Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተሹሞ ያልሠራ ሲሻር እንዳይፀፅተው!

ሰላም! ሰላም! ወዳጆቼ እኔ እንደሆነ በየትኛውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና ምርጫ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞና ቅሬታ እንደሌለኝ ልብ በሉልኝ፡፡ በእርግጥ በርካቶች ‘ጉልቻ ቢቀያየር…’ ቢሉም እኔ ግን አልስማማም፡፡ እስቲ ጊዜ እንስጣቸውና የሚፈጥሩልንን ለውጥ ለማየት እንታገስ፡፡ ውይ ይቅርታ ሰላምታዬን ዘንግቼው? እንደምን ከርማችሁልኛል? እኔ በጣም ደህና ነኝ፡፡

ዘመኑ የደላላ ነው፡፡ ስንቱ ዓይኑ እስኪሞጨሙጭ አንብቦ ያገኘውን የመጀመሪያ ዲግሪና ማስተርስ አሽቀንጥሮ እየጣለ ወደ ድለላው እየገባ ነው፡፡ በእርግጥ ለእኛ ዙሩ ትንሽ ከረር ቢልብንም እጅ አንሰጥም፡፡ ምናልባት ሌላው ተምረውና ተመራምረው ወደ ድለላው ዓለም ከገቡት ሰዎች ጋር ተፎካክሮ መቀጠል ቢያቅተውና የደላላነት ዘመኑ ቢገባድድ እንኳን፣ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የደላላነት ዘመኔ በምንም የማይገታ የደላሎች ቁንጮ፣ የደላሎች አውራ ነኝ፡፡ የማሻሽጠው አጥቼ የማላውቅ እኮ ነኝ፡፡ ቤቶች፣ ሕንፃዎች፣ መኪኖች ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ብቻ ይሽጠን እያሉ ሰላማዊ ሠልፍ የወጡልኝ የዘመኑ ምርጥ ደላላ ነኝ፡፡

ደግሞ በዚሁ ምርጥ ዘመን ላይ በመገኘቴ የሚሰማኝ ደስታና ኩራት ታላቅ  ነው፡፡ ይህንን ዘመን ያው ባሻዬ፣ ‹‹የዘመን ማኛ›› ብለውታል፡፡ ዘመን ሰመረ የሚባለው ከሰማይ ብር መዝነብ የጀመረበት ወቅት ላይ አይደለም፡፡ ይልቁንም አየሩ ላይ የነገሠ ውጥረት ረግቦ፣ ነጋዴው ነግዶ፣ ተማሪው ተምሮ፣ ደላላውም ደልሎ በሰላም የሚገባበት ዘመን ሲፈጠር ነው፡፡

አሁንማ ይኸው ከአዲስ አበባ ወጥቼ ሐዋሳ ድረስ እየሄድኩ፣ ጎንደር ድረስ እየዘለቅሁ፣ አምቦ ድረስ እየሰረፅሁ፣ ጋምቤላ ድረስ እየነጎድኩ መሬት ነሽ መኪና እዚህ መሀል አዲስ አበባ ቁጭ ብዬ የምሠራውን ሥራ ሁሉ እያቀላጠፍኩ እገኛለሁ፡፡ ወዳጆቼ ዘመኑ የኢትዮጵያም አይደል እንዴ? እንግዲህ እግዜሩ ያሳያችሁ ዓለም አንድ መንደር ናት እየተባለ በሚነገርበት ዘመን፣ መቼም ኢትዮጵያን የዚህ የአዲሱ መንደር ተብሎ የተሰየመው የዓለም ካርታ ውስጥ ቢካተት ኢትዮጵያዬ አንዲት ሳሎን ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ የላትም ብሎ የባሻዬ ልጅ የነገረኝን አልረሳውም፡፡ እርሱ እንዲህ ብሎ ነበር ያስቀመጠው፣ ‹‹ዓለም አንዲት መንደር ከሆነች ኢትዮጵያዬ እዚህ መንደር ውሰጥ ስትገባ እንደ ሳሎን ሆና ልትቀመጥ ብትችል ነው፤›› ሲለኝ አፌን ከፍቼ ነበር ሳደምጠው የነበረው፡፡

ታዲያ ዓለም ጠባ መንደር ስትሆን ቢቻለኝ ከኢትዮጵያም ወጣ ወጣ እያልኩ ዓለም አቀፍ የድለላ መረብ ውስጥ መግባት ነው እንጂ፣ የምን አስተሳሰብን መገደብ ነው? ወዳጆቼ የእኔ ሐሳብ በዓለም ላይ አለ የሚባል ድንቅ ደላላ መሆን ነው፡፡ ግን ያው ትንሽ ዶላር ቢጤ እንደሚያስፈልገኝ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ መቼም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባለሀብቶቻችንን በጠየቁት መሠረት በቻይና እና በዱባይ ካከማቹት የዶላር ተራራ ላይ በመጠኑም ቢሆን ናድ ናድ አድርገው ካመጡልን፣ እኛም ወደ ዓለም አቀፋዊነት ለምናደርገው ጉዞ እንደ መወጣጫ ከበሌቶ ይጠቅመናል፡፡

በዓለም አቀፋዊነት አስተሳሰብ ተጠምቄ ዶላር በብዛት የማገኝበትን መንገድ እየናፈቅኩ ነው፡፡ እንግዲህ እዚያ የምናውቀው አካባቢ ያሉ የጥቁር ገበያ ዶላር መመንዘሪያዎች በጠቅላይ ሚኒስትራችን ዕይታ ሥር ወድቀዋል፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ‘ዶላር’ ለመዘርዘር ብቅ ሳይሉ አይቀሩም፤›› እያለ ሲያስቀኝ ነበር፡፡ እግዜሩ ያሳያችሁ የባሻዬ ልጅ ያለው እውነት ከሆነ የጉዳዩ አሳሳቢነት ጣሪያ ነካ ማለት ነው፡፡ ባሻዬ እንዳሉት፣ ‹‹በመጀመርያ ዶላርን በተመለከተ ያለው የመንግሥት አሠራር መጥራት ይኖርበታል፡፡ ሁሉም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅኝት ካልተቃኙ በስተቀር፣ ይህንን ችግር የተወሰኑ ሱቆችን በመዝጋት እገታለሁ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፤›› በማለት ሥጋታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡

ታዲያ ዓለም አቀፋዊነቴን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና በምልበት በዚህ ሰናይ ዘመን ላይ፣ ማነው ጀግና በኢትዮጵያ ርዝመትና ስፋት አትደልል የሚለኝ? ማነው የአንተ ክልል ይኼ ነው ከዚህ ማለፍ አትችልም ብሎ አጥር የሚያበጅልኝ? የትም አገሬ ነው! የትም ቤቴ ነው! እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራ፣ በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውሬ የምሠራ፣ ዕብድ ያልኩ የደላላ ቁንጮ ነኝ፡፡

ወዳጆቼ ነጋዴዎች እንዴት ከርማችኋል? የዶላሯን ነገር ግን አደራ፡፡ እዚህ ይዛችሁት ከች በሉ፡፡ በቃ ለእኛ ይድረሰን፡፡ እኔ መቼም ዶላሩን የምፈልገው ከዱባይ ቴሌቪዥን ወይም ከታይላንድ ጨርቃ ጨርቅ ሰብስቤ ልመጣበት አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በርካታ ሰዎች የተፈጠረላቸውን ከቀረጥ ነፃ ዕድል ተጠቅመው የቴሌቪዥን ዓይነት ይዘው እየገቡ ይገኛሉ፡፡

እኔስ ምኔ ሞኝ? ውዷ ባለቤቴን አስደመምኳት፡፡ ለሥራ ዱባይ ወጣ ባልኩበት አንደኛውን የቤታችን ግድግዳ ሊያህል ትንሽ የቀረውን ቴሌቪዥን ይዤላት መጣሁ፡፡ ይኸው አሁን በ55 ኢንች ቴሌቪዥን ዓለምን ከቤታችን ሆነን እየኮመኮምን ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትራችንንም የሚኒስትሮች ምርጫ የተከታተልኩት አዲስ በገዛሁት ቴሌቪዥን ነው፡፡ እኔ ‘ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ’ ልለው አልደፍርም፡፡ ይልቁንም አዲስ የብልፅግና፣ የሥራና የፍትሕን ዘመን የሚያበስሩበትን መንገድ እንደየቀሱ ነው የማስተውለው፡፡ ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረጧቸው ሚኒስትሮች በተባለው ቦታ ካላገኟቸው መቼም ተጠያቂነታቸው እንደሚበረታባቸው እጠረጥራለሁ፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቀበሌ ተወካዮች ሕዝብን ያማከለ መልካም አስተዳደር ከጠበቁ፣ ከእነዚህኞቹማ የበለጠ እንደሚጠብቁ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ብቻ አዲሷ ቴሌቪዥናችን ጥሩ ነገር እያሳየችኝ ነው፡፡

