አውራሪስ ከታላላቆቹ አጥቢ እንስሳት መሀል ይመደባል፡፡ በብዛት በአፍሪካና በእስያ ታወቂ የሆነው ይህ እንስሳ በዓለም ላይ አምስት ዝርያዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ከእነዚህ አምስት ዝርያዎች ሦስቱ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ለቀንዳቸው ሲባል የሚታደኑት የአውራሪስ ዝርያዎች የሕገወጥ አዳኞች ሰለባም እየሆኑ ነው፡፡ ከአፍሪካ ዝሆን ቀጥሎ ትልቁ የምድራችን ግዙፍ እንስሳ የሆነው አውራሪስ እስከ 1.5 ቶን ክብደት አለው፡፡ ጠንካራ ቆዳውም 1.5 ሳንቲ ሜትር ውፍረት ሲኖረው፣ በግንባሩ መሀል ረጅም ቀንድ አለ፡፡ አውራሪስ ሳር፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የአትክልት እምቡጥና ፍራፍሬ ይመገባል፡፡ በአማካይ 60 ዓመት እንደሚኖርም ይነገራል፡፡