Monday, December 4, 2023

‹‹የማስተር ፕላኑን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው የኦሮሞ ሕዝብ ነው››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አቶ በፍቃዱ ተሰማ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ

ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተነሳው ግጭት አምስት ሳምንታት አስቆጥሮ ከሞላ ጎደል በቁጥጥር ሥር የዋለው የሰው ሕይወት ከጠፋበት፣ በሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት፣ በንብረት ላይ ውድመት ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት፣ በኦሮሚያና በፌዴራል መንግሥት የጋራ ጥምረት የተቋቋመው ማዘዣ ጣቢያ (ኮማንድ ፖስት) የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በእነዚህና በተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውድነህ ዘነበ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ አባልና የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል ላለፉት አምስት ሳምንታት ጥልቀትና ስፋት ያለው ግጭት ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባደረገው ግምገማ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ ምንድነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ነገሩን በደንብ ለመረዳት እንዲያስችል በሁለት ከፍሎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የመጀመርያው ለዚህ ችግር መንስዔ የሆነው በረቂቅ ደረጃ ያለው የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን በመሠረተ ልማት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም የአካባቢ ብክለት ለመከላከል እንዲያስችል የተዘጋጀው የጋራ ማስተር ፕላን በአጠቃላይ ሲታይ የከተሞቹን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ አዲስ አበባ ትልቅ ገበያ ያለው እንደመሆኑ መጠን በዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ተቀናጅተው ማደግ አለባቸው የሚል ነው፡፡ መሠረታዊ ዓላማው ይህ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ ዕቅድ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ በተገቢው መንገድ ግንዛቤ ያለመፍጠር ችግር ነበር፡፡ ሁለተኛው የግንዛቤ ክፍተትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ከአገር ውስጥም ከውጭ አገርም በማኅበራዊ ድረ ገጾች፣ ጽንፈኛ የሆኑና በውጭ አገር የሚገኙ ብዙኃን መገናኛዎች የሚያስተላልፏቸው አሉታዊ መረጃዎች ይነዙ ነበር፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች የሚያነሱት የኦሮሚያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሊቀላቀሉ ነው፣ በሕገ መንግሥት የተከለለው ክልል ሊፈርስ ነው፣ የኦሮሚያ መሬት ለአዲስ አበባ ሊሰጥ ነው፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሬት ላይ ሊስፋፋ ነው የሚል ነው፡፡

      ይህ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ነው፡፡ አዲስ አበባም ሆነ ኦሮሚያ የተዋቀረው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነው፡፡ ሌሎች ክልሎችም ሲዋቀሩ ባህል፣ ቋንቋ፣ አሰፋፈርን ታሪካዊ አመጣጥ መሠረት ተደርጎ የተዋቀሩ እንደመሆናቸው፣ ማንኛውም ዕቅድ በሚወጣበት ጊዜ ሕገ መንግሥቱን ሊቃረን አይችልም፡፡ ቀድሞውኑ ይህ ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ፣ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ፣ የአፍሪካና የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች መቀመጫ ናት፡፡ ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረች የራሷ ድንበር ያላት ናት፡፡ በኦሮሚያ መሬት ላይ የምትስፋፋበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ቢታሰብም ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም፡፡ የማስተር ፕላኑ ዓላማም ይህ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውን ነገር አጣመው በማቅረብ ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ይህንን ሊመጥን የሚችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ባለመሠራቱ፣ በቀላሉ ስሜት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ውዥንብሮች በስፋት ሊቀሰቀሱ ችለዋል፡፡ ግጽነትና ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ሊከሰት የቻለ ችግር ነው፡፡ መንስዔውን በአጠቃላይ ስንገመግም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ አለመፈጠሩ ያመጣው ችግር መሆኑ ታይቷል፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር በ2006 ዓ.ም. ተከስቶ ነበር፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በወቅቱ በአምቦ አካባቢ በዚህ ችግር መነሻነት ተመሳሳይ የሆነ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡ ይህ ማስተር ፕላን በረቂቅ ደረጃ ስለነበር የቆመበት ሁኔታ ነበር፡፡ ማስተር ፕላኑ ባለበት እንዲቆይ፣ አመራሩ ተግባብቶ ያለፈበት ሁኔታ ነበር፡፡ የሚያስፈልግ ከሆነ ወደፊት ከረቂቅ አልፎ ሙሉ ቁመና በሚይዝበት ወቅት ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ዓላማና ግቡ፣ እንዲሁም ጠቀሜታና ጉዳቱ በውል ተለይቶ እንደሚጠቅም ከታመነበት ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ አይጠቅምም ከተባለም እንዲቀር ይደረጋል ተብሎ ውሳኔ የተላለፈበት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በ2006 ዓ.ም. የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ በአዳማ ከተማ ዘጠነኛውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ወይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ማስተር ፕላኑ እንደሚጠቅም መግባባት ላይ ቢደረስም፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት ስላለባት ልዩ ጥቅም ሕገ መንግሥቱ ቢደነግግም፣ እስካሁን አለመተግበሩ ተገልጾ ሊቀድም የሚገባው ማስተር ፕላኑ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው ልዩ ጥቅም መሆን እንዳለበት በተለይ ከኦሮሚያ አመራሮች ተነስቶ ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ተገቢነት የለውም ይላሉ? በወቅቱ ከዚህ ውይይት በኋላ የተነሳው ብጥብጥን ለማብረድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተጀምሮ ነበር፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱ ለምን አልቀጠለም?

አቶ ፍቃዱ፡- በዚያ ወቅት እኔ እስከማውቀው የቀረበው በረቂቅ ደረጃ ያለው ማስተር ፕላን፣ ምን ይመስላል? የያዛቸው መዘርዝሮች ምን ይመስላሉ? የሚለው ጉዳይ በቴክኒክ ኮሚቴ ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ነበር ሐሳብ ሲሰጥ የነበረው፡፡ የ2006 ዓ.ም. ግጭት ከተፈጠረ በኋላ የማረጋጋት ሥራ ነው ይሠራ የነበረው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብ ይችላል፡፡ በግጭትና በሁከት ንብረት በማጥፋት መሆን የለበትም፣ ተገቢ አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይ ነው ውይይት የተካሄደው፡፡ ፕላኑ በዕቅድ ደረጃ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ መሬት የመቁረስ ዓላማ እንደሌለው ችግሩ በተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ ሕዝብ የማወያየት ሥራ ተሠርቷል፡፡ የቀረበው ዕቅድ የተሟላ ስላልነበር ወደ ማስተር ፕላን ውይይት አልተገባም፡፡ እንደሚታወቀው 2007 ዓ.ም. ትላልቅ አገራዊ ፕሮግራሞች የነበሩበት ነው፡፡ አንደኛ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የማጠናቀቂያ ጊዜ ነበር፡፡ ይህንን ዕቅድ መገምገምና ከዚያ የተገኙ ጠቃሚ ልምዶችን ለሁለተኛው ዕቅድ ዘመን ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጠቅላላ ምርጫ ነበር፡፡ ትልልቅ ሥራዎች ስለነበሩ፣ እነዚህን ሥራዎች ጨርሰን ወደ ማስተር ፕላን በመሸጋገር ውይይት ይካሄዳል የሚል ሐሳብ ነበረን፡፡ ሕዝቡ ተወያይቶ ይጠቅመኛል ካለ ተግባራዊ ለማድረግ፣ አይሆነኝም ካለ ይቀራል፡፡ ለሕዝብ የተሟላ ነገር ማቅረብ ነበረብን፡፡ ይህ ያልሆነበት ሁኔታ በመፈጠሩ ለሁከት በር ከፍቷል፡፡ እነዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች ፕላኑን አጣመው በማቅረብ፣ በመቀስቀስ፣ ያልሆነ አቅጣጫ በማስያዝ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በሚያንቀሳቅሷቸው ሚዲያዎች በመጠቀም የተለያዩ ውዥንብሮችን ነዝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፀረ ሰላም የምትሏቸው ኃይሎች በውል ተለይተዋል? ከተለዩ የትኞቹ ናቸው? በአብዛኛው ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ኦነግ ስሙ ከዚህ ግጭት ጋር እየተነሳ ነው፡፡ ከስሟል የተባለው ይህ ተቃዋሚ ቡድን ከዚህ ጉዳይ ጋር እንዴት ሊያያዝ ቻለ?

