– የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቅም ላይ ዋለ
ፓርላማው ባለፈው ዓርብ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ 18 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ሲያፀድቅ፣ ከበጀቱ 14.78 ቢሊዮን ብር የሚውለው ለድርቅ ተጎጂዎች እንዲውል ወስኗል፡፡
በሥራ አስፈጻሚው አማካይነት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ተጨማሪ በጀት ያብራሩት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ናቸው፡፡
ተጨማሪ በጀት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በአገሪቱ ኤልኒኖ በተባለው የአየር መዛባት ምክንያት የደረሰውን ድርቅ አደጋ ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት መሆኑን፣ በተጨማሪም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እንዲውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በ2008 ዓ.ም. ከተያዘው 223.4 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ በጀትነት 18 ቢሊዮን ብር መቅረቡን፣ ይህም በዓመቱ ሊሰበሰብ የሚችለውን ገቢ እንደገና በመገመት ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ተጨማሪ በጀቱን የሚደግፉ ገቢዎች መኖራቸው በመረጋገጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ከቀረበው 18 ቢሊዮን ብር ውስጥ 14.78 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የድርቁን አደጋ ለመከላከል ሲውል፣ የቀረው 3.22 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች የሚውል ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ከተደረገው አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ለተደረገው የስምንት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት የአንበሳውን ድርሻ የሚሆን ገቢ የተገኘው ከነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ነበር፡፡ በመሆኑም በወቅቱ ስድስት ቢሊዮን ብር ገቢ ከዚህ ፈንድ ለደመወዝ ጭማሪ ለሚውለው ተጨማሪ በጀት መዞሩ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ ሳምንት ለቀረበው 18 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት 12.5 ቢሊዮን ብር የተገኘው ከዚሁ የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ነው፡፡ የቀረው 2.2 ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ የዘቀጠ ትርፍ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘቀጠ ትርፍና ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት የዘቀጠ ትርፍ 250 ሚሊዮን ብር ለተጨማሪ በጀቱ የገቢ ምንጭ ሆነዋል፡፡
የድርቁን አደጋ ከመከላከል ውጪ ያለው 3.22 ቢሊዮን ብር የሚውለው ለውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የካፒታል ፕሮጀክቶች ነው፡፡