Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአካባቢ ጥበቃ ሰንኮፎች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲሱ የአካባቢ ጥበቃ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በመንግሥት ያልተለመደ አካሄድ የተከተለበትንና ሕዝብ ያቀረባቸው መሠረታዊ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ምላሽ የሚሰጥባቸውን ስልቶች ይፋ አድርጓል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአካባቢ ተቆርቋሪዎችና ተማጓቾች ሲጮህባቸው፣ የመፍትሔ ያለህ በማለት ሲያቀርቧቸው የነበሩ በርካታ የአካባቢ ነክ ችግሮችን አዲሱ ሚኒስቴር የተቀበላቸውና ለመፍትሔያቸውም ለመሥራት ቆርጦ መነሳቱን ሲገልጽ ተደምጧል፡፡

ሚኒስቴሩ በሳምንቱ አጋማሽ ከኅብረተሰቡ ከተውጣጡ ልዩ ልዩ ተቋማት ተወካዮች ጋር ባደረገው ውይይት ወቅት 14 ዋና ዋና ችግሮች ከኅብረተሰቡ እንደቀረቡለት አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ይፈታቸው ዘንድ ከሕዝቡ ተጠይቋል በማለት ችግሮቹን ያቀረቡት፣ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ይማም ናቸው፡፡

14ቱ ሰንኮፎች

እንደ አቶ ከበደ ማብራሪያ የመጀመሪያውና ትልቁ ችግር አካባቢን የሚበክሉ ፋብሪካዎች የሚደርሱት ጫና ነው፡፡ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ፋብሪካዎች የአካባቢንና የሕዝብን ጤና አደጋ ውስጥ በመክተታቸው፣ ከብክለት ነፃ በመሆን የምርት ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑበት ቴክኖሎጂ እንዲተገብሩ ቀነ ገደብ ተቀምጦ ነበር፡፡ ይኸውም በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ብክለትን የሚያስከትሉ ፋብሪካዎች ወደ አካባቢ የሚለቁት ዝቃጭ ተጣርቶ፣ ብክለት ሳያስከትል ሕዝብንም ሳይጎዳ የሚለቀቅበትን ዘዴ ለመተግበር የተቀመጠላቸው ገደብ ካበቃ ሁለት ዓመታት  አልፈዋል፡፡ ይሁንና እንደ አዲስ የተዋቀረው ሚኒስቴር ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለብክለት አስተዋጽኦ በሚያደርጉት ላይ ክትትል አደርጋለሁ፤ ዕርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ መልካም አስብሎታል፡፡

በሚኒስትር ዴኤታው የቀረበው ሌላኛው የብክለት መንስዔ ድምፅ ነበር፡፡ ተሳታፊዎችም በድምፅ ብክለት ላይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ዕርምጃዎችንና የተቸገሩባቸውን ጉዳዮች አስተጋብተዋል፡፡ በመኖሪያ አካባቢ የተከፈቱ ጭፈራ ቤቶች፣ ለንግድ በዋሉ የኮንዶሚኒየም ምድር ቤቶች ዙሪያ የሚታዩትና ከመኖሪያ አካባቢ መሳ ለመሳ የተንሰራፉ ኢንዱስትሪዎች ለድምፅ ብክለት መንስዔ በመሆን ሕዝብ እንዳማረሩ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች የሃይማኖት ተቋማትም ለዚህ ብክለት አስተዋጽኦ በማድረግ እንደሚያውኩ ሳይገልጹ አላለፉም ነበር፡፡ 

አቶ ከበደ ባቀረቡት የሕዝብ ቅሬታ መሠረት የልማት ፕሮጀክቶችና ኢንቨስትመንቶች ሲቀረጹ፣ ሲፀድቁና ሲተገበሩ ሕዝብን ሳያሳትፉ መሆኑ፣ የሕዝቡን ጥቅም ሳያስጠብቁ፣ በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳትና ተፅዕኖ በአግባቡ ሳያጠኑ ወደ ሥራ የሚገቡ ፕሮጀክቶች ጥቂት እንዳልሆኑ ሚኒስቴሩ የተቀበለው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በርካታ ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት አካባቢ ላይ ሊያደርሱ ስለሚችሉ ጉዳት አካባ ተፅዕኖ ግምገማ አካሂደው ነገር ግን ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ የተፅዕኖ ግምገማዎችን ባጠኑት መሠረትና ለአካባቢ የሚያደርጉትን ጥበቃ ቃል በገቡት መሠረት የማይወጡ እንዳሉ ሚኒስቴሩ ተቀብሏል፡፡

ለሚኒስቴሩ በሕዝቡ ዘንድ እየተነሱ ሲቆዩ የነበሩና ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል በሐይቆችና በውኃ አካላት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው ብሏል፡፡ እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ መሠረት ለሐይቆችና ለውኃ አካላት ጉዳት ዋናው መንስዔ በተራራማ አካባቢዎች የሚካሄዱ የእርሻ ሥራዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉትን አካባቢዎች ለእርሻ ሥራ ማዋል ሐይቆችን በደለል እንዲሞሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሲብስም በወራሪ አረሞች እንዲሞሉ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በእነዚህና በሌሎች አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች ምክንያት ሐሮማያ ሐይቅ ሊደርቅ ችሏል፡፡ እንደ ሻላና አብያታ ያሉ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆም የመድረቅ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ምሁራን ከዚህ ቀደም ደጋግመው ሲጮሁ ተደምጠዋል፡፡

በደን ላይ የሚደርሱ ጭፍጨፋዎች፣ የአቅም ክህሎት ችግሮች ለአካበቢ ጥበቃ የሚያግዙ የተሟሉ ሕጎች አለመኖር፣ አለአግባብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ አካባቢን በሚያጎሳቁሉ ባለሀብቶች የሚደርሱ ሕገወጥ ተግባራት፣ አከባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ ምክር የሚሰጡ አማካሪዎች ብቃት አጠያያቂ መሆን፣ ለክህሎትና ብቃታቸው የተሟላ ሰነድ አለማቅረብ ወዘተ. ያሉት ችግሮች የኢትዮጵያን የአካባቢ ጥበቃ ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ችግሮች ሆነው በሕዝቡ መነሳታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አቅርበዋል፡፡ መንግሥት የረጅምና የአጭር ጊዜ መፍትሔ ያላቸውን እንቅስቃሴዎችም አሰምተዋል፡፡

ከዚህ ጎን በአገሪቱ በየዓመቱ ለተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ሕዝቡ በዓመት የአንድ ወር ነፃ የጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ አፈር እንዳይከላ፣ እንዳይሸረሸር እርከን በመሥራት፣ ችግኝ በመትከል ከሚያደርገው አስተዋጽኦ በተጓዳኝ አገሪቱ ከ15 ወይም ከ20 ዓመት በኋላ ለሚያስፈልጋት የ150 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ሕዝቡ እንዲያወጣ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቃሬ ጫዊቻ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች