Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከስደት ተመላሾችን ለመታደግ

ከስደት ተመላሾችን ለመታደግ

ቀን:

ኤልሳ ተክላይ ተወልዳ ያደገችው ጎንደር ከተማ ሲሆን፣ የምትኖረውም ከቤተሰቦቿ ጋር ነው፡፡ የአሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ብትወስድም ውጤት ስላልመጣላት፣ የትውልድ ቀዬዋን ለቃ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር የሄደችው፡፡ ይሁን እንጂ ኤልሳ ብዙ አልማ የሄደችለት ሕይወት እንደጠበቀችው አልሆነላትም፡፡

ኤልሳ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የገባችው አዲስ አበባ ከሚገኘው አንድ ኢትዮጵያዊ ደላላ የመኖሪያ ፈቃድ በ15 ሺሕ የሳዑዲ ዓረቢያ ሪያል ከገዛች በኋላ ነው፡፡ ይኼንንም ያደረገችው ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በነፃነት ለመንቀሳቀስ፣ የፈለገችበት ቦታ እየተዘዋወረች ለመሥራት እንዲያመቻት ነበር፡፡

ይሁንና ሳዑዲ ዓረቢያ እንደደረሰች ነበር በ15 ሺሕ ሪያል የገዛችው የመኖሪያ ፈቃዱ ተቀባይነት እንደሌለው የተረዳችው፡፡ መውጣት መግባት የማትችል ግዞተኛ ሆና በአንድ ቤት ውስጥ ብቻ ተቀጥራ ለመሥራት ተገደደች፡፡

አገሯ ላይ ለደላላ ያን ያህል ገንዘብ መክፈሉ ሳያንሳት፣ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኘውና ከአሠሪዋ ጋር የሚያገናኘት ሌላው ኢትዮጵያዊ ደላላ ደግሞ የሁለት ዓመት ደመወዟን ሳትወስድ ወስጃለሁ ብላ እንድትፈርም አድርጓታል፡፡

በዚህ መንገድ ደላላው ለሁለት ዓመት ያህል ያለምንም ክፍያ ጉልበቷን አስበዝብዟል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ደላላውን ብትጠይቅም፣ ‹‹እኔ ባልኩሽ ዝም ብለሽ ለምን አትሠሪም?›› ብሎ በቦክስ መቷት ጥርሷን እንዳወለቀው ትናገራለች፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ብዙ ከተቸገረች በኋላ ወደ አገራችሁ ግቡ ሲባል ምንም ቅርስ ሳትይዝ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰች፣ አዲስ አበባ እንደገባችም ጎንደር ከቤተሰቦቿ ጋር ልትቀላቀል የቻለችው እናቷ በላኩላት የትራንስፖርት ገንዘብ እንደሆነ ገልጻለች፡፡

ኤልሳ እስካሁን ሥራ አላገኘችም፣ የሥራ ዕድል እንዲያመቻቹላት፣ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉላት የምትኖርበትን ቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ደጋግማ ብትጠይቅም፣ ዛሬ ነገ እያሉ ከማመላለስ በስተቀር ምንም ያልፈየዱላት መሆኑን ገልጻለች፡፡

‹‹ሥራ የማግኘት ተስፋዬ የጣልኩት በኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ነው፡፡ ከፌዴሬሽኑ በስተቀር አንድም አካል አልተመለከተኝም፡፡ የዓረብ አገር ተመላሾች ብዙ ጊዜ አይታዩም፡፡ ጮክ ብለን ብንናገር እንደ እብድ ነው የሚያስቡን፡፡ ፌዴሬሽኑ ግን ሊሰበስበን በመቻሉ በጣም ደስ ብሎኛል፤›› ብላለች፡፡

የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱ አቶ ፍትሕ ወልደሰንበት፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ለተመለሱ ከ200 በላይ ወገኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል ቃል ገብቶ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ የገባውን ቃል ለመፈጸምም ተመላሾችን በተለያዩ የሆቴል ማሠልጠኛ ተቋማት በቂ የሆነ ሥልጠና እንዲያገኙ ከሰሞኑ ፕሮግራም ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ዕውን መሆንም ከዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) በተገኘው ድጋፍ፣ የሥራ ዕድሎች እንዲመቻቹ ለማድረግና አሠሪዎችንም ለማብቃት የሚያስችል የሦስት ቀናት ሥልጠና መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናውም ላይ ከስደት ተመላሾችን ማቋቋሚያ መርሐ ግብር፣ የኢንተርፕራይዞች ዕድገትና የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሆቴል አመራር ጽንሰ ሐሳብ፣ የሆቴል ገበያ ትስስር፣ የደንበኛ አያያዝና ጥራት ቁጥጥር ላይ ትኩረት ያደረገ ትምህርት መስጠቱን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የአሠሪና ሠራተኞች ጉዳይ አዋጅ መሠረታዊ ሐሳቦች፣ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት እንዲሁም ማኅበራዊ ምክክር ላይ ትኩረት ያደረገ ትምህርታዊ ገለጻ ተደርጓል፡፡

የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) ተወካይዋ ወይዘሮ አይዳ አወል እስከዛሬ ድረስ ከ17 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተመላሾች የሥራ ፈጠራ ሥልጠና እንደተሰጣቸው፣ በዚህም ሥልጠና ላይ ወደ 200 የሚጠጉ የቴክኒክና ሙያ ላይ ያተኮሩ ትምህርትና ሥልጠና እንዲሰጥ መደረጉንና ለዚህም የአውሮፓ ኅብረት የ60 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ 2,000 የሚሆኑ ተመላሾች የደመወዝ ቅጥረኛ ሲሆኑ፣ 2,500 ተመላሾች ደግሞ የራሳቸውን ቢዝነስ ማቋቋቸውን ተወካይዋ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...