በእርግጥ የዶላር እጥረት ባያጋጥመኝ ኖሮ ሌሎች በርካታ ነገሮችን ለማምጣት አስቤ ነበር፡፡ ወዳጆቼ ይህንን ስል መቼም ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የሥራ ለውጥ አደረገ እንደማትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እኔ ዛሬም ድንቅ ደላላ ነኝ፡፡ ያው አለ አይደል የእግረ መንገድ ዓይነት ቢዝነስ ነው፡፡ እንጂማ የሄድኩበትን የመኪኖች ጉዳይ መግደሌን ልብ በሉልኝ፡፡

ብቻ አሁንም በመላው የኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ቢሮዎችን ከፍቼ ሥራዬን ማድራት እፈልጋለሁ፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እቤት የመክረም ዘመን አክትሞለታል፤›› ባለኝ መሠረት እኔም እየተሯሯጥኩ እገኛለሁ፡፡ የባሻዬ ልጅ በርካታ የሕይወት ሐሳቦችን ሲያቀብለኝ እኔም ዓይኔን ሳላሽ ሥጋ አለብሳቸዋለሁ፡፡ ታዲያ እሱ ባለኝ መሠረት ቤቱን ለማንጠግቦሽ ትቼላት ወጣ ወጣ ማለት ጀምሬያለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ፣ ከሐዋሳ ጎንደር፣ ከጎንደር መቐለ፣ ከመቐለ አዳማ፣ ከአዳማ ጋምቤላ እነዚህ አዲስ የንግድ መስመሮቼ ናቸው፡፡ በዚህም ብቻ አልተገደበም፡፡ ናይሮቢ፣ ዱባይ ነሽ ታይላንድ ጉዞ ወደ ዓለም ሁሉ ሆኖልኛለ፡፡

ባሻዬ ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› በማለት የነገሩኝ አባባል አሁን ሕይወቴ ላይ እየተፈጸመ ነው፡፡ ታዲያ ወዳጆቼ ይህንን ልብ ይበሉልኝ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የትም ዞሬ ዞሬ ማታ ወደ አገሬ እንደማዘግም፡፡ ደላላው በዚህ አካሄዱ የአሜሪካ ቪዛ ቢያገኝ በዚያው ጠፍቶ ይቀራል የሚል ሰው ካለ ያ ሰው ዘጠኝ ጊዜ የአሜሪካን ቪዛ የተከለከለ፣ አሜሪካ ሄዶ ለመጥፋት ያሰበ ምስኪን ነው ብዬ ሳልፈልግ እፈርዳለሁ፡፡ ዳሩ ግን መቼም ‘ዲሲንም አየነው…’ ብዬ ዛሬ ላይ ማንጎራጎር ባልችልም፣ እንዲሁ በግጥሙ ላይ ትንሽ ማሟሻ ቢጤ አድርጌ

‘ዲሲኒም አይቼው ከእግር እስከ ራሱ

አትላንታን አይቼው ከእግር እስከ ራሱ

ሁሉንም አይቼው ከእግር እስከ ራሱ

መቼም ደስ የሚለው፣

ዶላሩን አፋፍሰው፣

ሥራዎን ጨርሰው

ካገር ሲመለሱ፡፡’

ብዬ አሻሽያለሁ፡፡ እንግዲህ የሚያምን ይመን፣ የማያምን ግን ምን ይደረጋል? ያው ዱባይ ስሄድ አይመለስም ብለው ያሰቡ በርካታ ደላሎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም እምዬ አሜሪካ ቪዛዬን ከሰጠችኝ ብቻዬን እንደማልመለስ ቃል እገባለሁ፡፡ በርካታ ምሁራን ኢትዮጵያውያንን አሳምኜ እንደምመጣ ቃል እገባለሁ፡፡ መቼም ‘ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል’ የሚለው አስተሳሰብ ያከተመለት ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም ባሻዬ፣ ‹‹ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይፀፀታል›› ሲሉ ነበር፡፡ ባሻዬ ልክ ብለዋል፡፡ እኔም አዲስ ለተመረጡ ሚኒስትሮች መልካም የሥራ ዘመን እየተመኘሁ እዚህ ላይ ልሰናበት፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት