የሕግ የበላይነት የሚለው አነጋገር የሕግ ልዕልናን የሚጠይቅ ወይም በየትኛውም ደረጃና ከፍታ ላይ የሚገኝ ሰብዓዊ ፍጡር ከሕግ በታች ስለመሆኑ የሚያመላክት መርህ ሲሆን፣ ሰላማዊ፣ ከባቢያዊ ሁኔታ ብሎም በሥርዓት የሚመራ የተረጋጋ ማኅበራዊ መስተጋብር በመፍጠር የሕዝቦችን ሁለንተናዊና ዘላቂ ልማትን ዕውን በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ያለው ስለመሆኑ ዋቢ መጥቀስ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃነት ፈርጀ ብዙ በሆነ መልኩ በሚንፀባረቅበት ሰፊ አገርና ሕዝብ ውስጥ በመንግሥት የፖለቲካ፣ የሲቪልና የሕዝባዊ ተቋማት በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የሕግን የበላይነት በእምነት የመቀበልና የመተግበር ቁርጠኝነት የተረጋጋ ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ የሚኖረው ድርሻ መተኪያ የለውም፡፡
ከዚህ በተቃራኒ የሕግ የበላይነት ወይም ልዕልና ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ በሚወድቅበት ሁኔታ የመልካም አስተዳደር መሠረታዊ እሴቶችን በመሸርሸር፣ ተጠያቂነትን በማጥፋት ለሙስናና ብልሹ ተግባራት ምቹ መደላድል በመፍጠር፣ ለሰፋ ማኅበራዊ ቀውስ ከመዳረጉም አልፎ የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለመሆኑ በገሃድ ከምናያቸው ምልክቶች ባሻገር ማስረጃዎችን ለመፈለግ መድከም አያሻንም፡፡
የጽሑፌ ዓላማ የሕግ የበላይነትን ንድፈ ሐሳብ የመተንተንና የማብራራት ወይም ከዚህ አንፃር መንግሥታዊ ተቋማት በምን ደረጃ እንደሚገኙ ጥናት ማድረግ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጨባጭና ሁነኛ ምሳሌ ይሆን ዘንድ አንድ ግዙፍ መንግሥታዊ የልማት ድርጅትን በአጭሩ መዳሰስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንገድ ትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅት ይባሉ የነበሩትን ሦስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በማዋሃድ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 366/2008 ዓ.ም. ከተቋቋመ ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ይህ ተቋም ከምሥረታው ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጋቸው መዋቅሮችና የአሠራር መመርያዎች ሲፈተሹ፣ በአብዛኛው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አዋጆችንና ደንቦችን መሠረት ያላደረጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች የሚሰጣቸው ያልተገደበ ሥልጣንና ኃላፊነት ተጠያቂነትን እየሸረሸሩ ስለመሆናቸው የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ካወጣው የጥናት ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል ኮርፖሬሽኑ ያወጣውን ይህንኑ ገደብ የሌለው ሥልጣን የሚሰጥ መመርያን ወደ ጎን በመተው በዘፈቀደ ሲፈጽማቸው የከረሙትን የሥራ ኃላፊዎች ቅጥርና ምደባ ሒደት በመተቸት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከአደረጃጀት አንፃርም የግንባታ ተቋም ሆኖ ሳለ፣ የግዙፍ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ራሱ ተቋራጭና ባለቤት፣ እንዲሁም አማካሪ የሚሆንበት አሠራር የግንባታ ጥራትና የሀብት አጠቃቀም የመንግሥት የግዥ ሥርዓት ቁጥጥርን የሚያፋልስ ስለመሆኑ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን የግንባታ ዋጋው 4.6 ቢሊዮን ብር የሆነው የውኃ መውረጃ ካናል የግንባታ ፕሮጀክት የግዥ ሥርዓትን ባልተከተለ መልኩ ለቻይና የግል ተቋራጭ በቀጥታ የሰጠበት አካሄድ በግንባታ ኢንዱስትሪው ውስጥ ግዙፍና አደገኛ የሙስና ምዕራፍ እየተከፈተ ስለመሆኑ አመላካች ይመስለኛል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኮርፖሬሽኑ አደገኛ አካሄድ ያልተመቸው የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ የሥራ ተቋራጮች ማኅበር በኮርፖሬሽኑ አማካይነት የግንባታ ዋጋው ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅና ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሁለገብ አገልግሎት የሚውል ግዙፍ የሕንፃ ግንባታ የአገር ውስጥ ተቋራጮችን ያገለለና ለውጭ ተቋራጮች በተመቻቸ መንገድ የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ በመቃወም ታኅሳስ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ሥጋቱን መግለጹ ተገቢነት ያለው ነው፡፡
ከላይ በመጠኑ ለመዳሰስ እንደሞከርኩት፣ ኮርፖሬሽኑ ገና በጨቅላ ዕድሜው ከኃላፊነትና ተጠያቂነት ሥርዓት አንፃር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ኮርፖሬሽኑ አገሪቱ ያላትን እጅግ ውስን ሀብት በብቃት ሥራ ላይ ከማዋል አንፃርም ቢሆን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይስተዋሉበታል፡፡ ለአብነት ያህል የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን መምርያ በይፋዊ የማኅበራዊ ድረ ገጹ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 16 ቀን 2017 በለጠፈው መረጃ፣ በኮርፖሬሽኑ በሁለት ዓመታት ሊጠናቀቅ ታቅዶ በ2008 ዓ.