Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አንዳንዴማ እንተላለፍ እንጂ ጎበዝ!

ሰላም! ሰላም! “ይህቺን ዓለም ሦስት ዕፀ በለሶች ቀይረዋታል፤” ይለኛል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ብዙ ትርጓሜ ስለተዛባብን እዚህ ጋ ዕፀ በለስን ‘አፕል’ እንበለውና እንጫወት። ብርቱካንና ሙዝ ወይ ሰው ታሞብን ወይ እኛው ታመን የማንሸምት ሰዎች፣ ዘለን አፕል ስንል ባንበላውም ከስሙና ከታሪኩ ብንጠግብ ብለን ነው እሺ። ብራቮ! እናም ልባሙን ሁሉ ልበ ቢስ አድርጎታል አሉ አፕሉ። የባሻዬ ልጅ ‘ልብ በል’ እያለ አንዳንድ ባለፀጋ ደንበኞቼ ቤት ኮሚሽን ልቀበል ስሄድ ካልሆነ በስተቀር፣ ገዝቼ ለመግመጥ የማልደፍረውን የአፕል ቅደም ተከተል እንደሚከተለው ይዘረዝረዋል። ለዝርዝሩ የባሻዬ ልጅ ነው ነገሩ። አቢሲን ከመሰልኳችሁ ‘ቼንጅ’ አድርጉኝ! ዲሽ የሌላችሁ አርፋችሁ አዳምጡኝ! ቂቂቂ!

እንግዲህ ይህቺን ዓለም ከቀየሩት ሦስት ዋና ዋና አፕሎች አንደኛው ያው የፈረደበት አዳም በሔዋን ጋባዥነት በእባብ ጀንጃኝነት የገመጣት አፕል መሆኗ ነው። እዚህ ላይ ባሻዬ አይስማሙም። “አፕል ከኢትዮጵያውያን ባህልና የአመጋገብ ሥርዓት ሩቅ በመሆኑ ምክንያት ዕፀ በለስ በሚለው ትርጓሜ ብቻ መረዳት አለብን፤” ይላሉ። ሁለቱ ዘመኖች ታዲያ ሲከራከሩ እንዲህ አይምሰላችሁ። ልጃቸው “ዕፀ በለስ ምንድነው?” ይላል። “የታለ አሳየኝ?” ይላቸዋል። ባሻዬ፣ “አንዳንዴ ከሚታይና ከሚጨበጥ ማስረጃ ይልቅ አንድምታው ሰፊ የሆነ ትርጉም ተቀበል፤” ይሉታል። አሻፈረኝ ሲላቸው፣ “ኢሕአዴግን ይመስል በሚጨበጥና በሚዳሰስ ተግባራዊ ፍልስፍና ብቻ ከተመራህ፣ የሰው ልጅ የልብ ትርታና የሕዝብ የመንፈስ ጥማት ጉድለት መነሾው ይጠፋህና አጓጉል ትሆናለህ፤” አሉት። ይኼኔ፣ “መንግሥታችን አጓጉል ሆኗል እንዴ?” ብዬ እኔ ጣልቃ ስገባ፣ “እለፈኝ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው። የምለው ባጣ ነው፤” ብለው መለሱልኝ። አለፍኳቸው። ታዲያ ባሻዬን ያህል የአገር ሀብት፣ የወግና የባህል ባለፀጋ አዛውንት አፍዎን አዳጠው ብዬ አጓጉል ላድርጋቸው? አንዳንዴማ እንተላለፍ እንጂ ጎበዝ!