አቶ ፍቃዱ፡- ድርጅቶች በአደረጃጀት ደረጃ ሊዳከሙ ይችላሉ፡፡ አስተሳሰቡ ካለ ግን፣ አስተሳሰቡ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ ጠባብ ቡድኖችና ድርጅቶች ስላሉና ስለሌሉ ብቻ አይደለም፡፡ በህቡዕ ደረጃ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከሚያስተላልፏቸው ነገሮች፣ ማዕከል አድርገው ከሚያወጧቸው መረጃዎች፣ እንደገና ደግሞ ፅንፈኛና ትምክተኛ የዳያስፖራ አባላት በየሚዲያዎች ከሚያስተላልፏቸው ሐሳቦች ስትነሳ፣ ጉዳዩን ከኋላ ሆነው እየመሩ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ብጥብጡ በተነሳባቸው አካባቢዎች ሲታይ፣ ከሚተላለፉ መልዕክቶች፣ ከተያዙ አንዳንድ ቁሳቁሶች መነሻ ተደርጎ በሚታይበት ጊዜ ወደፊት ምርመራው ተጠናቆ ይፋ ሲደረግም የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያሉት መረጃዎች መኖሩን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ አገር ውስጥ ያሉትም ይታወቃሉ፡፡ በፅንፍ ሲጓዙ የነበሩ ናቸው፡፡ በምርጫ ወቅትም ፅንፍ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት፣ በማስተር ፕላኑ ይህንኑ ሐሳባቸውን ለመሸጥ መንቀሳቀሳቸው ታይቷል፡፡

ትምክህት አለ፡፡ ለምሳሌ የትምክህት ሥርዓት ፈርሷል፡፡ አመለካከቱ ግን አለ፡፡ ይኼ አመለካከትን ለማክሰም የትውልድ ቅብብሎሽ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ሕዝቡ በምርጫው ድምፅ የከለከላቸው ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ለአባሎቻቸው ከሚሰጡት አቅጣጫና ከሚያወጧቸው መረጃዎች በመነሳት ችግር እንዳለ ተስተውሏል፡፡ ለችግሩ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በጥቅሉ ስናይ አደገኛ የመረጃ ክፍተት መኖሩ፣ ይህንን የመረጃ ክፍተት በመጠቀም እነዚህ ኃይሎች ከውጭም ከውስጥም ሆነው በስፋት በመንቀሳቀሳቸው የመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጃ ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ ተገቢነት ያላቸው ጥያቄዎችን የሚያነሱ አሉ፡፡ በክልሉ የሰፈነው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ፍትሕ ማጣትና የሙስና መስፋፋት የፈጠራቸው ብሶቶች ለግጭቱ መንስዔ እንደሆኑ የሚያነሱ አሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም የኦሮሚያ ክልል ልሂቃን ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው ኦሮሚያን ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እንድታገኝ ቢደነግግም፣ ተግባራዊ አለመሆኑ አንዱ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ እነዚህ ቁም ነገሮች በክልሉ መንግሥት እንዴት ይታያሉ?

አቶ ፍቃዱ፡- ይኼ ጥያቄ መመለስ እንዳለበት ይታመናል፡፡ ጥያቄው መመለስ አለበት የሚለው ጉዳይ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለባት ልዩ ጥቅም እየተጠና ነው ያለው፡፡ ሕገ መንግሥት ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች በሙሉ ተተርጉመው ሥራ ላይ ውለዋል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥት ትልቅ ሮድማፕ (ፍኖተ ካርታ) ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ የማንነት ጥያቄ፣ ራስን የማስተዳደር፣ የማልማትና የማዳበር ጉዳዮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ላይ ነበር ክልላዊ መንግሥቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራ የነበረው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው በሙሉ በሥራ ላይ እየተተረጎመ አይደለም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ብቻ ሳይሆን ይህ ጉዳይ ቀደም ሲል ሲጠና ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥትና ድርጅታችን ኦሕዴድ ተቀብሎ፣ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እያስጠና ነው፡፡ በትክክል ልዩ ጥቅም ምን ማለት ነው የሚለውን፣ እንዴት በጋራ ማደግ ያስችላል የሚለው ጉዳይ ተቀባይነት አግኝቶ መሠረታዊ በሆነ ደረጃ ለመመለስ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ተገቢነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ክልሉ የሚቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን በሚመለከትም መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አሳይቷል፡፡ የርብርብ ማዕከሉን አራቱም ድርጅቶች በግንባር ደረጃ የወሰኑበት ጉዳይ ነው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ በሚዘጋጅበትም ጊዜ፣ ከሕዝብ ጋር በነበሩ ውይይቶች የተለዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ከሕዝብ ጋር በመተባበር በአደረጃጀቶች በመጠቀም ይፈታል፡፡ ብሶቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መጠየቁም ኃጢያት አይደለም፡፡ እየኮነንን ያለነው ብጥብጥ ሊነሳ አይገባም፣ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ሊቀርብ እየተገባ ሁከት ሊነሳ አይገባም ነው፡፡ የሰው ሕይወት እስኪያልፍ ድረስ፣ ፕላንና ኢንቨስትመንት ማውደም የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ ትምህርት ቤት ማውደምና መልካም አስተዳደር የሚያገናኘቸው ነገር የለም፡፡ ከዚህ ውጭ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢነት አላቸው፡፡ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የተነሳውን ግጭትና ውድመት ያስቆመው ሕዝቡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሕዴድ ምን ያህል ራሱን ፈትሿል? ተገቢነት ያላቸውን የሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ ምን ያህል ዝግጁ ነው? ይህን የምጠይቀው በልዩ ዞን አካባቢ የኦሕዴድ አመራሮች የተቀራመቱት መሬት ስላለ ማስተር ፕላኑ በሒደት ተቀባይነት አግኝቶ ቢተገበር፣ አመራሮቹ የሚጋለጡበት ዕድል በመኖሩ ከኋላ በመሆን ግጭቱን አባብሰዋል እየተባለ በመሆኑ ነው፡፡ መንግሥት ይህን በሚመለከት መረጃ አለው ወይ?

አቶ ፍቃዱ፡- አንዳንድ የግል ሚዲያዎች በተሳሳተ መልኩ እየሄዱ ነው፡፡ ይኼ የክልሉን መንግሥት፣ ሕዝቡንና ድርጅቱን መናቅ ነው፡፡ ትክልል አይደለም፡፡ ሙሰኛ ሊኖር ይችላል፡፡ ይኼ በኦሕዴድ ብቻ አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ደረጃም በየጊዜው የሚገመገም  ጉዳይ ነው፡፡ ባለንበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ነው ገዥ የሆነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሙሰኛ ቢኖር የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም፡፡ ከኦሕዴድ በላይ ሙስናን የታገለና ከፍተኛ ዕርምጃ የወሰደ አለ ብዬ አላንምንም፡፡ በስፋት ታግሏል፡፡ ማስተር ፕላኑና አሁን የምታነሳው ግንኙነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም በግለሰብ ደረጃ የሚወሰን አይደለም፡፡ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ደረጃ የሚወሰን ነው፡፡ ማስተር ፕላን የሚወሰነው በሕዝብ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የሚታይ ነገር፣ በዚህ ደረጃ ማውረድ እኔ ተገቢ  ነው ብዬ አልወስድም፡፡ ጠቃሚ ናቸው የሚባሉ ጉዳዮችም በጋራ መግባባት የሚተገበሩ በመሆናቸውና በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ቅድሚያ ሊያገኙ የሚገቡ ሥራዎች ስለነበሩብን፣ ፕላኑ በረቂቅ ደረጃም ስለነበር በጉዳዩ ላይ የሚፈለገውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ባለመሥራታችን የተከሰተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክልሉ የተፈጠረውን ችግር ተቆጣጥሮታል ተብሏል፡፡ ነገር ግን አምስት ሳምንታት የወሰደ በመሆኑ ችግሩን ለመቆጣጠር ረዥም ጊዜ አልወሰደባችሁም? ችግሩ ከመድረሱ በፊትስ እንደሚከሰት መረጃ አልነበራችሁም?