ም. በ1.21 ቢሊዮን ብር ውል የተገባበት የጂንካ መንደር መንገድ ግንባታ ከሁለት ዓመት በኋላ ግንባታው መጠናቀቅ ሲገባው 23 በመቶ ብቻ የተከናወነ ሲሆን፣ ድረ ገጹ በወቅቱ ለግንባታው መጓተት ከደረደራቸው የተለመዱና አሰልቺ ምክንያቶች መካከል ትኩረትን የሚስበው በቂ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ አለመኖርና የግብዓት እጥረት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ጉዳዩን አስገራሚ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ፣ በተመሳሳይ ወቅት ኮርፖሬሽኑ በዋናው መሥሪያ ቤት በርካታ ሚሊዮን ብሮችን በማፍሰስ ቪ8 ተሽከርካሪን ጨምሮ የተቀናጡ ፔዦና ኒሳን የቤት አውቶሞቢል መኪኖችን ለሥራ ኃላፊዎች ግዥ ከመፈጸም አልፎ የሥራ መሪዎች ቢሮዎችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በተገዙ የቅንጦት ቁሳቁሶች በማደራጀት ተግባር ላይ ተጠምዶ የነበረበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ስንመለከት፣ ኮርፖሬሽኑ በውስጡ አዋህዶ የያዛቸው የቀደሙት ተቋማት በግዥ አፈጻጸም ሒደት በተጨባጭ ይስተዋልባቸው የነበሩ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በአዲስና በተደራጀ ሁኔታ እያስቀጠለ ስለመሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡
በኮርፖሬሽኑ ከሀብት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮችን በተመለከተ ዘርዘር ባለ መልኩ በሌላ ጽሑፍ የምመለስበት ሆኖ፣ ከጽሑፌ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ በተገናኘ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር የሕግ የበላይነትን የደፈጠጠበትንና በአገሪቱ ሕግ የተቋቋሙ የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት ተደጋጋሚ ውሳኔዎችን ተቀብሎ ከመተግበር ይልቅ፣ በአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣናት ቀጭን ትዕዛዝ ሕጋዊ ውሳኔዎችን የማስቀልበስ ብቃት አለን በማለት ዘመኑን በማይመጥን አስተሳሰብ የተቋሙን የኢንዱስትሪ ሰላም እያወከ የሚገኝ አንድ ሁነት እንደ ማሳያ በማቅረብ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በኮርፖሬሽኑ ባልተገደበ ሥልጣን በቤተሰብና በአካባቢያዊ ትስስር የሥራ ኃላፊዎችን የመሰግሰግ ተግባራት መፈጸሙ ሳያንስ፣ ከስድስት ወራት በፊት 12 በተቋሙ በተለያየ ዕርከን ላይ የነበሩ ሥራ አመራሮች ምክንያቱ በውል በማይታወቅ ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን ተጥሶ በሥራ ልምድና በትምህርት ዝግጅት ብቃት ከተመደቡበትና ሲሠሩበት ከነበሩበት ኃላፊነት በማንሳት፣ ደመወዛቸውንና ጥቅማ ጥቅሞቻቸውን በማሳጣት የተወሰደባቸውን ሕገወጥ ዕርምጃ በማስመልከት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የተለያዩ የሲቪልና የፍትሕ ተቋማት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩን ከአገሪቱ ሕግጋትና ከሰብዓዊ መብት አንፃር የመረመሩት ተቋማቱ (የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ የአትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) ውሳኔው ሕገወጥና የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን የጣሰ በመሆኑ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ከሦስት ወራት በፊት በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም፣ ተቋሙ በእንቢተኛነት ሳይቀበለው ዘልቋል፡፡ በዚህም የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ ሌሎች ሕግጋቶችን የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ከአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣናት ጋር ባላቸው ቤተሰባዊ ትስስር በመመካት እንዳሻቸው መደፍጠጥ እንደሚችሉ በገሃድ ያሳዩበት እኩይ ድርጊት እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
በዚህ ጽሑፍ መግቢያ እንደገለጽኩት፣ የሕግ የበላይነት ወይም ልዕልና ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ በሚወድቅበት ሁኔታ፣ የመልካም አስተዳደር መሠረታዊ እሴቶችን በመሸርሸር፣ ተጠያቂነትን በማጥፋት ለሙስናና ብልሹ ተግባራት ምቹ መደላድል የሚፈጥር ስለመሆኑ በኮርፖሬሽኑ ከውልደቱ ማግሥት ጀምሮ እየተስተዋሉ ያሉትና የተዘረዘሩት ድርጊቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሌሎች መሰል ተቋማት ተመሳሳይ ሕገወጥ ድርጊቶች ላለመፈጸማቸው ማረጋገጫ የለም፡፡ በመሆኑም እነዚህን የመሰሉ የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽሩ ተግባራት በሕዝብና በመንግሥት መካከል የመተማመን ድልድይን የሚሰብሩ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ በድምር ውጤታቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው ያለመረጋጋትና የዜጎች የሥጋት ምንጭ መሆናቸው አሌ አይባልም፡፡ ስለሆነም፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በበላይነት የሚቆጣጠረው አካል ሕገወጥነቱ እየሰፋ ከመሄዱ በፊት ሪፖርቶችን ከማውጣት ባሻገር፣ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ተጨባጭና በድርጊት የታገዘ ዕርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኝነቱን ሊያሳይ ይገባል እላለሁ፡፡
(ይሁን ያለው፣ ከአዲስ አበባ)