Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚዎችና የወጣት ሊግ አመራሮች ታሰሩ

የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚዎችና የወጣት ሊግ አመራሮች ታሰሩ

ቀን:

– ሰማያዊ ፓርቲም አባሎቹ መታሰራቸውን አስታውቋል

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሁለት ሥራ አስፈጻሚዎችና ስድስት የወጣት ሊግ አመራሮቹ ታኅሳስ 14 እና 15 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደታሰሩበት ገለጸ፡፡

የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነገአ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሌላ የወንጀል ክስ ከአራት ዓመታት በላይ የእስር ቅጣት ተወስኖባቸውና የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ከተፈቱ ስድስት ወራት የሆናቸው፣ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና ምክትል ዋና ጸሐፊው አቶ ደጀኔ ጣፋ ታስረዋል፡፡

- Advertisement -

ከወጣት ሊግ አመራሮች ደግሞ፣ የኦፌኮ ወጣት ሊግ ሊቀመንበርና የመድረክ ወጣቶች ሊቀመንበር የሕግ ባለሙያው አቶ ደስታ ዲንቃ፣ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጉርሜሳ አያና፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ ቡላ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ደረጀ መርጋ፣ የድርጅቱ ኦዲተር አቶ አለሙ አብዲሳና የአባታቸው ስም ያልተገለጸው አቶ ታሪኩ መታሰራቸውን ዋና ጸሐፊው አረጋግጠዋል፡፡

የፖለቲካ አመራሮቹ የታሰሩት ያለምንም ጥፋት የኢሕአዴግን አካሄድና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን በደልና ግድያ አምርረው በመቃወማቸው መሆኑን አቶ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ለኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚዎችና ለወጣት ሊግ አመራሮች መታሰር ዋናው ምክንያት፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በክልሉ ተወላጆች ተቃውሞ ገጥሞት የነበረው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ላለፉት አምስት ሳምንታት የተካሄደው ተቃውሞ መሆኑን አቶ በቀለ አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩ መፈታት ያለበት በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ኦፌኮ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማሳወቁንም ተናግረዋል፡፡

የአገር ጉዳት ወይም ችግር የሚፈታው በግድያ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት መሆኑን በመግለጽ፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰሞኑ ግጭት ድረስ ለፓርላማው፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለክልሉ መንግሥትና ለሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለድርሻ አካላት ደብዳቤ ማስገባታቸውን አቶ በቀለ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የጦር መሣሪያ የላቸውም፡፡ ምን ያመጣሉ ብለው መሰለኝ ምንም ምላሽ አልሰጡንም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቀደም ብለን ባስገባነው የእንወያይ፣ የእንመካከር ደብዳቤ መሠረት ውይይቱ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ የሰው ሕይወት ላይጠፋ ይችል ነበር፤›› ያሉት አቶ በቀለ፣ ባለፉት ሳምንታት የተቃውሞ ሠልፍ በተደረገባቸው በሁሉም አካባቢዎች በድምሩ የ86 ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አቶ በቀለ ገለጻ፣ የታሰሩት እነ አቶ በቀለ ገርባ ብቻ ሳይሆኑ፣ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች እየታሰሩ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር 4,000 የሚደርስ ሲሆን፣ 500 ያህሉ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚገኙ የኦፌኮ አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከፍተኛና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር 1,500 አካባቢ መድረሱን የጠቆሙት አቶ በቀለ፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስ፣ በዳግማዊ ምንሊክ፣ ወሊሶ በሚገኘው ቅዱስ ሉቃስ ሆስፒታሎችና በተለያዩ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ሆስፒታሎች በመታከም ላይ እንደሚገኙ አቶ በቀለ አስረድተዋል፡፡

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የወጣት ሊግ አመራሮች የታሰሩት፣ በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መሆኑንና ሌሎች የኮንግረሱ አባላትና በረብሻው የተጠረጠሩ ወገኖች ክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶችም መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው አለመግባባት ሕይወታቸው በጠፉ ወገኖችና በወደመው ንብረት ማዘናቸውን የገለጹት አቶ በቀለ፣ ለአገሪቱም ሆነ ለገዢው መንግሥት የሚጠቅመው ጠብመንጃ አንስቶ ንፁኃንን መግደል ሳይሆን፣ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታት በመሆኑ ይህንኑ እንዲተገብር የኦፌኮ ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ግጭት የጠፋውን ሕይወት ብዛትና የንብረት ውድመት መጠን አስመልክቶ በተደጋጋሚ የተጠየቁት የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥታት፣ በቁጥር ጉዳይ ላይ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርላማ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፌርሜሽን ዕቅድ ያስፀደቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በተመሳሳይ ዘለውታል፡፡ ባለፈው ሳምንት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፍት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳም፣ ‹‹የቁጥር እንካ ሰላንትያ ውስጥ አንገባም፤›› በማለት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት መታቀባቸው ይታወሳል፡፡

ይሁንና የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊዎች ለግጭቱ ተጠያቂ በሆኑ አካላት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ግን ገልጸው ነበር፡፡ ከሕዝቡ ተገቢ ጥያቄ በስተጀርባ የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት ግጭቱን ያባባሱ አካላት መኖራቸው እንደሚታወቅ፣ ከእነዚህም አንዱ ኦፌኮ መሆኑን አቶ ጌታቸው ጠቅሰው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዓርብ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ የሕዝቡን ሰላማዊና ሕጋዊ የግልጽነት ጥያቄ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የመሩት ፀረ ሰላም ኃይሎች እንደሆኑ አስታውቀው፣ እነዚህ ኃይሎች ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለዋል፡፡ ‹‹ድብቅ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የተንቀሳቀሱ ኃይሎች በሕጋዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ሰርገው በመግባት የሕዝቡን ጥያቄ ለመጠምዘዝ የተንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎች መኖራቸውን መንግሥት በመረጃ አረጋግጧል፤›› ብለው፣ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ ሁለት አባላትና የፓርቲው ልሳን የሆነው ‹‹ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ›› ዋና አዘጋጅ፣ ባልታወቀ ምክንያት በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ንጋት ላይ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ማዕከላዊ የተወሰዱት የፓርቲው አባላት አቶ ቴዎድሮስ አስፋውና አቶ ዳንኤል ተስፋዬ፣ እንዲሁም የፓርቲው ልሳን ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው መሆናቸውን ሊቀመንበሩ አረጋግጠዋል፡፡ የፓርቲው አባላት አቶ ቴዎድሮስና አቶ ዳንኤል፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ተደርጎ በነበረው አይኤስን የማውገዝ ሠልፍ ላይ ከተፈጠረ ረብሻ ጋር በተገናኘ ታስረው ሁለት ወራትና ሦስት ወራት ተፈርዶባቸው ከመፈታታቸው በስተቀር ምንም የፈጸሙት ድርጊት እንደሌለ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከመንግሥትነት አልፎ በዜጎች ላይ እያደረገው ያለው ያልተገባ ድርጊት ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው የሚመጣውን እየተጋፈጡ በሰላማዊ መንገድ መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...