አቶ ፍቃዱ፡- ኦሮሚያ ሰፊ ክልል ነው፡፡ ትልልቅ 18 ዞኖች፣ ትልልቅና እንደ ዞን የሚታዩ 16 ትላልቅ ከተሞች፣ ከ300 በላይ ወረዳዎች፣ ከሰባት ሺሕ በላይ ቀበሌዎችና 14 ሺሕ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ችግሩ የተከሰተባቸው ከ300 የማይበልጡ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ችግሩ ረዘም ላለ ጊዜ የቆየባቸው ሦስት ዞኖች ናቸው፡፡ በማንኛውም ጊዜ ኦሕዴድ ችግር ፈጣሪዎችን ለመቆጣጠር ወደ ሕዝብ  ይሄዳል፡፡ ከሕዝብ ጋር ነው በቅድሚያ ውይይት የተካሄደው፡፡ እነዚህ ውይይቶች ረዘም ላለ ጊዜ ነው የተካሄዱት፡፡ ችግሩ ረዥም ጊዜ የወሰደ ሊመስል ይችላል፡፡ ውይይቶቹ ብዙ ቦታ ሲካሄዱ፣ ችግሩ ብዙ ቦታ ያለ ሊመስል ይችላል፡፡ ችግሩ ከሌላው ጊዜ መልኩን የለወጠ ነበር፡፡ የተደራጀ፣ መንግሥታዊ ተቋማት ላይና የመንግሥት መዋቅሮች ላይ፣ ኢንቨስትመንት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ሰፋፊ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ችግሩን በኃይል ለመቀልበስ ቢሞከር የሚከሰተው ጉዳት የከፋ ይሆን ነበር፡፡ መንግሥት ጉዳዩን በትዕግሥት ይዞ የጥፋቱን ስፋት ለመቀነስ የተቻለውን አድርጓል፡፡ በያዝነው ሳምንት መጀመርያ ጀምሮ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመማር ማስተማር ሒደቱ ወደ ቀድሞው ቦታው ተመልሷል፡፡ ቀደም ብሎ መረጃው አልነበረባችሁም ወይ? ለሚለው መረጃው ነበረን፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በዕቅድ እየተመራን ነው፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ፅንፈኛ ሚዲያዎች እንደቀድሞ ሁሉ ያራግቡት ነበር፡፡  ጨፌ ኦሮሚያ ያወጣው የከተሞች አዋጅ ነበር፡፡ ይህ አዋጅም ጥርጣሬ እንዳይፈጥር መረጃ እያጣመሙ ያሰራጩ ነበር፡፡ አካሄዳቸው ይታወቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ ብጥብጥ ይነሳል የሚል ግምት አልነበረንም፡፡ ፅንፈኞቹ እያነሳሱ መሆኑ ቢታወቅም በዚህ ደረጃ ውዥንብር ተነስቶ በዚህ ፍጥነት ወጣቱ ወደ ስሜት ያመራል የሚል እምነት አልነበረም፡፡ ግጭቱ ሲጀመር ከተወሰነ ቦታ ነው የጀመረው፡፡ እየሠፋ ሄደ፣ ስታበርደው እንደገና ይነሳ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚዎች በየጊዜው እያወጡት ባለው መረጃ በርካታ ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካታ ሰዎችም ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የደረሰው የንብረት ውድመትም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ መንግሥት ችግሩን ለመቆጣጠር የወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም እየተባለ ነው፡፡ በእናንተ በኩል ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ምድነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ይኼ እየተጣራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር ኦሮሚያ የራሱ ፖሊስና የራሱ ልዩ የፀጥታ ኃይል አለው፡፡ በእርግጥ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ሊገባ የሚችልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ሆኖ፣ የኦሮሚያ ክልል የፌዴራል መንግሥት ኃይል እንዲያሰማራ ጥያቄ አቅርቧል?