መተላለፍ የማይሆንላቸውን እንተዋቸውና ወደ ሁለተኛው ትንተና ስንሄድ ሁለተኛዋ ዓለምን የቀየረች አፕል (በባሻዬ ትርጉም ዕፀ በለስ) የኒውተን አፕል ናት ይላል ልጃቸው። አዳምን የጣለችው አፕል ቀን ጣላትና ወደቀች። ስትወድቅም የአዳም ልጅ (ስንተኛ ልጁ እንደሆነ ዳርዊን አጣሪ ኮሚቴ እንዲያቋቁም መንገር ነው) በወደቀባት እሾህና አሜኬላ በምታበቅል ዓለም ቁጭ ብሎ በጥሞና አስተዋላት ነው ንግርቱ። እናም “ለምን ወደቀች?” ብሎ ተነሳ። እዚህ ላይ ላቋርጥና እንዲያው መቼ ነው የሰው ልጅ የገዛ ራሱን ሥልጣኔ፣ ንቃት፣ ዕውቀትና ምጥቀት ላይ አድርሶ ፈጥፍጦ ሲጥለው ለምን ወደቅኩ እያለ መጠየቅ የሚጀምረው? እውነቴን እኮ ነው። በበኩሌ ምን እንደተጣባን አላውቅም። በተለይማ እኛ ሐበሾቹ . . . የሰው አወዳደቅ፣ የጎረቤት ልጅ አይሆኑ ሆኖ መቅረት፣ ጠላታችሁን ውደዱ የሚል መጽሐፍ አማኝ ነን እያልን የወዳጅንም የጠላትንም ፍፃሜ አለማማር በጉጉት ስንጠብቅ ለሚታዘበን አስገራሚዎች ነን። ተሳሳትኩ? ግድ የለም ስለኛ ሰፊ ጊዜ አለ። ዳርዊንን ለምን እንርሳው? እሱም እኮ የሰው ዘር ነው። ነው የግድ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት በእሱ ለመኩራት? አይ ምናልባት እኮ ይኼ የዘረኝነት አባዜ እንዴት ዥዋዥዌ እንደሚያጫውተን አይታወቅም ብዬ ነው።

እናማ ጋሼ ዳርዊን ምን እንደጣላት ሲመራመር የስበት ኃይልና መጠን ደረሰበት። አዳሜ እንደ ፊኛ የማትንሳፈፊው 9.8 ምናምን (አሁን እስኪ ደላላ እመስላለሁ ቁጥር ስረሳ?) መሬት ጠፍንጋ ስላሰረቻችሁ ነው አለ። ይገርመኛል ብቻ! ዛሬ ዛሬ ማማካኛ ፍለጋ በየአገሩ ሕዝብና መንግሥት መብቴን ጣሰ ግዴታውን ረሳ እየተባባለ ሲተሳሰር ሲፈታታ መሬት ያለምንም ግዴታና መብት ውል ያለፈቃዳችን፣ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ አሰረችን ብሎ የሚጠይቅ ሰምቼ አላውቅም። ዳርዊን ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር የማድረግ የሰው ልጆችን ሒደት ሀ ብሎ እንዲህ ሲጀምር፣ እርሱም በቁጥጥር ሥር መዋላችንን አላሰመረበትም። ለዚህ እኮ ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን የተተረተው ይባላል። ይባላል ነው ደግሞ!

ሦስተኛዋ ታዲያ ወዲህ ናት። ይህቺ በጆሮ እየሰካናት የሰሚ ደንቆሮ የምታደርገን ነገር የለችም? ስቲቭ ጆብስና ተባባሪዎቹ ናቸው አሉ አፕል ለመግመጥ የማያወጣውን ወጪ፣ የአፕል ምርት ለመግዛት ሲሆን ዘርግፎ እንዲያወጣው ያደረጉት። ማንን? ሰውን ነዋ! ሰው ለጤና የሚሰጠው ጥቅም የሚበልጠውን ፍሬ ከመግመጥ ይልቅ፣ ዓይንና ጆሮ የሚያዳክም ታብሌትና አይፓድ ሲሸምት ይውላል። “አይ ሐበሻ!” ይለኛል የባሻዬ ልጅ። “ምን አሥር ጊዜ ሐበሻ ሐበሻ ትላልህ?” እለዋለሁ፡፡ “ዶሮና በግ ተወደደብኝ ብሎ እሪ ይላል። በገበያው እህሉ ዋጋው ናረ ብሎ እግዚኦ ይላል። አይፎን ታድሶ በወጣ ቁጥር ታዲያ ከእኛም ብሶ አዲስና አሮጌ እናማርጣለን። በውድ የገዛነውን ስልክ በኩራት በአደባባይ እናሳየዋለን። የምንበላው ግን ያንገበግበናል። አጃኢብ እኮ ነው!” ሲለኝ ፈገግ አልኩ።

አንድም ፈገግ ያልኩት፣ “አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ ጣለች። ቤቲም ቧሏ የገዛላትን ስምንተኛ አይፎን ጣለች። ጥለህ የማትጥል አምላክ እባክህ እኔንም አንድ ቪላ ቤት ያላት ላይ ጣለኝ፤” ብሎ ፖስት ያደረገ ወዳጄ ትዝ ብሎኝ ነው። ትዝታውስ ትዝታ ነው። ደግሞ አንዴ እንዲሁ በየወሩ አዳዲስ አይፎን ስሎክች መግዛት የምትወድ ቀበጥ ልጅ አጋጥማኛለች። የተዋወቅነው ዱባይ ሄዳ ኮሮላ ጭና ትመጣና እዚህ መሸጥ ስትፈልግ ነው። ለካ እዚያ ዱባይና አቡዳቢ አካባቢ ልጥጥ ያሉት ቱጃር ዓረቦች ስልካቸውን አውጥተው ራሳቸው አይነካኩም። ስልክ የሚደውል ምን ልበላችሁ በቃ የሚጎረጉርላቸው ሰው ይቀጥራሉ አሉ። ልማታዊ ከሆናችሁ የሥራ ፈጠራ ትሉታላችሁ። ካልሆናችሁም ደግሞ የምትሉትን በሉት። እኛ በስያሜ እንጣላለን እነሱ በመኖር ይስማሙበታል። አለቀ!

ታዲያላችሁ ልጅት ያንኑ ሰሞን የስልክ ቀፎ በየሳምንቱ መቀያየርን አልፋ ቁጥር አውጥቶ ደውል ለማለትም ሰነፈች። ይኼን ጊዜ አንድ የዘመድ ልጅ ከገጠር አስመጥታ ይዛው ትዞር ጀመር። ያን ሰሞን ትዝ የሚለኝ ሦስት ኮሮላዎች በጥሩ ዋጋ መሸጣችን ነው። እናም ያ ገራገር የዋህ ለራሱ አዲስ አበባ ብርቅ ሆናበት ፎቁን ቆጥሮ መጨረስ አቅቶታል። ሲያይ ከወንዱ በላይ ሴቱ ይኼን አውቶሞቢል ለጉድ ያሽከረክረዋል። ምን ይበል? ጭራሽ ይኼን ምስኪን ገና የመጀመሪያዋ የዕፀ በለስ መንደር የነበረ ጉብል ያለሒደት አይፎን ላይ መጥቶ ሲቀመጥ አያብድም? አበደ! በአጭር ጊዜ ቀልጣፋ ሆነ። ስልኩ በውድ ዋጋ እንደሚገዛና እንደሚሸጥ ሰማ። ከዕለታት አንድ ቀን፣ “ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ጋ ደውል፤” ልትለው ዘወር ስትል የለም። ጎንበስ ስትል አይፎኖቿም የሉም። ቦርሳዋም የለም። ያለ ተዋረድ ሦስተኛዋ አፕል ላይ የደረሰ ይኼው እንደዚህ ባዳ ሥጋ ሳይል ቢጨካከን አይገርምም። የጊዜያችንም ችግር ይኼ ይመስለኛል። ሒደት አልባነት!

“ለመሆኑ እዚህ ስልክ ላይ አንዴ የተገመጠች ፖም ማተም ለምን አስፈለገ?” የሚለው የብዙ ጊዜ ጥያቄም በነገርኳችሁ ታሪክ ምላሽ አገኘ። “አዳምም ፍሬውን ወስዶ በላ። ዕርቃኑንም እንደሆነ አወቀ፤” እንዲል መጽሐፉ ከሥጋ አልፈን በመንፈስ ዕርቃናችንን መቅረታችን የአፕል ‘ሪቮሊውሽን’ እያሳየን እንደሆነ ገባኝ። “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ያለቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሔዋን ናት ይባላል። ምናልባት ዘመነ ቴክኖሎጂን በዚህች ለአፍታ የተገመጠች አፕል ቅርፅ የሚመራው የፈጠራ ውጤትም የሰው ልጅ ዕውቀት በበራለት ቁጥር ከመልካምና ከሰናይ ዕሳቤ እየራቀ መሄዱን ሊጠቁም የሔዋንን ፍሬ መጠቀም ፈልጎም ይሆናል፤” ያለኝ ታዲያ የባሻዬ ልጅ ነው። ለማንኛውም አንድ የሚሸጥ አይፎን እጄ ላይ ላይ አለ። የፈለገ ይደውልልኝ። ምን ብንፈላሰፍ ቢዝነስ ቢዝነስ ነዋ ወዳጃቼ!

እንሰነባበት። ያልነገርኳችሁ በዚህ ሁሉ የዕፀ በለስ እሰሳቤያዊ ታሪኮች መሀል ሦስት ከባድ የጭነት መኪናዎች ማሻሻጤን ነው። ቆጠብ እያደረግን ካልተናገርን እኮ የዘንድሮ ገቢያችንን ሞጭላፊውን አልቻልነውም። “እንዴ እንኳን ትርፉን ሊያስበላ የተከልነውን ያስነቅለናል እንዴ?” ብላ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ባለቤት አልባ ዓረፍተ ነገር መጠቀም አብዝታለች። “ግሎባል ዋርሚንግ እንዴት እየበረታ እንደሄደ እያየሽ አንችስ የተከልሽውን መንቀል ብሎ ነገር ምን አሳሰበሽ?” ስላት አስቀየሰችና ሌላ ጨዋታ አመጣች። አንዱ (ገጠር የሚኖር ዘመዷ መሆኑ ነው) “እናቴ የተከለችው ዛፍ ነው እቆርጠዋለሁ፤” ብሎ ተነሳ አሉ። “የለም ትነካውና ወየውልህ!” አሉ የአውራጃው አስተዳዳሪ። “እናቴ በተከለችው ዛፍ እኔ ልጇ እንጂ መንግሥት ምን ያገባዋል?” ብሎ ቢሟገት የሚሰማው አጣ። ቢጨንቀው በሌሊት ወደ ዛፉ ሄዶ ምሳሩን ተደግፎ እዬዬውን አስነካው። እሪታው ናኘ። ኋላ አስተዳዳሪው የምን ጩኸት ነው ብለው ቢሄዱ እሱው ነው። “ደግሞ ምን ሆንክ?” ሲሉት ምን ቢል ጥሩ ነው? “ይኼ መንግሥት ስላልተስማማኝ ይቀየርልኝ፤” አይላቸውም? እስኪ አሁን በምርጫ በምንቀያየርበትና በምንቀያየምበት በዚህ ዘመን ዛፍ ሥር ምሳር ተደግፎ በማልቀስ መንግሥት ይቀየርልኝ ይባላል? እንዲህ እየተባባልን እኔና ባሻዬ አንድ ግብዣ ነበረብንና ወደዚያው ተጓዝን። ደርሰን ብናይ ይጠጣል፣ ይጨፈራል፣ ይበላል። “እኔ የምለው?” አሉኝ ባሻዬ፣ “እንዲያው በቲፎዞ ሲሆን መብላት፣ መጠጣት፣ መጨፈር፣ መቃወምና ማደም ብቻ ነው የምናውቅ?” አሉኝ። “ምን ይጨመርርበት?” ስላቸው፣ “መሥራት፣ መተባበር፣ መትጋት፣ መደጋገፍ ምነው በቲፎዞ አይሰምሩ?” ብለው ሌላ ጥያቄ። በጥያቄ ላይ ጥያቄ። ‘ጥያቄው ስላልተስማማኝ ይቀየርልኝ’ ልበላቸው ይሆን? ለካ ጥያቄ ለማስቀየርም በቲፎዞ ነው። ኧረ ሰው ለመባልም በቲፎዞ ሆኗል አሉ። አራተኛዋ አፕል ትሆን እንዴ ይህቺ ቲፎዞ የሚሏት? ኧረ ጎበዝ አንዳንዴ እንተላለፍ እንጂ፡፡ ቸር ሰንብቱልኝ። መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት