Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢራፓ ከጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ራሱን አገለለ

ኢራፓ ከጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ራሱን አገለለ

ቀን:

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በተፈጠሩበት አስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መልቀቁን አስታወቀ፡፡ የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ምክር ቤቱ የፓርቲውን ጥቅም ሊያስከብር አልቻለም፡፡

አቶ ተሻለ፣ ‹‹ምንም እንኳን ላለፉት ስድስት ዓመታት በምክር ቤቱ በነበረን ቆይታ በርካታ ችግሮችን እያስተዋልንና የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማቅረብ የምናደርገው ጥረት ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቶ ነገሮች ይሻላሉ በሚል ተስፋ እስካሁን ብንዘልቅም፣ ምንም ዓይነት መሻሻሎች ባለመከሰታቸው እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰናል፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

ፓርቲው ለጋራ ምክር ቤቱ በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው አጀንዳዎች ውድቅ መደረጋቸው እየተለመደ በመምጣቱ፣ በተለይም በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ፓርቲው ያቀረባቸው አጀንዳዎች ተቀባይነት ማጣታቸው ለዚህ ውሳኔ አፋጣኝ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኅዳር ወር ፓርቲው ለጋራ ምክር ቤቱ ያቀረባቸው የውይይት አጀንዳዎች ሦስት እንደነበሩ ገልጾ፣ ካቀረባቸው ሦስት አጀንዳዎች መካከል ግን በጋራ ምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ለውይይት የቀረበው አንዱ ብቻ እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል፡፡

ፓርቲው በአጀንዳነት ለውይይት እንዲቀርቡ ያቀረባቸው ሐሳቦች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም በአገሪቱ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ስለተሠጋው ረሃብ፣ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን በስፋት እየዘገቡበት ስላሉት የኢትዮ-ሱዳን የድንበር አከላለል ጉዳይ፣ እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ስለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎችና እንቅስቃሴያቸው የተመለከተ እንደነበር ፓርቲው አስታውሷል፡፡

‹‹ምንም እንኳን እነዚህን ሦስት አጀንዳዎች በምክር ቤቱ ውይይት እንዲካሄድባቸውና ዝርዝር አጀንዳ ውስጥ ቀዳሚ ሆነው እንዲቀመጡ የጠየቅን ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ግን የድርቁን ጉዳይ ብቻ በመውሰድ ሁለቱን አጀንዳዎች በመረጃ የተደገፈ ዝርዝር መረጃ ይቅረብ በማለት ሳይቀበለው ቀርቷል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው እነዚህን ጥያቄዎች በአጀንዳነት እንዲያዙለት የጠየቀው በተሻሻለው የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ 5 መሠረት መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ጥያቄያችን ግን ተቀባይነት ባለማግኘቱ የጋራ ምክር ቤን ለመልቀቅ ወስነናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ደንብ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ 5፣ ‹‹በማንኛውም አገራዊና ሕዝባዊ እንዲሁም ወቅታዊ አጀንዳዎች/ጉዳዮች ላይ በመመካከርና በመወያየት የጋራ አቋሙን ወይም ልዩነቶችን ለሕዝቡና ለሚመለከታቸው አካላት የማቅረብ ዓላማ አለው፤›› ይላል፡፡ አቶ ተሻለ፣‹‹ቋሚ የምክር ቤቱ ስብሰባዎች የጊዜ ሰሌዳ ከሕገ ደንቡ ውጪ በኢሕአዴግ በጎ ፈቃድና ፍላጎት ብቻ እየተለጠጠ ነው፡፡ የአጃቢነት ሥነ ልቦና ውስጥ አባል ፓርቲዎች እንዲጠመቁ ማድረግ፣ እንዲሁም አስቸኳይ ስብሰባዎች በደንቡ መሠረት እንዲጠሩ ስንጠይቅ በምክንያቶች መብዛት የኢሕአዴግ ፈቃደኝነት ካልታከለበት፣ በምክር ቤቱ የአቻነት ዴሞክራሲያዊ መርህ እንዳይጎለብት በማድረግ አጀንዳዎች ተጥለውና ተረስተው እንዲቀሩ መደረጋቸው፣ ከምክር ቤቱ ለመውጣት ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች ናቸው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ራሱን ቢያገልም፣ በቀጣይ ግን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እስከ መዋሀድ በሚደርስ እንቅስቃሴ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በተካሄደው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከኢሕአዴግና ከአጋሮቹ በመቀጠል ከፍተኛ የመራጮች ድጋፍ ያገኙት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤቱ አባል እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ኢዴፓ ከምክር ቤቱ ራሱን ለማግለል እንደሚገደድ ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም አባል ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ የሥነ ምግባር አዋጅ 662/2002 ዓ.ም. በአንቀጽ 22(9) ላይ የምክር ቤት አባል ለመሆን የሚፈልጉ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር ደንቡን መፈረም እንደሚጠበቅባቸው ይደነግጋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...