Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበፌዴራል ተቋማት የሠራተኞች የብሔር ስብጥር የተመጣጠነ እንዲሆን ሊደረግ ነው

በፌዴራል ተቋማት የሠራተኞች የብሔር ስብጥር የተመጣጠነ እንዲሆን ሊደረግ ነው

ቀን:

– የፓርላማ አባሉ በገጠማቸው ጉርምርምታ ተቃውሟቸውን ገለጹ

በሁሉም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ የሠራተኞች ብቃትና ክህሎትን ባረጋገጠ መንገድ የተመጣጠነ የብሔር ስብጥር እንዲፈጠር እየተሠራ መሆኑን፣ በተገቢው የሕግ ማዕቀፍ እንዲደገፍም እንደሚያደርግ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ታኅሳስ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ፓርላማው በተወያየበት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው፣ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የፌዴራል ሥርዓቱን መምሰል እንዲችሉ የተመጣጠነ የብሔር ስብጥርን በተቋማቸው ውስጥ መፍጠር እንደሚገባቸው የተናገሩት፡፡

- Advertisement -

የተመጣጠነ የብሔር ስብጥር በፌዴራል ተቋማቱ ለመፍጠር ሲባል ሠራተኞችን በብቃትና በክህሎት መምረጥ መርህ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ መፍጠር እንደማይገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የብሔር ስብጥሩን ተግባራዊ ለማድረግ ጥናቶችንና ተሞክሮዎችን በመገምገም ላይ እንደሆነና ለትግበራውም ተገቢ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ወ/ሮ አስቴር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ያለውን ተሞክሮ ለመገምገም በተሞከረበት ወቅት፣ ብሔራዊ ባንክ ብቻ ሞዴል ሊሆን የሚችል ልምድ ይዞ እንደተገኘ፣ በባንኩ ውስጥ 37 ብሔሮችን የሚወክሉ ሠራተኞች በሥራ ላይ እንደሚገኙ በምሳሌነት አውስተዋል፡፡ ከብሔር ብሔረሰብ ስብጥር ውጪ የወጣቶችና የፆታ ስብጥር በየፌዴራል ተቋማቱ ተመጣጥኖ ሊቀመጥ እንደሚገባም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ተቋማት ሠራተኞች የብሔር ስጥርን አስመልክቶ እስካሁን በአገሪቱ ዝርዝር ሕጋዊ ማዕቀፍ ባይኖርም፣ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39(3) ላይ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ይኸው ሕገ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል ሲል በአንቀጽ 87 (1) ላይ ይደነግጋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዙሪያ ሐሳባቸውን እየሰነዘሩ በነበረበት ወቅት በገጠማቸው ጉርምርምታ ጥያቄያቸውን አቋርጠው፣ ‹‹ሐሳቤን የመግለጽ መብቴ እየተደፈጠጠ ነው፤›› ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ፓርላማው ውይይት እያደገ የነበረው በዕቅዱ ማኅበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች ማለትም በጤናና በትምህርት ላይ ቢሆንም እኝህ አባል ግን ጥያቄያቸውን ሰፋ አድርገው፣ ‹‹የውጭ አገር ጉዞ እየተባለ የውጭ ምንዛሪ እያወጡ ጥቅም የሌለው ጉዞ ማድረግ፣ ለትምህርት እየተባለ በገፍ እየወጡ መቅረት አባዜ በመሆኑ ገደብ ይደረግበት፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚይዟቸው ተሽከርካሪዎች ወጪ ገደብ ይደረግበት ብለዋል፡፡

‹‹እኔ ኮሪያ ሄጄ አላውቅም፡፡ ግን የኮሪያ ባለሥልጣናት ከከፍተኛ አመራሮች በስተቀር በሕዝብ ትራንስፖርት ነው የሚገለገሉት፤›› ሲሉ ከምክር ቤቱ አባላት ጉርምርምታ ገጥሟቸዋል፡፡

ጉርምርምታውን ለማስቆምም፣ ‹‹ሐሳቤን ልጨርስበት! ይኼ ቤት ዴሞክራሲያዊ ነው ይባላል፡፡ ግን ሐሳብ የሚደፈጠጥበት እየሆነ ነው፤›› በማለት ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው የፓርላማ አባሉ ሐሳባቸውን የመግለጽ መብት እንዳላቸው፣ ነገር ግን በቦታው ሊሆን እንደሚገባ ያለበለዚያ ግን ነፋስ የሚወስደው ሐሳብ ወይም የሚመለከተው ባለቤት የማያዳምጠው ሐሳብ ይሆናል በማለት መልሰውላቸዋል፡፡ በቅርቡ የፓርላማ የኢሕአዴግ የፓርላማ አባላት በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከፓርቲው አቋም መለየት እንደማይችሉ፣ ይህንን ማድረግ ከፈለጉ ከፓርቲው መልቀቅ እንዳለባቸው በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ መግለጻቸውን ማስነበባችን ይታወሳል፡፡   

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...