አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር)፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ወደ ሁለት ሰዓት ከ40 ደቂቃ የቆየ ውይይት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል ከቀረቡ ጥያቄዎች በተጨማሪ፣ በምክክር መድረኩ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ባነሷቸውና እንዲሁም ከንግድ ምክር ቤቱ የቀረቡት ጥያቄዎችና ምላሻቸው ዙሪያ፣ እንዲሁም የምክክር መድረኩን ይዘት በተመለከተ በዕለቱ የንግዱን ማኅበረሰብ ወክለው ጥያቄዎችን ያቀረቡትን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘውን (ኢንጂነር) ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የመተዋወቂያ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ይህ የውይይት መድረክ እንዴት ተሰናዳ? ካቀረባችሁት ጥያቄ አንፃር የንግድ ማኅበረሰቡን ያረካ ምላሽ ተገኝቷል ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ መላኩ፡- መድረኩ የተዘጋጀው በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አማካይነት ሲሆን፣ እኛ የኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ወኪል በመሆናችን ተጋብዘን ነው የተገኘነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የትውውቅ መድረክና በንግዱ ማኅበረሰብ በኩል ያሉ ዋና ዋና ጥያቄዎችን በመገንዘብ፣ እንዲሁም በጀመሩት አዲስ አደረጃጀት የንግድ ሥራ ስትራቴጂያቸውን ለንግዱ ማኅበረሰብ ያሳወቁበትና የገለጹበት ነው ማለት እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግዱ ማኅረሰብ ወኪል እንደመሆኑ፣ በአዋጅ 341/95 ሲቋቋም በመንግሥትና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል እንደ ድልድይ በመሆን ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ በሥራ ሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተጠናና በተደራጀ እንዲሁም ሙያዊ በሆነ መንገድ በማደራጀት ለመንግሥት አስፈጻሚ አካል በማቅረብ መፍትሔ እንዲመጣ መሥራት ዓላማው ነው፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት መንግሥት በተለያዩ ችግሮች የተተበተበውን የአገራችንን የንግድ አሠራር ለማስተካከል ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ለውይይት ሲዘጋጅ፣ እኛም ምንም እንኳን በርከት ያሉ ጉዳዮች ቢኖሩም በዚህ መድረክ ይመጥናሉ ያልናቸውን ጥያቄዎች በማዘጋጀት፣ የግሉ ዘርፍ ተወካይ በመሆናችን የንግዱን ማኅበረሰብ ድምፅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማሰማት ሞክረናል፡፡
ሪፖርተር፡- ያቀረባችኋቸው ጥያቄዎች ምን ያህል የንግድ ማኅበረሰቡን የልብ ትርታ ያደመጡ ናቸው ብለው ያምናሉ? እንዴትስ ተመረጡ?
አቶ መላኩ፡- ጥያቄዎቻችንን በደንብ ማብራራት እፈልጋለሁ፡፡ የመጀመርያው ጥያቄ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ያነሳነው ጥያቄ ነው፡፡ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የውጭ ምንዛሪ የኦክስጅን ያህል አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ አሁን በደረስንበት ከፍተኛ ችግር መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ አቅጣጫዎች ቢቀመጡም፣ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ዛሬም የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ የሁሉም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በጥያቄያችን ለማሳያ ያቀረብነው ኢንሱሊን መግዣ እስከማጣት መደረሱን፣ በስንት ውጣ ውረድ ያገኘነውን የውጭ ምንዛሪ ለስንዴና ለዘይት ግዥ የምናውል፣ አንገብጋቢ ያልሆኑ የቅንጦት ዕቃዎች መግዣ የምንጠቀም ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንና ግኝታችን ሲነፃፀር 6.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢና 16 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚሆንበትን አካሄድ ማጥበብ የሚቻልበት መንገድ እንዲፈለግ ለማድረግ አስበን ያቀረብነው ነው፡፡
ፋብሪካዎቻችን ጥሬ ዕቃና መለዋወጫ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ በማጣታቸው እጃቸውን አጣጥፈው እየተቀመጡ ሲሆን፣ ቀጣዩ ዕጣ ፈንታ አትራፊ እስካልሆኑ ድረስ ሠራተኛ ወደ መበተንና የባንክ ብድራቸውም እስከ መበላሸት ይደርሳል፡፡ እነዚህ በተለይ ከውጭ አገር የሚመጡ ምርቶችን በመተካት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎችን ተወዳዳሪ፣ ብቁና በጥራት ላይ የተመሠረቱ ማድረግ ካልቻልን አሁንም የሸቀጥ ማራገፊያ መሆናችን ይቀጥላል፡፡ ሌላው መሠረታዊ ያልሆኑ ምርቶች ከውጭ ወደ አገር ሲገቡ ሲታይ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደራችንን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያውያን ባለቤቶች የተያዙ ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት አንድ ዓመትና ሁለት ዓመት የፈጀ ወረፋ ሲጠብቁ፣ በውጭ አገር ባለቤትነት ያሉ ፋብሪካዎች ግን የፍራንኮ ቫሉታ ግዥ ስለሚፈቀድላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የውድድሩ ዙር ከሮባቸዋል፡፡
እዚህ ላይ ትልቁ መነሳት ያለበት ጥያቄ ዕውን እነዚህ በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ አገር ባለሀብቶች ለሚፈልጉት ዕቃ የፍራንኮ ቫሉታ ግዥ ከትውልድ አገራቸው የውጭ ምንዛሪውን እያመጡ ነው ወይ? የእነዚህ ጉዳዮች ውስብስብነት በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ ለመገበያየት፣ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ያለ ደረሰኝ ለመሸጥ፣ ወጪዎቻቸውን ማለትም በባንክ የውጭ ምንዛሪና በጥቁር ገበያ ባለው የውጭ ምንዛሪ ልዩነት በሒሳብ መዝገብ የሚታይ ባለመሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕገወጥ ንግድ እየተስፋፋ ነው፡፡ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ግብርና ቀረጥ እያጣ ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እየጠፋ በመሆኑ፣ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበናል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ትልቁ ምንጫችን በአገራችን የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች ቢሆኑም፣ በአገር ውስጥ የሚሸጡበት ዋጋና ወደ ውጭ አገር ሲላኩ የሚሰጣቸው ዋጋ ልዩነቱ የገዘፈ በመሆኑ ሌላው ሊታይ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንዴት? ቢያብራሩልኝ?
አቶ መላኩ፡- ለምሳሌ ያህል አንድ ኪሎ ሰሊጥ በአሁኑ ጊዜ በምርት ገበያ 39 ብር ይሸጣል፡፡ ይህ ማለት ወደ 1.43 ዶላር ማለት ነው፡፡ አንድ ላኪ ሰሊጥ ኤክስፖርት ሲያደርግ ወጪዎች አሉበት፡፡ የማበጠሪያ፣ የትራንስፖርት፣ የትራንዚተር፣ የብጣሪና የመሳሰሉት ሲጨመሩ በኩንታል እስከ 300 ብር የሚደርስ ወጪ አለበት፡፡ ይህ ማለት አንድ ኪሎ ሰሊጥ እስከ 42 ብር ድረስ ወይም 1.54 ዶላር ድረስ የመግዣ ዋጋው ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ሰሊጥ ኤክስፖርት እየተደረገበት ያለው ዋጋ 1.35 ዶላር ነው፡፡ በዚህ ሥሌት ላኪዎቻችን አንድ ኩንታል ሰሊጥ ለመላክ እስከ ብር 500 ብር ኪሣራ ይደርስባቸዋል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ላኪዎቻችን ኤክስፖርት በማድረግ ሒደት የደረሰባቸውን ኪሣራ በሚያስመጡት ዕቃ ዋጋ ላይ ስለሚጨምሩት፣ ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶች ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ አብሮ የሚታየው መንግሥት በቅርቡ የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ሲያደርግ ዋነኛ ዓላማው፣ ላኪዎች እንዲበረታቱና በሚልኳቸው ምርቶች የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ ሲመነዘር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ሆኖም ትርፍን መሠረት በማድረግ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ላይ ብቻ ትኩረት በመደረጉ፣ በተለይ የጥራጥሬ ምርቶች አምና ከሚሸጡበት ዋጋ በታች እየተሸጡ እንደሆነ የንግድ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ማለት በኢትዮጵያ ብር ከአምናው ባይቀንስም በዶላር ግን ከአምናው በቀነሰ ዋጋ የጥራጥሬ ምርቶች እየተላኩ ነው፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየው የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያችን የእኛን አገር ላኪዎች ሳይሆን፣ ገዢዎቻችንን እየጠቀመ መሆኑንና የእኛ ላኪዎች በዋጋ የመደራደር አቅማቸው አነስተኛ መሆን ነው፡፡ እንዲሁም እንደ አገር የቀነሰ የውጭ አገር ምንዛሪ ገቢ መሆኑ አገራዊ ጥቅም ጭምር እያቀረብን መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተገዝተው የሚላኩ ምርቶች በምን ያህል እንደተገዙ፣ በምን ያህል ደግሞ እንደተሸጡ ብሔራዊ ባንክ የሰነድ ማስረጃ አለው፡፡ ይህ ማለት ኪሣራውንም መንግሥት እያወቀው እንደሚያልፍ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን አባባልዎን በምሳሌ ይገልጹልኛል? የአገልግሎት አሰጣጡስ?
