Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በካይ ፋብሪካዎች ዕርምጃ ይጠብቃቸዋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የኢንዱስትሪ ኬሚካል ምዝገባ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ሕጎች ይወጣሉ

እንደ አዲስ የተዋቀረው የአካባቢ ጥበቃ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ሲገለጽ በነበሩ በካይ ፋብሪካዎች ላይ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ታኅሳስ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ውይይት ወቅት እንዳስታወቀው፣ የአካባቢ ብክለትን የሚከላከሉ ቴክኖሎጂዎችን የማይጠቀሙ፣ በካይ ዝቃጮችን፣ አደገኛ ጋዞችንና ልዩ ልዩ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በሚለቁ ፋብሪካዎች ላይ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ይማም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 44 መሠረት አካባቢ ደኅንነት መብት መደንገጉን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ሰዎች ሁሉ ንፁህና ጤነኛ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡ ‹‹ሕጉ ይህንን ቢደነግግም ኅብረተሰቡ ከኢንዱስትሪዎች በሚወጡ በካይ ዝቃጮች ምክንያት ጤናው፣ አካባቢውና የእንስሳት ሀብቱ እንደተጎዳበት እየነገረን ነው፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከዚህ ቀደም የቆሻሻ ፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓታቸውን እንዲያስተካክሉና ተገቢውን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በታኅሳስ 2006 ዓ.ም. እንደሚያበቃ ይጠበቅ የነበረው የጊዜ ገደብ፣ በካይ ተብለው በተለዩ ከ40 በላይ ፋብሪካዎች ላይ ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንዳላስከተለ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በካይ ዝቃጭ አወጋገድ ላይ በአግባቡ ያልሠሩት ላይ ክትትልና ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ ዕርምጃው ከገንዘብ ቅጣት እስከ ማሸግ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባሻገር በድምፅ ብክለት፣ በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነድ አዘገጃጀትና አተገባበር፣ በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጥ ተግባራት ላይ ሚኒስቴሩ የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንደሚኖሩ አቶ ከበደ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በዚህ ዓመት የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ምዝገባ አዋጅን ጨምሮ የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የተሰኙ አዳዲስ ሕጎች እንደሚወጡ ሚኒስትር ዴኤታው ይፋ አድርገዋል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት የቆየውና ማስተግበሪያ መመርያና ደንብ ሳይወጣለት የከረመው የደን አጠቃቀምና ልማት አዋጅም ማሻሻያ ተደርጎበት በዚህ ዓመት ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ዓላማዎች ያብራሩት ሌላኛው ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቃሬ ጫዊቻ ናቸው፡፡ አቶ ቃሬ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በማያስከትልና ከበካይ ጋዞች ልቀት ነፃ በሆነ መንገድ ለመምራት እንዲቻል፣ ከ15 ዓመት በኋላ 150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡ በየዓመቱም 7.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያፈልገው ጠቁመው፣ በቅርቡ በፓሪስ በተደረገው ድርድርም መንግሥት ዝቅተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመልቀቅ የሚያስችለውን ዕቅድ በማቅረብ መደራደሩን አስታውሰዋል፡፡ አገሪቱ በዓለም ላይ ዕቅዳቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካቀረቡ ቀደምት አራት አገሮች አንዷ ለመሆን እንደቻለችም ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉትን የመንግሥት ዕቅዶችና ዕርምጃዎች የተገለጹበትን መድረክ የመሩት የአከባቢ ጥበቃ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፣ ከኅብረተሰቡ የተወከሉ አካላት በየሩብ ዓመቱ እየተገናኙ የሚመክሩበት መድረክ በቋሚነት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች