- 21 የውጭ አገር ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ዜግነት አግኝተዋል
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር ከሚገኙ ሰባት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ፣ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያስነሱ የቆዩ ሥር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታቱን አስታወቀ፡፡
ዋና መምርያው ከወታደራዊው መንግሥት ውድቀት በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በአገሪቱ የተገልጋዮችን ፍላጎት በማርካት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይመደብ ነበር፡፡
ነገር ግን በራሱ ውስጣዊ ችግሮች ተተብትቦ ዕድገቱን ከማስቀጠል ይልቅ፣ አገልግሎት አሰጣጡ በማሽቆልቆሉ ከተገልጋዮችም ሆነ ከተቆጣጣሪ የመንግሥት ተቋማት ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት መምርያው አዳዲስ አመራሮች እንደተሾሙለት፣ አዲሶቹ አመራሮች የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት መዋቅራዊ ማስተካከያዎችን በማድረግ ጥፋተኛ በተባሉ 45 ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረ ዮሐንስ ተክሉ፣ ምክትሎቻቸው አቶ ዘለዓለም መንግሥቴና አቶ መንግሥቱ ዓለማየሁ በጋራ ዓርብ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ባለሥልጣናቱ በመግለጫቸው የመምርያው ስም እንዲጎድፍ ምክንያት የሆኑ አካላት፣ ሕግና መመርያ በመጣስ ችግር የፈጠሩ አመራሮችና ሠራተኞች ከቦታቸው ተነስተው ጉዳያቸው በሕግና በዲሲፕሊን እየታየ ነው ብለዋል፡፡
ለአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ ለነበሩ ችግሮች ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ የቪዛ አገልግሎት አምስት፣ የፓስፖርት አሰጣጥ ቀደም ሲል ሁለት ወራት ይፈጅ ነበር፡፡ አሁን ግን በሦስት ቀናት፣ አስቸኳይ ሰነድ ደግሞ በአንድ ቀን አትሞ መስጠት ተችሏል በማለት ባለሥልጣናቱ አስረድተዋል፡፡
አቶ ገብረ ዮሐንስ እንደተናገሩት፣ አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ በተለይ ከኢትየጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ የዜጎች መጉላላትን ለማስቀረት ፓስፖርት ለመውሰድ ወደ መምርያው ዋና መሥሪያ ቤት መምጣት ሳያስፈልግ፣ በፖስታ ቤት በኩል መውሰድ የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቷል ብለዋል፡፡ ዜጎች ፓስፖርታቸውን በአዲስ አበባ፣ በክልልና በመላው ዓለም በፖስታ አገልግሎት በኩል መውሰድ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም አዲስ አበባ መምጣት ሳያስፈልግ ዜጎች ባሉበት አካባቢ ፓስፖርት የሚያወጡበት ዕድል የተመቻቸ መሆኑን፣ በመጪው ግንቦት በአዳማ፣ በሰመራና በጅግጅጋ ከተሞች ቅርንጫፎች እንደሚከፍቱ አቶ ገብረ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የኤሌክትሮኒክ ቪዛ በተለይም ለቱሪዝምና ለኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የተጀመረ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአውቶሜሽን ሲስተም የተገልጋዮችን መረጃዎች መሙላት፣ ክፍያ መፈጸምና ቀጠሮ መያዝና ወደ ኢምግሬሽን ሲስተም መላክ የመሳሰሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡
አገሪቱ በቦሌና በድሬዳዋ ዋና መግቢያ በር፣ ከእነዚህ በተጨማሪ በኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር አንድ ኬላ፣ ከዚያ በተጨማሪም ዘጠኝ የየብስ ኬላዎች አሏት፡፡
በእነዚህ ኬላዎች በቀን ከ8,500 በላይ ሰዎች የሚገቡና የሚወጡ ሲሆን፣ ሰባት ሺሕ የሚሆኑት በቦሌ ኤርፖርት የሚስተናገዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የኢምግሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት በቀን ከ2,500 እስከ 3,000 በሚደርሱ ተገልጋዮች የሚጎበኝ እንደሆነ፣ ለተገልጋዮች የተሻለ ግልጋሎት ለመስጠት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ መምርያው በተያዘው በጀት ዓመት ለ21 የውጭ አገር ሰዎች የኢትዮጵያ ዜግነት መስጠቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባት የመናውያንና አንድ የሶማሊያ ተወላጆች እንደሆኑ ታውቋል፡፡
አሁንም 20 የሚሆኑ የውጭ አገር ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለመሆን ጥያቄ ማቅረባቸው፣ 13 የሚሆኑት መሥፈርቱን በማሟላታቸው በቅርብ ኢትዮጵያዊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑት የየመን ተወላጆች ሲሆኑ፣ አራቱ ኤርትራውያን እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