አቶ መላኩ፡- የሚያስገርመው እዚህ አዲስ አበባ ባሉ ሱፐር ማርኬቶች ሄደህ ከእስራኤል የመጣ ጣሂና ማለትም የተቀነባበረ የሰሊጥ ምግብ 450 ግራም 95 ብር ይሸጣል፡፡ ይህ ማለት እኛ በጥሬው ከምንልክበት በኪሎ 40 ብር ጋር ሲነፃፀር አምስት እጥፍ ማለት ነው፡፡ የሚገዙን አገሮች ጥሬ ምርት በርካሽ ዋጋ ያገኛሉ፡፡ እሴት ጨምረው፣ የሥራ ዕድል ፈጥረው፣ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለአገራቸው ሲያስገቡ የሚጠቀሙት የሌላ አገርን ጥሬ ምርት ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ሁሉ ውስብስብ ጉዳዮች የተተበተበውን የኤክስፖርት ችግር ጊዜያዊ፣ መካከለኛና ዘላቂ ስትራቴጂ በመንደር በጋራ መፍትሔ ለማምጣት እንዲሠራ ታስቦ የጠየቅነው ነው፡፡ ከብድርና ከባንኮች አሠራር ጋር የተያያዘው ጥያቄያችንም ቢሆን በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ገና በዕድገት ላይ ያለው የባንክ ኢንዱስትሪ በአሠራር፣ በአቅርቦትና በአገልግሎት አሰጣጥ መጠንከር እንዲችል፣ ብሔራዊ ባንክ በትልቅ ጥድፊያ በየጊዜው የሚቀያይራቸው መመርያዎች፣ የወለድ መናርና የግልጽነት ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ከመንግሥት የፖሊሲ ባንኮች የብድር አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮች ስለሚታዩ ከቀዳሚዎቹ የንግዱ ማኅበረሰብ ጥያቄዎች የሚደመር በመሆኑ በጥያቄ መልክ ቀርቧል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተነሳው ጥያቄ የንግዱ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለማግኘት በሚሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ ያለ መማለጃ ጉዳይ ማስፈጸም እንደማይቻል በመረጋገጡ፣ ነጋዴዎች ሥራ ላይ ማዋል ያለባቸውን ውድ ጊዜያቸውን ጉዳይ ለማስፈጸም እንዲያውሉት በመገደዳቸው በአገራዊ ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ይህም በየግል ድርጅቶች በመዋቅር ያልተካተተና ትልቅ ገቢ የሚያስገኝ ‹‹ጉዳይ አስፈጻሚ›› የሚል የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ከማድረጉም ባሻገር፣ በእጃቸው ሄደው ጉዳዩ እንዲፈጸም የሚያደርጉትን ደግሞ ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› እንዲባሉ አድርጓቸዋል፡፡ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን ስብሰባ ብሶታቸውን ያሰሙ የነበሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አካላት ለአምስት ዓመታት በሳምንት ሦስት ቀናት አንድ መሥሪያ ቤት ይመላለሱ እንደነበር መግለጻቸው የዚህ ማሳያ ነው፡፡