አቶ ፍቃዱ፡- ከንብረቶቹ በላይ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረቶቹን ሠርተን እናገኛለን፡፡ የሰው ሕይወት ግን አንድም መሞት አልነበረበትም፡፡ ጥያቄ መጠየቅ ኃጢያት አይደለም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ማንሳት ይቻል ነበር የሚል አቋም አለን፡፡  ለሟቾችና ለተጎጂ ቤተሰቦች ክልላዊ መንግሥቱ በይፋ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል፡፡ ለቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል፡፡ ጥቅም ላይ የዋለው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ነው፣ ተመጣጣኝ አይደለም የሚለው፣ የጠፋው ሕይወት ምን ያህል ነው? የወደመው ንብረትስ የሚለው ጉዳይ በተለይ ችግሩ በሚከፋባቸው አካባቢዎች ላይ የተለያዩ የውጭ ኢንቨስተሮች፣ የመንግሥት፣ የሕዝብ ንብረትና የሰው ሕይወትን ጨምሮ በመጣራት ላይ ነው፡፡ እናም ያልተጣራ መረጃ አንሰጥም፡፡ አጣርተን ስናበቃ ይፋ የምናደርገው ይሆናል፡፡ በአንፃራዊነት ችግሩ በቆየባቸው ቦታዎች ችግሩን መቆጣጠር የተቻለው በቅርቡ በመሆኑ ማጣራቱ ይቀጥላል፡፡ ይህንን ችግር በዋናነት ያረጋጋው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ችግሩን ያረጋጋው የክልሉ መንግሥት ነው፡፡ በተጨማሪ ችግሩ በከፋባቸው ቦታዎች ምክንያቱም አካሄዱ ኃይል የመበተን ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ አንድ ቦታ ይጀመራል፣ የክልሉ ኃይል ወደዚያ ይጓዛል፡፡ እንደገና ሌላ ቦታ ይጀመራል፡፡ መንገድ የመቆራረጥ ሁኔታ በሰፊው ስለነበር፣ በእነዚህ ቦታዎች በሙሉ ኃይል መሰማራት አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት እጥረት ባጋጠመ ጊዜ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመወያየት ኃይል ተሰማርቷል፡፡ ድጋፍ እንዲሰጡ የፌዴራል ኃይል የተመደበበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደተነገረው አይደለም፡፡ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ ፌዴራል ሙሉ በሙሉ ገብቶ፣ የክልሉ መንግሥት ተዳክሞ የሚባለው ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉም ቦታ በዛ ያሉ ዞኖች ላይ ችግሩ ቢነሳ፣ በዛ ያሉ ቦታዎች ኃይል መመደብ የሚያስፈልግ በመሆኑ ነው፡፡ ፌዴራልም የኛ መንግሥት ነው፡፡ ሌላ አካል አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ክልሎች አዋጥተው የመሠረቱት መንግሥት ነው፡፡ መከላከያ ከሕዝብ የወጣ ነው፡፡ ከኦሮሞ የወጣ ነው፡፡ የባሰ ጥፋት እንዳይደርስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ መከላከያ ሠራዊታችን እዚህ ብቻ አይደለም ሌላ አገር ሄዶ ሰላም የሚያሰፍን ኃይል ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ የሟቾች ቁጥር 86 ደርሷል የሚል መረጃ አውጥቷል፡፡ የኦሮሚያ መንግሥት ማጣራቱን ባይጨርስም፣ ያለው መረጃ ከዚህ ቁጥር ጋር ምን ያህል የተቀራረበ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- መረጃዎቹን እንዲህ ናቸው ብለን መግለጽ አንችልም፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስና የሚመለከታቸው አካላት ማጣራቱን እያካሄዱ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ሰዎችንም እያወጡ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሮ በዚህ መሀል የሞቱት፣ በዋናነት ይህንን ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩት ቢሆኑም ከፀጥታ ኃይሎችም የሞቱ አሉ፡፡ መሞት አልነበረባቸውም፡፡ የፀጥታ ኃይሎችም፣ ሁከቱን ያካሄዱትም መሞት አልነበረባቸውም፡፡ በውይይት መፈታት ነበረበት፡፡ ክዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሞቱትን ነው ሟቾች የምንለው፡፡ በአሁኑ ወቅት የእነዚህ ሟቾች ቁጥር ለዚህ የቀረበ ነው፣ ያልቀረበ ነው ማለት አንችልም፡፡ እየተጣራ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከማስተር ፕላኑ ባልተናነሰ የከተሞችን አደረጃጀት በሚመለከት ጨፌ ኦሮሚያ ያወጣው አዋጅ ለግጭቱ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይነገራል፡፡ በዋናነት የዚህ አዋጅ አስፈላጊነትና ይዘት ምንድነው?

አቶ ፍቃዱ፡- አዋጅ ሳይሆን የአዋጅ ማሻሻያ ነው፡፡ አዋጁ የወጣው ከ15 ዓመታት በፊት  ነው፡፡ ይህንን አዋጅ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ማሻሻል አስፈላጊ ነበር፡፡  በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያለችበት ደረጃ የዛሬ 15 ዓመት ባለችበት ደረጃ አይደለም፡፡ ከተሞቻችን የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ማዕከል መሆን አለባቸው፡፡ በከተሞች የሚኖረው የሕዝብ ቁጥርም ትልቅ ዕድገት አለው፡፡ የከተሞቹን ዕድገት የሚመጥን አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ሕዝቡ የመንገድ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ አቅርቦቶችን ይፈልጋል፡፡ የሥራ ዕድልና የፅዳት አገልግሎት አቅርቦትን ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት እነዚህን አገልግሎቶች ለማቅረብ ከተሞች የሚያመነጩት ገቢ ወደ ክልል ፈሰስ ያደርጉና ክልሉ በበጀት መልክ ይመድብላቸው ነበር፡፡ በዚህ አዋጅ የተደረገው ከተሞቹ ላይ እየተጠየቁ ያሉ የልማት ጥያቄዎች ሰፊና ዘርፈ ብዙ ስለሆኑ ከተማው የሚሰበስበውን ገቢ እዚያው መቶ በመቶ እንዲጠቀም የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ከተሞች በጀት ወደ ላይ ልከው የተወሰነው ከሚመደብላቸው ይልቅ ሙሉውን እዚያው እንዲጠቀሙ ማድረግ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሁለተኛ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ በከተሞች የነበረውን አደረጃጀት ለአብነት አዳማን ብንወስድ፣ ባለው መዋቅር የከተማ አስተዳደርና የቀበሌ መዋቅር ብቻ ነው የነበረው፡፡ በጣም ሰፊ ለሆነው አዳማ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ከተማ ለሆነው አዳማ፣ የከተማና የቀበሌ መዋቅር ብቻ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሊፈታ አይችልም፡፡ ስለዚህ በቀበሌና በከተማ መከካከል አንድ መዋቅር እንዲጨመር ተደረገ፡፡ በሌላ በኩል ለምሳሌ ሻሸመኔና ኩየራን እንውሰድ፣ ኩየራ ከዓመታት በፊት ጥያቄ አቅርቦ በሻሸመኔ ሥር አንድ ክፍለ ከተማ ሆኖ ተቀላቀለ፡፡ ስለዚህ ከተሞቹ ተወያይተው ሲስማሙ የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ በገጠር ያሉ ተጎራባች ከተሞች እየተወያዩ መግባባት ላይ ሲደርሱ የሚፈጥሩት አንድ መዋቅር ነው፡፡ ከፈለጉ ይተሳሰራሉ፡፡ ካልፈለጉ ይተውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያ ትልቅ ስፋት አለው፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት ከተሜነት እየተስፋፋም ይገኛል፡፡ የገጠር ቦታዎች ለከተማ ልማት በሚፈለጉበት ወቅት ለተነሺዎች የሚከፈለው የካሳ ክፍያ አነስተኛ ነው፡፡ ለተነሺዎች የሚሰጠውም የከተማ ቤት መሥሪያ ቦታ አነስተኛ መሆን፣ እንዲሁም የካሳ ክፍያ የተከፈላቸው ተነሺዎች በቂ ሥልጠና የሚሰጣቸው ባለመሆኑ ገንዘቡን በማጥፋት ወደ ድህነት ኑሮ መመለሳቸው አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ይነሳል፡፡ ክልሉ ይህን ችግር አጢኖታል?

አቶ ፍቃዱ፡- ከተሞች መስፋፋታቸው እርግጥ ነው፡፡ ከተሞች ሲስፋፉ ግን አርሶ አደሩን በማፈናቀል መሆን የለበትም፡፡ ከቦታው የሚነሳው አርሶ አደር ከከተሜነት ተጠቃሚ መሆን አለበት፡፡ የክልሉ መንግሥት በዚህ በኩል ጽኑ እምነት አለው፡፡ ካሳ አከፋፈል ላይ የገበያ ሁኔታ በየጊዜው የሚለዋወጥ በመሆኑ በአንድ ወቅት ልክ የተባለው ክፍያ በሌላ ጊዜ የገንዘብ የመግዛት አቅም ሊያንስ ይችላል፡፡ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህቺ የተገኘችውን ገንዘብ ግን በአግባቡ በንግድ ላይ አውሏታል ወይ? የሚለውን መንግሥት ክፍተት እንዳለ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት በመሙላት መንግሥት በጥልቀት ጥናት አጥንቷል፡፡ ተነሺው ከከተማ መስፋፋት እንዴት ሊጠቀም ይችላል? በተሰጠው ካሳ በአግባብ እንዴት ሊጠቀም ይችላል? በሚለው ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በውይይት ዳብሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ጥናቱ አንድ ዙር በክልሉ መስተዳድር ታይቷል፡፡ የተሰጠው ግምት ተወስዶ በድጋሚ ታይቶ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡    

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተዘጋጀው ማስተር ፕላን ጠቀሜታ ምን ያህል እምነት አለው?  ከጥር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል በማስተር ፕላኑ ሥራ አመራር ቦርድ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ተሳታፊ አይደለም ይባላል፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱ የለም የሚል አቋም እየያዘ መመጣቱም ታይቷል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ እንደሌለ ገልጿል፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ አስተዳደር በ2006 እና በ2007 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ለማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱ የካፒታል በጀት አፅድቋል፡፡ ኦሮሚያም በተጠቀሱት በጀት ዓመታት ለፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤቱ መደበኛ በጀት እንዳፀደቀ ይነገራል፡፡ እነዚህ ክስተቶች አይጋጩም? እውነታው የቱ ጋ ነው ያለው?

አቶ ፍቃዱ፡- ይኼን በተደጋጋሚ ገልጸናል፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በረቂቅ ደረጃ ያለው ማስተር ፕላን ሕዝብ ሳይወያይ ተግባራዊ አይደረግም፡፡ የሕዝብ ይሁንታ ሲያገኝ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ድርጅታችን ግልጽ አቋም አስቀምጧል፡፡ አሁን በተፈጠረው ሁኔታም በኦሮሚያ በኩል ግልጽ የሆነ የተንቀሳቀሰ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ማስተር ፕላኑ ገና ረቂቅ ነው፡፡ እሱ አይደለም ነጥቡ፡፡ ነጥቡ የማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የመሥራትና ያለመሥራትን ጉዳይ ነው የምልዎ?

አቶ ፍቃዱ፡- የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱም የኦሮሚያ ልዩ ዞንን በሚመለከት ምንም እንዳይሠራ መግለጫ ሰጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- መግለጫውን የሰጠው የአዲስ አበባ አስተዳደር ነው፡፡

አቶ ፍቃዱ፡- የአዲስ አበባ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር የአቋም ልዩነት የለኝም ብሎ ነው መግለጫ የሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- የጋራ ማስተር ፕላኑ ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚሆነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ዕጣ ፋንታው የሕዝብ ውይይት ነው የሚያውቀው፡፡ አሁን የማረጋጋት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ይህን ከጨረስን በኋላ ሕዝብ እናወያያለን፡፡ በጥልቀት መወያያት ያስፈልጋል፡፡ የያዝነውን የማረጋጋት ምዕራፍ አጠናቀን ከገመገምን በኋላ፣ ወደዚህኛው ምዕራፍ (ማስተር ፕላኑ ላይ ማወያየት) እንገባለን፡፡ አሁን በሰላም ጉዳይ ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ ሥራችንን በአግባቡ ከጨረስን በኋላ ቁርጥ ያለ ቀን ባይኖርም፣ በዚህ ዓመት ወደ ውይይት እንገባለን፡፡ የማስተር ፕላኑን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -