Wednesday, February 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለተኛው ሸራተን ሆቴል በአዲስ አበባ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሥራ ከሚታወቁ ኩባንያዎች ጋር በመዋዋል በአገሪቱ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ አገር በቀል ኩባንያዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ይህም በዘርፉ ስመጥር የሆኑ ዓለም አቀፍ ሆቴል ብራንዶች ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ኧረነስት ኤንድ ያንግ በመባል የሚታወቀው ኩባንያ እንዳስታወቀው፣ ኩባንያው የሚያማክራቸውና ዓለም አቀፍ ብራንዶችን እያፈላለገላቸው ያሉ ስድስት የኢትዮጵያ ሆቴሎች ፕሮጀክቶች በእጁ መኖራቸውንና ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች መንገድ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡

አሁን አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ሆቴሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በስማቸው ከአንድ በላይ ሆቴሎች እንዲገነቡ እየፈቀዱም ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሒልተን ኢንተርናሽናል ብራንድ ሁለተኛውን ሒልተን ለመገንባት መዋዋሉ ይታወሳል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ሥራዎች ላይ የተሰማራው ዓለም ገነት ንግድና ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለው አገር በቀል ኩባንያ፣ ሸራተንን ጨምሮ ከስድስት በላይ የሚደርሱ ብራንድ ሆቴሎችን ከሚያስተዳድረው ስታር ውድ ሆቴልና ሪዞርት ጋር በመዋዋል ፎር ፓይንትስ ባይ ሸራተን ሆቴልን እየገነባ ነው፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጥለት ኮንትራት ከስታር ውድ ጋር ባለፈው ማክሰኞ ታኀሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡ ስታር ውድ ሥር የማተዳደሩት ሸራተን፣ ሴትሬጂስ፣ ዘ ሌግዥሪ ኮሌክሽን ሆቴልስ፣ ደብልዩ ሆቴልስ፣ ዌስቲን ሆቴልና ሪዞርት፣ ለሜዲያን፣ ትሪቢውት ፓሪትፎልዩ፣ ፎር ፓይንትስ ባይ ሸራተን፣ አሎፍት ሆቴልስ፣ ኢለመንት ሆቴልና ዲዛይን ሆቴል የተባሉት ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ብራንድ ሆቴሎች ውስጥ የመጀመሪያው ሸራተን ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ እንዲውል አስችሏል፡፡ በስታር ውድ ሥር የሚተዳደረውን ሁለተኛውን ሆቴል ደግሞ ከዓለም ገነት ኢንዱስትሪ ጋር ተዋውሎ የሆቴል ግንባታው እንዲካሄድ ፈቅዷል፡፡

በዓለም ገነት ንግድና ኢንዱስትሪስ እየተገነባ ያለው ሆቴል ምን ዓይነት ይዘት ይኑረው ከሚለው ጀምሮ የዓለም አቀፍ ሆቴል ብራንድ እንዲኖረው ለማድረግ አጠቃላይ የሆቴሉን የአዋጭነት ጥናትና ብራንድ የማፈላለጉን ሥራ ያሳካው ኧረነስት ኤንድ ያንግ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ሆቴል ለመገንባት ያስፈልጋሉ የተባሉ ግብዓቶች እንዲካተቱ ከማድረግ ባለፈ፣ ለሆቴሉ ግንባታ የሚሆን ፋይናንስ የማፈላለግ ኃላፊነቶችንም ኧረነስት ኤንድ ያንግ ወስዶ እየሠራ ነው፡፡ ይህንን ታዋቂ ብራንድ ለማምጣትም እጅግ አድካሚ እንደነበር የሚገልጹት የኧረነስት ኤንድ ያንግ የሥራ ኃላፊዎች በመጨረሻ ላይ ግን ተሳክቶልናል ይላሉ፡፡

የዓለም ገነት ንግድና ኢንዱስትሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዓለም ፍጹም እንባ እየተናነቃቸው እንደገለጹት፣ ለዚህ ሆቴል መፈጠር የኧረነስት ኤንድ ያንግ ሥራ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ ያለእነርሱ እገዛ እዚህ ሊደረስ አይችልም ነበር ይላሉ፡፡

በጀሞ ኬንያታ መንገድ ፍላሚንጎ ሬስቶራንት አካባቢ በ2,200 ካሬ ሜትር ላይ እየተገነባ ያለው ፎር ፓይንትስ ባይ ሸራተን አዲስ አበባ ሆቴል 120 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ የሆቴሉ ዲዛይን የተሠራው ደግሞ በስታርውድ ኩባንያ ነው፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ወጥቶበታል የተባለው ዲዛይን፣ ኢትዮጵያዊ አሻራ እንዲኖረው ጭምር ተደርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ዘመናዊ ዲዛይኑን የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቁ ንድፎች እንዲኖረው ከመደረጉ ሌላ፣ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ሙዚየም እንዲካተትበት ተደርጓል፡፡  ሆቴሉ እስካሁን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉ ሆቴሎች በርዝማኔው ቀዳሚ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ኧረነስት ኤንድ ያንግም ይህንን ያረጋግጣል፡፡

አቶ ዓለም እንደገለጹትም በርዝማኔው ብቻ ሳይሆን ሆቴሉ ያሉት የመኝታ ክፍሎች ብዛትም ሆቴሉን ቀዳሚ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ትላልቅ የሚባሉ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ሆቴሎች የመኝታ ክፍሎቻቸው ከ400 ያልበለጠ ሲሆን፣ ፎር ፓይንትስ ባይ ሸራተን ሆቴል ግን 506 የመኝታ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ አሥር የሚሆኑ ሬስቶራንቶች አሉት፡፡ ለእንግዶች ማስተናገጃን ጨምሮ በአደጋ ጊዜ ለመውጫ የሚያገለግሉ 10 ሊፍቶችን ይዟል፡፡ በሕንፃው 25ኛ ወለል ላይ ደግሞ መዋኛ ገንዳን አካትቶ እየተገነባ ያለው ይህ ሆቴል፣ በዘርፉ ለአገሪቱ አማራጭ የሆቴል አገልግሎትን እንዲስጥ፤ እንዲሁም በዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በማሳደጉ ረገድ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ይሆናል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡ የሆቴሉ ዝርዝር ጥናትም ይህንኑ የሚያሳይ መሆኑን አቶ ዓለም ገልጸዋል፡፡ አምስትና ስድስት ቡና ላኪዎች ሊያስገኙ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ ፎር ፓይንትስ ሆቴል በአንዴ ሊያስገኝ ይችላል የሚል ዕምነትም አላቸው፡፡ ከኧርነስት ኤንድ ያንግ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ ደግሞ ሆቴሉ አሁን በከተማዋ ውስጥ ካሉት ሆቴሎች የተሻለ ይዘት እንዲኖረው ብዙ መደከሙን ነው፡፡ እስካሁን ካሉት ሆቴሎች በርዝማኔውና በመኝታ ክፍሎቹ ብዛት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ውስጣዊ ይዘቶቹም የተሻለና የተለየ አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሆን ተደርጎ ዲዛይኑ ተሠርቷል፡፡ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ሆቴሎች ያለባቸውን ክፍተት እዚህ ሆቴል ላይ እንዳይታይ ለማድረግ ረዥም ርቀት መኬዱንም ይናገራሉ፡፡

አቶ ዓለም ከገለጹት ሌላ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ኃላፊዎች እንደ ምሳሌ ያነሱትም የመዋኛ ገንዳውን ነው፡፡ 25 ሜትር ስፋት ያለው የሆቴሉ መዋኛ ገንዳም በከተማ ውስጥ በትልቅነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ በ2000 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ የስብሰባ አዳራሹም ከሌሎች ሆቴሎች እንዲልቅ ተደርጓል፡፡ የመኝታ ክፍሎቹም ቢሆኑ ከአነስተኛ እስከ ፕሬዝዴንሻል ስዊት ድረስ በየደረጃው የተሠሩ ናቸው፡፡

ሆቴሉ በአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ የራሱን አሻራ ያሳርፋል ያሉት አቶ ዓለም፣ በተለይ ቱሪስቶች የሚፈልጓቸው ኢንተርናሽናል ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የፎር ፓይንትስ ባይ ሸራተን ሆቴል ሥራ መጀመር ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የራሱ አስተዋጽኦ ያበርክታል ብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ሆቴሎች እየጨመሩ መሆናቸውም የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከዋናው ሆቴል ግንባታ ሌላ እንደ ሁለተኛ ፕሮጀክት የሚቆጠረውን ለመኪና ማቆሚያ የሚሆን ተጨማሪ ግንባታ ይካሄዳል፡፡ እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ሕንፃ ሥር ከደኅንነት አንፃር ፓርኪንግ እንደማይሠራ የጠቀሱት አቶ ዓለም፣ እስከ 500 የሚደርስ ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ የተሽከርካሪዎች ማቆያ ሕንፃ ለመገንባት አሁን ሆቴሉ እየተገነባበት ካለው ስፍራ ጎን የመገንቢያ ቦታ ጥያቄ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ቀርቧል፡፡ ጥያቄው አወንታዊ ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን፣ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ ግንባታም ከዋናው ሆቴል ሕንፃ ጋር እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የሆቴሉ ግንባታ ከሁለት ዓመት ተኩል እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ዋናውን ስኬለተን ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲሁም የማጠናቀቂያ ሥራውን ደግሞ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ታቅዷል፡፡

ዋናውን የስኬለተን ሥራ ለመሥራትና በተያዘለት ጊዜ ለመጨረስ በቂ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት አቶ ዓለም፣ ግንባታው ያለችግር እንዲጓዝ ለምሳሌ መንግሥት በሰጠው ማበረታቻ ለግንባታው የሚያስፈልገው 3,500 ቶን ብረት ከቀረጥ ነፃ ተገዝቶ አስገብቷል፡፡ ሌሎች ግብዓቶችም በመሟላትቸው ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለሥራ ይበቃል ተብሎ ይታመናል፡፡ ዓለም ገነት ንግድና ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለሆቴል ኢንቨስትመንት አዲስ አይደለም፡፡ ሪቬራ የተባለ ሆቴል ገንብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ሆቴል አሁን ለመከላከያ ተሽጧል፡፡

የፎር ፖይንትስ ባይ ሸራተን ሆቴልን የማስተዳደሩ ሥራ የስታር ውድ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታውን በማካሄድ ላይ ያለው ደግሞ ባማኮን የተባለ ተቋራጭ ነው፡፡ ይህ ሆቴል እስከ 2,000 ሠራተኞችን ይቀጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከስታር ውድ ጋር በተደረገው ስምምነት ስታር ውድን በመወከል የፈሙት ሚስተር ጂቪድ ግሮስኒ ክላስ (የኦፕሬሽን ማናጀር) ሲሆኑ፣ ዓለም ገነትን በመወከል ደግሞ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ዓለም ፍጹም ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች