በልዩ ልዩ መንገድ ይፈጸማል፡፡ አንደኛውና ጥንታዊ የሚባለው ሥርዓት የእህት ለእህት ቅይይር ነው፤ ይህም ማለት አንድ ወንድ ማግባት የሚችለው በቅያሬ የሚሰጣት እህት ካለችውና የእጮኛው ወንድም የእሱን እህት ለማግባት በሽማግሌዎች ተጠይቆ ፈቃደኛ ከሆነ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥርዓት የፈቃድ ጠለፋ ሲሆን፣ ወንድ ልጅ ለማግባት ያሰባትን ሴት ፈቃደኝነቷን ካረጋገጠ በኋላ ለማግባት መፈለጉን ለመግለጽ ሲል ብቻ ያለ ምንም ግዴታ ከልጅቱ ጋር በመስማማት ይጠልፋታል፡፡ በዚህ ዓይነት ጋብቻ ወላጆቿ ከሰሙ በኋላ ልጅቷ ወደ ቤቷ ትመለሳለች፤ ከዚያም በሽማግሌዎች አማካይነት የሠርግ ቀን ተወስኖ ይፋዊ ሠርግ ይፈጸማል፡፡

በሠርጉ ጊዜ ወንዶች የሰጎን ላባ ጭንቅላታቸው ላይ አሥረው፣ ሴቶች ጨርቅ በአናታቸው ላይ ጣል አድርገውና ‹‹ተቁ›› (ቀይ አፈር) ተቀብተው ይዘፍናሉ፡፡ ወንዶች በግራ ክንዳቸው ባሠሩት የቀጭኔ ወይም የፈረስ ጭራ ሴቶቹን ጠጋ ጠጋ እያሉ ወገባቸውን ወንጨፍ በማድረግ ይጨፍራሉ፡፡ በሠርግ ላይ ከሚከወኑ ጭፈራዎች ‹‹ሲያቦት›› የተባለውን የትንፋሽ መሣሪያ በመጠቀም የሚታገዝ ከስምንት እስከ አሥራ ሁለት የሚሆኑ የሠለጠኑ ሰዎች የሚሳተፉበት፣ የመሣሪያ ተጫዋቾቹ ክብ ሠርተው እየነፉ መሬት እየመቱ መሣሪያዎቹ ድምጽ ሲያወጡ ሴቶች በኋላ በኩል እየተሽከረከሩና ተያይዘው በእግራቸው መሬቱን እየመቱ በእልልታ እየጨፈሩ የሚሳተፉበት የተለየ ጭፈራ ነው፡፡

በኮሞ ብሔረሰብ የተለያዩ የጋብቻ ሥርዓቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በሽምግልና (ማሽ) የወንድ ቤተሰብ ልጃችሁን ለልጃችን ስጡን ብለው የሴት ቤተሰብን ጠይቀው ይሁንታን ካገኙ በኋላ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህም የሴት ቤተሰብ የልጅቷን መታጨት ለማመልከት ጨሌና አንባር ያደርጉላታል፡፡ በጉሎ ዘይትም መላ ሰውነቷን ይለቀልቋታል፡፡ ብዙም ጊዜ ሳይቆይ ለሠርግ ቀጠሮ ተይዞ ይደገሳል፤ ቦርዴ ተጠምቆ ጎረቤት ተሰብስቦ እየተጨፈረ ሙሽራውና ሚዜዎቹ መጥተው ሙሽራዋን ሊወስዱ ሲሞክሩ ሙሽራዋ እምቢ ትላለች፤ ከዚያ ወንዶቹ አሸንፈው ተሸክመው ይወስዷታል፡፡ ሁለተኛው የጋብቻ ዓይነት በጠለፋ የሚደረግ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ወንዱ ሊያገባት የወደዳትን ሴት ጠልፎ ወደቤቱ ይወስዳታል፤ በልጅቱ ቤተሰቦች ዘንድ ልጃቸውን ማን እንደወሰዳት ሲታወቅ አባቷና  ወንድሞቿ ሄደው ተጠልፋ ካደረችበት ቤት ያመጧታል፡፡ ወዲያውም የወንድ ቤተሰብ ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ቤት ይመጡና ከእኛ ጋር ያደረችውን ልጅ ለጋብቻ እንፈልጋታለን በማለት ጠለፋውን ይፋ በማድረግ ሠርግ እንዲፈጸም ያደርጋሉ፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ጋብቻ በቀድሞ ጊዜ ይደረግ የነበረውና አሁን እየቀረ የመጣው የእህት ለእህት ለውጥ ጋብቻ ነው፡፡ አራተኛው የጋብቻ ዓይነት በአሁኑ ጊዜ በሰፊው የሚዘወተረው በሁለቱ መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ጋብቻ ነው፡፡

በኮሞ ብሔረሰብ ወንዶች በመጀመሪያ ሚስቶቻቸው ወይም በራሳቸው መራጭነት እስከ ሦስት ሚስት ድረስ ሊያገቡ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያዋ ሚስት ሌሎቹን ሚስቶች አትቃወምም፤ ምክንያቱም በአንድ በኩል እንደቀናተኛ እንዳትቆጠር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ ስለምታግዛት ነው፡፡ በኮሞ የሠርግ ቀን የሚሆነው በብዛት የበቆሎ ምርት በሚደርስበት ወቅት በሐምሌ አካባቢ ሲሆን፣ ቦርዴ ጠላና የበቆሎ ገንፎ ተዘጋጅቶ፣ ሙሽራዋ ከቤቷ ስትወጣ ‹‹ሿበጣማሽ›› የተባለ ጭፈራ እየተጨፈረ፣ አጃቢዎቿና ጓደኞቿ በእግራቸው መሬቱን እየመቱ፣ በ‹‹ቡል›› (ከበሮ) ታጅቦ ነው፡፡ በኮሞዎች የታወቀው የትንፋሽ መሣሪያ (ሼን) በሠለጠኑ አሥራ ሁለት ሰዎች ይቀርባል፡፡ በኮሞ ብሔረሰብ ባህል አንድ ወንድ የጎሳውን አባል ማግባት አይፈቀድለትም፤ ስለዚህም የትዳር አጋሩ የግድ የሌላ ጎሳ አባል መሆን ይኖርባታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...