Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክ​የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ለማይፈጽምና ለዳኛ አልታዘዝም ላለ ፖሊስ ‹‹የፈተና ጊዜ›› ቅጣት እንዴት...

​የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ለማይፈጽምና ለዳኛ አልታዘዝም ላለ ፖሊስ ‹‹የፈተና ጊዜ›› ቅጣት እንዴት ያስተካክለዋል?

ቀን:

የፖሊስ ተቀዳሚ ሥራና ተግባር ሕግን ማስከበር ነው፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የወንጀል ተግባር ፈጽሞ የሚገኝንና በመፈጸም ላይ ያለን ማንኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል፣ እንዳስፈላጊነቱ የፍርድ ቤት መያዢያ ትዕዛዝ በማውጣት ተጠርጣሪውን አካል ወደ ሕግ ማቅረብ የፖሊስ ተቀዳሚና ዋና ተግባር መሆኑ አያከራክርም፡፡ ራሱ ሕግ አስከባሪው ፖሊስ ግን ሕግ ጥሶ ከተገኘስ ምን ይደረጋል? በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የተፈጸመው ይኸው ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ እየመረመረው ባለ መዝገብ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸውን ግለሰብ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቱ የሰጠውን ትዕዛዝ አልተገብርም ያሉ ፖሊሶች ምክንያታቻውን እንዲያስረዱ በዳኛው ቢጠሩም እምቢተኛነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ጠንከር በማድረግ ፖሊሶቹን ለ15 ቀናት እንዲታሰሩ በማድረግ፣ የጥፋታቸው መጠን ዝቅተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ ወርና በአንድ ዓመት ‹‹የፈተና ጊዜ ቅጣት›› ጥሎባቸዋል፡፡ ሪፖርተር ይኸንኑ መዘገቡም ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር በዘገባው ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ከልደታ ፖሊስ መምሪያ ፖሊሶች ጋር ውይይት በማድረግ በዋስ የሚፈቱ እስረኞችን ፖሊስ እንዴት መልቀቅ እንዳለበት ያስገነዘበውን የአሠራር ሒደት፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ከፖሊስ ጋር በመወያየትና በመነጋገር እየተስማማ የመሥራት አካሄድ›› እንዳለው የሚያስመስል ዘገባ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲታረም አዟል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ከፖሊስ ጋር ተወያይቶና ተመካክሮ የሚሠራ ሳይሆን፣ ፍርድ ቤቱ በዋስ የሚፈታቸውን እስረኞች ፖሊስ እንዴት መልቀቅ እንዳለበት ትዕዛዝ ከመስጠት ባለፈ ሌላ ውይይት ውስጥ የማይገባ መሆኑን አንባቢዎቻችን እንዲረዱ ሪፖርተር ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን የፍርድ ሙሉ ሐሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡    

ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት

ዳኛ፡- ዳንኤል አረጋዊ

- Advertisement -

ከሳሽ፡- የኢትዮ/ገ/ጉ/ባ/ዐ/ሕግ – አልተጠሩም

ተከሳሾች፡- 1ኛ. ሲ.ኢ.ቢ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ

   2ኛ. ሚስተር ታንግሊ                        አልተጠሩም

መዝገቡ ከቀጠሮ በፊት የቀረበው በዚህ መዝገብ በችሎት መድፈር ምክንያት በማረሚያ ቤት ቆይተው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤና ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ ቀጠሮው ተሰብሮ እንዲታይላቸው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም አቤቱታውን ተቀብሎ ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡

ፍርድ

ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ጊዜያዊ እስረኞች ማረፊያ ቤት ውስጥ ተመድበው በማገልገል ላይ የነበሩት ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤና ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ ፍርድ ቤቱ ኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ለዚህ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ሚስተር ታን ሊ በዋስትና እንዲፈቱ በመዝገቡ ላይ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በትዕዛዙ መሠረት ተከሳሽ የዋስትና ገንዘብ በሞዴል 85 ገቢ አድርገው ይኸው ከተረጋገጠ በኋላ የችሎቱ ጸሐፊ የመፍቻ ትዕዛዝ አዘጋጅተው ለችሎቱ ዳኛ ካቀረቡ በኋላም የችሎቱ ዳኛ ሁለተኛ ተከሳሽ በትዕዛዙ መሠረት የዋስትና ገንዘቡን ገቢ ማድረጋቸውን ከሒሳብ ክፍል ከተላከው መረጃና ከሞዴል 85 ገቢ አድርገው ይኸው ከተረጋገጠ በኋላ የችሎቱ ጸሐፊ የመፍቻ ትዕዛዝ አዘጋጅተው ለችሎቱ ዳኛ ካቀረቡ በኋላም የችሎቱ ዳኛ ሁለተኛ ተከሳሽ በትዕዛዙ መሠረት የዋስትና ገንዘቡን ገቢ ማድረጋቸውን ከሒሳብ ክፍል ከተላከው መረጃና ከሞዴል 85 ደረሰኝ ቁጥር ጋር ካመሳከረ በኋላ ግዴታውን ሁለተኛ ተከሳሽ የተወጡ መሆኑን በማረጋገጥ ፍርድ ቤቱ የሚከተለውን ትዕዛዝ የያዘ ትዕዛዝ በዳኛው ፊርማና ማህተም በማረጋገጥ የመፍቻ ትዕዛዙን ለፖሊስ አባላቱ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ትዕዛዙ የሚከተለውን የሚል ነው፡፡ ‹‹የልደታ ምድብ ችሎት ጊዜያዊ ማረፊያ ፖሊስ ክፍል አዲስ አበባ ሚስተር ታንግ ሊ በተከሰሰበት ግብር አለመክፈል ወንጀል ክስ ጉዳይ ተከሳሹን በሞዴል 85 ካርኒ ቁጥር 75164 ዋስትና ያስያዙ ስለሆነ ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ከእስር እንዲለቀቁ አዟል፡፡›› ይህንን ትዕዛዝ የአንደኛ ተከሳሽ ድርጅት ነገረ ፈጅ የሆኑት አቶ መስፍን አየለ ፈርመው ወስደው ለእስረኛ ክፍል ፖሊስ ውስጥ ለነበሩት ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤ ሲሰጧቸው፣ በሞዴል 85 ደረሰኝ ካልመጣ አልፈታም በማለታቸው ነገረ ፈጁ በችሎት ቀርበው በማመልከታቸው ጉዳዩን የችሎት ጸሐፊዋ ወ/ሮ ለምለም ፍስሃና የችሎቱ ተላላኪ ወ/ሪት ሃና እንዲያጣሩ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ሲያጣሩ በወቅቱ በክፍሉ የነበሩት የፖሊስ አባላቱ ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤና ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ የሞዴል 85 ደረሰኝ ካልመጣ አንፈታም ማለታቸውን በማረጋገጣቸው የችሎቱ ዳኛ የፖሊስ አባላቱ አልፈታም ያሉበትን ምክንያት ቀርበው እንዲያስረዱ ቢጠሩም የፖሊስ አባላቱ ግን ለመቅረብ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ የክፍሉ ፖሊስ አባላት ኃላፊ የሆኑትን ምክትል ኢንስፔክተር ወልደ ሩፋኤልን አስቀርቦ የፖሊስ አባላቱን እንዲጠሩ ሲደረጉ አባላቱ አንመጣም ብለው ከግቢ ወጥተው መሄዳቸውን ካረጋገጠ በኋላ ኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በወቅቱ በክፍሉ ነበሩ የተባሉት ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤ፣ ረዳት ሳጅን አሸብር ገብረ መስቀልና ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ የክፍሉ ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ አዟል፡፡ የትዕዛዙ መሠረትም በወቅቱ የነበሩት የፖሊስ አባላት በስም የተጠቀሱት መሆኑን የአንደኛ ተከሳሽ ድርጅት ነገረ ፈጅ፣ የችሎት ጸሐፊና የፖሊስ ኃላፊን አስቀርቦ ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ኅዳር 3 ቀ 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በትዕዛዙ መሠረት የቀረቡትን የፖሊስ አባላትና የችሎት ጸሐፊዋን እንዲሁም የፖሊስ ኃላፊውን ቃል በችሎት መርምሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ የፖሊስ አባላቱ በመዝገብ ቁጥር 214653 በቀን 19/2/2008 ዓ.ም. በተከሳሾች አቶ ሀብታሙ ጌቱና ወ/ሮ እታፈራሁ ከተማ በገደብ እንዲፈቱ ለዋስትናነት የሰጠውን ትዕዛዝ ከፍለው ሳያጠናቅቁ ሁለቱንም ተከሳሾች በመፍታታቸውና አንደኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ጌቱ በመዝገብ ቁጥር 214653 በቀን 22/2/2008 ዓ.ም. በችሎት ቀርበው ያልከፈልኩት ብር ስላለ ልከፍል ነው በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ይህንኑ አጣርቷል፡፡

በተጠቀሰው መዝገብ ቁጥር ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው እንደቅደም ተከተላቸው 5,000 ብርና 350 ብር እንዲሁም 500 ብርና 100 ብር ግዴታቸውን እንዲወጡ ይህም ሲረጋገጥ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ የ5,000 ብርና የ500 ብር ግዴታቸውን ብቻ ተወጥተው የ350 ብርና የ100 ብር ግዴታቸውን ሳይወጡ ፖሊስ በዕለተ ዓርብ ከእስር ፈትቷቸው ቀሪ ክፍያ ለመክፈል ከሁለት ቀን በኋላ ሰኞ ዕለት አንደኛ ተከሳሽ ቀሪ ክፍያ አለኝ በማለት ለክፍያ በችሎቱ ጽሕፈት ቤት ቀርበዋል፡፡ በዕለተ ዓርብ ተረኛ የነበሩት ኮሎኔል ሃሮኒ እንደሆነ ሳጅን ከበደ ካናየ የገለጹ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ውጪ ተከሳሾችን ከእስር የፈቱትን የዕለት ተረኛ የፖሊስ አባላት አስሮ ጉዳዩን እንዲያጣራ የወንጀል ምርመራ እንዲያደርግ ለልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመዝገብ ቁጥር 214653 ከሰጠ በኋላ ከምድቡ አስተባባሪ ጋር ተወያይቶና በምድቡ ጊዜያዊ ማረፊያ ፖሊስ ክፍል አባላት ከነበሩት ምክትል ሳጅን ከበደ ካናየ፣ ኮሎኔል ሃሮኒና ከረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤ ጋር በችሎቱ ጽሕፈት ቤት ከተወያየ በኋላ ከዚህ በኋላ እስረኛ የዋስትና ግዴታውን መወጣቱ በዳኛ ፊርማ ተረጋግጦ ከተፈረመ እንዲፈቱ በችሎት ቀርበው ተግሳጽና መመርያ በመስጠት በተግሳጽ እንዲታለፉ በማለት ፖሊስ አባላቱ ታስረው ምርመራ እንዲጣራ የተሰጠውን ትዕዛዝ ፍርድ ቤቱ አንስቶታል፡፡

በሌላ ቀንም በዚህ ትዕዛዝ መነሻነት በመፍቻ ትዕዛዝ እስረኛ እንዲፈቱ ትዕዝዛ ሲሰጥ የፖሊስ አባላቱ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያታቸውን በችሎቱ ጽሕፈት ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ሲጠሩ፣ ለመምጣት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው በስተመጨረሻ ቀርበው ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤና ሌሎች በዕለቱ የነበሩ የፖሊስ አባላት ከፖሊስ መመርያ በተሰጠን መመርያ መሠረት ሞዴል 85 ደረሰኝ ቁጥር የእስረኛ መፍቻ መዝገብ ላይ የሚሞላ በመሆኑና ችሎቱ የሰጠው ትዕዛዝ የሞዴል 85 ቁጥር ስለሌለው ለመፈጸም ተቸግረን ነው በማለታቸው ከዚህ በኋላ በመፍቻ ትዕዛዝ ላይ እስረኛው የዋስትና ግዴታውን የተወጣበትን የሞዴል 85 ደረሰኝ ቁጥር የችሎቱ ጸሐፊ ሞልተው በችሎቱ ዳኛ ተረጋግጦ በጽሑፍ የመፍቻ ትዕዛዝ እንደሚሰጣቸው መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ በዚህ መሠረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ትዕዛዝ በችሎቱ ጽሕፈት ቤት በችሎቱ ዳኛ ተሰጥቷቸው ተሰናብተዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በዚህ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ሚስተር ታን ሊ የዋስትና ግዴታቸውን የተወጡ መሆኑን የችሎቱ ዳኛ አረጋግጦ የፈረመበትን ትዕዛዝ የፖሊስ አባላቱ አልፈጽምም ማለታቸውን አግባብነት ያላቸውን ሰዎች አስቀርቦ አረጋግጧል፡፡ ምክንያታቸውንም እንዲያስረዱ ቢሉም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ የፖሊስ አባላቱ ታስረው ሲቀርቡ ግን ትዕዛዙን አንፈጽምም ያሉ መሆኑን በችሎት ካመኑ በኋላ ያልፈጸሙበት ምክንያት ትዕዛዙ የችሎቱን ዳኛ ስም ያልያዘና የፍርድ ቤቱ ክብ ማኅተም ስለሌለው ነው ማለታቸው የእስር ትዕዛዙ ከተሰጠ በኋላ የመጣ ምክንያት እንጂ በዕለቱ አንፈታም ለማለት ያቀረቡት ምክንያት የሞዴል 85 ደረሰኝ ካልመጣ የሚል መሆኑን ፍርድ ቤቱ በማስረጃ አረጋግጧል፡፡

በእርግጥም ፖሊስ አባላቱ ምክንያታቸው የችሎቱ ዳኛ ስም አለመታየት ወይም ክብ ማኅተም አለመኖር ቢሆን በችሎት ቀርቦ መጠየቅ አልያም በችሎት ጸሐፊዎች ማስረዳትና ማረጋገጥ ሲጠበቅባቸው የችሎቱ ዳኛ ምክንያታቸውን እንዲያስረዱ ሲጠራቸው እምቢተኛ መሆናቸው የችሎቱን ትዕዛዝ ላለማክበር ቁርጥ አቋም ያላቸው መሆኑን ከሚያሳይ በቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ የፍርድ ቤቱ ዳኛ አረጋግጦ የሰጠውንና በተደጋጋሚም ትዕዛዝ በሌሎች መዝገቦች የሰጠበትን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው እስረኞችን ማጉላላት ተገቢነት የሌለውና የፍርድ ቤቱን ክብር የማይመጥንና የችሎቱን ሥራ ያስተጓጎለ በመሆኑ ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያና ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤ ፍርድ ቤትን በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው በማለት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 449/1 (ለ) መሠረት የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

የፖሊስ አባላቱ ጥፋተኛ የተባሉበት የወንጀል ድርት ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 191 የተደነገገ በመሆኑ በዚሁ መሠረት ተከታዩ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ትዕዛዝ

  1. ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያ ላይ የሚጣለው ቅጣት ከዛሬ ጀምሮ በሚታሰብ የአንድ ወር የፈተና ጊዜ ተራዝሟል፡፡
  2. ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤ ላይ የሚጣለው ቅጣት ከዛሬ ጀምሮ በሚታሰብ የአንድ ዓመት የፈተና ጊዜ ተራዝሟል፡፡
  3. ጥፋተኞቹ የፈተና ጊዜ ውስጥ ባህሪያቸው ከታረሙ የጥፋተኝነት ፍርዱ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል፡፡
  4. የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ረዳት ሳጅን መልካሙ መኩሪያና ረዳት ሳጅን አወቀ ንጉሤን ከእስር ይፍታ፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...