Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለጎዳና ልጆች ያልተዳረሰ ፈውስ

ለጎዳና ልጆች ያልተዳረሰ ፈውስ

ቀን:

ቀን ወዲህ ወዲያ በማለት የዛለ ጎናቸውን የሚያሳርፉበት ማደሪያ ለሌላቸው እንደ ስንታየሁ ትዕዛዙ ላሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች አልጋቸው በረንዳ፣ ትራሳቸው ደግሞ ድንጋይ ነው፡፡ ከብርድ የሚከላከላቸው የሚከናነቡት ነገር ባይኖርም በራሳቸው ግን አደገኛ በሆነ መንገድ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንዲወሰዳቸው ያደርጋሉ፡፡ በሹራባቸው ደብቀው የሚይዙትን ማስቲሽ እንደሳቡ ራሳቸውን ስተው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል፡፡

     በዚያ ሰዓት እንኳንስ ብርድና ረሀብ ሌላም ነገር ቢደረጉ አይሰማቸውም፣ ራሳቸውንም አያውቁም፡፡ ይህ አሳዛኝ እውነታ ከማንም ያልተደበቀ የጎዳና ተዳዳሪዎች ገፅታ ነው፡፡ እነሱ እንደ እንቅልፍና ዕረፍት የሚቆጥሩት ራሳቸውን በሚስቱበት አጋጣሚ ብዙ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

     እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ነበር ስንታየሁ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ የነበረውን አጋጣሚ ያስተናገደው፡፡ ለእንቅልፍ ብሎ በአፍንጫው የሳበው ማስትሽ በማስተኛት ፋንታ ወዲህ ወዲያ ሲያደርገው እንደነበር የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ራሱን ያገኘው በደም ርሶ ነበር፡፡ እግሩ፣ እጁ፣ በተለይም አንገቱ በተደጋጋሚ ጊዜ በስለት ተቆርጧል፡፡ ጉሮሮው አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ ተቆርጦ ስለነበር የተረፈው በተዓምር ነው፡፡ እንዴትና በምን ዓይነት አጋጣሚ ይህንን በራሱ ላይ ሊያደርግ እንደቻለ በውል አያውቅም፡፡ ወደ ራሱ የተመለሰውም በሞትና ሕይወት መካከል ካለፈ በኋላ ነው፡፡

     ‹‹ማስትሽ የምንስበው ለብርድ ብለን ነው፡፡ ስንስብ ግን ራሳችንን ስለምንስትና የምናደርገውን ስለማናውቅ ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚያ አጋጣሚ ነው እኔም ራሴን የቆራረጥኩት፤›› አለ ገና በ18 ዓመቱ የጎዳና ሕይወቱ ብዙ ያሳየው ስንታየሁ እንዳቀረቀረ፡፡ መላ ሰውነቱ አገሩን ከጠላት ሲከላከል እንደኖረ ጦረኛ ጠባሳ የበዛበት ነው፡፡ አንገቱ አካባቢ ያሉት ተደራራቢ ጠባሳዎች ደግሞ ከሞት የተመለሰ የዶክተር ፍራንክ አንስታይን ፍጡር አስመስሎታል፡፡ ብርድና ፀሐይ የተፈራረቀበት ጠይም ገፁ ከስሏል፡፡ ውኃ ነክቶት የማያውቅ ልብስና ገላው አድፏል፡፡ በአጠቃላይ ገጽታው ወጣቱ የሚኖርበትን መከራ የበዛት ሕይወት ቁልጭ አድርጎ ያንፀባርቃል፡፡

     ሲያዩት ኃይለኛ ይምሰል እንጂ ሲያወራ አንገቱን ደፍቶ በዝግታ ነው፡፡ የተሞነጫጨረ ፊቱ ተደባዳቢ ቢያስመስለውም፣ አልፈው ተርፈው መስመሩን ካልተጋፉ በስተቀር ማንንም አይነካም፡፡ ከእሱ የተሻሉ ከሚመስሉ ሰዎች ጋር በአንድ ወንበር እኩል መቀመጥ ይከብደዋል፣ ያቀለላቸውም ይመስለዋል፡፡ ቀርበው ያናገሩትን ውለታ የዋሉለት ያህል ያከብራቸዋል፡፡ አይዞህ ሲሉት በአራድኛ  አገላለጽ  አንገቱን ደፍቶ ‹‹ቴንኪው ጀለሴ፤›› ይላል፡፡ ፈራ ተባ እያለና ፈገግታው እየቀደመው ቀልድ ይጀምርና ከምንም እንደማይቆጥሩት ሲገባው፣ የማይሆን ነገር እንደሆነ ገምቶ መልሶ አንገቱን ይደፋል፡፡

     የስንታየሁና የመሰሎቹ የጎዳና ሕይወት በሥጋት የተሸበበና አደጋ የበዛበት ነው፡፡ የመጥፎ አጋጣሚ ተምሳሌት የሚያደርጋቸው ማኅበረሰቡ ከሌላ ፕላኔት የመጡ ያህል ሲያገላቸው፣ ችግር ገፍቷቸው ጎዳና ስለወጡ ብቻ እንደ ሌባ ሲያባርራቸው ይታያል፡፡ ጎዳና የወጡበትን አጋጣሚ ሳያውቁ ስንቶች ያንቋሽሿቸዋል፡፡ በጎዳና ሕይወት የሚያጋጥማቸው ከባድና አስከፊ ገጠመኞች መኖራቸውን የሚረዱ፣ እንደ ሰው እንደሚከፋቸው፣ ቀዝቃዛ አየር እንደሚበርዳቸው፣ ዱላ እንደሚያማቸው የሚረዱ ከስንት አንድ ናቸው፡፡ ቀርቦ ለማናገር የሚጠየፋቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ገና ከርቀት ሲያያቸው ስልኬን ብሎ ኪሱን የማይፈትሽ፣ ቦርሳውን ጠበቅ የማያደርግ የለም፡፡  አጭበርባሪ ሌባ ናቸው የሚለው አስተሳሰብም ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡  ተጎጂ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሊኖር ቢችልም፣ ጎዳና ተዳዳሪ መሆናቸው ብቻ ወንጀለኛና ጥፋተኛ ስለሚያደርጋቸው የሚተባበርባቸውና ዱላ የሚመዝባቸው ይበዛል፡፡

     በስንታየሁም ላይ ከቀናት በፊት  ተመሳሳይ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ‹‹አንዳንዴ በቀን እስከ 200 ብር ድረስ እንሸቅላለን፡፡ ቁርስ ምሳ በልተን ከተረፈን በረንዳ 20 ብር ከፍለን በጋራ ማደሪያ ክፍሎች እናድራለን፤›› የሚለው ስንታየሁ መሰል አገልግሎቶችን የሚሰጡ ማደሪያ ቤቶች ከስቴዲየም በስተጀርባ እንደሚገኙ ይናገራል፡፡ በእነዚህ ማደሪያዎች ማደራቸው ግን ለደኅንነታቸው ዋስትና አይሰጥም፡፡

     ስንታየሁ አንድ ጠጥቶ ሞቅ ካለው ሰውዬ ጋር የተጋጨው ወደ ማደሪያው እያቀና ሳለ ነበር፡፡ ‹‹ድንገት ዘሎ ያዘኝና መደባደብ ጀመርን፡፡ ከዚያም በምላጭ ቆረጠኝ፤›› አለ በሹራቡ ደብቆ የያዘውን ቁስሉን ገልጦ እያሳየ፡፡ በምላጭ የተቆረጠው ገላው እንደቦይ ተከፍቶና መግል ይዞ ሲታይ፣ በምላጭ ሳይሆን በቢላዋ የተቆረጠ ነው የሚመስለው፡፡ ቁስሉን ወዲያው ስላልታከመው ኢንፌክሽን ፈጥሯል፡፡ እስከ ጣቶቹ ድረስ አብጦ የሚጠዘጥዘው ቢሆንም፣ ስንታየሁ ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ በሹራቡ ሸፈን አድርጎት ይጫወታል፤ የሚወደው ሙዚቃ ሲመጣ ይጨፍራል፡፡

     እንደ ምግብና መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማግኘት ጣር የሆነባቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ እንዲህ ባለው አጋጣሚ በሚከሰትባቸው አደጋ በተጨማሪ ለተለያዩ በሽታዎችም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን የዕለት ጉርሳቸውን ፍለጋ ምፅዋት ሲያሳድዱ ጊዜ ስለማይበቃቸውና ክፈሉ የሚባሉትን የሕክምና ወጪ መሸፈን ስለማይችሉ፣ ሕመማቸውን ችለው መንቀሳቀስ ይመርጣሉ፡፡ ወደ ሕክምና የሚሮጡት በድንገተኛ አደጋ በሞትና ሕይወት መካከል ሲሆኑ፣ ብዙ ጊዜም በስለት ተወግተው አልያም በሌላ አጋጣሚ በደረሰባቸው አደጋ ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸውና ደማቸው አልቆም ሲል ነው፡፡

     በስንታየሁ ላይ የደረሰው ዓይነት አደጋ ቀላልና በጊዜ ሒደት የሚድን እስከሆነ ድረስ ብዙም የማያስጨንቅ ነው፡፡ ስንታየሁ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገ ኢንፌክሽን ፈጥሮ ሕይወቱን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚለው ጉዳይ ሳይሆን፣ የዳቦ መግዣ መሸቀል ነው፡፡ ማንኛውንም የጤና እክል ታክሞ የመዳን ባህሉ ባልዳበረበት ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ ስንታየሁ ላሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ወዲያው የሚገድላቸው አደጋ እስካላጋጠማቸው ድረስ ወደ ሕክምና መሄድ የማይታሰብ፣ ከአኗኗራቸው ጋር ትልቅ ተቃርኖ ያለው ቅብጠትና በከንቱ ጊዜ የማጥፋት ያህል ነው፡፡

     እሁድ ሚያዚያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ከሚሠራው አራዳ ኬር ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ በነበረው የጎዳና ተዳዳሪዎች ነፃ የሕክምና ፕሮግራም ላይ ወደ 200 የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ለዓመታት የቆየባቸውን ሕመም ሊታከሙ የመጡ ሲሆን፣ ጊዜ የማጥፋት ያህል የሚሰማቸው እንደ ስንታየሁ ያሉት ደግሞ ልብስ እንደሚሰጥ፣ የምሳ ፕሮግራምም እንዳለ ሰምተው ነበር በቅጥሩ የተገኙት፡፡

     አብዛኞቹ የታከሙ ሲሆን፣ ምሳ በልተው ብቻ እንደታከሙ አስመስለው ጥፍራቸውን ጂቢ አስነክተው የወጡም ነበሩ፡፡ ሕክምናውን ፈልገው ከታከሙት መካከል ግን ሶፊያ ኸይረዲን አንዷ ነች፡፡ የ18 ዓመቷ ሶፊያ ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ በልጅነቷ የልጅ እናት ሆናለች፡፡ ትውልድና ዕድገቷ አዳማ ከተማ ላይ ቢሆንም ከወላጆቿ ጋር ባለመስማማት ወደ ጎዳና ከወጣች አምስት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ አንድ ጎዳና ላይ ከምታውቀው ወጣት ጋር እንደባልና ሚስት ሆነው ይኖሩም ነበር፡፡ ልጇን ያረገዘችውም ከዚሁ ሰው እንደሆነ ትናገራለች፡፡

     ሁለቱም የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሰርክ ልመና መውጣት ግድ የሚላቸው ችግርተኞች ቢሆንም፣ በፍቅር ከመፈላለግና እንደ ባለትዳር አብሮ ከመኖር አላገዳቸውም፡፡ አብሮ ለመኖር ጎጆ ባይወጡም ጎዳናው ቤት ሆኗቸው አብረው ለወራት ያህል መቆየት ችለው ነበር፡፡

     ሶፊያ የእኔ የምትለው መጠጊያ ሳይኖራት ማርገዟ አላስጨነቃትም፡፡ ሌላው ቢቀር ያለፕሮግራም እንደተፀነሰ ልጅ እንኳን አላሳሰባትም፡፡ ሁሉም ሞልቶላት እንደምትኖር ሴት ወይዘሮ እርግዝናዋን በፀጋ ተቀብላ ከዓመት ከአምስት ወራት በፊት ሴት ልጅ ተገላገለች፡፡ ልጇን ከወለደች በኋላ ግን ነገሮች ቀላል አልነበሩም፡፡ ባሌ ከምትለው ወጣት ጋርም መለያየቷን ‹‹ለእኔም ለእሷም ምንም ስለማያደርግ ተለያይተናል፤›› ስትል የተናገረችው ያለእንክብካቤ ያደገች ልጇን እያየች ነበር፡፡

     የተመጣጠነ ምግብ የማታውቀው ሕፃኗ ዓመት ከአምስት ወር የሆናት ቢሆንም፣ ገና የስድስት ወር ጨቅላ ነው የምትመስለው፡፡ በአንድ ጎን እንደታዘለች የምትስበው የሶፊያ ጡት የጠቀማትም አይመስልም፡፡ ሶፊያም ይህ ጠፍቷት ሳይሆን እያለቀሰች እንዳታስቸግራት ስትል ነው ጡት የምትሰጣት፡፡

     ልጇ ከእሷ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራትም ትፈልጋለች፡፡ ይሁንና ይህ ከፍላጎት ባለፈ ዕውን ለማድረግ ተራራ የመግፋት ያህል ከባድ ሆኖባታል፡፡ በየቀይ መብራቱ ተሯሩጣና ለምና የምታገኘው ገንዘብ የቀን ወጪዋን እንኳ የሚችል እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡ ሕፃን ልጇን ይዛ በረንዳ ላይ ማደር ስለሚከብዳት ከምግብ ባለፈ ለማደሪያ የሚሆናትን ተጨማሪ ገንዘብ ማፈላለግ ግድ ይላታል፡፡ እንደ አብዛኞቹ ጓደኞቿ በአንድ ክፍል ውስጥ ተሰብስቦ ማደር ስለሚከብዳት ለብቻዋ አንድ ክፍል ይዛ ለማደር ትገደዳለች፡፡ ለብቻ ለማደር ደግሞ በየቀኑ 50 ብር በወር ደግሞ 1,500 ብር ያስፈልጋታል፡፡

     በከተማው ሥር የሰደደ የቤት ችግር ቢኖርም፣ በቀን 50 ብር ከፍላ ከምታድርበት ክፍል የተሻለ ቤት ከ1,500 ብር ባነሰ ዋጋ ተከራይታ መኖር እንደምትችል ታውቃለች፡፡ በቀን ለምና የምታገኘውም ከዚህ አንፃር ሲታይ በቂ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን በየቀኑ የምታገኘውን ቆጥባ የመጀመሪያውን ወር የቤት ኪራይ ከፍላ መከራየት ጣር ሆኖባታል፡፡ ‹‹በየቀኑ ካልከፈልኩኝ ሴትየዋ አታሳድረኝም፡፡ የልጄንና የእኔን ልብስ ስለምትይዝ የግድ ተሯሩጬ ቀፍዬ መክፈል አለብኝ፡፡ ገንዘቡን አንዴ ስለማላገኘው የአንድ ወር በአንድ ጊዜ ከፍሎ መከራየት ስለማልችል ነው እንዲህ የምንገላታው፤›› ትላለች፡፡

     በእሷና በአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የገቢ ልዩነት በጣም የሰፋ ነው፡፡ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ሰጪና ተቀባይ መሆን ብቻ ቢመስልም፣ የሁለቱ ወገኖች የኑሮ ሁኔታ ግን የሰማይና የምድር ያህል የተጋነነ ልዩነት ይታይበታል፡፡  የሚያገኙትን በየፊናው ስለሚያወጡ የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን አቅቷቸው በሕይወታቸው ይፈርዳሉ፡፡ አልያም በቀላሉ ሕክምና መዳን በሚችል በሽታ እየተሰቃዩ ለመኖር ይገደዳሉ፡፡

     ሶፊያም ከባድ የኩላሊት ሕመም ይሰማት ከጀመረ ዓመት ያለፋት ቢሆንም፣ ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በጠና ታማ ጓደኞቿ ወደ ሕክምና መስጫ ቦታ ወስደዋት እንደነበር ትናገራለች፡፡ ሕክምናው በነፃ ቢሆንም ለተጨማሪ ምርመራ 150 ብር እንድትከፍል ስለተጠየቀች ሳትታከም የተመለሰችባቸው ጊዜያት ቀላል አይደሉም፡፡ በዚህ ተስፋ ቆርጣ ሳለ ነው ይህንን በጳውሎስ ሆስፒታል የተዘጋጀውን ነፃ የሕክምና ፕሮግራም ያገኘችው፡፡ ‹‹ሰሞኑን ታምሜ ተኝቼ ነው የከረምኩት፡፡ ሕክምና አለ ሲሉኝ እንደምንም ተነስቼ መጣሁ፤›› አለች የመዳን ተስፋ ወደሰጣት በኪሷ ወደ ያዘችው መድኃኒት እያየች፡፡

    ሌላ የሚያስጨንቃት ነገር ቢኖር የልጇ ሁኔታ ነው፡፡ ‹‹ልጄ እንደኔ እንድትሆን አልፈልግም፡፡ ትምህርት ቤት ገብታ ተምራ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራት እፈልጋለሁ፤›› አለች እንደማልቀስ ስትል እያባበለቻት፡፡ በዚህ ሁኔታዋ ለልጇ የተሻለ ሕይወት መፍጠር እንደማትችል ቢገባትም፣ አሳልፋ ለሌላ ሰው መስጠት እንደማትፈልግ ትናገራለች፡፡ ከልጅ ጋር ስትቸገር ያዩዋት ጥቂት የማይባሉ ልጅሽን ስጭን ብለዋት በጄ አላላቻቸውም፡፡ 

     አስከፊው የጎዳና ሕይወት እንደ ሶፊያ ላሉ ሴቶች ይበልጥ ፈታኝ ነው፡፡ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያድሩበት ቤት፣ የሚዘጉት በር የላቸውም፡፡ ከቤት ገፍቶ ጎዳና ላይ ያወጣቸውን ክፉ ዕጣቸውን እየረገሙ ከአንዱ ጥግ ውለው ያድራሉ፡፡ አጋጣሚው ሴትነታቸውን መጠቀም ለሚፈልግ ሰው እንደፈለገ እንዲያደርጋቸው ፈቃድ የመስጠት ያህል ስለሆነ፣ ማንኛውም ነገር ሊያደርስባቸው ይችላል፡፡ በተኙበት የሚደፍራቸው ብዙ ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት ወንዶች የጎዳና ተዳዳሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በአካባቢው የሚያልፉ መንገደኞች ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ከተኙበት  ቦታ ተጎትተው ተወስደው በቡድን የሚደፈሩበት ሁኔታም የተለመደ ነው፡፡

     እንዲህ ካሉ አደጋዎች ራሳቸውን ለመከላከል ከመካከላቸው አንድ የሚፈራ ወንድ ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመርን እንደ መፍትሔ እንደሚወስዱ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በበጎ ፈቃደኝነት የምትረዳዋ ሕይወት (ስሟ ተቀይሯል) ትናገራለች፡፡ ይህ የሚደርስባቸውን የመደፈር አደጋ የሚቀንሰው ቢሆንም፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሚጠቀሙበት አጋጣሚ ባለመኖሩ ግን አብዛኞቹ እንደሚያረግዙ ሕይወት የታዘበችውን ትገልጻለች፡፡

     ዋናው ነገር አለመደፈሩ ነው እንጂ ማርገዛቸው እንደሆነ ብዙም አያስጨንቃቸውም፡፡ ሳያስቡት በአጋጣሚ የተፈጠረ ነገር ቢሆንም ‹‹እወልደዋለሁ፤›› የሚሉ አሉ፡፡ እርግዝናውን ባይፈልጉትም እንዴት አደርጋለሁ ብለው ብዙ አይጨነቁም፡፡ ‹‹ካልፈለገችው ምንም አትጨነቅም፡፡ አሁኑኑ ሄዳ ኮካ ትገዛና በአመድ በጥብጣ ጠጥታ ትተኛለች፡፡ ከዚያም ደም ይፈሳታል፡፡ ፅንሱ ግን ሊወጣም ላይወጣም ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም እንዲህ ነው የሚያደርጉት፡፡ ከዚህ ሌላም በመድኃኒት ኃይል እንዲወጣ ሲሉ እስከ 50 ፍሬ ክኒን በኮካ ይውጣሉ፤›› የምትለው ሕይወት ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ትናገራለች፡፡

      ከሳምንት በፊት ተዘጋጅቶ በነበረው በዚህ የሕክምና ፕሮግራም ላይ በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዘርፍ በበጎ ፈቃደኝነት ስትሠራ የነበረችው ዶ/ር ፂዮን ላሎቶም በዚህ ትስማማለች፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ጠቅላላ ሐኪሟ ዶ/ር ፂዮን፣ በዕለቱ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 20 ሴቶችን አይታለች፡፡ ከ20ዎቹ ሴቶች መካከል ሦስቱ በቅርቡ የወለዱ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 17ቱ የፀነሱ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን የሚያውቁት ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ 15ቱ ማርገዛቸውን አያውቁትም፣ ሲነገራቸውም ብዙ አልተደነቁም አልያም እንዴት ይሻላል ብለው አለመጨነቃቸውን ትናገራለች፡፡

     ወቅቱን ጠብቀው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መከታተል እንዳለባቸው ሲነገራቸው፣ እንዲህ ባለ ውጣ ውረድ ከመንገላታት አንደኛውን መውለዱ እንደሚሻላቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ ገንዘብ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው መንገድ ፅንሱን ማቋረጥ እንደሚችሉ እያሰላሰሉ ዝም የሚሉም አሉ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ የሕክምና ፕሮግራም ላይ ከተካተቱ 200 ሰዎች መካከል ኤችአይቪ፣ ሄፒታይተስ፣ ቲቢና የቆዳ በሽታ የተገኘባቸው ተጨማሪ ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ማኅበረሰቡ ገሸሽ ላደረጋቸው እነዚህ የኅብረተሰቡን ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ቋሚና ነፃ የሕክምና ፕሮግራም መኖር ወሳኝ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...