Saturday, December 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የሚሳካው ብቃት ባለው የሰው ኃይል ብቻ ነው!

ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፀድቆ ለመጨዎቹ አምስት ዓመታት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በመጀመሪያው ዕቅድ በታዩ መልካም አፈጻጸሞችና ጉድለቶች ላይ በመመሥረት የተዘጋጀውና በፓርላማ የፀደቀው ሁለተኛው ዕቅድ፣ አገሪቱን በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ደረጃ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ወሳኝ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሮለታል፡፡ ይህ ዕቅድ በዋነኝነት የያዛቸው ግቦች ኢኮኖሚውን በየዓመቱ 11 በመቶ በማሳደግ ማስቀጠል፣ ግብርናው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ መሠረት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ፣ የወጪ ንግድን በስፋት ማሳደግ፣ በገጠርና በከተማ ለወጣቶችና ለሴቶች በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠርና አምራች ኢንዱስትሪውን በማስፋፋት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ነው፡፡ የዕቅዱ ግቦች በጣም የተለጠጡ ሲሆኑ፣ ለዚህም በምክንያትነት የቀረበው የኢኮኖሚው መሠረት በከፍተኛ ደረጃ በመስፋቱና የዕድገት ምጣኔው እየገዘፈ በመምጣቱ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ከፍተኛ ጥረትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ተግባር ለማሳካት ደግሞ ብቃት ያለው አመራርና ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡

ይህ ዕቅድ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ተዘጋጅቶ በረቂቅ ደረጃ ሲቀርብ መንግሥት በየዘርፉ ካሉ ምሁራን፣ ባለሙያዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲመክርበት ጥሪ ቀርቦለት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በተደረገው ውይይት የተለያዩ ሐሳቦች ሲቀርቡ በዋናነት ይነሳ የነበረው ብቃት ያለው የሰው ኃይል ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም በጉልህ የሚጠቀሰው በመጀመሪያው ዕቅድ ዘመን አርኪ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው መስኮች ብቃት ባላቸው ሰዎች የተመሩ ሲሆኑ፣ የአፈጻጸም ጉድለት የነበረባቸው ደግሞ ከብቃት ማነስ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ሌሎች የሚጠቀሱ ተያያዥ ምክንያቶች ቢኖሩም፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ልዩ ትኩረት የተሰጠባቸው መስኮች ቁርጠኝነትን ይጠይቃሉ ሲባል፣ በተለይ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ጉዳይ ፈጽሞ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ብቃት ያለው የሰው ኃይል የሚያፈሩ ትምህርት ተቋማት ጥራትም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን እናነሳለን፡፡

ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሚገባ ተቀርፀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ሲፈለግ፣ የአስፈጻሚውና የፈጻሚው የሰው ኃይል ጉዳይ ሲዘነጋ ይታያል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ብዙዎቹ አስፈጻሚ የመንግሥት የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ባለሙያዎች በደመወዝ፣ በዕድገት፣ በጥቅማ ጥቅምና በመሳሰሉት ምክንያቶች ጥለዋቸው እየኮበለሉ ነው፡፡ ለዚህም የሚጠቀሱት በፍትሕ፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በመሳሰሉት ከፍተኛ ፍልሰት ታይቷል፡፡ እነዚህ አጥጋቢ የሆነ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድና ዲሲፕሊን ያላቸው ባለሙያዎች በውጭ ኢንቨስትመንቶችና በአገር ውስጥ ኩባንያዎች በመወሰዳቸው፣ ብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች ተራቁተዋል፡፡ ከማዕድን፣ ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከንግድ፣ ወዘተ ከመሳሰሉት ተቋማትም ከፍተኛ የባለሙያ ፍልሰት ተካሂዷል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የሚጠቅሙ በርካታ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በሌሉበት ምን ታስቧል? የቀሩትንስ ለማቆየት ምን ዓይነት ማበረታቻዎችና ጥቅሞች አሉ? ይህ ትኩረት ይሻል፡፡

የብቃት ጉዳይ ሲነሳ አብሮት ያለው የሥነ ምግባርና የሞራል ጉዳይም እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ኃላፊነታቸውን በተጠያቂነት መንፈስ የሚወጡ ባለሙያዎች ከሙስናና አላስፈላጊ ተግባራት የፀዱ ናቸው፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው፣ የሥራ ልምዳቸውና ሥነ ምግባራቸው ሕገወጥ ከሆኑ ተግባራት ስለሚታደጓቸው ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ይችላሉ፡፡ መንግሥት እንዲህ ዓይነቶቹን ዜጎች ከያሉበት እየፈለገ፣ ተገቢ በሆነ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መመደብ አለበት፡፡ ነፃነታቸው ተጠብቆ በተመደቡበት ኃላፊነት አገራቸውን እንዲያገለግሉ ያስፈልጋል፡፡ ሙያዊ ነፃነትና ብቃት ያላቸው ዜጎች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢነርጂ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በጥናትና ምርምር፣ ወዘተ ሊሰማሩ የግድ ይላል፡፡ ይህንን እጅግ በጣም የተለጠጠ ዕቅድ ከሞላ ጎደል ለማሳካት የሚቻለው አመራሩና ባለሙያው ነፃነትና ብቃት ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡

ይህ ዕቅድ አገር ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች በተጨማሪ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን (ዳያስፖራ) ጭምር ማሳተፍ አለበት፡፡ አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ሽግግር ታደርግበታለች የሚባለው ይህ ዕቅድ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን ወገኖች ማካተት አለበት፡፡ ዳያስፖራው በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርገው አስተዋጽኦ በሐዋላ ከሚልከው ገንዘብ በላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፡፡ የህንድና የቻይና ዳያስፖራዎች ለአገሮቻቸው የሚያበረክቱት ወደር የሌለው አስተዋጽኦ ምሳሌ መሆን አለበት፡፡ ዳያስፖራው ከሚኖርባቸው አገሮች ለአገሪቱ በተጨባጭ ሊጠቅሙ የሚችሉ ተዋፅኦዎችን ይዞ እንዲመጣ የማግባባት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከንግግር በላይ ተግባራዊ ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን አገር ውስጥ ባሉ ዜጎችና በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አማካይነት መፈብረክ የሚቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ፍላጎት አልፎም ኤክስፖርት ለመደረግ የሚችሉ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው፡፡ ይህንን አቅም በሌሎች ዘርፎችም መጠቀም እንዲቻል ደግሞ መንግሥት በሁሉም አቅጣጫዎች ማማተር አለበት፡፡ በብቃት የተገኘን አቅም እያጣጣሉ የውጭ ምርት ማጋበስ ተገቢ ስላልሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ዜጎች ዕድሉ ይመቻችላቸው፡፡ ወቅቱ የብቃት ነው፡፡  

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ከምንም ነገር በላይ ሰው ሰው መሽተት አለበት፡፡ ከቁሳዊው ዕድገት በላይ በተጨባጭ የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች በማሟላት የእያንዳንዱን ዜጋ ጎጆ ሊያንኳኳ ይገባል፡፡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚዳረስ ሀብትም መፍጠር አለበት፡፡ ጥቂቶች እየከበሩ ብዙኃን የሚደኸዩበት ኢፍትሐዊ ሥርዓት መፈጠር የለበትም፡፡ በተጨማሪም የሕዝቡን ጤና፣ የኑሮ ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ተስፋና አንድነት የሚያሳድግ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና በማለምለም የእኩልነት አገር መመሥረት ይጠበቅበታል፡፡ የሕግ የበላይነትና ፍትሕ የሚያሰፍን መሆን አለበት፡፡ አድሎአዊነትንና ራስ ወዳድነትን የማይታገስ ሊሆን ግድ ይለዋል፡፡ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የበለፀገችና አንድነቷ የጠነከረ ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትፈጠር ማገዝ አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ተስፋና ምኞት የሚሰምረው ብቃት ያላቸው ዜጎች በቁርጠኝነት እንዲሳተፉ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡

መልካም አስተዳደርን በማጥፋት ሕዝብ የሚያስመርሩ፣ በሙስና እስከ አንገታቸው ተዘፍቀው አገር የሚቦረቡሩ፣ ሕዝቡን ፍትሕ በማሳጣት የሚያስለቅሱና አገራዊ ራዕይ የሌላቸው ቦታ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ይህንን ታላቅ የአገር የአምስት ዓመት ዕቅድ ለማስፈጸም የተነሳ መንግሥት በፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ውስጥ የበላይነት የያዘውን የሙስናና የጥፋት ኃይል ማስቆም ካልቻለ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡ ይህ ኃይል ብቃት ያለው አስከፊ ተግባራትን ብቻ ለማሳካት በመሆኑ፣ ለአገር የሚጠቅመውን ዕቅድ ከመሠረቱ ይንደዋል፡፡ በብልሹ አሠራሮችና በሙስና የተበከለ በመሆኑ ለሕዝቡም ለአገርም እንቅፋት ነው፡፡ በዚህ ኃይል ላይ የበላይነት ማግኘት የሚቻለው፣ አገራቸውን በሙሉ ፈቃድ ለማገልገል ዕውቀት፣ ልምድ፣ ብቃትና ድፍረት ያላቸው ዜጎች በዕቅዱ ተፈጻሚነት ላይ ጉልህ ተሳትፎ ሲኖራቸው ነው፡፡ አሁንም የምንለው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የሚሳካው ብቃት ያላቸው ዜጎች ሲሳተፉበት ብቻ ነው!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...