Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ካሩቱሪ በኢትዮጵያ የነበሩትን እርሻዎች እንደ አዲስ ለማስጀመር መቃረቡን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በጋምቤላ ከነበረው የ100 ሺሕ ሔክታር እርሻው በ25 ሺሕ ይጀመራል አለ

የህንድ የግብርና ምርቶች ኩባንያ ካሩቱሪ ግሎባል በኢትዮጵያ ሲንያንቀሳቅሳቸው የነበሩና በመንግሥት የተወረሱበትን እርሻዎች ዳግም እንደ አዲስ ለማስጀመር፣ ከመንግሥት ጋር ዕርቅ ማውረዱን አስታወቀ፡፡ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥም እንደ አዲስ ስምምነት በመፈረም በጋምቤላ እርሻው ሥራ እንደሚጀምር ገለጸ፡፡

ባለፈው ዓመት በመንግሥት በደል ደርሶብኛል፣ ያላግባብ እርሻዎቼን ተነጥቄያለሁ በማለት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ደብዳቤ ያስገባው ካሩቱሪ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከመንግሥት ጋር በተደረገ ዲፕሎማሲያዊ ውይይትና ድርድር ምክንያት መንግሥት ላይ ያቀረበውን ቅሬታና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመክሰስ እንቅስቃሴውን በመግታት፣ እንደ አዲስ ሥራ ለመጀመር መነሳቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳይራምክሪሽና ካሩቱሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ ኩባንያቸው በመንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ በኢትዮጵያና በህንድ አምባሳደሮች ሸምጋይነት ወደ ድርድር በመምጣት የተወረሱበትን እርሻዎች ዳግመኛ ሥራ ማስጀመር የሚችልበት ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት፣ ኩባንያው ‹‹በሕገወጥ መንገድ ተወረሱብኝ›› ላላቸው እርሻዎች መንግሥት ካሳ እንዲከፍለውና ቋሚ ንብረቶቹንም ከአገር ማስወጣት እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቆ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው መግባባት ምክንያት በጋምቤላ ክልል ከዚህ ቀደም ከነበረው የ100 ሺሕ ሔክታር መሬት ይልቅ፣ በ25 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የእርሻ ሥራውን ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ የኩባንያውን እንደ አዲስ የመጀመር እንቅስቃሴ በመምራትና በማስተባበር ላይ የሚገኙት የራም ካሩቱሪ ልጅ ዪሾዳ ካሩቱሪም ይህንኑ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ወይዘሮዋ ከመንግሥት አካላት ጋር ለወራት በተደረገ ድርድር መንግሥት ይሁንታውን በመስጠቱ፣ ኩባንያው ከጋምቤላ እርሻው በተጨማሪ በሆለታና በወሊሶ የሚገኙ የአበባ እርሻዎቹን ዳግም ሥራ ያስጀምራል ብለዋል፡፡ በወሊሶ የሚገኘው የአበባ እርሻ የመሬት ጠረጋ ሥራ እንደተጀመረም አክለዋል፡፡

ራም ካሩቱሪ በበኩላቸው በሆለታ ለሚገኘው የአበባ እርሻ የ28 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሆለታ አበባ እርሻ ከተለያዩ ገበሬዎች ላይ በቀጥታ ግዥ የተፈጸመበት በመሆኑና ገበሬዎቹም ለይዞታቸው ተገቢውን ክፍያ እንዳላገኙ በመግለጽ የኦሮሚያ ክልል ለመሬቱ ባለይዞታዎች ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲከፍል መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ኩባንያው የካሳ ጥያቄው በዝቷል በማለት ሙግት በመጀመሩ የክልሉ መንግሥት መሬቱን መንጠቁ ይታወሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ከሁለቱ የአበባ እርሻዎች በተጨማሪ በባኮ 12 ሺሕ ሔክታር ገደማ ሰፊ የእርሻ መሬት ተረክቦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በመሬቱ ይህ ነው የሚባል ሥራ አለማከናወኑ ተጠቅሶ ይህም የእርሻ መሬት እንደተወሰደበት ይታወቃል፡፡

የጋምቤላው እርሻ ግን ኩባንያውን ከፍተኛ ንትርክ ውስጥ በመክተት ከመንግሥት ጋርም ዓይንና ናጫ በማድረጉ አገር ጥሎ እንዲወጣ ምክንያት እስከመሆን ያበቃው እጅግ ሰፊ መሬት ነው፡፡ ከ100 ሺሕ ሔክታር ውስጥ ማልማት የቻለው 1,200 ሔክታር ብቻ ነው በማለት፣ መንግሥት በይፋ መሬቱን መንጠቁንና ወደ መሬት ባንክ ማካለሉን አስታውቆ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ይሁንና ካለፈው ወር አጋማሽ ወዲህ ግን በኩባንያውና በመንግሥት መካከል መስማማት ለመኖሩ ከኩባንያው ባሻገር ፍንጭ የሰጠ ጉዳይ የታያው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኩባንያው የቀረበለትን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ይሰጠኝ ጥያቄ ተቀብሎ በማጥናት ላይ እንደሚገኝ መረጋገጡ ነው፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ ካሩቱሪ ፊኒክስ ግሩፕ ከተሰኘውና ዱባይ ከሚገኘው በግብርናና በምግብ ሸቀጦች ንግድ ላይ ከተሠማራ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ባገኘው የ125 ሚሊዮን ዶላር ከፊል ብድር፣ እንዲሁም የድርሻ ሽያጭ ስምምነት ሳቢያ ማገገም የሚችልበትን ዕድል እንዳገኘ ኩባንያው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ካሩቱሪ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ኬንያ ውስጥ በነበረበት የባንክ ብድር ዕዳ ተይዞ ከአራት ዓመታት በላይ ሲኤፍሲ ስታንቢክ በተባለው ባንክ ንብረቱ ተይዞበት ቆይቷል፡፡ ኩባንያው የነበረበት ዕዳም 18 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ሲገለጽ፣ ፊኒክስ ግሩፕ ባደረገው ኢንቨስትመንት ሳቢያ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የኬንያ አበባ እርሻው ከመወረስ ተርፎለታል፡፡ በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የዘመን ባንክ የብድር ዕዳዎች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡

 በኬንያ ኔቫሻ በተሰኘችው የሪዞርት ከተማ ከ200 ሔክታር በላይ የአበባ እርሻ እንዳለው ሲታወቅ፣ በኢትዮጵያና በህንድም ከ550 ሚሊዮን ዘንግ በላይ በዓመት ያመርትባቸው የነበሩ የአበባ እርሻዎችን ሲያስተዳድር እንደቆየ ይነገርለታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች