በውብሸት ሙላት
ባለፈው ሳምንት በሠራተኞች የሥራ ማቆም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተወሰኑ ሰዓታት ዓለም አቀፍ በረራዎች መስተጓጎላቸው ይታወቃል፡፡ የሥራ ማቆምን ምንነት፣ የመብቱን ይዘት፣ ገደብና ክልከላዎችን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ሕግ አንፃር መቃኘት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የሥራ ማቆም መብትን የማይኖራቸው የሥራ ዓይነቶችን ትኩረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ከልተገለጸ በስተቀር የሚጠቀሱት የሕግ አንቀጾች የሚመለከቱት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ነው፡፡
የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሦስት ወገኖችን ይመለከታል፡፡ እነዚህም አሠሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት ናቸው፡፡ በአሠሪውና በሠራተኛው መካከል ተነፃፃሪ መብትና ግዴታዎች አሉ፡፡ ለአንዱ መብት የሆነው ለሌላው ግዴታ ይሆናል፡፡ ተነፃፃሪ መብቶቹና ግዴታዎቹ በአብዛኛው የሚመነጩት ሁለቱ ወገኖች ከሚያደርጉት ውል ነው፡፡ ለውሉ ዝቅተኛ መሥፈርት በመሆን የሚያገለግሉ መሥፈርቶችን ማስቀመጥ ደግሞ የመንግሥት ሚና ስለሆነ በሦስተኝነት ይመጣል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚደረግ የቅጥር ውልም መተላለፍ የሌለበትን መለኪያዎች በሕግ ማስቀመጥ የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ የመብትና ግዴታ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉት ሕግና ውል ናቸው ማለት ነው፡፡
በሕግ ዋስትና ከተሰጣቸው የሠራተኛ መብቶች አንዱ የሠራተኛ ማኅበር ማቋቋም ወይም የመደራጀት መብት ነው፡፡ ይህ መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠው ነው፡፡ ሠራተኞች በመደራጀት ማኅበራት፣ ፌደሬሽን፣ ኮንፌዴሬሽን በመመሥረት በጋራ በመሆን ስለሥራ ሁኔታ ከአሠሪዎቻቸው ጋር ይደራደራሉ፡፡ በድርድርም የተለያዩ ስምምነቶች ላይ በመድረስ መብቶቻቸውን ያስከብራሉ፤ ያስጠብቃሉ፡፡ ይህ ሳይሆን በሚቀርበት ጊዜ ደግሞ በተናጠል ወይም በጋራ ሆነው አሠሪያቸውን መብቶቻቸውን እንዲያከብርላቸው የሚስገድዱበት ሥርዓቶች አሉ፡፡ በጋራ በመሆን ከሚያስጠብቁባቸው መንገዶች አንዱ ‘የሥራ ማቆም’ ነው፡፡
የሥራ ማቆም መብትን ለመጠቀም ከአንድ በላይ ሠራተኞች መሆን አለባቸው፡፡ አንድ ሠራተኛ የሚያደርገው ሥራ ማቆምን አይመለከትም፡፡ በመሆኑም ‹‹አንድ ሰው ቢጣራ አይሰማም ቃሉ እስኪ ሁላችሁም ው በሉ ው በሉ፤›› እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ሠራተኞች ባይሆኑም እንኳን በጋራ መሆንን ግን ይጠይቃል፡፡ በጋራ ሆኖ አሠሪን እጁን መጠምዘዝ ነው የሥራ ማቆም፡፡
ይህ የሥራ ማቆም መብት ሠራተኞች ከአሠሪው ጋር ላላቸው ውዝግብ አንደ መፍትሔ ማምጫ የሚጠቀሙበት መሣሪያ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥታዊ እንዳለው ከአንቀጽ 42 መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አንቀጽ የምናገኛቸው መብቶች ውስጥ በማኅበራት መደራጀት፣ ሠራተኞች በኅብረት መብቶቻቸውን የሚያስከብሩበትን ሁኔታዎችና መሠረታዊ የሥራ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
ከሠራተኛው የመደራጀት መብት አንፃር ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42/1/ሀ/ ሠራተኞች ከሌሎች እንደ የአሠሪዎች ማኅበራት ካሉ አካላት ጋር የመደራደርና ለድርድሩም ብቃት እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ በማኅበራት የመደራጀት መብት አጎናጽፏቸው ይገኛል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰንም ሠራተኛው ቅሬታዎችን በማሰማት መብት በሚለው ሳይገደብ ሥራ እስከማቆም የሚደርስ ድርጊት ሊፈጸሙ እንደሚችሉ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /ለ/ ሥር ሠፍሯል፡፡
ይኼው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አሠሪው ማሟላት የሚኖርበትን የሥራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለሠራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የሥራ ሰዓት ዕረፍት፣ የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የዕረፍት ቀኖች፣ ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት፣ እንዲሁም ጤናማና አደጋ የማያደርስ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብቶች እንዲከበሩ ዋስትና ሰጥቷል፡፡ እንግዲህ እነዚህን የሥራ ሁኔታዎች አሠሪው ያሟላላቸው ዘንድ ሠራተኞች አሠሪውን የሚያስገድዱበት ዕርምጃ ነው የሥራ ማቆም፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 136 ንዑስ ቁጥር 5 ላይ በተሰጠው ትርጓሜ መሠረት የሥራ ማቆም ድርጊት ቁጥራቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ሠራተኞች የሚፈጸም ነው፡፡ ስለዚህ በኀብረት ሆነው በሠራተኞችና በአሠሪና መካከል የሚኖርን ክርክር በጋራ መፍትሔ ይሰጣቸው ዘንድ የሚወሰድ ዕርምጃ ነው፡፡ አሠሪያቸው ማናቸውንም ዓይነት የሥራ ሁኔታን እንዲቀበል በማስገደድ ጥቅማቸውን የማስከበር ወይም የሚፈልጉትን ውጤት ለማግኘት ተፅዕኖ የማድረግ ሒደትም ነው፡፡ ጉዳዩ በአሠሪው ፈቃደኝነትና ችሮታ የሚደረግ ስላልሆነ ከፍላጎቱ ውጪ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የሥራ መጠን መቀነስ ብሎም የተለመደው የሥራ ውጤት እንዲቀንስ ለማድረግ አንድም ሠራተኞች ሥራቸውን በማቀዝቅዝ አለበለዚያም ባለመሥራት የሚወስዱት ዕርምጃ ነው፡፡
በዚህ ትርጓሜ ውስጥ ቢያንስ የሚከተሉትን ነጥቦች ነቅሰን ማውጣት እንችላለን፡፡ የሥራ ማቆም በአሠሪና በሠራተኛ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ሠራተኞች ፍላጐታቸውን ለማስፈጸም እንደ መፍትሔ መሣሪያነት የሚጠቀሙበት መንገድ ነው፡፡
ለሥራ ማቆሙ መሠረት የሚሆኑት ጉዳዮች የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የዕረፍት ሰዓት፣ የመሳሰሉት ዓይነት የሥራ ሁኔታዎች ሊሆኑ ቢችሉም ከእነዚህ ውጭ ማናቸውንም ዓይነት የሥራ ሁኔታ በሚመለከት አሠሪን ለማስገደድ የሚደረግ ዕርምጃ ነው፡፡
ዕርምጃው በተናጠል ሠራተኞች አቋም የሚወሰድበት ሳይሆን በኅብረት ያለመግባባት በመፈጠሩ ምክንያት በሆኑት ነጥቦች ላይ የዕርምጃዎቹን ዓይነቶች፣ የሚወሰዱበትን ጊዜና እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው ሠራተኞች በጋራ አቋም የሚወስዱበት ነው፡፡ በኅብረት አቋም የተያዘበት ውሳኔ ቀጥተኛ ውጤቱ ሥራን በማቀዝቀዝ ወይም በማቆም ላይ ሊሆን መቻሉ ነው፡፡
ሌላው ነጥብ ዕርምጃው ከአሠሪው ፍላጐት ውጪ የሚፈጸም መሆኑና የመጨረሻ ግቡም በአሠሪው ላይ የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር ጥያቄያቸውን ወይም የመደራደሪያ ነጥባቸውን እንዲቀበል ማስገደድ መሆኑ ነው፡፡
የሥራ ማቆም ዕርምጃ ሠራተኞች የሥራ ሁኔታን በተመለከተ ከአሠሪው ጋር በሚኖራቸው አለመግባባት በአሠሪው ላይ የሥራ ማቀዝቀዝ ዘዴን በመጠቀም ወይም ሥራ በማቆም በሥራ ውጤታቸው በሚጠቀመው አሠሪ ላይ የኢኮኖሚ ጫናን በማሳደር የመደራደር አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት መሣሪያ ነው፡፡
ማንኛውም አሠሪ በየትኛውም ሁኔታና ዋጋ ቢሆን ከፍ ያለ ትርፍ የማግኘት ፍላጐት አለው፡፡ ሠራተኛው በሌላ በኩል ሰብዓዊ ክብሩና የሥራ ደኅንነቱ ተጠብቆ የሚሠራበት ጊዜና ሁኔታ ተመቻችቶለት ለጉልበቱ ተገቢ የሆነ ክፍያ እንዲያገኝ ይፈልጋል፡፡ እኒህ ተቃራኒ የሆኑ ፍላጐቶች በአሠሪውና በሠራተኛው መካከል አለመግባባትን የመፍጠር ኃይል አላቸው፡፡ በሒደቱም ችግሩን በቀና መንገድ ለመፈጸም አልተቻለም የሚለው ወገን ሥራ ማቆም ወይም የሥራ መዝጋት ዕርምጃ ለመውሰድ ሊገፋፋ ይችላል፡፡
እነዚህ ሁለት ወገኖች አንዱ በሌላው ላይ የኢኮኖሚ ጫናን በማሳደር ሌላውን ለጥያቄው ተገዢ እንዲሆን ለማስገደድ የሚያደርጉት ፍልሚያ መሆኑ ነው፡፡ ድርጊቱ ለአሠሪው ሆነ ለሠራተኛው በራሱ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚያም አልፎ ኅብረተሰቡን የሚጎዳ ይሆናል፡፡
በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩና ወደ ሥራ ማቆም የሚያስኬዱ ችግሮች አሰቀድሞ አለመፍታ እንዲሁም ሁሉም ወገን ያሰኘውን እንዲያደርግ ልቅ ማድረግ ውሎ አድሮ የኢንዱስትሪ ሰላምን ማናጋቱ አይቀሬ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሒደቱም ያደናቅፋል፡፡ ለአብነትም በሥራ ማቆም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተወሰኑ በረራዎች መስተጓጎሉ በድርጅቱም በደምበኞችም ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ዕሙን ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሠራተኞቹም መብቶቻቸውን ስላልተከበሩላቸው የወሰዱት ዕርምጃ በመሆኑ መብቶቻቸውን ተከብሮላቸው ይሆን ይሆናል፡፡ ሥራ ማቆም በራሱ ግብ ሳይሆን ሌላ ግብ ለማሳካት የሚወሰድ ዕርምጃ ስለሆነ፡፡ በመሆኑም አለመግባባቶች ሥርዓት ባለው መንገድ የሚፈቱበትን የሕግ መንገድ ማዘጋጀት ይገባል፡፡
የሕጉ ግብም የኅብረተሰቡን ሰላምንና ደኅንነት ለመጠበቅና የኢኮኖሚ ሒደቱን ሳይደናቀፍ በሁለቱም ወገኖች ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች ምንነት፣ ስለዕርምጃዎቹ አወሳሰድ ሥርዓትና ቅደም ተከተል፣ ስለሚወሰዱበት ጊዜ፣ ስለሚወሰዱት ሰዎች ማንነት በየትኞቹ ሥራዎች ላይ መፈጸም እንዳለባቸው የሕግ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው መካድ አይቻልም፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ዘርዘር ባለ መልኩ የምናገኛቸው በአዋጁ ከአንቀጽ 157 ጀምሮ ባሉት ድንጋጌዎች ላይ ነው፡፡
የሥራ መቆም በተለያዩ ዘዴዎች ይገለጻል፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሥራ ማቀዝቀዝ ነው፡፡ የሥራ ማቀዝቀዝ ሲባል በመደበኛው ሁኔታ ሥራው ቢከናወን ሊገኝ የሚችለው ውጤት እንዳይኖር ማድረግን ይመለከታል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ሠራተኞች ሥራቸውን ይሥሩ እንጂ ቀድሞ ከሚሠሩበት በተለየ ሁኔታ በሚፈለገው ፍጥነትና የመሥራት አቅም ባነሰ ሲሠሩ እንደ ሥራ ማቆም ይቆጠራል፡፡
እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በአሠሪውና በደንበኞች ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል አሠሪውን ለማስገደድና ሠራተኞች የሚፈልጉትን ውጤት ለማግኘት ይጠቅማል፡፡
ሥራ ሳይቆም በመቀዝቀዙ ብቻ ዕርምጃው እንደ አንድ አማራጭ በሥራ ማቆም ዕርምጃ ሥር መገኘቱ በተወሰነ መልኩ ግርታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ያው ዞሮ ዞሮ በአዋጁ በአንቀጽ 158 ላይ እንደተገለጸው ሥራ ማቆም በከፊልም ሊሆን እንደሚችል ስለተገለጸ እንዲሁም ስለሥራ ማቆም ትርጓሜ በተሰጠበት አንቀጽም ላይ በግልጽ ስለተቀመጠ ሥራ በማቀዝቀዝን የሥራ ማቆም ማድረግ ይቻላል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም አንዳንድ በጣም አስፈላጊ የሚባሉ አገልግሎቶች ላይ የሠራተኞችን የሥራ ማቆም መብት ሙሉ በሙሉ በሕግ ከመንፈግ የሥራ ማቀዝቀዝን ሙሉ በሙሉ ካለመሥራት በመነጠል አማራጭ ማበጀት ለሠራተኛው መብት የተሻለ ዋስትና ይሰጣል፡፡
የሥራ ማቀዝቀዝ ግብ የታለመውን መደበኛ ውጤት እንዳይኖር ማድረግ በመሆኑ በከፊል ሥራውን የማቆም ያህል ኃይል አለው፡፡ በዚህ የተነሳ የሥራ ማቀዝቀዝ በሥራ ማቆም ዕርምጃ ሥር ከመቀመጡ በተጨማሪ በአንዳንድ የሥራ ዓይነቶች ላይ ነጥሎ ማስቀመጡ በአንድ በኩል አገልግሎት ማግኘት ያለበትን ደንበኛና በጥቅሉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳትን ለመቀነስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሠራተኞችን የመደራጀት መብት ሙሉ በሙሉ ከመንፈግም መፍትሔ ይሆናል፡፡
ከሥራ ማቀዝቀዝ ባለፈም ሠራተኞች ሥራቸውን ላለመሥራት በመወሰን ሥራ የሚያቆሙበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ መሠረት ወደ ሥራ ቦታቸው ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ ከሄዱም በኋላ ሥራቸውን ላይሠሩ ይችላሉ፡፡ ሄደው ሥራቸውን ከመሥራት ይልቅ በመሥሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ወይም በአካባቢው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን በመሳሰሉት መንገድ በመጠቀም አሠሪው በማስገደድ ተገቢውን መልስ እስኪሰጥ ድረስ ሥራቸውን እንደተቋረጠ የሚቀጥል ሒደትም ያው የሥራ ማቆም ነው፡፡
የሥራ ማቆም ዕርምጃ ከላይ እንደተገለጸው በኢንዱስትሪ ሰላምን ሊያናጋ የሚችልና በኢኮኖሚውም ላይ ጫናን ሊያደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር በቂ ዝግጅት እንዲደረግበትና መፍትሔም እንዲገኝለት ከዚያም ውጤታማ መንገድ ለማፈላለግ እንዲቻል ዕርምጃው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ሊከተላቸው የሚገባ ሥርዓቶች በአዋጁ ተዘርዝረዋል፡፡
በቅድሚያ ዕርምጃው የጋራ መብትን የሚመለከት በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሠራተኛ ማኀበር አባላት ቢያንስ ሁለት ሦስተኛው በተገኙበት በአብዛኛው የተደገፈ መሆን አለበት፡፡ ሁለት ሦስተኛው የተባለው ከአጠቃላይ የሠራተኛው ማኅበር አባል ውስጥ ውሳኔውን ለማሳለፍ በአካል የሚገኙት አባላት ቁጥርን የሚመለከት እንጂ ሳይሳተፉም ድጋፋቸውን ሊሰጡ በሚችሉት በሁለት ሦስተኛው የማኅበር አባላት የተደገፈ ማለት አይደለም፡፡ በአካል ከሚገኙት ውስጥ ደግሞ በአብላጫ ድምፅ የሥራ ማቆም ዕርምጃውን ከደገፉት በቂ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ የሥራ ማቆም ለመወሰን የሚደረጉ ስምምነቶች የተፈጸሙት በተለያዩ የኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ዘዴዎች ከሆነ ሕጉ ዕውቅና የሚሰጥ አይመስልም፡፡
በአብላጫው ድምፅ የተደገፈው የሥራ ማቆም ውሳኔ ለሥራ ማቆሙ ምክንያት ከሆኑት ሁኔታዎች ጋር በግልጽ ተጽፎ ዕርምጃው ከመወሰዱ ከአሥር ቀን በፊት ለአሠሪውና በአካባቢው ለሚገኘው የሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ወይም አግባብ ላለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ እንዲህ በሚደረግበት ሁሉ ሁለቱም ወገኖች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በስምምነት ለመጨረስ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ የድርጅቱ የሥራ ደኅንነት መመርያዎችና የአደጋ መከላከያ ዘዴዎች በሠራተኛው መጠበቅ አለባቸው፡፡
ከላይ የተገለጹት ሁኔታዎች የተሟሉ ቢሆንም ቅሉ ክርክሩ ለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ወይም ለፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሳይሰጥበት 30 ቀን ከማለፉ በፊት ወይም ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሰጥበት በሕግ የተወሰነው የጊዜ ገደብ ከማለፉ በፊት የሥራ ማቆም ዕርምጃ መውሰድ ሕገወጥ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ ወይም ፍርድ ቤቱ የሥራ ክርክርን ጉዳይ በሙሉ ወይም በከፊል ለመጨረስ ያሳለፈውን ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ አለመቀበል፣ ወይም ውሳኔው በሚፃረር አኳኋን የሥራ ማቆም ዕርምጃ መውሰድ፣ የፍርድ ቤቱን ወይም የቦርዱን ትዕዛዝ ሳይፈጽሙ ማዘግየትም እንደዚሁ ሕገወጥ ናቸው፡፡
በእርግጥ ይህ ማለት ቦርዱ ወይም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በሥራ ላይ እንዲውል ለማስገደድ የሚወሰደው ሥራ ማቆም ሕገወጥ አይሆንም፡፡ ሌላው የሥራ ማቆሙ ዕርምጃ ከአመጽ፣ ከግዙፋዊ ኃይል ወይም ዛቻ ወይም በግልጽና በይፋ ሕገወጥ አድራጐት ጋር የተፈጸመ እንደሆነ ሕገወጥ ይሆናል፡፡
ከላይ የተገለጹት የሥራ ማቆም ዕርምጃ ሲወሰድ መጠበቅ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሲሆኑ፣ ሠራተኞች የሚወስዱትን ይህን ዕርምጃ ተከትሎ አሠሪዎች በሒደቱ ውስጥ የተሳተፉትን ሠራተኞችን ከሥራ የሚያባርሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ቀጥለን ደግሞ ገደቦቹን እንመለከት፡፡
በተደጋጋሚ ከላይ እንደገለጽነው የሥራ ማቆም ዕርምጃ የሚያስከትለው ውጤት በተዋዋይ ወገኖች ላይ የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር ብቻ የመወሰን ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ መዘዙ ከዚያም ያለፈ ስለሚሆን በሥራው መቀጠል ምክንያት የሚጠቀመውን ሕዝብን ሊጎዳና ሊያውክና ይሆናል፡፡
በተለይ ደግሞ የሥራ ማቆም ዕርምጃው እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የሥራ ማቆም ዕርምጃ ቢወሰድ ከፍ ያለ ጉዳትን የሚያመጣ ነው፡፡ ይህንን ነጥብ ለማብራራት አንድ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ የእሳት አደጋ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሠራተኞች የሥራ ማቆም ዕርምጃ ቢወስዱ የእሳት ቃጠሎ ቢነሳ ሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ማንም ይረዳዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥታት በዚህ መብት አጠቃቀም ላይ ገደብ ያስቀምጣሉ፡፡
ገደብ የሚያመለክተው መብቱ ፍጹም አለመሆኑን ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ዘንድ የሥራ ማቆም ዕርምጃ ፈጽሞ የተከለከለ ተግባር ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ደግሞ ይህን መብት መገልገል የማይችሉት በሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የሚሠሩት ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ሌላም በአንዳንድ አገሮች የሚታየው አሠራር የሚመሰክረው ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ናቸው በተባሉት አገልግሎቶች ላይ የተሰማሩት ሠራተኞች የሥራ ማቆም ዕርምጃ ለመውሰድ የማይችሉ መሆኑን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕግ ከላይ ከተጠቀሱት አካሄዶች ውስጥ ወደ ሦስተኛው ያደላ አካሄድን መርጧል፡፡ እጅግ አስፈላጊ አገልግሎቶች ማለት የትኞቹ ናቸው የሚለውን በተመለከተ አገሮች የተለያየ ትርጓሜን ይሰጣሉ፡፡
በአዋጁ እጅግ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ የሕዝብ አገልግሎት ተለይተዋል፡፡ እነዚህም የአየር መንገድ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ የውኃ አገልግሎት የሚሰጡና የከተማ ጽዳት የሚጠብቁ ድርጅቶች፣ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የመድኃኒት ማከፋፈያ ድርጅቶችና የመድኃኒት መሸጫ ቤቶች፣ የእሣት አደጋ አገልግሎትና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ናቸው፡፡
እነዚህ እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ የሠራተኞች ሥራ የማቆም መብትን በክፍል ሁለት ይቀጥላል፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