ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ንብረትነቱ የካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሆነውን 100 ሺሕ ሔክታር መሬት በሐራጅ ለመሸጥ ያወጣውን ጨረታ፣ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አገደው፡፡
የህንዱ ካሩቱሪ ግሎባል ኩባንያ አካል የሆነው ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ሐራጅ የተባለው ከንግድ ባንክ የተበደረውን 55.8 ሚሊዮን ብር በወቅቱ ባለመክፈሉ እንደነበር ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሆኖም ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ የወጣው ሐራጅ እስከ መጪው ጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ታግዶ ይቆያል፡፡
ካሩቱሪ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት የመጠባበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዓት እንዲከፈትለት መጠየቁን ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህንን የመጠባበቂያ ስምምነት ሥነ ሥርዓት የሚያፀድቀው ከሆነ፣ የህንዱ ኩባንያ ከአበዳሪው ጋር በመደራደር ዕዳውን ለመክፈል የሚያስችለው ተጨማሪ ጊዜ ያስገኝለታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኩባንያው ለፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ መሠረት በጋምቤላ ክልል የሚገኘው 100 ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬቱ ለሦስተኛ ወገን ቢሸጥ ‹‹የማይመለስ ጉዳት›› እንደሚደርስበት በመግለጽ፣ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡ የፍርድ ቤቱ የዕግድ ትዕዛዝ ለባንኩ ታኅሳስ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደደረሰው የባንኩ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኩሪያ አረጋግጠዋል፡፡
የሕግ ባለሙያዎች ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ ዕገዳው ካሩቱሪ ያለበትን ዕዳ በድርድር እንዲከፍል አሊያም የከሰረ ስለመሆኑ እንዲያስታውቅ ያስችለዋል፡፡
ለሃምሳ ዓመታት በሚቆይ የሊዝ ስምምነት መንግሥት በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ለካሩቱሪ የሰጠው መሬት፣ እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ዋጋ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ኩባንያው ከስድስት ዓመታት በላይ በተሰጠው እርሻ ቦታ ላይ ተገቢውን ልማት ማከናወን ሳይችል ቆይቷል፡፡ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት ዓምና በጉዳዩ ላይ በሪፖርተር ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ፣ ኩባንያው ይጠበቅበት የነበረውን ሥራ እያከናወነ እንዳልሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