ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማፅደቅ ባለፈው ዓርብ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከዕቅዱ እኩል ትኩረቱን በሳቡ ወቅታዊ ሁነቶች ላይ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም በተፈጠረው ግጭት፣ በቅማንትና በአማራ ብሔረሰቦች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በሱዳን የድንበር ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል፡፡
በኦሮሚያ ግጭት ላይ
በኦሮሚያ አንዳንድ ዞኖችና ወረዳዎች አካባቢ የተፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦችን መሠረት አድርጎ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ከቅማንት ማኅበረሰብና ከአማራው ማኅበረሰብ ወይም ብሔር ጋር የተነሳ ግጭትና ያደረሰው የሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም አለ፡፡
የተፈጠረውን ጉዳይ በሁለት መንገድ ማየት አለብን፡፡ አንደኛው የጥያቄውን ሁኔታ በተመለከተ ነው፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ልማታቸውን አቀናጅተው ለመሥራት እንዲመቻቸው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ለመሥራት አቅደዋል፡፡ ስለማስተር ፕላኑ በተሳሳተ መንገድ ወደ ሕዝቡ በደረሱ መረጃዎች አማካይነት ጉዳዩን ለማጥራት ሕዝቡ ያነሳው ጥያቄ አለ፡፡ ይኼ ፍትሐዊና ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ ሕዝቡ መቼም ቢሆን መንግሥት ጥሩ ነው ብሎ የሚያወጣቸው ዕቅዶች ላይ ጥያቄ ከማንሳት መቆጠብ የለበትም፡፡ በመወያየት፣ በመነጋገርና በመተማመን ወደ ተግባር የሚያስገባ መንግሥት አለ፡፡ መርጦ ያቋቋመው መንግሥት እንደመሆኑ መጠን ማንኛውንም ጥያቄ ለመንግሥት አቅርቦ ግልጽ እንዲሆንለት ሊያደርግ ይችላል፣ ይገባዋልም፡፡ ይህንን በማድረጉ ምንም ስህተት የለውም፡፡ ይህ ዛሬም ነገም መደረግና መቀጠል ያለበት ነው፡፡
ስለዚህ በእኛ በኩል ይህ ጥያቄ በ2006 ዓ.ም. ተነስቶ መለስተኛ ማብራሪያ ተሰጥቶ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ወደዚህ መደነጋገር እንዳይገባ የማብራራት፣ ግልጽነት የመፍጠር ጉዳይ ከእኛ በኩል በበቂ መጠን እንዳልሠራን ጥያቄው የሚገልጽ ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ያለውን ጉድለት ማየት ትልቁ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ጉድለታችንን ወስደን ሕዝቡን በተከታታይ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስረዳት ይኖርብናል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ በዚህ መደነጋገር ምክንያትና በሌሎች የራሳቸው ምክንያቶች ምናልባትም በየገጠሩና የከተሞች ለወጣቶቻችን በበቂ መጠን የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የኢኮኖሚውና የዕድገቱ ተጠቃሚ በማድረግ ዙሪያ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ባሉ ጉድለቶች ምክንያት፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚሰማቸው ወጣቶች እንዳሉ ግን የማይካድ ነው፡፡ ይህንን በምርጫ ጊዜም አይተናል፡፡ ከዚያም በኋላ ባሉ ጉዳዮችም አይተናል፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ቅሬታ በውስጣቸው የያዙ ወጣቶች የሆነ አጀንዳ በሚፈጠርበት ጊዜ ቢሳተፉ የሚገርም አይሆንም፡፡ እነዚህንም ኃይሎች ለይተን ማየት ይገባናል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ በዚህ ሒደት ውስጥ ሕዝቡ እንዲደናገር ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ፣ አርሶ አደራችን ለልማት ጉዳይ ካሳ ተከፍሎት መሬቱን የሚለቅበት አሠራር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያለ ቢሆንም፣ አርሶ አደራችንን የበለጠ ተጠቃሚና ልማታዊ በሚያደርገው መንገድ ማስተዳደርና መልክ ማስያዝ ላይ ክፍተት አለ፡፡ አርሶ አደሩ በዚህ ምክንያት ቅሬታ እንዳይፈጠርበት የማድረግ ሥራ ላይ አሁንም በበቂ ሁኔታ ያልተፈቱ ጉድለቶች አሉ፡፡ በዚህ ቅሬታ የያዘ አርሶ አደር ቢኖር የሚገርም አይሆንም፡፡ እነዚህንም ለይተን ማየት አለብን፡፡
በመጨረሻ ግን ይኼ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው የሚለው ደግሞ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ስለዚህ ማየት ያለብን ከዚህ ውጪ ይህንን ጥያቄ በተሳሳተ መንገድ የሚያሰራጩ አካላት ሕዝቡ ሊለያቸው ይገባል፡፡ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ወደፊትም ቢሆን እናወያያለን፡፡ ይህ የኢሕአዴግ ባህሪ ነው፡፡ ሕዝቡ ይቆይልን የሚለን ከሆነ እናቆያለን፡፡ ነገር ግን ደግሞ በሒደት ከተሞክሮው ተምሮ ራሱ ጥያቄ የሚያቀርብበት ሁኔታ ስለሚፈጠር፣ ይህንን ታግሰን እናያለን ተብሎ የሚወስን ኢሕአዴጋዊ አሠራር አለን፡፡
መቼም ቢሆን ሕዝብ በግዴታ ዕቅድ እንዲተገብር አድርጎ አያውቅም፣ አይገባውምም፡፡ ይህ ከራሳችን መርህ ጋር የሚፃረር ነው፡፡
ሌላው እነዚህ ኃይሎች የሚያሰራጩት ማወናበጃ በማስተር ፕላኑ ምክንያት እስከ 150 ኪሎ ሜትር ድረስ ይወስዳል፣ ይነጥቃል የሚል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ መንዛታቸው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሕዝባችን ግልጽ ሊሆን የሚገባው የፌዴራላዊ መዋቅራችን ሕገ መንግሥታዊ እንደመሆኑ መጠን፣ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎችም ለአዲስ አበባም እንዲሁም ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሰጠው መብት በምንም መልኩ ሊሸራረፍ የማይችልና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው፡፡ ስለዚህ የሐሰት ፕሮፓጋንዳው መመዘን ያለበት በዚህ የሕገ መንግሥት መርህ ነው፡፡
የአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያለው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ዕቅዳቸውን ለማቀናጀት ፈለጉ እንጂ በራሳቸው በተናጠል መሄድ ይችላሉ፡፡ አናቀናጅም ካሉ የሚከለክላቸው የለም፡፡ ግን ደግሞ በመቀናጀታቸው የሚመጣ ሰፊ ጥቅም ስላለ ነው መቀናጀት የተፈለገው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ካሉ ከተሞች አንድ ስንዝር መውሰድ አይችልም፣ አይገባውምም፣ አይሆንምም፡፡ የፌዴራል ሥርዓታችንም ሆነ ሕገ መንግሥታችን ለዚህ ጠበቃ ነው፡፡
በሰላማዊ መንገድ መቅረብ በሚችል ጥያቄ ምክንያት የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ይዘው ሕዝቡን ለማደናገር የሞከሩ፣ ተግባራዊም አድርገው የሰው ሕይወት እንዲጠፋ አቅደው፣ ወጥነው፣ ቀስቅሰው፣ መርተው ያስፈጸሙ አካላት በሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ሽፋን የሽብርተኛ ድርጅት ሴሎችን በውስጣቸው አስቀምጠው ይህንን ብጥብጥ የመሩ አካላት፣ እንደዚሁም ደግሞ የሻዕቢያ መንግሥት የሚሰጠውን አመራር ተከትለው ይህንን ለማስፈጸም ሌት ተቀን የሮጡ አካላት በመታገል ረገድ መንግሥት ቁርጥ ያለ አቋም ነው ያለው፡፡ እነዚህን አካላት በመታገል ረገድ መንግሥት ድሮም አይታገስም፣ ዛሬም አይታገስም፣ ወደፊትም እንደዚሁ፡፡
ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመውና ታጥቀው ከፀጥታ ኃይሎቻችን ጋር ታግለዋል፣ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኃይሎች ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡
እነዚህን የጥፋት ኃይሎች የአሸባሪ ድርጅቶች ተላላኪ የሆኑትን ጨምሮ፣ እንዲሁም በሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሴላቸውን አስቀምጠው ይህንን ነገር ለማንቀሳቀስ የሞከሩ ኃይሎችን ጭምር፣ መንግሥት መረጃና ማስረጃ መሠረት አድርጎ ሕጋዊና የማያዳግም ዕርምጃ ይወስዳል፡፡
በአማራ ግጭት ላይ
ሌላኛው የተነሳው በሰሜን ጐንደር የተከሰተው ከቅማንት ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአገራችንም ሕገ መንግሥትም ሆነ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መብት የማስከበር ጉዳይ ላይ ብዙ ትግል ያካሄደበትና የተሰዋበት ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝቦች መብት ያላንዳች መሸራረፍ መከበር እንዳለበት አምኖ የታገለበት ጉዳይ ነው፡፡
እኔ ባለኝ መረጃ በአካባቢው ያሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሳይቀሩ የቅማንት ማኅበረሰብ ጥያቄ መመለስ አለበት ብለው፣ ይህንን ጥያቄ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትንም ጭምር ሲደግፉ ነበር፡፡ በማኅበረሰቡ ጥያቄ ላይ የአማራ ብሔር ምንም ዓይነት ብዥታ እንደሌለው የሚታወቅ ነው፡፡
የቅማንት ማኅበረሰብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የአስተዳደር ክልል ስለሚያስፈልገው፣ ይህንን የአስተዳደር ክልል የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፍተኛ ቁጥር ያሉባቸው ቀበሌዎችን መሠረት አድርጎ የክልሉ ምክር ቤት የከለለው የልዩ ወረዳ ቦታ አለ፡፡ ይህ የተከለለው ቦታ ሙሉ በሙሉ የቅማንት ማኅበረሰብ፣ በአብዛኛው የሚገኙበትን ኩታ ገጠም የሆኑ ቀበሌዎችን የሚያካትት ስላልሆነ እንዲያካትት መደረግ አለበት የሚል ጥያቄ በማኅበረሰቡ በኩል ተነስቷል፡፡
ይህ ጥያቄ መነሳቱ ምንም ችግር የለውም፡፡ ለመፍታትም ውስብስብ አይደለም፡፡ በአገራችን የማካለል ጥያቄዎችን በተመለከተ የመለስናቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ልምዶች አሉን፡፡ ስለዚህ ወደ ሕይወት መጥፋት፣ ወደ ንብረት ማውደም ሊወስደን የሚችል አንዳችም ምክንያት የለም፡፡
የሁለቱን ሕዝቦች አብሮነትና የቀደመ ትስስር ያልተገነዘቡ ኃይሎችና በተለያዩ የጠባብነትና የትምክህት አጀንዳ የሚመሩ ኃይሎች በሕዝቡ መካከል በፈጠሩት ውጥረት ወንድማማች የሆነው ሕዝብ ተጋጭቷል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የማንነት ጥያቄው እንዴት ይፈታ አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሳተፉና የሕዝቡን ትክክለኛና ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ጥያቄ በማይመጥን ደረጃ የቀሰቀሱ፣ ያጋጩ፣ የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ያደረጉ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሥራ ማመቻቸትና መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ሁለቱ ማኅበረሰቦች ወደ ቀድሞው የወንድማማችነት ግንኙነታቸው እንዲመጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎችም ተሰሚነት ያላቸው አካላት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን በዚህ ግጭት ላይ እጃቸውን ያስገቡ በፈጸሙት ጥፋት ልክ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ነው፡፡
