ከጥቂት ወራት በፊት አንድ ዓመት ከሰባት ወራት በላይ የፈጀበትንና በአካባቢው ካገኛቸው ቁሳቁሶች የፈጠራትን አውሮፕላን ለማብረር ሞክሮ ያልተሳካለት ወጣቱ አስመለሽ ዘፈሩ፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ በድጋሚ ከሚያደርገው ሙከራ በኋላ እጮኛውን ለማግባት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
አስመላሽ ከልጅነቱ ጀምሮ የመብረር ህልም እንደነበረው የገለጸ ሲሆን፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በአውሮፕላን ተሳፍሮ አያውቅም፡፡ ሆኖም ከ14 ዓመት በፊት በአብራሪነት ለመሠልጠን በድሬዳዋ ከሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፍ ማሠልጠኛ አመልክቶ ውድቅ እንደተደረገ ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ ከሚጠበቅበት የቁመት ልክ አንድ ሴንቲ ሜትር ብቻ ዝቅ በማለቱ መውደቁን አስታውሶ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ራሱ በሠራው አውሮፕላን የመብረር ህልሙን ለማሳካት ሲያልም እንደኖረ ይናገራል፡፡
በሰንዳፋና በሌሎች አከባቢዎች በጤና መኮንንነት ሲሠራ የቆየው አስመላሽ፣ እንደምንም ያለውን ሸጦ ባጠራቀውና ከሰዎች ባገኘው 160 ሺሕ ብር አዲስ አውሮፕላን በመሥራት ከአገር ውስጥ አልፎ እንደ ሲኤንኤን ያሉ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን እስኪዘግቡለት ድረስ አትኩሮትን ሊስብ ችሏል፡፡ በዚህም ሳያበቃ ከውስጥም ከውጭም የተለያዩ ተቋማት ድጋፋቸውን እየቸሩት ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑን የቻይናው ቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ መግለጽ ያልፈለገውን ገንዘብ በስፖንሰርነት አበርክቶለታል፡፡
ይህንኑ ምክንያት በማድረግም በዜድቲኢ መሥሪያ ቤት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የመግባቢያ ስምምነት ከኩባንያው ኃላፊዎች ጋር ዓርብ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮ ቴሌኮም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዳደረገለት አይዘነጋም፡፡
ከውጭ የኔዘርላንድስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነው ኢን ሆላንድ ዩኒቨርሲቲ ኤሮናቲካል መስክ ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቶታል፡፡ በጥቅምት ወር ወደ ዩኒቨርሲቲው ማቅናት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ይሁንና አውሮፕላኑን ለማብረር ካለው ፍላጎት በመነሳት ትምህርት የሚጀምርበትን ጊዜ ማራዘሙን ገልጿል፡፡ አውሮፕላን በመሥራት ከአስመላሽ ቀድሞ ስማቸው በመገናኛ ብዙኃን የሚነሱ አፍሪካውያንን በማብረር ጭምር የመብለጥ ፍላጎት እንዳለውም ይናገራል፡፡
የመጀመሪያውን መኩራ በሚያደርግበት ወቅት ከሪፖርተር ጋር በነበረው ቆይታ፣ የመሞትም ሆነ የመትረፍ ዕድሉ ሃምሳ ከመቶ ቢሆንም ከመብረር ወደ ኋላ እንደማይል ፈርጠም በማለት ገልጾ ነበር፡፡
ከሁለት ሳምንት በኋላ በሰንዳፋ ዳቢ ሜዳ የማብረር ሙከራ በድጋሚ የሚደረግባት አውሮፕላን፣ ብዙ ማሻሻያዎች እንደተደረጉላት አስመላሽ ይናገራል፡፡ ሞተሯ ከዚህ በፊት ከነበረው ይልቅ የተሻለ እንደሆነ፣ አዳዲስ የሞተር ብስክሌት ጎማዎች እንደተገጠሙላትና አካላዊ ሥሪቷም ብዙ ለውጥ እንደተደረበት ገልጿል፡፡ አብራው ከቆየችው እጮኛው ጋር አውሮፕኗን አሥር ሜትር ከፍታ ያህል በማብረር ካሳረፈ በኋላ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ለማድረግ ዝግጅት እያደረግ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