በሠለጠኑት አገሮች ጉዳዮችን ባሉበት ኦንላይን በመመልከት እንደሚፈጸሙ ስንሰማ፣ ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንደሚባለው በአካል ተገኝተን ተገቢውን መልስ ቢሰጡን ምንኛ ደስ ባለን፡፡ ከብዙ ዓመታት ምልልስ በኋላ የሚገኘውም አሉታዊ ምላሽ ለባለጉዳዩ የእግር እሳት ይሆናል፡፡ አንድ ባለጉዳይ በጊዜ እንደማይሆን ከተነገረው ትልቅ መልስ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህም በላይ እኛ አገር ባለ አሠራር አለመሥራት ወይም አይሆንም ማለት አያስጠይቅም፡፡ ስለዚህ አስፈጻሚ አካላት በመመርያ የተቀመጠላቸውን ነገር በባለጉዳዩ ጥያቄ መሠረት ቢፈጽሙ ሊጠየቁ ወይም ሊከሰሱ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ ባይሠሩና መልሳቸው አይሆንም ከሆነ የሚጠይቃቸው የለም፡፡ ስለዚህ በመሥራታቸው ምክንያት እንዲህና እንዲያ እየተባሉ እንደሚጠየቁት፣ በተቀመጠላቸው የሥራ ዝርዝርና መመርያ መሠረት የማይሠሩና ሁልጊዜ ተጠያቂነተን በመፍራት አይሆንም ብለው የሚመልሱትንም መጠየቅ ያሻል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ካቢኔ ሲያዋቅሩ ለሚኒስትሮቻቸው ይህንኑ አባባል የሚያሳይ ንግግር አድርገዋል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ሕዝብ የሚማረርበት፣ ብልሹ አሠራር ሰፍኖ የሚታይበትን ጉዳይ ጠንክሮ መፍታት እንደሚገባ በማስረገጥ ጭምር፡፡ በመሆኑም ለዘመናት ያነጋገረው የዝርክርክነት፣ የብልሹ አሠራር፣ የሙሰኝነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በሲስተም መፍትሔ ለመስጠት አንድ ዕርምጃ ወደፊት ማለት ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- በጥያቄዎቻችሁ ያልተገባ የንግድ ውድድር መስፈን አደጋ እየሆነ ስለመምጣቱ ገልጻችኋል፡፡ ይህ ጥያቄ እንደ ቀዳሚ የንግድ ማኅበረሰቡ ጥያቄ ሆኖ የቀረበበት ምክንያት ሊብራራ ይችላል?
አቶ መላኩ፡- ያልተገባ የንግድ ተወዳዳሪነት ጥያቄያችን በተደጋጋሚ ከንግዱ ማኅበረሰብ የሚቀርብ በመሆኑ ነው፡፡ በንግዱ ዓለም ሜዳው ለሁሉም እኩል መሆን ካልቻለ ኢፍትሐዊነት ይነግሳል፡፡ ስለዚህ ተገቢ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለምሳሌ በአትሌቲክስ ውድድር ሁሉም ተወዳዳሪዎች በእኩል ርቀት ሜዳው በእኩል ተዘጋጅቶላቸው ተወዳድረው ጥሩ ዝግጅትና ልምድ ያለው የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ተከታዮቹ ደግሞ ብርና ነሐስ እየተባለ ደረጃ ያሰጣቸዋል፡፡ በንግዱም ዓለም የመሮጫ ሜዳው ለሁሉም እኩል ካልሆነ የውጭ ምንዛሪ ቢጠፋም ባይጠፋም ዶላር የማያጣ፣ ወረፋ ቢኖርም ባይኖርም ባንክ የሚያስተናግደው፣ ሳይወጣና ሳይወርድ ቤቱ ቁጭ ብሎ ሁሉም ነገር የሚፈጸምለት፣ ጨረታ ለማሸነፍ የተመቻቸለት ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ ቢወጣና ቢወርድ፣ አቀበት ቁልቁለት ሜዳ ጋራውን ቢያካልል ጉዳዩ የማይሳካለት፣ ሕጋዊ ሆኖ እየሠራ የማይበረታታና ሕገወጦቹ የሚበረታቱ ከሆነ የመሮጫ ሜዳውን ማስተካከሉ ላይ መንግሥት ትልቅ ሥራ እንዳለበት ጥያቄ አቅርበናል፡፡
ካልተገባ የንግድ ተወዳዳሪነት ጋር በሕገወጥ መንገድ ምርት እያመረቱ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ውጪ እያደረጉ ያሉትንና የኮንትሮባንድ ንግድን በተመለከተ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ካላስቀመጠ፣ ሕገወጦቹ ትልልቅ ዓሳዎች ሕጋዊዎችን ትንንሽ ዓሳዎች እንዳይውጧቸው ያሠጋል፡፡ የኢንቨስትመንት ዋስትናን ስለማረጋገጥ ሌላው ያቀረብነው ጥያቄ ነው፡፡ በአገራችን አጋጥሞ በነበረው የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ ለሞትና ለከፋ አካል ጉዳት በርካቶች ተዳርገዋል፡፡ እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖም አሳድሯል፡፡ ስለዚህ ችግሮቹን በማለባበስ ሳይሆን መልሶ እንዳያገረሹ በማድረግ በዘላቂነት ለመፍታት መግባባት ያሻል፡፡ ከዚህ ጋር በአገሪቱ እየተመዘገበ ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሁሉም ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ አንዱ የእንጀራ ልጅ፣ ሌላው የእናት ልጅ የማይሆንበት የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት እንዲሆን በማጠቃለያችን ላይ አቅርበናል፡፡
ሪፖርተር፡- የንግዱን ማኅበረሰብ በመወከል ያቀረባችሁዋቸው ጥያቄዎች ምክንያታዊ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ ምን ያህሉ ምላሽ አግኝተዋል ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ መላኩ፡- የቀረቡት ጥያቄዎች ተግባር የሚሹ ናቸው፡፡ በመንግሥት በኩል መፍትሔ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን ተገልጾልናል፡፡ በተለይ የአሠራርና የአስተዳደራዊ ጉዳዮች በቅርቡ መፍትሔ ያገኛሉ የሚል ተስፋ አለን፡፡ ሁሉም መሬት ላይ ወርዶ በተግባር አፈጻጸሙን እንጠብቃለን፡፡ ከአሠራርና ከአስተዳደር ጋር ያሉትን ችግሮች አዲስ በሚፈጠር አደረጃጀት ለመፍታት መንግሥታቸው ቁርጠኛ እንደሆነና ሁሉም ችግሮች በአንድ ጀንበር እንደማይፈቱ፣ እርሳቸው ላቀረቧቸው አዳዲስ የመፍትሔ ሐሳቦች የንግዱ ማኅበረሰብ ተባባሪ እንዲሆንና የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ የወደፊቱን በማሰብ ተስፋ የሰነቀበትና አሉብን ያላቸው ችግሮች ሊፈቱለት እንደሚችሉ በተነገረው አቅጣጫ መሠረት፣ ነገን በጉጉት እንዲጠብቅ ያደረገ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ በምክክር መድረኩ ላይ የተለየ ነገር ይኖራል ብለው ጠብቀው ነበር?
አቶ መላኩ፡- የትውውቅ ጥያቄዎች የምናቀርብበትና እሳቸውም የሚመልሱበት መድረክ እንደሚሆን ጠብቄያለሁ፡፡ ለቀረቡት ጥያቄዎች የሚሰጡዋቸውን መልሶችና የሚያስቀምጧቸውን አቅጣጫዎች ነበር ለመስማት የፈለግኩት፡፡ በአመዛኙ የጠበቅኩት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነትዎ የዕለቱን ውይይት እንዴት ተመለከቱት? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ምክክር እንደ መተዋወቂያ የተወሰደ ቢሆንም፣ ከቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር የንግድ ማኅበረሰቡ ካደረገው ውይይት የተለየ ነገር አለው? በአጠቃላይ የአሁኑን የውይይት መድረክ እንዴት አገኙት?
አቶ መላኩ፡- ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት በየዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የምክክር መድረክ ይዘጋጃል፡፡ ይህም በእኛ በኩል የተለዩና የተጠኑ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲሰጥባቸው የሚያደርግ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ነው፡፡ የአሁኑ ምክክር አዘጋጅ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ እኛ የተገኘነው በተጋባዥነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ ድምፅ እንደ መሆናችን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ያልናቸውን ጉዳዮች አነሳን እንጂ፣ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻል ነበር፡፡ ስለዚህ መንግሥት ራሱ ማዘጋጀቱ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡበት መንገድ ሁላችንም ውስጣችን እንድንመረምር የሚያደርግ ነው፡፡ ምንም እንኳ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ወደ ኃላፊነት ቢመጡም ብቻቸውን ሳይሆን፣ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለአገራችን ዕድገትና ብልፅግና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት አገራዊ ጥሪም በመኖሩ፣ እኛም እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ለማድረግ የበለጠ የሚያነቃቃ ነው፡፡ የንግዱን ማኅበረሰብ ሮሮ ለማድመጥ የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር መረዳት ችለናል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች ለመድረኩ የማይመጥን ጉዳዮችን ቢያነሱም እንኳን በትዕግሥት አዳምጠው ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቀጥታ ወደ ተግባር የሚያስገባ አቅጣጫና ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውም በዕለቱ ሊጠቀስላቸው የሚገባ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ይኸውም ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እነዚህንና ሌሎች የነጋዴዎችን ችግሮች በሰነድ በማደራጀት እንዲያቀርብና የሚመለከታቸው ተቋማት መልስ እንዲሰጡበት፣ የመገናኛ ብዙኃንም ተከታትለው እንዲያስተላልፉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በተለይ ነጋዴዎች ውስጥ ያለውን ዕምቅ የረጅም ጊዜ ዕውቀትና ልምድ (በእርሳቸው አገላለጽ ኦዲት ያልተደረገ ዕውቀት የምስክር ወረቀት ያልተሰጠው) ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለምሁራን ማካፈል እንደሚገባ የተጠቀሙበት አገላለጽ፣ ለንግዱ ማኅበረሰብ ያላቸውን ታላቅ ዋጋ ያስረዳል፡፡ በማጠቃለያቸው ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ችግሮች ዘርፈ ብዙ እንደሚሆኑና ሁሉንም እርሳቸው መመለስ እንደማይችሉ፣ ነገር ግን በየዘርፍ በየዘርፉ በጥናትና በምርምር በመለየት ለሚመለከተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እየቀረበ መፍትሔ እንዲሰጥበት እንዲደረግ ያስቀመጡት አቅጣጫ፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል እስከ ዛሬ ድረስ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ላቅ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ ከመንግሥት ጋር እናደርገው የነበረውን ውይይት የበለጠ የሚያጠናክርና ቅርፅ የሚሰጥ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ሊኖር የሚገባው የምክክር መድረክ ምን ዓይነት ቅርፅ ሊኖረው ይገባል ይላሉ? ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቤኔያቸው ምን ይጠብቃሉ?
አቶ መላኩ፡- ዳትወየምክክር መድረኩ የወደፊቱ ቅርፅ ወደፊት ከተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በዘርፍ በዘርፍ በዝርዝር በመነጋገር፣ ለምሳሌ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ሌጦ፣ የእንስሳት ሀብት፣ የፋይናንስ አገልግሎት፣ የመንግሥት ግዥ፣ አስመጪነት፣ ትልልቅ እርሻዎች፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የሆቴል፣ የሊዝ፣ የሪል ስቴትና የመሳሰሉት እያልን እያጠናን በማስረጃና በምርምር እያስደገፍን ያለብንን አገራዊና ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት እንሠራለን፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያት ይህ የምክክር መድረክ ወደላቀ ደረጃ እንደሚደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በግልጽ ተወያይተን፣ የንግድ ሥራ በሽታዎች ወደ ካንሰርነት ሳይቀየሩ ገና በእንጭጩ መፈታት የሚቻልበትን ስትራቴጂ ነድፈን እንሠራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የምክክር መድረኮች በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን፣ በክልሎችም ደረጃ ከዚህ በፊት እየተደረጉ ያሉት በተጠናከረ መንገድ እንዲቃኙ ፍላጎቱ አለን፡፡ ምክንያቱም የችግሮች ደረጃና የሥራ ባህሪ ከክልል ክልል ስለሚለያይ ይህንኑ በመያዝ እንደ ሁኔታው እያየን እንሠራለን፡፡ እንግዲህ የምክክር መድረኮቻችንን ቀጣይነት ተሰብስቦ ይህን አሉ ከማለት ባለፈ፣ ወደ ውጤት ወደ ተግባር የሚቀየር፣ ክትትል የሚደረግበት፣ በሚቀጥለው ጉባዔ ስንገናኝ ያለፉትን፣ የተፈጸሙትንና ያልተፈጸሙትን ከእነ ምክንያታቸው የምንገመግምበት፣ ተጠያቂ የምናስቀምጥበት የተግባር ሥራ የምናከናውንበት ቦታ አንዲሆን እንጂ፣ ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ የሚውል መሆን እንደሌለበት እምነታችን ነው፡፡
ንግድ ምክር ቤታችን የኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ብቸኛ ወኪል እንደመሆኑ መጠን፣ የንግዱን ማኅበረሰብ ድምፅ በማሰማት ችግሮችን ለመፍታት፣ የነጋዴው መብት እንዲከበርና ግዴታውን እንዲወጣ ጠንክሮ ይሠራል፡፡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴርና ካቢኔ ምን ትጠብቃለህ ለሚለው ጥያቄ፣ ቀደም ብዬ ያነሳኋቸውንና ሌሎች በርካታ የተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታት የችግሮችን ጥልቀት፣ መነሻና መድረሻ በአግባቡ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ማስታገሻዎች ለጊዜው ሊጠቅሙ ይችላሉ፡፡ ግን ዘላቂነት አይኖራቸውም፡፡ አንድ የራስ ምታት የሚኖረው ሰው ማስታገሻ ወሰደ ማለት በሽታው ጠፋ ማለት ሳይሆን የሕመም ስሜት መቀነስ ነው፡፡ በሽታው ግን አለ፡፡ በተደጋጋሚ ቢወሰድ ደግሞ ወደ ከባድ የማስታገሻ መድኃኒት መውሰድ ይሸጋገራል፡፡ ለንግድ ሥርዓቱ መፍትሔ ለማምጣት ሲሠራ ጊዜያዊ ማስታገሻ ሳይሆን በዘላቂነት በሽታው በሚወገድበት ላይ አዲሱ ካቢኔ ይሠራል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለያዩ መድረኮች የኢኮኖሚው ሞተርና ጀርባ አጥነት ነጋዴው ነው ከተባለ ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው የነበረውን አጠቃላይ አሠራር በመገምገም ጥሩውን በማስቀጠል መጥፎውን ቆርጦ በመጣል፣ የጎደለውን ደግሞ መሙላት ከባለድርሻ አካላት፣ ከነጋዴዎች፣ ከአገልግሎት ሰጪዎችና ከባለሙያዎች ጋር ሥራ ይሠራሉ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግዱ ማኅበረሰብ ይመለስልኝ ብሎ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ፣ የንግድ ምክር ቤቱም ሊፈጽም ይገባል ብለው ያስቀመጡት ነገር አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእርስዎን ስም ጠቅሰው መፈጸም አለበት ብለው ያሳሰቡዎ በውጭ አለ ያሉትን የውጭ ምንዛሪ እንዲመለስ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱን አባላት ጠርተው እንዲመልሱ ማድረግ የሚለውም ይገኝበታል፡፡ ይህንን ጥያቄ እንዴት አገኙት? እርስዎስ ምን ያደርጋሉ?
አቶ መላኩ፡- አገራዊው ጥሪ የሚገባ ነው፡፡ ዜጎች በቃል ብቻ አገራችንን እንወዳለን ማለት ብቻ ሳይሆን፣ የአገራችን ፍቅር በግብር (በተግባር) እንዲገለጽ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህንን ጥሪ በሚቀጥለው የቦርድ ስብሰባ በዝርዝር በመወያየት እንዴት ሊፈጸም እንደሚችል አቅጣጫ በማስቀመጥ የምንሄድበት ይሆናል፡፡