በዚህ ግጭት ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከላይ እስከ ታች ቋምጠው ነበር፡፡ አገር ለመናድ ይህ አጀንዳ ይጠቅመናል ብለው ተረባርበው ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ሕዝባችን የሚጠቅመውን ስለሚያውቅ ተደናግሮ እንኳን ወዲያው ወደነበረበት የሚመለስ ሕዝብ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን እዚህም እዚያም በሚፈጠር ግጭት የሚናጋ መስሏቸው ከሆነ ሥርዓቱን አለማወቅ ነው የሚሆነው፡፡
በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር መካለል ላይ
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሱዳን መሬት ቆርሶ ሰጥቷል የሚል መረጃ በእነዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች ተነዝቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕዝብ ሆይ ተነሳ የሚል ጥሪ ሲያቀርቡ እንሰማለን፡፡ በመጀመሪያ በመሬት ጉዳይ የተደረገ ስምምነት የለም፡፡ የተሰጠ መሬትም የለም፡፡ ተቆርሶ ሊሰጥ የሚችል ነገርም የለም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዷን አጀንዳ ሕዝቡን ሊያነሳሳ ይችላል ብለው ባመኑበት መጠን በየጊዜው ሲዘምቱ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ጥያቄ እኮ በ2005 ዓ.ም. እዚሁ ምክር ቤት ውስጥ ተጠይቄ ማብራሪያ ሰጥቻለሁ፡፡ ታዲያ የታለ ተቆርሶ ሄደ የተባለው መሬት? ከ2005 እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ግን ወሬው ይነዛል፡፡
ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር እስከ ዛሬ እንዳልተካለለ ቀድሞውንም የሚታወቅ ነው፡፡ ዛሬም ያለ አጀንዳ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት የጋራ ድንበር ኮሚሽን መሥርተው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አሁንም የሚቀጥል ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች የድንበር ኮሚሽን ያቋቋሙት እኮ ዛሬ አይደለም፡፡ በየመንግሥታቱ የኮሚቴ አባላት ስም ይቀያየራል እንጂ፡፡
ስለዚህ ይህ ጉዳይ በሒደት ላይ ያለ በመጨረሻ ላይም የአገራችን ሕዝብ ተወያይቶበት ድምዳሜ ላይ ይደረሳል እንጂ እነሱ እንደሚሉት ዝም ብሎ እየተነሳ ተቆርሶ የሚሄድ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ አገር ነው፡፡ እኛ እየመራን ያለነው ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ ሳያውቅ የሚከናወን ነገር ሊኖር አይችልም፡፡
የእኛን ብቻ አይደለም ማየት ያለብን፡፡ ከእኛ አካባቢ እየተንቀሳቀሱ ሱዳን ላይ ችግር እየፈጠሩ፣ ሰው እየገደሉ የሚመለሱትንም ማየት አለብን፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳን ወዳጅ ባይሆኑ ኖሮ በዚህ ምክንያት የተነሳ ሁለቱ አገሮች ግጭት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡
ሌላው ማየት ያለብን በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ሱዳን ውስጥ ገብተው የሚያርሱ እኛም የምናውቃቸው ሱዳኖችም የሚያውቋቸው፣ የእኛ ባለሀብቶችና ውስን አርሶ አደሮችም አሉ፡፡ የማካለል ሥራውን እስክንሠራ ድረስ እነዚህን አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች አትንኩብን ብለን በወዳጅነታችን ምክንያት ዝም ያሏቸው አርሰው የሚበሉ የእኛ ዜጎች አሉ፡፡ ስለዚህ ወዳጅነታችንን ለማናጋት በጋራ የምንሠራውን ሥራ ለማበላሸት የሚነዛውን ትክክለኛ ያልሆነ ፕሮፓጋንዳ ልንቋቋም ይገባል፡፡
አሁንም ወደፊትም የኢትዮጵያና የሱዳን ወዳጅነትና መልካም ጉርብትና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ይሆናል፡፡